Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪዎች ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን በ21 በመቶ አደገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2013 የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከአጠቃላይ የኢንሹራንስ ሥራ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 21 በመቶ ዕድገት በማሳየት 11.27 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻላቸውንና የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሚባለው ዓረቦን የተገኘበት መሆኑ ተመለከተ፡፡  

የ18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸምን የተመለከተው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳው፣ በዘጠኝ ወራት የሰበሰቡት ዓረቦን ከ2012 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸማቸው ሲነፃፀር የ1.95 ቢሊዮን ብር ወይም 21 በመቶ ዕድገት የታየበት ሆኗል፡፡ 18ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2012 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት አስመዝግበው የነበረው የዓረቦን መጠን 9.31 ቢሊዮን ብር እንደነበር ታውቋል፡፡

ኩባንያዎቹ ከሕይወትና ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፍ በጥቅል ካሰባሰቡት 11.27 ቢሊዮን ብር የሚሆን ዓረቦን ውስጥ 10.64 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበ ሲሆን፣ ቀሪው 630.2 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበ ነው፡፡

 በዘጠኝ ወራት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አፈጻጸም ላይ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ኩባንያዎቹ ዘጠኝ ወራት ያሰባሰቡት አጠቃላይ የዓረቦን መጠን እስካሁን በኢንዱስትሪው በዘጠኝ ወራት ያልተመዘገበ ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበት ነው፡፡ የተመዘገበው የዓረቦን መጠንም በ21 በመቶ ዕድገት ያሳየበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኩባንያዎቹን የገበያ ድርሻ በተመለከተ ከዘጠኝ ወራት ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያሰባሰበው አረቦን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት 18ቱም ኩባንያዎች ከአጠቃላይ ሕይወት ነክና ሕይወት ነክ ካልሆነ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ካገኙት 11.27 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ውስጥ 5.58 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያሰባሰበው ነው፡፡ ቀሪው 5.69 ቢሊዮን ብር ደግሞ 17ቱ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሰባሰቡት ነው፡፡

በዚህ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከኢንዱስትው ገበያ ግማሽ ያህሉን ወደ መያዝ ደርሷል፡፡ ሪፖርቱ በዓረቦን አሰባሰቡ ረገድ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የኢንዱስትውን 49.6 በመቶ የገበያ ድርሻ መያዙን ያመለክታል፡፡ በቀደመው 2012 ዘጠኝ ወራት የነበረው የገበያ ድርሻ 47.4 እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት የገበያ ድርሻውን ከፍ ለማድረግ ካስቻሉት ውስጥ አንዱ ዓምና አግኝቶት ከነበረው የዓረቦን መጠን ከ1.16 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ገቢ በማግኘት 5.58 ቢሊዮን ብር በማድረሱ ነው፡፡ ድርጅቱ በ2012 የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት አሰባስቦት የነበረው የዓረቦን መጠን 4.41 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የዓረቦን ገቢ መጠኑን እያሳደገ መሄዱ ኢንዱስትሪው ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከጥቂት ዓመታት በፊት የገበያ ድርሻው እስከ 33 በመቶ ወርዶ ነበር፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን ይህንን የገበያ ድርሻ ቀስ በቀስ እያሳደገ በመሄድ አሁን ያለበት ደረጃ ሊደርስ ችሏል፡፡

በዘጠኝ ወራቱ የኩባንያዎቹ የሥራ አፈጻጸም መረጃ መሠረት፣ በ2012 ዘጠኝ ወራት አግኝተውት ከነበረው የዓረቦን መጠን ከቀሪዎቹ 17 የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ማሰባሰብ የቻሉት ሦስት ኩባንያዎች ብቻ ናቸው፡፡

እነዚህም አዋሽ ኢንሹራንስ 829.9 ሚሊዮን ብር፣ ኅብረት ኢንሹራንስ 550.4 ሚሊዮን ብር፣ ኒያላ ኢንሹራንስ ደግሞ 503 ሚሊዮን ብር ዓረቦን በማሰባሰብ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ቀጥሎ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ 17ቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም የሚያሳየው፣ ሁሉም የዓረቦን ገቢያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ነው፡፡ ይህም እንደየኩባንያዎቹ አፈጻጸም የሚለያይ ሲሆን፣ በ2012 ዘጠኝ ወራት አግኝተውት ከነበረው የዓረቦን መጠን ከ1.3 ሚሊዮን ብር እስከ 139.2 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የተለየ ክስተትና ከሌላው ጊዜ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ነው፡፡

