በአኅጉራችን አፍሪካ የአገር መሪን መምረጥ ማለት እጅግ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ፣ አንድ መሪ በከፍተኛ ሁኔታ በቅድሚያ በደንብ ታስቦበት ሊመረጥ ይገባል፡፡ የአገር መሪ መምረጥ ማለት እናትና አባት እንደ መምረጥ ስለሆነ፣ ከውሳኔ በፊት በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ወደ ኋላ ተመልሰን ያለፉትን መሪዎቻችንን ስናይ የማንወቅሳቸው የሉም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት የሥልጣናቸው ገደብ ግልጽ ባለማስቀመጣችን፣ በእኛ ጥፋት እነሱን ስንወቅስ ቆይተናል፡፡ ይህ ጥፋት እንዳይደገም በዚህ ዓመት ብሔርን መሠረት ያደረገ መሪ ሳይሆን፣ ጠንካራና ለአንድነታችንና ለሰላማችን በትጋት የሚሠራ ኢትዮጵያዊ መሪ መምረጥ ይኖርብናል፡፡ ይህም መሪ ባልተሰጠው ጉዳይ ሥልጣን ከጨረሰ በኋላ ከመውቀስ የሚጠበቅበትን የሥራ ድርሻ በቅድሚያ አፅድቀን፣ በኋላ ሲመረጥም ይህን በመሃላው ሊያፀድቀው ይገባል፡፡ ይህን የማይቀበል መሪ ሊመረጥም አይገባም፡፡
- የሚመረጠው መሪ ከሁሉም በላይ የአገር ሰላም ማስጠበቅ አለበትና ብቃት ያለው መሪ ሊሆን ይገባል፡፡
- የአገሪቱን ዳር ድንበር በትጋት ብቃት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡
- የአገሪቱ ሕጎች የሚያሻሽል ከሆነ በፓርላማ ቢያንስ በ2/3ኛ ድምፅ በማፅደቅ ያስፈጽማል፡፡
- የዜጎች በየትም ክልል የመኖርና የመሥራት ዋስትና ማስጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በየትኛውም ቦታ ችግር ተከስቶ ለልመና እጅ ከመዘርጋት ከፍተኛ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
- ሁሉንም ብሔሮች በቅንነትና በእኩልነት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡
- በሁሉም ክልሎች ከብሔርተኝነትና ዘረኝነት ለማጥፋት ጥረት የሚጠበቅበት ሲሆን የሁሉንም ብሔሮች ባህል ማጠናከር አለበት፡፡
- የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሻሻልና ለማሳደግ ያላለሰለሰ ጥረት የሚያደርገው መሪ ሊሆን ይገባል፡፡
- በአገሪቱ ሙስናንና የፍትሕ መጓደል ላይ ጥብቅ ዕርምጃ የሚወስደው መሪ ሊሆን ይገባል፡፡
- በአገር ለልማትና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ያላለሰለሰ ጥረት መደረግ አለበት፡፡
- የመንገድ፣ የውኃና የመብራት፣ እንዲሁም ሌሎች ሕዝባዊ አገልግሎቶች በጥራት ለማድረስ የሚጥር ሊሆን ይገባል፡፡
- የትምህርትና የጤና ተቋማት በጥራት በሁሉም ክልሎች ለማዳረስ ብቃት ያለው መሪ ሊሆን ይገባል፡፡
- የአገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር መሪ ሊሆን ይገባል፡፡
- ከላይ የተዘረዘሩትን ለማስፈጸም ሚኒስትሮችን በመመልመል በምክር ቤት ያፀድቃል፡፡
- የአገሪቱ ምርጫ ታማኝነት እንዳይጓደል ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡
- የአገልግሎት ዘመኑ ቢጠናቀቅም ሥልጣኑን በሰላም ያስረክባል፡፡
በአጠቃላይ መምረጥ ያለብን መሪ እነዚህን ነጥቦች የሚያሟሉ ሲሆን፣ እንደ አንድ ዜጋ ለአገሪቱ ሰላምና ዕድገት ባለን ፍላጎት እነዚህን አስተያየቶች አቅርቤያለሁ፡፡ እነዚህን በስፋት በመገምገምና በማሻሻል ለአገራችን መሪ መምረጥ እንደ አንድ መመርያ ብንጠቀም፣ ለአገራችን ሰላምና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ስለሆነም የተከበረው ምክር ቤት ይህን ጉዳይ በጥልቀት በማየት ከምርጫ በፊት ውሳኔ ቢያገኝ ይመረጣል፡፡
ስለተመራጭ መሪ የአገልግሎት ዘመን
ይህ መሪ ለአምስት ዓመታት ይመረጣል፡፡ ተወዳጅ መሪ ከሆነ ግን ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ ሊወዳደር ይችላል፣ ግን ለሦስተኛ ጊዜ ሊመረጥ አይገባም፡፡
(ዱቤ ጡሴ (ዶ/ር)፣ ከአዲስ አበባ)