Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቅሬታ ፈጥሮ የነበረው የኢፍጣር ዝግጅት በድምቀት ተከናወነ

ቅሬታ ፈጥሮ የነበረው የኢፍጣር ዝግጅት በድምቀት ተከናወነ

ቀን:

ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ሊደረግ ታቅዶ ሲያበቃ በፈቃድ አሰጣጥ ላይ በተነሳ ውዝግብ ሳቢያ በአግባቡ ያልተከወነው የረመዳን ወር የኢፍጣር መርሐ ግብር፣ ወደ ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ተዘዋውሮ ቀድሞ በታቀደለት ሥፍራ በድምቀት ተከናወነ፡፡ መርሐ ግብሩ የተከወነው ከሜክሲኮ እስከ ባምቢስ በሚሄደው ጎዳና ላይ ነው፡፡

በሃላል ፕሮሞሽን ‹‹ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በኢትዮጵያ›› በሚል ስያሜ የጎዳና ላይ ዝግጅት ለማድረግ ከመንግሥት ፈቃድ አግኝቶ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ መንግሥት የዝግጅት ቦታውን ቀይሩ የሚል ማሳሰቢያ ማስተላለፉ በድርጅቱ ተቀባይነት አለማግኘቱን በመጥቀስ በተለዋጭነት የቀረበው ቦታ ላይ ዝግጅቱን ለማከናወን እንደማይችል አስታውቆ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ዝግጅቱን ለመሰረዝ እንደተገደደ ሃላል ፕሮሞሽን ያስታወቀ ቢሆንም፣ ሕዝበ ሙስሊሙ በተባለው ሰዓት አደባባይ በመውጣት ወደ መስቀል አደባባይ በመትመም፣ የኢፍጣር ሥርዓቱ መታገዱን የሚቃወሙና አድሏዊ ሥርዓት መኖሩን በማንሳት የሚወቅሱ መፈክሮችን ሲያሰሙ ቆይተው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡

መርሐ ግብሩን ለማድረግ እንደማይቻል በደብዳቤ ለሃላል ፕሮሞሽን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ 10,000 ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ለታሰበው መርሐ ግብር ጥበቃ ማድረግ እንደማይቻልና የከተማው ፖሊስና የፀጥታ ኃይል ተደራራቢ ፕሮግራም አለበት ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ቁጥሩ ወደ 5,000 ቀንሶ እንዲካሄድ ሲል በድጋሚ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ የኢፍጣር መርሐ ግብሩ የሚካሄድበት አደባባይ የመስቀል ደመራ የሚከናወንበት በመሆኑ፣ ግጭት ይፈጥራል የሚል ሥጋት ያዘለ ደብዳቤ ለፀጥታ ቢሮ በማስገባት ተለዋጭ ሥፍራ ለኢፍጣር እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ጥያቄ በሕዝበ ሙስሊሙና በክርስቲያኑ ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል፡፡ አደባባዩ ከሙዚቃ ድግስ እስከ ስፖርታዊ ዝግጅቶችና የፖለቲካ ቅስቀሳዎች የሚከናወኑበት ሆኖ ሳለና በዓመት ውስጥ ጥቂት መርሐ ግብሮችን ካስተናገደ በኋላ ክፍቱን የሚቆይ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለው ክልከላ አግባብ የለውም በማለት በጋራ ተቃውመውታል፡፡ ለሌሎች ዝግጅቶች ሲሆን የሚፈቀድና ኢፍጣር የሚከለከልበትም አግባብ አግላይነት ያለበት ነው ሲሉም፣ በርካቶች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ድምፃቸውን ሲያሰሙ ነበር፡፡

ለአብነትም የእስልምና ንቁ አቀንቃኝና የመብት ተሟጋች አህመዲን ጀበል በፌስቡክ ገጻቸው እንዳሰፈሩት፣ ‹‹ጉዳዩ የፈጥር ሳይሆን በእኩል የመታየት ጉዳይ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየት ይብቃ ብለዋል፡፡

