ከዊንጌት የያዝኩት ሚኒባስ ታክሲ ወደ ፒያሳ እያመራ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ብዙዎችን እያሳጣን ባለበት በዚህ አስፈሪ ጊዜ፣ ታክሲውን እጭቅ አድርገው የሞሉት ወያላና ሾፌር በዕድሜ ተቀራራቢ በመሆናቸው በማይገባን የንግግር ዘዬ እየተቀላለዱ ይሳሳቃሉ፡፡ በዚህ መሀል አንድ ትልቅ ሰው፣ ‹‹እናንተ ምናለባችሁ ሕግ እየጣሳችሁ እኛን እንደ ጌሾ ጠቅጥቃችሁ ተጫወቱብን እንጂ…›› እያሉ በምሬት ተናገሩ፡፡ ወያላው ተንጠራርቶ እያያቸው፣ ‹‹ፋዘር ታክሲና ኑሮ መቼ ሞልተው ያውቃሉ? ካልተመቸዎት እኮ ቢፈልጉ ራይድ፣ ፈረስ፣ ሄሎ ታክሲ ሞልቷል…›› እያለ ሲያሾፍ አነጋገሩ አናደደኝ፡፡ ታክሲው በትርፍ ከያዛቸው ሰዎች በተጨማሪ በዕቃ ተጨናንቋል፡፡ በስጨት ብዬ፣ ‹‹አባትህ አይሆኑም? እንዴት በእሳቸው ትቀልዳለህ? ሕግ እየጣሳችሁ መተንፈሻ አጥተን ተጣበን አንተ ታሾፋለህ?›› ስለው እየሳቀብኝ፣ ‹‹ፍሬንድ አትበሳጭ፣ ንዴት የድመትን ጀርባ ከማጉበጡ በቀር የሚፈይደው የለም…›› ሲለኝ ታክሲው በተሳፋሪዎች ሳቅ ተሞላ፡፡
ይህ ቀልደኛና ተረበኛ ወያላ እኔና አዛውንቱን ሲያሾፍብን የሌሎቹ ተደርቦ መሳቅ አናዶኝ ስለነበር፣ ‹‹ግድ የለም ቀልድ፣ ቁምነገር በተዘነጋበት በዚህ ዘመን ቀልድ በዝቶ ነው አገር መላ ያጣችው…›› አልኩኝ፡፡ በዚህ መነሻ አንዷ ዘመናይ፣ ‹‹የእኔ ወንድም አገሩ በሙሉ በኮሜዲ ፊልም ተጥለቅልቆ መሳቅ እንጂ መናደድ ዋጋ የለውም…›› እያለች ስትንጣጣ ገረመኝ፡፡ ቀልድና ቀልደኞች በዝተው ምን መናገር ያስፈልጋል ብዬ የታክሲውን ዙሪያ ገባ ስቃኝ የተለያዩ ጥቅሶች ተለጥፈዋል፡፡ ‹‹መጨቃጨቅ ከአሸባሪነት አይተናነስም››፣ ‹‹ኮሮናንና የጫማ ሽታን በጋራ እንከላከል››፣ ‹‹ሾፌሩን በፍቅር እንጂ በነገር መጥበስ ክልክል ነው››፣ ‹‹መብትዎ ታክሲ ውስጥ ብቻ ትዝ አይበለዎት››፣ ‹‹ታክሲያችን የፍቅር እንጂ የጭቅጭቅ መድረክ አይደለም››፣ ወዘተ የሚሉ ጥቅሶች ተለጥፈዋል፡፡ ከሆሊውድ እስከ ቦሊውድ አክተሮች በየዓይነቱ ምሥላቸው በብዛት ይታያል፡፡
በዓይኔ ያደረግኩትን አሰሳ ስጨርስ ከወያላው ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጠምን፡፡ ‹‹ፍሬንድ ተመቸህ?›› ሲለኝ ‹‹ምኑ?›› በማለት ጠየቅኩት፡፡ ‹‹የታክሲያችንን ሙዚየም ማለቴ ነው…›› አለኝ፡፡ ‹‹እንቶ ፈንቶውን አይቼልሃለሁ፣ የደረደርከው ሁሉ ለማንም አይጠቅምም…›› አልኩት፡፡ ወያላው የኮሜዲ ፊልም ወይም ድራማ የሚያይ ይመስል ተንከትክቶ ሳቀ፡፡ ሳቁን ሲጨርስ፣ ‹‹ፍሬንድ የአንተ ችግር ምን እንደሆነ ደረስኩበት…›› አለ፡፡ በጣም ከመገረሜና ከመደንገጤ የተነሳ፣ ‹‹የእኔ ችግር ምንድነው?›› ማለት፡፡ ወያላው አሁንም እየሳቀ፣ ‹‹የአንተ ችግር በምታየው ነገር አለመዝናናት ነው፣ በምታየውና በምትሰማው ካልተዝናናህ ድብርት አለብህ ወይም ሕመም ይኖርብሃል…›› ሲለኝ ወይ ድፍረት እያልኩ መናደድ ጀመርኩ፡፡
