Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ...›› የኢትዮጵያ ባንኮች ነገር

‹‹የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ…›› የኢትዮጵያ ባንኮች ነገር

ቀን:

በስንሻው ወገኔ

አገራችን በነፃ ገበያ የሚመራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደምትከተል ስታውጅ በወቅቱ ከነበረው አንፃራዊ አቅም አኳያ ትልቅ ሊባል የሚችል ካፒታል ይዘው ገበያውን የተቀላቀሉት ባንኮች ናቸው፡፡ ባንኮቹ ኢኮኖሚውን ለመቀላቀል የወሰዱት ዕርምጃ ገበያውን ከማሳለጥ፣ የተቀየዱ የአሠራር ሥርዓቶች ከማዘመን፣ በተለይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ የኢንቨስትመንት መስኮች የአገራችንን ኢኮኖሚ ደፍረው እንዲቀላቀሉ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወተው ገንቢ ሚና በሒደት እያደገ ቢመጣም፣ ራሱን በአዳዲስና ዘመናዊ አሠራር እያጎለበተ፣ እንደ አዲስ አሠራሮችንና አገልግሎቶችን ሰርቪሶችን እየቀረፀ አዳዲስ ደንበኞችን በመሳብ ዕድገቱን በሚፈለገው መጠን ማመጣጠን አልቻለም፡፡

ለዚህም ምንም እንኳን የሥራው ባህሪ ቢሆንም በአንድ በኩል ብሔራዊ ባንክ ኢንዱስትሪው በሚፈልገው የዕውቀት፣ የአቅምና የብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘት፣ አቅጣጫ ከመስጠት ይልቅ ክልከላና ቁጥጥር ላይ ብቻ ከሚገባው በላይ ማተኮሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባንኮች ከባንኮቹ አመራሮችና ከአክሲዮን ባለቤቶች ጋር ባለው የትርፍ ተጋሪነትና ከተወካይ ወካይ (Agent Principal) ጋር በተያያዘ ሚናቸው ተገቢውን አገልግሎት ሰጥቶ ተገቢውን ክፍያ ማግኝት ሳይሆን፣ ወደ ስግብግብነት የተጠጋና አንዳንዴም ኃላፊነት የጎደለው ትርፍ የማግበስበስ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየተንሰራፋ መምጣቱ፣ ባንኮቹ የተገኘውን ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመው ሕገወጥ አሠራር ሁሉ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል፡፡ ባንኮች ከገንዘብና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር ካላቸው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ቁጥጥር (Monopoly and Control) አኳያ አካሄዳቸው በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አደገኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የሚያገኙበት አቅም ላይ ለመድረስ የብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠሪያ ሥልቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ የምናያቸው የፋይናንስ ተቋማት ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ሊገኙ ይችሉ እንደነበር ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ይህ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ታክሎበትም ቢሆን የባንክ ኢንዱስትሪው በተለይ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የሚታየው አሳሳቢ ክፍተት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ የሚያሠጋ ነው፡፡ ዶላር በድርድር ከተፈቀደለትና ተራ ካልያዘ ደንበኛ ጋር በጥቁር ገበያ ዋጋ ተደራድሮ መሸጥና ለራስ በዶላር እስከ አንድ ብር የሚደርስ ኮሚሽን መውሰድ፣ ተራ ጠብቆ የውጭ ምንዛሪ ከማቅረብ ይልቅ ተቀማጭን በመያዣነት መደራደሪያ ማድረግ፣ በተለያየ መንገድ በደላላ፣ በዝምድና፣ በወዳጅነትና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አማካይነት የእጅ መንሻ በመቀበል የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሸሽና ባልተቀመጠ የውጭ ምንዛሪ ኤልሲ መክፈት የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ሰሞኑን የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ባንኮች መንግሥትን ጨምሮ 200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እጅግ የዘገየና አስተማማኝ ያልሆነ የኤልሲ ክፍያ ዕዳ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ዕዳ የተከማቸው ላኪው ድርጅት ኤልሲ ከተከፈተና ዕቃውን ከላከ በኋላ ከባንኩ ጋር ባለው ስምነት መሠረት ክፍያ ሳይፈጸምለት እስከ አንድ ዓመት ድረስ በመቆየቱ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር አስመጪው በብር የውጭ ምንዛሪውን ተመጣጣኝ ለባንኩ ከፍሏል፡፡ ባንኩ ተገቢውን ኮሚሽንና የአገልግሎት ክፍያውን ወስዷል፡፡ ዕቃውም ለአስመጪው ደርሷል፡፡ ላኪው ክፍያውን የነፈገው ባንኩ መሆኑ ነው፡፡

