Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአፍሪካ ልማት ባንክ የሕፃናት መቀንጨርን ለመቀነስ 31 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አደረገ

የአፍሪካ ልማት ባንክ የሕፃናት መቀንጨርን ለመቀነስ 31 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አደረገ

ቀን:

የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ የሕፃናት መቀንጨርን ለመቀነስ ወደ ሥራ የገባውን የሰቆጣ ቃል ኪዳን መተግበሪያ ፕሮጀክት ለመደገፍ የሚረዳ 31.2 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አደረገ፡፡

መንግሥት ከሰድስት ዓመት በፊት ይፋ ያደረገው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ‹‹ዘርፈ ብዙ መቀንጨርን የመቀነስ ፕሮጀክት›› በ2022 ዓ.ም. ከሁለት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ቀጥተኛ የሆኑና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥርዓተ ምግብ ተግባራትን በመተግበር፣ የሕፃናት መቀንጨር መግታትን ዕውን ለማድረግ የተቀረፀ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህም የሚፈጸመው በተመረጡ የአማራና የትግራይ ክልሎች ውስጥ ነው፡፡

ለፕሮጀክቱ የተደረገውን የዕርዳታ ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የባንኩ የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱል ካማራ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሪት ያስሚን ወሃብረቢ በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ተፈራርመዋል፡፡

ወ/ሪት ያስሚን በሰምምነቱ ወቅት እንዳስረዱት፣ በኢትዮጵያ የሕፃናትና የእናቶች ሥነ ምግብ ባህሪ በማሻሻል ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም ከአሥር ዓመት በፊት 12 በመቶ የነበረውን የመቀንጨር ሥርጭት ወደ ሰባት በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን፣ ክብደታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሕፃናት ቁጥርም ቀድሞ ከነበረበት 33 በመቶ ወደ 21 በመቶ ዝቅ ማለቱን፣ ሆኖም በዚህ ወቅት ከፍተኛ ሥር የሰደደ የተመጣጣነ ምግብ እጥረት ችግር እንዳለ ሚኒስትር ድኤታዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የ31.2 ሚሊዮን ዶላር (1.3 ቢሊዮን ብር) ዕርዳታ ያደረገለት ፕሮጀክት በአራት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር መሆኑን፣ በአጠቃላይ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 48.12 ሚሊዮን ዶላር አንደሆነ፣ ከዚህ ውስጥ 31.2 ሚሊዮን ዶላር በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ 16.05 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መንግሥት፣ እንዲሁም ቀሪው 1.11 ሚሊዮን ዶላር ከተጠቃሚው ኅብረተሰብ ወጪ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ከውኃ አቅርቦት በተጨማሪ መስኖ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የግብርና መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሥርዓተ ምግብ የበለፀጉ ሰብሎችንና እንስሳትን ማምረት፣ የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻልና ከተቀናጀ ሥርዓት አሠራር ጋር የተገናኙ ተግባራት እንደሚከናወኑበት በስምምነቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

አብዱል (ዶ/ር) በአፍሪካ ልማት ባንክ የተደረገው የዕርዳታ ድጋፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጥልቅና ሰፊ የሆነ አጋርነት የሚያሳይ እንደሆነ በመግለጽ፣ ይህንን መሠረት በማድረግ በአፍሪካ ልማት ባንክ ከዚህ በፊትም ሆነ ወደፊት የሚደረጉት ድጋፎች ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመመደብ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዙ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከሰዎች ዕድገት ጋር በተገናኘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ የጋራ ስምምነት እንዳለ ያስታወቁት አብዱል (ዶ/ር)፣ ይህም የተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብ ትግበራን በሌሎች መሠረት ልማቶች ላይ እንደሚደረግ የልማት ሥራ መቁጠር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ያለመችውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማሳካት የሕፃናት መቀንጨር መቀነስ ላይ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ይፋ ከተደረገ በኋላ መንግሥት የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ ከመደበኛ በጀት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳወጣ የተገለጸ ሲሆን፣ ትግበራው ተጨማሪ ሀብት የሚፈልግ በመሆኑ ይህንን ሀብት የማፈላለግ ሥራ ሲከናወን መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነት የወደመውን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠገን ተቋራጮች ሊመረጡ ነው

ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ምትክ...

ለአደጋ መከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ የድንገተኛ እሳትና አደጋን ለመከላከልና በፍጥነት ምላሽ...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ...

ብሔራዊ ባንክ ኅብረተሰቡና ባንኮች በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች እንዳይጭበረበሩ አሳሰበ

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በማሳተምና በማሠራጨት ግብይት ላይ ለማዋል ጥረት...