ያቺው ሴት፣ ‹‹ትክክል ነው፣ አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ዘና የሚያደርግ ነገር የማይፈልጉት ወይም የሚሸሹት ውስጣዊ ችግር ስላለባቸው ነው…›› ብላ ራሷን እንደ የሥነ ልቦና ባለሙያ አቀረበች፡፡ እኔና አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት ስንቀር ሌሎቹ ይስቃሉ፡፡ በዚህ መሀል ሾፌሩ፣ ‹‹ለዚህች ለማትሞላ ዓለም እየተጨነቅን ራሳችንን ድብርት ውስጥ ለምን እንደምንከት ይገርመኛል፡፡ ጥለነው ለምንሄድ የታክሲ መቀመጫና ለማይሞላው ዓለም እየተንገበገብን ራሳችንን እናቆራምዳለን፡፡ ለዚህች ከንቱ ዓለም መድኃኒቱ ፊት ሳይሰጡ ባገኙት ነገር መዝናናት ነው…›› ሲል ሌሎቹ ‹ልክ ነህ› በሚል ስሜት ሳቁለት፡፡ ዛሬ ደግሞ ሰው ምን ነክቶት ነው የሚፈላሰፈው እያልኩ ተገርሜያለሁ፡፡
የታክሲው ሾፌር፣ ወያላውና ሌሎቹ ተሳፋሪዎች ዓለምን ንቀው ሲደሰኩሩ አዛውንቱ ወደኔ ጠጋ ብለው፣ ‹‹ልጄ አትበሳጭ፣ ይኼ ሁሉ ወፈ ሰማይ እኮ የውስጡን ጭንቀት ለማስተንፈስ ሲል ዝባዝንኬውን ቢለፈልፍ እውነት እንዳይመስልህ…›› እያሉኝ ሳለ አንዱ የተደወለለትን ስልክ አንስቶ፣ ‹‹ኧረ እባክህ? መቼ? አሁን?…›› እያለ በድንጋጤ ይርበተበት ጀመር፡፡ ስልኩን ዘግቶ፣ ‹‹ሾፌር እስቲ ሬዲዮ ክፈት…›› እያለ ሲጮህ ሁላችንም በድንጋጤ ምን ተፈጠረ ብለን ዓይናችን ፈጠጠ፡፡ ሾፌሩ በፍጥነት የኤፍኤም ጣቢያዎችን ሲጎረጉር ዘፈን ብቻ ነው የሚደመጠው፡፡ በመጨረሻ አንደኛው ጣቢያ ሙዚቃውን አቁሞ አንዲት ታዋቂ ኢትዮጵያዊት በኮሮና ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን ተናገረ፡፡ ድንጋጤ ነው መሰል ታክሲያችን በፀጥታ ተሞላ፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና እኚህ ሴት በተለይ የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ልጆችን ሕይወት የቀየሩ መሆናቸው ስለሚታወቅ፣ ሁላችንም በድንጋጤ ነበር ዜናውን የሰማነው፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነገር ሲገጥም ማዘን ያለ በመሆኑ አንገቴን ደፍቼ ተከዝኩ፡፡
በፀጥታው መሀል ያቺ ሴት፣ ‹‹ፊጣሪዬ ይቅር በለን፣ ስናውቅ በድፍረት ሳናውቅ በስህተት ለምንሠራው ሥራ ሁሉ ይቅርታህ አይለየን..›› እያለች ስትማፀን፣ ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹ምን ዓይነት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው እባካችሁ?›› ማለት ጀመረ፡፡ ሾፌሩ፣ ‹‹በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ምን እንደምል ግራ ይገባኛል…›› እያለ ሲናገር ሌሎቹ ከንፈራቸውን እየመጠጡ ተክዘዋል፡፡ ፒያሳ ደርሰን ታክሲው ሲቆም አዛውንቱ፣ ‹‹ልጄ አየህ አይደል? የብዙዎች ፉከራ ከአንገት እንጂ ከአንጀት ባለመሆኑ ብዙም አትገረም…›› ብለውኝ ሲሰናበቱኝ፣ ‹‹እኛ እኮ የአንድ አገር ሰዎች ብንሆንም እንደ አንድ ቤተሰብ ስለሆንን ቀልዳችንን፣ ቁጣችንንና የተለያዩ ፍላጎቶቻችንን በልክ ብናደርግ የሚያስቸግረን ነገር የለም፡፡ የሚያምርብን አንተ ትብስ አንቺ ስንባባል ነው…›› ካሉ በኋላ አቅፈው ስመውኝ ተለያየን፡፡ እንዲህ ነው አባትነት፣ ወገንነት፣ ትልቅ ሰውነት፡፡
(መሳፍንት በዛብህ፣ ከዊንጌት)