Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኮሜርሻል ኖሚኒስ በሕግ ሽፋን ሕገወጥ ድርጊት ላይ መሰማራቱን ፓርላማው አስታወቀ

ኮሜርሻል ኖሚኒስ በሕግ ሽፋን ሕገወጥ ድርጊት ላይ መሰማራቱን ፓርላማው አስታወቀ

ቀን:

አብዛኛው ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ የሚነገርለት ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለባንኩ በድጋፍ ሠራተኝነት በሚያቀርባቸው ሠራተኞች ላይ የመብት ጥሰት እያካሄደ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ፣ በዋነኛነትም በኮሜርሻል ኖሚኒስ ላይ አካሄድኩት ያለውን የዳሰሳ ጥናት ሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ኮሜርሻል ኖሚኒስ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011ን እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን የአሠራር መመርያ በመጣስ፣ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ መሰማራቱን አመላክቷል፡፡

እስካሁን ወደ 30,000 የሚደርሱ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ አቅርቧል የተባለው ኮሜርሻል ኖሚኒስ፣ ለሠራተኞቹ እንዲከፈል በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አፈጻጸም መመርያ ላይ የቀረበውን 80 ለሠራተኛውና 20 ለኤጀንሲው ተብሎ የተቀመጠውን የደመወዝ መመርያ በመጣስ፣ ሠራተኞች ሲቀጠሩ ከሚዋዋሉት ጠቅላላ ክፍያ ውስጥ እስከ 61 በመቶ የሚሆነውን በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚቆርጥባቸውና ከ40 በመቶ በታች እጃቸው ላይ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በሕጉ መሠረት አንድ ሠራተኛ ለ60 ቀናት ብቻ በሙከራ ጊዜ እንዲቆይ የተወሰነ ቢሆንም፣ ተቀጣሪዎች ከሕጉ ውጪ የኮንትራት ሠራተኛን እየተባሉ ለስምንትና ለዘጠኝ ዓመታት ቋሚ ሳያደርግ ማቆየቱ፣ የሠራተኛ ደንብ ልብስ እንደሚሰጥ ካሳወቃቸው በኋላ ከሠራተኛው ደመወዝ እየተቀነሰ ደረጃውን ያልጠበቀ ልብስ እንዲሚያቀርብ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ሪፖርቱ ከጠቀሳቸው በሠራተኞች ላይ የሚደርሱ በደሎች ውስጥ የዓመት ፈቃዱን በገንዘብ መግዛትና ቤተሰብ ቢሞትባቸው እንኳ የዓመት እረፍት አለማግኘት፣ ሠራተኞች ላይሠለጥኑ ለሥልጠና ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉ፣ በድርጅቱ መከፈል የነበረበትን 11 በመቶ የጡረታ ክፍያ በሠራተኞቹ እንዲከፈል መደረጉና ሠራተኞች ለምን እንደተቆረጠ የማያውቁት 1,937 ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ከደመወዝ ላይ እንደሚቆረጥባቸው ተገልጿል፡፡

ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርት፣ ለዓመት ፈቃድ፣ ለፐብሊክ ሊያቢሊቲ ኢንሹራንስ አበል፣ ለቀን አበል ክፍያ፣ ለወሊድ ፈቃድ፣ ለዳኝነት፣ ለቁሳቁስ፣ ወዘተ በሚል ከደመወዝ ላይ እንደሚቆረጥ የፓርላማው የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል፡፡

በኤጀንሲው ያልተገባ የደመወዝ መቆረጥን አስመልክቶ ለአብነት የቀረበው ማሳያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሳይት መሪነት ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ ሠራተኛ የመነሻ ጥቅል ደመወዙ 6,804 ብር እንደሆነ፣ ለሠራተኛው የሚደርሰው የተጣራ ደመወዝ ከአጠቃላይ ደመወዝ 42.7 በመቶ ወይም 2,910 ብር መሆኑን፣ የአንድ ጥበቃ መሪ ጥቅል ደመወዝ 6,099 ብር ሲሆን፣ ለሠራተኛው በእጁ የሚደርሰው የተጣራ ክፍያ 2,380 ወይም 39 በመቶ ብቻ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ለጥበቃ ሠራተኞች መፀዳጃ ቤት እንደሚቆለፍባቸው፣ ለሌሎች ሠራተኞች የተፈቀደ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ የደረጃ ዕድገት እንደሚከለከሉና በርከት ያሉ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው መሆኑ በጥናቱ ተገልጿል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱን ካካሄዱት የፓርላማ አባላት ውስጥ ወ/ሮ ሳራ አቢ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ ሠራተኞችን ለማነጋገር በተለያዩ ተቋማት በሄዱበት ወቅት ሠራተኛው እያለቀሰ እንደነገራቸው፣ ‹‹ኤጀንሲውና ባንኩ በማናለብኝነት እኔ ከቀጠርኩት እናንተ ምን አገባችሁ በሚመስል ሁኔታ ሕጋዊ ባርነትን እያካሄዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የተወከሉት አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው፣ ኮሜርሻል ኖሚኒስን ጨምሮ በርካታ የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አድማ በሚመስል ሁኔታ ለሕግ ተገዥ እንዳልሆኑና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን መመርያ እንዳይፈጸም በፍርድ ቤት እስከ ማሳገድ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህም የተነሳ አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ላይ ተደምሮ በእሳት ላይ ቤንዚን ላለመሆን ስንል፣ በርካታ ሠራተኞች የሚያቀርቡትን የሰላማዊ ሠልፍና ሌሎች የመብት ጥያቄዎች አፍነን ይዘናል፤›› ብለዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በአገሪቱ ካሉ አጠቃላይ የአሠሪና ሠራተኛ ኤጀንሲዎች አራት በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሕጉን አክብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚቀርቡ የበርካታ ኤጀንሲዎች ጥያቄ ከአመዛኙ፣ ‹‹ለምን በሕግ እንገዛለን የሚሉ የሚመስሉ ከሕግና ከሥነ ሥርዓት ውጪ በመንቀሳቀስ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ እንዳይተገበር እንቅፋት ሆነውብናል፤›› ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

‹‹ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን የጉልበት ብዝበዛ ለማስቆም ምክር ቤቱ ያወጣው ሕግ እንዲፈጸም ያግዘን፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ በመሩት የውይይት መድረክ፣ በዳሰሳ ጥናቱ በዋነኛነት የተመለከተውን ኮሜርሻል ኖሚኒስ በሠራተኞች ላይ ያደረሰውን በደል በማጣራትና በማስተካከል፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የወሰደውን ዕርምጃ ለፓርላማው እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...