Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ በተፈጠረው የውስጥ ውዝግብ

በሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ በተፈጠረው የውስጥ ውዝግብ

ቀን:

ዋና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ታግደዋል

ተጫዋቾች መብታቸውን በሕግ ለመጠየቅ ወስነዋል

በኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ከኮቪድ-19 በኋላ ከታዩ ጠንካራ ቡድኖች ሀዲያ ሆሳዕና ይጠቀሳል፡፡ ክለቡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሊጉን ዋንጫ ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ከሰሞኑ በክለቡ ውስጥ ተፈጥሮ ለብዙዎች መነጋሪያ ሆኖ ብቅ ያለው አለመግባባት ግን የተነገረለትን ያህል እንዳይጓዝ አድርጎታል፡፡ ችግሩን ተከትሎ በርካታ ተጨዋቾች ታግደዋል፣ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡

ክለቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሆነው ችግሩ እስከ ተከሰተበት ድረስ ሲሠሩ የነበሩት አሸናፊ በቀለ ከግንቦት 04 እስከ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ማንሳቱ አሳውቋል፡፡ ክለቡ ቀደም ሲል 15 ተጨዋቾቹ ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ መውሰዱ አይዘነጋም፡፡ በዚህም በውድድር ዓመቱ ሲያሳይ የነበረው ጠንካራ የተፎካካሪነት አቅሙ እየቀነሰ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡

ክለቡ የአሠልጣኙን ስንብት አስመልክቶ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያስገባው ደብዳቤ፣ አሠልጣኙ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለማሠልጠን ውል መግባታቸውን ያትታል፡፡ ይሁንና አሠልጣኙ በክለቡ ደንብና መመርያ መሠረት ሥራቸውን ከመሥራት ይልቅ የክለቡን ሁለንተናዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ቡድኑ ወደ አላስፈላጊ ችግር ውስጥ እንዲገባ የዲሲፕሊን ጥሰት መፈጸማቸውን ያስረዳል፡፡

አሠልጣኝ አሸናፊ ጥሰዋቸዋል ብሎ ክለቡ ከዘረዘራቸው የዲሲፕሊን ጉድለቶች መካከል፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት አለመወጣት ይህም ሀዲያ ሆሳዕና በቀን 29/08/2013 ዓ.ም. ከሐዋሳ ከነማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በትክክለኛ ቦታቸው ላይ ሆነው ጨዋታውን ለመምራት ፈቃደኝነት አለማሳየት አንዱ ነው፡፡ ለአወዳዳሪው አካል ሊግ ካምፓኒውና ለክለቡ አመራሮች ክብር አለመስጠት፣ አሠልጣኙ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ የክለቡን ስምና ዝና በሚያጎድፉ ድርጊቶች ማለትም የክለቡን የውስጥ አሠራር ለመገናኛ ብዙኃን አሳልፎ መስጠት፣ የክለቡን ደንብና መመርያ አለማክበር፣ እንዲሁም ተጨዋቾችን በእኩል ዓይን አለመመልከት ሌሎቹ ምክንያቶች፡፡

የቡድኑ ተጨዋቾች በቀን 27/08/2013 ዓ.ም የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ እንደ አሠልጣኝ ፍላጎት አለማሳየት፣ ክለቡ በተለያዩ ጊዜያት በዋናነት ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ በሆቴልና መሰል ጉዳዮች ላይ ችግሮቹ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ፣ እንዲሁም ተጨዋቾች አሠልጣኞች ለሚያወጡት መደበኛ ዝግጅት ተነሳሽነት እንዲያጡ ማድረግ የሚሉትና ሌሎችንም ከዘረዘረ በኋላ ክለቡ የወሰደውን የዲሲፕሊን ውሳኔ አሳውቋል፡፡