በአገሪቱ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የዕድገት ምጣኔው እጅግ አዝጋሚ ከመሆኑም በላይ፣ ለዓመታት በአማካይ በዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በታች ዓረቦን የሚሰባሰብበት ሆኖ የቆየ ነው፡፡ በ2013 ግን በዘጠኝ ወራት ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከሕይወት ኢንሹራንስ የሰበሰቡት የዓረቦን መጠን 630.2 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ይህ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ከፍተኛው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል መሆኑንም ካነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በዓመት እንኳን 600 ሚሊዮን ብር ዓረቦን የተሰበሰበበት ወቅት እንዳልነበረ የሚጠቅሱት የሥራ ኃላፊዎች፣ በዘጠኝ ወራት ከዘርፉ 630..2 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተወሰነም ቢሆን ለውጥ እየታየ መሆኑን አመላክች ነው ብለዋል፡፡

ዘንድሮ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘው የዓረቦን መጠን ከፍተኛ ነው ሊባል የሚቻልበት ማሳያ የተሰበሰበው ዓረቦን ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ በ27.5 በመቶ ማደጉ ነው፡፡

በ2012 ዘጠኝ ወራት ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰባሰበው የዓረቦን መጠን 494.4 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያሳይ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን 630.2 ሚሊዮን ብር የተገኘበት በመሆኑ በንፅፅር ሲቀመጥ የዘንድሮው  ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን በሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የማይሰጥ ነው፡፡ አሁን ካሉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ሕይወት ነክና ሕይወት ነክ ያልሆኑ ኢንሹራንሶች አጠቃለው የመድን ሽፋን የሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሥር ሲሆኑ ከእነዚህ አሥር ኩባንያዎች በዘጠኝ ወራት ከሕይወት ኢንሹራንስ ከተሰባሰበው 630.2 ሚሊዮን ብር ውስጥ 181.1 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በመሰብሰብ የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ62 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ቀጥሎ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን በማሰባሰብ የሚጠቀሱት አዋሽ ኢንሹራንስና ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ አዋሽ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 121.1 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ ደግሞ 102.2 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል፡፡

ከአኃዛዊ መረጃው መረዳት እንደሚቻለው ከአሥሩ የሕይወት ኢንሹራንስ መድን ሽፋን ከሚሰጡ ኩባንያዎች ውስጥ አንድ ኩባንያ ብቻ ከቀዳሚው ዓመት ያነሰ ዓረቦን ያሰባሰበ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ዘጠኝ ኩባንያዎች ከዘጠኝ በመቶ እስከ 62.4 በመቶ ዕድገት ያሳዩ ናቸው፡፡

እንዳነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ገለጻ፣ የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁን ደረሱበት የተባለው የዓረቦን አሰባሰብ ዕድገት ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ ለዚህም የሚሰጡ ምክንያት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የኢንሹራንስ ሽፋን እጅግ ዝቅተኛ የሚባልና በተወሰኑ የኢንሹራንስ ሽፋኖች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በመሆኑ ኢንዱስትሪው አድጓል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ዘንድሮም ከተሰበሰበው ዓረቦን ውስጥ ከ60-70 በመቶ የሚሆነው ከሞተር ወይም ከተሽከርካሪዎች የመድን ሸፋን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ኢንዱስትሪው በዓረቦን ዕድገት ብቻ አድጓል ሊባል አይችልም የሚሉም አሉ፡፡ በብዙ አገሮች እንደሚሆነው ሁሉ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ብልጫ ያለውን ድርሻ እስካልያዘ ድረስ አሁን ባለውና በአብዛኛው በሞተር ኢንሹራንስ ላይ በተንጠለጠለው የመድን ሸፋን ኢንዱስትሪው እያደረገ ነው ለማለት የሚቸግራቸው መሆኑን ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

በዘንድሮ ዘጠኝ ወራት ከቀደሙት ዓመታት ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የተጠጋ ብልጫ ያለው ዓረቦን መሰብሰቡ እርግጥ ቢሆንም፣ ይህ መጠን አሁን ላይ ካለው የብር የመግዛት አቅም ጋር ሲመዛዘን ዕድገቱ ኢምንት ሊባል የሚችል ስለመሆኑም ያክላሉ፡፡

ኢንዱስትሪውን የበለጠ ለማሳደግ አሁን ካለው የተለመደ አሠራር በመላቀቅ የመድን ሸፋኑን በተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶች መታደግ የግድ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በቅርቡ የተፈቀደው ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ታካፉልን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

የታካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት ብዙዎቹ ኩባያዎች እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ አገልግሎቱ የመድን ኢንዱስትሪን ተደራሽነት በተወሰነ ደረጃ ይቀየራል የሚል እምነት አላቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች