የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሁሉም አቅጣጫ ደስታቸውን ሲገልጹ የነበረበት ሁኔታ ቢኖርም በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት ድባቡ ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ቃል የተገባው የማበረታቻና የዕውቅና ፕሮግራም ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ሌዊ ሆቴል ተከናውኗል፡፡
የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በጋራ ስለ ፕሮግራሙ አጠቃላይ ይዘት አስቀድመው ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ያኮራ ከመሆኑ ባሻገር የስፖርት ወዳድ ማኅበረሰቡን አንድ ያደረገ፣ በቀጣይ በአፍሪካ ዋንጫም ሆነ በሌሎች ውድድሮች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑ ሲነገርም ቆይቷል፡፡
ብሔራዊ ለቡድኑ አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለማለፍ ከስምንት ዓመት በፊት ሦስት አሠርታትን መጠበቅ ግድ ብሎት እንደነበር ያስታወሱት ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር፣ ዘንድሮ የነበረው ታሪክ ተቀይሮ ብሔራዊ ቡድኑ በአዲስ ምዕራፍ ተከስቷል፡፡ ይህ ዕውን መሆን ይችል ዘንድ በተለይ ለእግር ኳስ ወዳዱ ሕዝባችን መነቃቃትን የፈጠረ ቢሆንም ቀጣይነት እንዲኖረው ታዳጊ ወጣቶች ላይ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ ቡድኑ ቀጣይ ባሉት ውድድሮች ከተሳትፎ ባለፈ ጠንካራ ተፊካካሪ መሆን ይችል ዘንድ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ጠንካራ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ መሠራት እንዳለበት ጭምር መናገራቸው ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡
እንደ መግለጫው ከሆነ መንግሥት ለስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራቸው ካሉት መካከል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ትላልቅ ስታዲየሞች፣ ከሥልጠና ጣቢያ እስከ ሥልጠና ማዕከላት እንደሁም ከ26 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመጀመርያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በስፖርት ሳይንስ ሙያተኞችን ለማፍራት ሀብት መድቦ እየሠራ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው ኢትዮጵያን በቀጣይ በእነዚህና መሰል ተሳትፎዎች ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርሻን የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