ክለቡ ጥፋቱን ከግምት በማስገባት በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 2.8 መሠረት አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ 04/09/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከዋና አሠልጣኝነታቸው እንዲነሱ ስለመደረጉ፣ በተጨማሪም ከሚያዝያ ወር ደመወዛቸው 70 ሺሕ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ፣ ውሳኔው ከተላለፈበት ዕለት ጀምሮ ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ አሠልጣኙ ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይከፈላቸው የሚጠይቅ ዕገዳ መጣሉን አስታውቋል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ምላሻቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ከሐዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ አመራሮች ክለቡን እንዳሠለጥን ጥያቄ ሲቀርብልኝ የጠየኳቸው ጥያቄ የሥራ ነፃነት የምትሰጡኝ ከሆነ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ኃላፊነቱን የተቀበልኩትም እነዚህን እንደሚያሟሉልኝ ማረጋገጫ ካገኘሁ በኋላ ነበር፡፡ ይሁንና ቃል የተገቡት ነገሮች ብዙም ሳይቆዩ ነው ጣልቃ ገብነቱ የተጀመረው፡፡ በዚሁ መነሻነት በጥር ወር 2013 ዓ.ም. አመራሩ በሥራዬ ጣልቃ እንዳይገባብኝ የሚል ደብዳቤ ለክለቡ አስገብቻለሁ፡፡ ያም ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም፡፡ በዚያ ላይ ክለቡ ገንዘብ የለውም፡፡ ችግሩን ለማቃለል በሚል ለአንዳንድ ተጨዋቾች ከኪሴ ሳይቀር በማውጣት የከፈልኳቸው አሉ፡፡ አመራሮቹ ለምን ከፈልኩ ትላለህ የሚል ቅሬታም ያቀርባሉ፡፡ እውነት መናገር ምኑ ነው ወንጀሉ?›› በማለት ያለውን ሁኔታ የሚናገሩት አሠልጣኙ፣ ‹‹በግሌ ነፃነት በሌለበት ሁኔታ ሙያዬን ለገንዘብ አሳልፌ መስጠት አልፈልግም፡፡ ውሌ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ በውሉ መሠረት ማግኘት ያለብኝን ማግኘት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ገብቶ ውሳኔ እንዲሰጠኝ እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ተጨዋቾችን በእኩል ዓይን አይመለከቱም›› ለሚለው ክስ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ ‹‹እኔን ጨምሮ አሠልጣኞች ለሚፈልጉት የጨዋታ ስታይል ተጨዋቾችን የሚመዝኑበት የራሳቸው ምልከታ ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ መመዘኛ መሠረት አቅሙ ያለውን ተጨዋች የማልጠቀምበት ከሆነ የመጀመርያው ተጎጂ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገሮች በዚህ መልኩ ቢታዩ ነው ጠቃሚነት የሚኖራቸው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ክለቡ የዕገዳ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ተጨዋቾች ቀደም ሲል ለማትጊያ በሚል የተሰጣቸው ደረቅ ቼክ በመሆኑ፣ ይህ ማለት በሕግ ፊት ምን ዓይነት ወንጀል እንደሆነ ስለሚታወቅ  ችግሩ በውይይት ዕልባት የማይሰጠው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ የምንገደድ ይሆናል፤›› ሲሉ ነው የሚያስረዱት፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ በሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ከተፈጠረው አለመግባባትና ውዝግብ ጋር ተያይዞ ክለቡ በተጨዋችም ሆነ አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለ ‹‹ተላልፈውታል›› የተባለው የዲሲፕሊን ጥፋት ከፌዴሬሽኑ ደንብና መመርያ አኳያ ታይቶ ውሳኔ የሚሰጠው ይሆናል፡፡

ለሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ ቅርበት ያላቸው፣ ነገር ግን ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሙያተኛ ለሪፖርተር እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ‹‹ከአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር ተያይዞ ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠመው ችግር በብዙ ክለቦች ሲከሰት የኖረ ችግር ነው፡፡ የአገሪቱ ብዙዎቹ ተጨዋቾች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ ሲዘዋወሩ ከተወሰኑ አሠልጣኞች ጋር (ጥቅም ሊሆን ይችላል) ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በክለቡ ውስጥ በተለይ ለጨዋታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተጨዋቾች በዚህ ሒደት ያለፉ ለመሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ እንደ ዘርፉ ሙያተኛ አንድ አሠልጣኝ ለሚከተለው የአጨዋወት ዘይቤ (ስታይል) ተጨዋቾችን ከሚመርጥበት ሙያዊ ሒደት ጋር ፈጽሞ ግንኙነት እንደሌለው ልብ ሊባል ይገባል፡፡›› አያይዘውም በሀዲያ ሆሳዕና ውስጥ የተከሰተው ችግር የአመራሩ ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ሙያዊ አተያይ ታይቶ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚገባው ጭምር ይመክራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...