Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተግባራዊነት የጎደለው የኮቪድ የትራንስፖርት ዘርፍ መመርያ

ተግባራዊነት የጎደለው የኮቪድ የትራንስፖርት ዘርፍ መመርያ

ቀን:

የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ለመከላከልና ሥርጭቱን ለመቀነስ የተለያዩ መመርያዎች ይተግበሩ ቢባልም፣ ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ለወረርሽኙ መስፋፋት አንዱ ምክንያት ነው ባለው ትራንስፖርት ላይ መመርያ አውጥቶ ይተግበር ቢልም፣ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ግን ከተፈቀደላቸው ልክ በላይ በመጫንና የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም የወጣውን መመርያ ሲጥሱ ይታያሉ፡፡ ይኼም በትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ከሳሪስ ሃና ማርያም በሚገኘው መስመር ላይ ተሠልፎ ያገኘነው ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ታክሲና ሃይገር ወይም ቅጥቅጥ መኪናዎችን የሚነዱ አሽከርካሪዎች መመርያው ከመውጣቱ በፊትም ሆነ ከወጣ ጀምሮ ከተፈቀደላቸው ልክ በላይ በመጫን እንዲሁም ምሽት አካባቢ መንግሥት ካወጣው ታሪፍ በላይ በማስከፈል ተሳፋሪውን ያሰቃያሉ፡፡

ይኼም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ በመስመሩ ላይ ተቆጣጣሪዎች ባለመኖራቸው መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፣ መንግሥት ይኼንን ታሳቢ በማድረግ በአካባቢው ላይ አፋጣኝ ዕልባት በመስጠትና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን በማጠናከር የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስፋት እየተሠራጨ በመጣበት ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ሥራ መሠራቱ ግራ እንዳጋባው፣ በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠቀሙ ሰዎች ሳይኒታይዘርና ማክስ በአግባቡ አለመጠቀማቸው ወረርሽኙን ይባስ ሊያባብሰው እንደሚችል ይናገራል፡፡  

ይህ ችግር በአንድ ሥፍራ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በብዙ የታክሲ መጫኛና ማውረጃ ሥፍራዎች ላይ የሚታይ ነው፡፡ ተሳፋሪዎች ማስክ እንዲያደርጉ ከሚጠይቀው የታክሲ ረዳት ጀምሮ ከውጪ ተሳፋሪን ከሚያሳፍሩት መካከል ማስክ በአግባቡ አሊያም ከነጭራሹ የማያደርጉ በርካታ ናቸው፡፡ ታክሲ ላይ ከተሳፈሩ በኋላ ማስክ የሚያወልቁ፣ ታክሲ ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ብቻ የሚያደርጉ እንዳሉ ይታያል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ማሩ አረጋዊ እንደገለጹት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ከተፈቀደው ልክ በላይ እየጫኑ የሚገኙ አሽከርካሪዎች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህንም ለመቆጣጠር በአሥር ክፍላተ ከተማ ላይ ባለሙያዎችን በማሰማራት እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

መመርያው ከወጣበት ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ለትራንስፖርት ተጠቃሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደተሠራ አክለዋል፡፡

የሸገርና የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ኃላፊዎች ሚያዝያ 30 ቀን ባደረጉት ውይይት፣ አውቶቡሶች 70 ሰዎችን ብቻ በመጫን አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ዳይሬክተሩ አስተውሰዋል፡፡

 ሚያዝያ ወር ላይ ከታሪፉ በላይ በማስከፈል፣ ታፔላ ባለመስቀልና ትርፍ በመጫን የተያዙ አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው 5‚602 ብር መቀጣታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ቅጣት የተጣለው መመርያው ከመውጣቱ በፊት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ቅጣቱ ከተጣለባቸው አሽከርካሪዎች ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱንና ገንዘቡም ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት መመርያውን ተግባራዊ በማድረግና ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ ሰፊ ሥራ ከተሠራ ዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡

ኮቪድ-19ን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆምና ኃላፊነቱን ለመወጣት መረባረብ አለበት ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በሳሪስ፣ በቦሌ፣ በመገናኛ፣ በሃና ማርያም፣ በቃሊቲና በሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚገኙ አሽከርካሪዎች መመርያውን በመተላለፍና ከተፈቀደላቸው ልክ በላይ በመጫን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት ማየት ችሏል፡፡

ከተፈቀደው ተሳፋሪ በላይ ለሚጭኑ ሚኒባሶች 1,000 ብር፣ ለሃይገር ወይም ለቅጥቅጥ 1,500 ብር፣ ታክሲ (ላዳ፣ የሜትር ታክሲ) 500 ብር፣ ባለሦስት ወይም ባለአራት እግር ባጃጅ ወይም ሞተር ሳይክል 500 ብር ቅጣት እንደሚቀጡ መመርያው ይፋ በተደረገበት ወቅት መነገሩ ይታወሳል፡፡

ከታሪፍ በላይ ለሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎችም 1,500 ብር የሚቀጡ ሲሆን፣ አሽከርካሪም ሆነ ረዳት ማስክ ሳያደርጉ ከተገኙ 100 ብር፣ ማስክ ያላደረጉ ተሳፋሪ በሚጭኑበት ወቅት 500 ብር እንደሚቀጡም ተገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይሠራጭ ለማድረግ መመርያ ወጥቶ ለመተግበር ቢሞከርም ችግር ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ችግሩ እየታየ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...