በዚህ መንገድ ክፍያ በወቅቱ ባለመድረስ በላኪና በአስመጪ መካከል የሚነሱ ውዝግቦች አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በተለያየ ጊዜ ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ባንክና ለመንግሥት የተለያዩ አካላት አቤት ቢባልም፣ ባንኮቹንርዓት ማስያዝ ግን አለመቻሉ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ የአገራችንን ገጽታ ከማጥፋቱም በላይ ላኪ ድርጅትና አስመጪዎችን የሚያቆራርጥ፣ አቀባባይ ባንኮችን የሚያሳጣና የውጭ ግብይት ሥርዓታችንን ሊያዛባ የሚችል አደገኛ የስግብግብነት አካሄድ ነው፡፡

ከላይ እንዳነሳሁት የባንክ ኢንዱስትሪውን የሚጎረብጡ አንዳንድ መመርያዎችና ፖሊሲዎች የመኖራቸውን ያህል፣ የባንክ ኢንዱስትሪው መስመር እንዳይስትና ለአገር ውድቀት ሰበብ እንዳይሆኑ ለማድረግ እስካሁን ተግባራዊ ሲያደርገው የነበረውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠሪያ ሥልት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመመርመር፣ በማዘመንና አሠራሩን በዕውቀትና በአቅም ላይ የተመሠረተ ማድረግ አለመቻሉ፣ ባንኮቹ መሠረት በሌለውና በስግብግብነት ላይ ብቻ በተንጠለጠለ የትርፍ ህዳግ ጉጉት ላይ ተመሥርተው ተቋሙን መጫወቻ እንዲያደርጉት ከመሆኑም በላይ፣ ለናረ የግል ጥቅማቸው የአገርን ጥቅም ቅስ በቀስ በመሸርሸርገርና ሕዝብን በሚጎዳ መልኩ ለኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል እየዳረጉን ነው (ጋዜጣው ከተባበረ፣ የባንክ ከፍተኛ አመራሮች የደመወዝ፣ጥቅማ ጥቅም፣ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና አጠቃላይ ክፍያ በሚመለከት ራሱን ችሎ ተገቢው ትንታኔ ሊቀርብት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን በዚህ ጉዳይ ትንታኔ እንዲሰጡበት እጋብዛለሁ)፡፡

በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባንኮቹ አሳሪ የሚሏቸው፣ ነገር ግን ሥርዓተ አልበኛነትንና አልጠግብ ባይነትን የሚገቱ፣ በሒደት ባንኮችንም ሆነ አገሪቱን የሚጠቅሙ አንዳንድ ሕጎችብሔራዊ ባንክ በኩል ተሻሽለዋል፡፡ በተለያየ ደረጃ ማሻሻያ የተደረገባቸው መመርያዎችና ሕጎችም 70 በላይ ደርሰዋል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ መሪዎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመራሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው፣ ለኢንዱስትሪው ዕድገት በሚበጁ አጀንዳዎች ላይ የመወያየት ዕድል ሁሉ እስከ መፍጠር መድረሱም በራሱ እንደ መልካም ዕርምጃ የሚታይ ዕድል ነው፡፡ በአጭሩ ቁጥጥሩ እንዳለ ሆኖ ይብዛም ይነስም የመደማመጥ ዓውድ ተፈጥሯል፡፡ እኔ የበላይ ነኝ ብሎ እንደ ቀድሞው ጫና ያሳድራል ብሎ ለመግለጽ አይቻልም፡፡ እንዲያውም ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያለ ዕርምጃ ወሰደ እየተባሉ ይነገሩ የነበሩ ዜናዎች ያለ መሰማታቸው በራሱ ለውጡን ያሳያል፡፡ ኢንዱስትሪው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ እየተደረገ ነው፡፡

ኢንዱስትሪውን የበለጠ ጤናማ ለማድረግና የተሻለ እንዲሆን ግን አሁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ግድ ይላል፡፡ ጊዜ የሚወልዳቸውን ችግሮች በመገንዘብ ተስማሚ የሆነ አሠራር መዘርጋት የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ጡንቻዬን እዩልኝ ለማለት ሳይሆን አግባብ ባለው ሁኔታ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሊፈጠር የሚችውን ችግር በመፈተሽ፣ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን ማከናወን አለበት፡፡
ይህንን ለማለት የወደድኩትና ጉዳዩን ወደ መሬት ለማውረድ የፈቀድኩት፣ ከሰሞኑ አንድ የግል ባንክ 2012 በጀት ዓመት ያገኘውን ትርፍ ለባለአክሲዮኖች ማከፋፈል እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕገዳ ከመጣሉ ጋር ተያይዞ ችግር መኖሩ ይታያል ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡

