በጌታቸው አስፋው
ምንም እንኳ የ1997 ዓ.ም. ያህል የተጋጋለ ባይሆንም፣ በዘንድሮው የምርጫ ክርክርም የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢኮኖሚ ፕሮግራማቸውን ከማስተዋወቅ አንስቶ በሚከተሉት ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ከጋዜጠኞች በሚነሱላቸው ጥያቄዎች መሠረት ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃዎች በሚደርሱ ጊዜያት መልስ እየሰጡ በመከራከር ላይ ይገኛሉ፡፡ የሙግቶቹ ብመረጥ ይህን እሠራለሁ፣ ያን እሠራለሁ አቀራረብ ዓይነቶች በቅርቡ በትራምፕና በባይደን ክርክር መንፈሶች የተቃኙ ይመስላሉ፡፡ እነርሱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምርጫውን ከጨረሱ ምዕተ ዓመታት ያስቆጠሩ ስለሆኑ በይህን እሠራለሁ፣ ያን እሠራለሁ ክርክር ሊገላገሉ ይችላሉ፡፡ የእኛው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምርጫ ያልተገባደደበት ክርክር ግን፣ በፖለቲካል ኢኮኖሚው ምርጫ ላይ ቢያዘነብል ይበልጥ በተደሰትኩ ነበር፡፡
እኔም ከተዘጋጁት የክርክር መድረኮች በሁለቱ የመከራከር ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ አንዱን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር በትብብር በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ባዘጋጀው፣ ሁለተኛው ደግሞ አሀዱ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ በድሬዳዋ ሳምራት ሆቴል ባዘጋጀው ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡
በተሰጡት ሦስትና አምስት ደቂቃዎች በግል ውስጣችን የታመቀውንና በቡድን ፓርቲዎቻችን በፕሮግራም የያዙትን በወራት እንኳ አብራርቶ ለመግለጽ የማይቻልባቸውን የኢኮኖሚ ጉዳዮች መግለጽ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ፣ አድማጭም ሆነ አንባቢም ይረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ በግሌ አንዳንድ ያነሳኋቸውን ጉዳዮች በኅትመት ሚዲያው አብራርቼ ለንባብ ከማቅረብ የሚከለክለኝ ሕግ አለ ብዬ አልገምትም፡፡
በአዲስ አበባ ባደረግሁት ሙግት ብልፅግና በፕሮግራሙ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎትና አቅርቦት ሊጣጣሙ ያልቻሉትና የዋጋ ውድነቶች የተከሰቱት፣ ኢሕአዴግ ባሳለፋቸው ሰላሳ ዓመታት ፍላጎት ላይ አትኩሮ ስለሠራ ስለሆነ፣ ብልፅግና በሚቀጥሉት ዓመታት አቅርቦት ላይ አትኩሮ እንደሚሠራ በፕሮግራም መያዙ ትክክለኛ መስመር አለመሆኑን ለማስረዳት፣ በገጠር ገበሬው ውኃ በጣሳ እየጠጣ፣ ምግብ በሰፌድ እየተመገበ፣ መደብ ላይ እየተቀመጠና መሬት ላይ እየተኛ እንደምን ፍላጎት ተሟልቷል ብለን ልንል እንችላለን በማለት የሞገትኩ ሲሆን፣ በከተሞችም ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ ያሉትን ልዩነቶች ለአብነት ያህል አቅርቤያለሁ፡፡
