የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለወትሮው ከሚታወቅበት አለመረጋጋትና ግጭት አሁንም አልተላቀቀም፡፡ በአካባቢው ያሉ አገሮች እርስ በርስ አልያም ደግሞ በሚጋሩት የተፈጥሮ ሀብት፣ ወይም ድንበር አካባቢ ያሉ መቆራቆዞች በርክተዋል፡፡
ምንም እንኳን ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም የኤርትራ ጦር በትግራይ ጦርነት መሳተፉ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በመሬት ይገባናል ጥያቄ መወጠራቸው፣ ኬንያና ሶማሊያ በውኃ አካል የይገባኛል ጥያቄ መፋጠጣቸው፣ በሁለቱ ሱዳኖች መሀል ያለው መቋጫ አልባ ግንኙነትና የመሳሰሉት ፍጥጫዎች አካባቢውን ከምንጊዜውም በላይ አስከፊና አስፈሪ አድርገውታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ፣ የሱዳንና የግብፅ ተቃውም በቀጣናው ያለውን የጂኦ ፖለቲካል ሁኔታ ‹‹በእንቅርት ላይ …›› ዓይነት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በአካባቢው እየጨመረ የመጣው የውጭ አገሮች ጣልቃ ገብነትም እንዲሁ አሳሳቢ ጉዳይ ከሆነ ከራርሟል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የጦር ሠፈር ያልገነባ አልያም ለመገንባት የማይቋምጥ የመካከለኛው ምሥራቅ ወይም የአውሮፓ አገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ለአብነትም ያህል ቻይና በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ከአገሯ ውጪ በጂቡቲ ጦር ሠፈር መገንባቷ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
ልዕለ ኃያል የሚባሉት አገሮች ሩሲያም ሆነች አሜሪካ፣ ቻይናም ሆነች ቱርክ በአካባቢው ከፍተኛ ተፅዕኖ የመፍጠርና በአካባቢው የሚተላለፈውን ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ሳይታወክ እንዲከናወን፣ የየራሳቸው ቁጥጥር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡
በዚህም የተነሳ በአካባቢው አገሮች ላይ የእነዚህ አገሮች ተፅዕኖ የጎላ ነው፡፡ በተለይ በአካባቢው ያሉ አገሮች ካላቸው የኢኮኖሚ ችግር አኳያ፣ ከእነዚህ አገሮች በሚሰጣቸው ዕርዳታዎች አማካይነት ሐሳባቸውን የማስፈጸም አልያም እጅ የመጠምዘዝ አካሄዶችን ማስተዋል ይቻላል፡፡
ከዚህ አኳያ ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ በአካባቢው ባሉ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ግብፅ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አንጋፋው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማን፣ የጉብኝታቸው መጠናቀቅን ተከትሎ የሚያቀርቡት ሪፖርት በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል፡፡
ከሳምንት በላይ የዘለቀው የእኚህ አንጋፋ ዲፕሎማት የአካባቢው ጉብኝት የተጀመረው በግብፅ ሲሆን፣ በግብፅ ቆይታቸውም የአገሪቱን ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲን ጨምሮ የውጭ ጉዳይና የውኃና መስኖ ሚኒስትሮችን አግኝተው ማነጋገራቸው ተዘግቧል፡፡
በግብፅ ቆይታቸው ልዩ ልዑኩ ከሁለትዮሽ ጉዳዮች ይልቅ በዋነኛነት የተወያዩት በኢትዮጵያ እየተገነባ የሚገኘውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አሁንም ‹‹አንዲት ጠብታ ውኃ አናስነካም›› በሚለው አቋማቸው መፅናናታቸውንና ለልዩ ልዑኩም ይህን ሐሳብ ማንፀባረቃቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዘመን ወቅት አሜሪካ በህዳሴ ግድቡ ላይ ስታራምደው የነበረው አቋም በርካቶችን ማስቆጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ አሜሪካ በግልጽ በሚታይና ከዲፕሎማሲያዊ መርህ ባለፈነገጠ መንገድ ለግብፅ የወገነ አቋም በማራመዷ ኢትዮጵያ አሜሪካ በታዛቢነት ስትሳተፍበት ከነበረው ድርድር ራሷን በማግለል፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ፍላጎቷን ስታንፀባርቅ ቆይታለች፡፡ አሁንም ይህ አቋሟ እንደሆነ በማስታወቅ ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚህ አንፃር የልዩ ልዑኩ የሰሞኑ የግብፅ ጉብኝት ውስጡ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ቅሉ፣ ላዩ ግን አሜሪካ ሦስቱ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ልዩነታቸውን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማግባባት ያለመ መሆኑም ተዘግቧል፡፡
ግብፅ ግድቡ ‹‹የህልውና›› ሥጋት የሚፈጥርባት እንደሆነ በተደጋጋሚ ስትናገር የቆየች ሲሆን፣ ይህን አቋሟን አሁንም በማንፀባረቅ ላይ ትገኛለች፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያ ግድቡ ማንንም የሚጎዳ ችግር እንደሌለው አፅንኦት በመስጠት፣ አሁንም የመልማት መብቷ መከባበር እንዳለበት ትሞግታለች፡፡ እነዚህን አቋሞች ቀድመው የሚያውቁት ልዩ ልዑኩ ይህን የተካረረ አቋም አለዝበው ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርግ ወደሚችል አማካይ መንገድ እንዴት እንደሚያመጡት በሚያቀርቡት ሪፖርት፣ ወይም አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ በምትይዘው አቋም እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡
በተመሳሳይ ዓላማ ወደ ሱዳን ያቀኑት ልዩ ልዑኩ የሦስትዮሽ ድርድሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ቢከናወን፣ እንዲሁም እንዲህ ዓይነት ትኩረት የሚሻ ዓብይ ጉዳይ ላይ ሦስቱ አገሮች በቅን ልቦና የሚያከናውኑት ድርድር ወሳኝ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
በመጀመሪያው የግድቡ ግንባታ ዓመታት ከሱዳን በኩል ያን ያህል የጎላ ተቃውሞ ያልነበረ ሲሆን፣ በተለይ ለረዥም ዓመታት አገሪቱን ሲመሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በሕዝባዊ አመፅ ከሥልጣን ከተነሱ ወዲህ፣ አቋሟን ሙሉ በሙሉ በመቀየር የህዳሴ ግድቡ ሙሌት ሥጋት እንደሚፈጥርባት በመግለጽ ላይ ትገኛለች፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከልዩ ልዑኩ ጋር መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ያጋሩት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከልዩ ልዑኩ ጋር ግልጽና ወዳጃዊ ውይይት ማድረጋቸውን ከመግለጽ ባለፈ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር እየተካሄደ ባለው የድርድር ሒደት ሁሉም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ ለመድረስ ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ለልዩ ልዑኩ መግለጻቸውን ጽፈዋል፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በአስመራ ቆይታ ያደረጉት ልዩ ልዑኩ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አራት ሰዓታት የፈጀ ውይይት ማድረጋቸውን፣ የኤርትራው ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው አሳውቀዋል፡፡
አራት ሰዓታት የፈጀ ውይይት በሁለቱ መካከል መደረጉን ከመግለጽ ባለፈ፣ ‹‹ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ችግር ለመፍታት ከአሜሪካ ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን አሳውቀዋል፤›› ከማለት በዘለለ፣ በውይይቱ ወቅት የተነሱ ዝርዝር ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ግን የተብራራ ነገር የለም፡፡
ምንም እንኳን በዝርዝር የሁለቱ የውይይት አጀንዳ ይፋ ባይደረግም አሜሪካ የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ከሚጠይቁ አገሮች ተርታ የምትሠለፍ አገር ከመሆኗ አኳያ፣ አብዛኛውን ጊዜ የፈጀው ይኸው አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ በርካቶች ናቸው፡፡
ከበርካታ ዓመታት በኋላ ኤርትራን የጎበኙት ልዩ ልዑኩ ከዚህ አጀንዳ በተጨማሪም፣ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይም ሊወያዩ እንደሚችሉም የሚገምቱም አልታጡም፡፡
ስድስት ወራት ያስቆጠረውን የትግራይ ክልል ጦርነት ተከትሎ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በምታራምደው አቋም የተነሳ፣ የልዩ ልዑኩ የኢትዮጵያ ቆይታ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን የሚያስቀምጡም አሉ፡፡
በእስካሁኑ የልዩ ልዑኩ ቆይታ ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን ማግኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁለቱም በህዳሴ ግድብ የድርድር ሒደትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡
የልዩ ልዑኩ የአፍሪካ ቀንድ ጉብኝት በርካታ አጀንዳዎች የሚነሱበት እንደሆነ የተገለጸ ከመሆኑ ባለፈ በአካባቢው ባሉ የፀጥታ፣ የፖለቲካ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውስን አስመልክቶ ያሉት በርካታ ችግሮች በዘላቂ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የአሜሪካ መንግሥት ያለውን ፍላጎት ለማሳየት ያለመም ነው ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ይህ የጉብኝቱ ጥቅልና ለሕዝብ የሚነገረው ዓላማ ቢሆንም፣ የትግራይ ጦርነትና ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በሚኖራቸው ቆይታ የሚነሳ አጨቃጫቂ አጀንዳ እንደሚሆንም የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ጄፍሪ ፊልትማን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ የሚሰጡት መግለጫ ወይም የሚያወጡት ሪፖርት በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