ባለፉት 25 እና 26 ዓመታት ውስጥ የአንድ ባንክ ትርፍ ክፍፍል ድርሻ እንዲታገድ ከብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ሲሰጥ የመጀመርያ ባይሆንም፣አንድናሁለት ጊዜያት በጊዜያዊነትም ቢሆን ከተለያዩ ችግሮች በመነሳት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትርፍ ክፍፍል ዕግዶች የተላለፉበት ጊዜ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

ከሰሞኑ እንደተሰማው ደቡብ ግሎባል ባንክ የበጀት ዓመቱ የትርፍ ክፍፍል እንዳይፈጸም ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ የሰጠው፣ ባንኩ በተለያዩ ጊዜያት በተከፈተ ኤልሲ የተፈቀደ የውጭ ምንዛሪ ከኢትዮጵያ ውጭ ሊከፈል ለሚገባው ኩባንያ በወቅቱ ካለመከፈሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በወቅቱ ክፍያው አለመፈጸሙ ደግሞ ባንኩን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርገዋል፡፡ እዚህ ላይ ግን መታሰብ ያለበት ባንኩ መፈጸም የሚገባውን ክፍያ ተግባራዊ አለማድረጉ ባንኩ ላይ የሚፈጥረው ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገሩን ከፍ ካደረግነው ደግሞ እንደ አገር በኢትዮጵያ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ያለው ችግር ግን የአንዱ የደቡብ ግሎባል ባንክ ብቻ ችግር አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ዛሬ የደቡብ ግሎባል ባንክ አፍጥጦ ወጣ እንጂ፣ ችግሩ የሰነበተ ስለመሆኑም እየተሰማ ነው፡፡ ባንኮች የሚገባንን ክፍያ ሊፈጽሙልን አልቻሉም ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ መሰማቱ አዲስ አይደለም፡፡ እንዲያውም ለብሔራዊ ባንክ ሳይቀር አቤት ያሉ እንዳሉም ይገለጻል፡፡ ስለዚህ ችግሩ አለ ማለት ነው፡፡ ችግሩ የሁሉም ነው፡፡ ችግሩ ለአገርም ሥጋት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ሊያሳስብ እንደሚገባና ብሔራዊ ባንክ ይህን ክፍተት በትኩረት መመልከት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡

እስካሁን ለዚህ ጉዳይ ለምን መፍትሔ አላበጀም የሚለው ጥያቄም አንድ ያደርገናል፡፡ አንድ ኤልሲ ተከፍቶለት ግብይቱ ተፈጽሞ ወደ አገር የገባ ምርት ሒሳብ መወራረድ ያለበት በአምስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ አሁን በብዙ ባንኮች እየታየ ነው የሚባለው ግን በአምሰት ቀናት መክፈል ያለበት ክፍያ ሳይከፈል ዓመታት እያስቆጠረ እየሆነ ነው፡፡ ይህ እየታወቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ዕርምጃ አለመውሰዱ ያመጣው ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ማንኛውም ባንክ በሌለው የውጭ ምንዛሪ የሚከፈተው ኤልሲ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ክፍያ ለሚፈልገው የውጭ ኩባንያ ካልተከፈለ የአገርንም ስም ያስነሳል፣ እየተነሳም ነው፡፡

ክፍያው ሳይፈጸም ከሦስት ወራት በላይ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ምን ይጠብቅ ነበር? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንኮች በወቅቱ ላለመክፈል ከሥር ከሥር ብዙ ኤልሲ እየከፈቱ መዝለቃቸው ዋነኛ ምክንያት ሲፈተሸ አንድ ሁለት ገፊ ምክንያቶች ልብ እንዲባሉ ያስገድዳል፡፡ ይህም ባንኮች ለከፈቱት ኤልሲ በወቅቱ ክፍያ ላለመክፈታቸው አንዱ ምክንያት የባንኮች ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔያቸው ከፍ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ ጭምር የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ አልሲውን በመክፈት የሚገኘውን ኮሚሽን ትርፋቸውን ለማሳደግ ይጠቁሙበታል መባሉ ለጆሮ ደስ አይልም፡፡ ለእነርሱም አደጋ መሆኑን እያወቁ ማድረጋቸው ደግሞ ለምን ያሰኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ባንኮች ወደ በጀት ዓመቱ መጨረሻ፣ በሌላቸው የውጭ ምንዛሪ ኤልሲ ከፍተው በኮሚሽን የሚያገኙትን ገቢ እንደ አንድ የትርፍ ማሳደጊያ የሚጠቀሙበት ዋና ምክንያት ደግሞ፣ ወደ ችግሩ ሁለተኛ ገፊ ምክንያት ይወስደናል፡፡ ለምን እንዲህ ይፈርጃሉ ከተባለም በሁሉም ባንኮች ባለአክሲዮኖች ከፍ ያለ ትርፍ አገኘን ለማለት ነው፡፡