እነዚህን ተቃውሞዎች ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቃውሞውና ዝግጅቱ ሰላማዊ እንዲሆን ያደረጉትን በማመሥገን፣ ‹‹በከተማችን አዲስ አበባ ብዙ ቁጥር ያለውን የሙስሊም ማኅበረሰብና ሌሎችን ያሳተፈ የጎዳና ላይ አፍጥር ለማካሄድ የተዘጋጀው ዕቅድ፣ በአዘጋጁት አካላትና ግለሰቦች እንድናውቀው ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮግራሙ በተሳካና የዓለም ሪከርድ በሚሰብር ሁኔታ እንዲፈጸም ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከአዘጋጆቹ ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኘን ለፕሮግራሙ ውጤታማነት በሙሉ ልባችን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ለስኬቱም እስከ መጨረሻዋ ድረስ በሙሉ አቅማችን ሠርተናል፡፡ ይህን ትልቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለአብሮነትና ለአገር አንድነት ለማዋል የተሠራው ሥራ የሐሳቡን አመንጪዎችና አዘጋጆቹን የሚያስመሠግን ታላቅ ተግባር መሆኑን እናምናለን፡፡ በእርግጥም ዛሬም በከተማዋ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የአፍጥር ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፤›› በማለት ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አደባባዩ የእኛና የእናንተ መባል እንደማይኖርበትና በጋራ ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው እንደሆነ፣ የከተማ አስተዳደሩ በመግለጫው አትቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት መንግሥት ሁሉንም ሃይማኖቶች እኩል ማየትና በህንድ እንዳለው ልምድ ለአንዱ የሚሰጠው ድጋፍ ለሁሉም በእኩል መደረግ እንዳለበት በመጥቀስ የሚያሳስቡት የሕግ ምሁሩና የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት (ሴኩላሪዝም) ባለሙያው መሐመድ ደጀን (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ሥፍራዎች የሁሉም እኩል መጠቀሚያና መገልገያ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከደርግ ዘመን አንስቶ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ የተደነገገ ቢሆንም፣ በታሪካዊ አጋጣሚዎች ሳቢያ የተፈጠረውን የመንግሥታትና የሃይማኖቶች መቀራረብና አብሮ መሥራት በቀላሉ ማፋታት አልተቻለም ሲሉም ያክላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሥፍራዎችን ለተወሰኑ ሃይማኖቶች የመስጠት አዝማሚያዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታና ከመንግሥትና ከሃይማኖት መለያየት ፍላጎት አንፃር፣ ሁሉንም እኩል ማስተናገድና የማያደላ መንግሥት መፍጠር ካልተቻለ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ ይላሉ፡፡ በሒደት ግን መንግሥት ግልጽ አሠራሮችንና መመርያዎችን እያዘጋጀ ሲሄድ ይቀረፋል፤›› ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹በሠለጠነ ማኅበረሰብ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥት የሁሉም ነው፡፡ ሃይማኖት ደግሞ የግል ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ለምናየው ችግር አንዱ መነሻ መንግሥትና ሃይማኖቶች ያሏቸው ቅርበት ነው፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

በሕገ መንግሥት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም፣ አንዱ ሌላኛውን መጠቀሚያ የማድረግ አዝማሚያዎች አሁንም አሉና ሊስተካከሉ ይገባል ይላሉ፡፡

‹‹መንግሥት በማያወላዳ ሁኔታ በግልጽ ገለልተኝነቱን ማሳየት አለበት፡፡ ድጋፍ ሲያደርግም ለሁሉም እኩልና ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፤›› በማለት ያሳስባሉ፡፡ በዚህም ሃይማኖቶች የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ በተከተለችው የብሔር ፖለቲካ ሳቢያ የብሔር ማንነት የግጭት መንስዔ ሆኖ አንዱን የሌላው ጠላት እያደረገ መቆየቱን፣ ይኼም ለ30 ዓመታት በሕግ ዕውቅና ተሰጥቶት የቆየው በብሔር ማንነት በፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀት መብት እንደሆነ በማሳየት፣ በተለያዩ ሁኔታዎችም ማንነቴ በተግባር አልተስተናገደም የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ የሁሉንም ፍላጎቶች እኩል ማርካት ስለማይቻልም በማንነቴ ሳቢያ ተጠቅቻለሁ የሚሉ ቅሬታዎችን ሊያስከትል ይችላል ባይ ናቸው፡፡ የዚህም አንዱ ማንነት ሃይማኖት ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡

ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ሊኖር ባይችልም ቅሉ፣ ለግጭት በር በሚከፍት ሁኔታ የክርስትናንም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶችን መሠረት ያደረጉ ፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው በአደባባይ ስለሚሰማ የግጭት መነሻ ከመሆኑ በፊት፣ መንግሥት በቅርበት መመርመር ይኖርበታል ሲሉም ምክረ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

‹‹መንግሥት በአደባባይ የወጣውን ብቻ ሳይሆን፣ ውስጡንም መመርመር የሚያስችለው አቅም ስላለው እንዲህ ያሉ አደረጃጀቶችን አሠራራቸውንና አጀንዳቸውን እያጠና ሊቆጣጠር ይገባል፤›› ሲሉ መሐመድ (ዶ/ር) ይጠቁማሉ፡፡

ስለዚህ ምንም እንኳን በግልጽ ሃይማኖታዊ ፓርቲ ነን ባይሉም የግጭት መነሻ ሊሆኑና ኅብረተሰቡን ሊያራርቁ ስለሚችሉ፣ መንግሥት ሊለያቸውና ሊከታተል ይገባል ይላሉ፡፡

ሆኖም በዘላቂነት ሃይማኖቶች እኩል እንዲስተናገዱና የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ለማስቻል ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች መተግበር እንደሚገባቸውና ገለልተኝነቱንም በተግባር ማሳየት እንዳለበት መሐመድ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...