ዛሬ ደግሞ ባለአክሲዮኖች የኢንዱስትሪውን ፈተና ከግምት ባለማስገባት የትርፍ ክፍፍላቸው ሲያንስ ስላልሠራችሁ ነው፣ ለምንድነው ትርፋችን የሚቀንሰው ብለው የሚሞግቱ ስለሆነ፣ በዚህ ፍራቻ ስህተቶች ሲፈጽሙ እናያለን፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች በእርግጥም ትርፍ ይሻሉ፡፡ ሁሌም ግን ትርፍ ላይኖር ወይም በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ የማንኛውም ድርጅት ዓላማ ትርፍና ትርፍ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ሀብት ላይ እየወሰኑ ከለላ የሚደረግላቸው ተቋማት ከትርፍ በላይ የሞራልና የሕግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ባለአክሲዮኖችም ሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ተግባራቸው ‹‹የስሙኒ ዶሮ የአንድ ብር ገመድ ይዛ ጠፋች››ራቸው እንዳይሆን፣ ጫናቸው ከአገራዊ ጉዳትን ጥቅም አኳያ መመዘን አለባቸው፡፡

በእርግጥእነዚህ ገፊ ምክንያቶች ባሻገር ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዙ ያሉ ችግሮች ዋነኛ መንስዔ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ከውጭ የሚገባ መርፌ ሳይቀር ዶላር ይፈልጋል፡፡ ባንኮች እንደ ምንም ካገኟት የውጭ ምንዛሪ ላይ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ 30 በመቶ የእኔ ድርሻ ነው ብሎ ባወጣው አስገዳጅ መመርያ መሠረት ይቀበላቸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር በሆነበት አገር 30 በመቶ መውሰድ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ሲጠቃለል ግን የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዙ አሠራሮቻቸው ተገደውም ሆነ ሆን ብለው እየፈጸሙዋቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ አገር አደጋ እየሆነ ስለመምጣቱ አጥብቆ መናገር ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ ባንኮች ለውጭ ኩባንያዎች እንዲከፍሉ ግድ የሆነባቸውን ክፍያ ባለመፈጸማቸው፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር መሥራት አንፈልግም እስከ ማለት የደረሱበት ሁኔታ ይሰማል፡፡ ይህ መስተካከል ካልቻለ አደጋው የበረታ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዓለም የግብይት ሥርዓት ውስጥ የአገር ስም እየተነሳ ነው ማለት ነው፡፡ ውሎ አድሮ የሚፈለግ ምርት ወደ አገር እንዳይገባ እንቅፋት ይሆናልና ችግሩ ገዝፎ የማንወጣው ችግር ውስጥ ከመግባት በፊት ብሔራዊ ባንክ ሁኔታውን መርምሮ መስመር ማስያዝ አለበት፡፡

አሁን ችግሩ የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለመሆኑ እየታየ ነውና ድብብቆሹን በማቆም ተነጋግሮ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ጉዳይ ለውጭ ኩባንያዎች መከፈል ያለበት የውጭ ምንዛሪ በዘገየ ቁጥር፣ የሚባክነው የውጭ ምንዛሪ ብዙም ሳይታሰብበት የቆየ ነው፡፡ በመከራ የሚገኝን ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪን የሚመለከቱ ሕግጋቶቻችንን፣ ብሎም አሠራሮችን በመፈተሽ ነገሮችን ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ አለ የሚባለው ችግር እንደ አገርም አደገኛ መሆኑን በማሰብ ብሔራዊ ባንክን ጥቅሙ የጥቂት ስግብግብ ትርፍ አዳኞች፣ ጉዳቱ ደግሞ የአገርና የሕዝብ ስለሆነ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ባንኮችና እፍኝ የማይሞሉ የባንክ ከፍተኛ አመራሮችገር ወደ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንድታመራና ገጽታዋ እንዲበላሽ በር እንዲከፍቱ መደረግ የለበትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...