በከተሞች ስላለው የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ሁለት ክፍለ ከተሞችን ቦሌንና ኮልፌን በማነፃፀር ቦሌ ቢጫ ታክሲ እንዳለና የኮልፌው ሚኒባስ እንደሆነ፣ ቦሌ የአዳዲስ ልብሶች መሸጫ ሞሎች እንዳሉና የኮልፌው የልባሽ ጨርቆች መሸጫ የጨረታ ገበያ እንደሆነ፣ ቦሌ ሱፐር ማርኬቶች እንዳሉና የኮልፌዎቹ ጉልት ገበያዎች እንደሆኑ፣ ቦሌ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች እንዳሉና የኮልፌ ሆቴሎች በላስቲክ የተሠሩ ሻይ ቤቶች እንደሆኑ ጠቃቅሼ በጊዜ እጥረት ምክንያት የቦሌውን ሀምበርገርና የኮልፌውን ጮርናቄ ቁርስ፣ አንዲሁም የቦሌውን የሦስት መቶ ብር ሽሮ ተጋቢኖ ምሳና የኮልፌውን የሰላሳ ብር ሽሮ ፈሰስ ምሳ ሳላነሳ ቀርቼያለሁ፡፡ የረጅም ሰዓታት ሙግት ቢኖረን ኖሮ ዕልፍ አዕላፍ የኑሮ ደረጃ ልዩነቶችን ማንፀባረቅ ይቻል ነበር፡፡
በተሰጡኝ የሦስትና የአምስት ደቂቃ ጊዜያት በግል እምነቴ የሆነውንና ፓርቲዬም እንደ መርህ በያዘው ከዓመታት በፊት ጀምሮ ፍላጎትና አቅርቦት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ስለሆኑ፣ ለአንዱ ትኩረት ሰጥቼ ለሌላው ትኩረት እነሳለሁ የሚባሉ እንዳልሆነ የብልፅግና ተከራካሪዎችን ልሞግት ሞክሬያለሁ፡፡ ለእኔ ያነሱኝ ሦስትና አምስት ደቂቃዎች ለእነሱም ስላነሷቸው አቅርቦት ላይ አትኩረን እንሠራለን ሲሉ የቦሌውን ቢጫ ታክሲ አቅርቦት ይሁን ወይም የኮልፌውን ሚኒባስ አቅርቦት፣ የቦሌውን ሱፐር ማርኬት ይሁን ወይስ የኮልፌውን ጉልት ገበያ አቅርቦት፣ የቦሌውን ሞሎች ይሁን ወይስ የኮልፌውን ጨረታ፣ የቦሌውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ይሁን ወይስ የኮልፌውን ሻይ ቤት መልስ ለመስጠት የሚበቃ ጊዜ አላገኙም፡፡
ለገበሬው ውኃ መጠጫና ምግብ መመገቢያ ብርጭቆና ሳህን አቅርቦት ላይ ይሁን፣ ወይስ ለንግድ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩት በግልጽ ሊያመለክቱ አልቻሉም፡፡ እንዲያው በደፈናው የገበያውን የፍላጎትና የአቅርቦት ሥራ በአዛዥነት መንፈስ ተክተውት እንደሚሠሩ ከመግለጽ በቀር፣ አቅርቦት ላይ እንሠራለን ሲሉ የየትኛውን ገበያ አቅርቦት ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ በሠራተኛ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት የሠራተኛውን አቅርቦት ተክተውት አቅራቢ ሊሆኑ ይሆን? በካፒታል ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት ገበያውን ተክተው የካፒታል አቅራቢ ሊሆኑ ነው? ወይስ የምርት ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት በእነዚህ ግብዓተ ምርቶች ፍላጎትና አቅርቦት ላይ እንደሚመሠረት ሳይገለጽላቸው ቀርቶ ነው?
በድሬዳዋው ሙግቴም ከፓርቲዬ የኢኮኖሚ ፕሮግራም መስመር ሳልወጣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የገበያ ውዝግብ የተፈጠረው መንግሥት ገበያውን እኔ አዘዋለሁ ብሎ፣ ሸማቹንም ሆነ አምራቹን እንዲሁም የገበያውን በውስጣዊ ኃይሎች ተመርቶ የመከናወን ጥበብ በውጪያዊ አላዋቂ ጣልቃ ገብነት መበጥበጥ ከጀመረበት ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ፣ ይህም እስከ ዛሬ 2013 ዓ.ም. ድረስ እንደ ቀጠለ፣ ገበያው ከቀን ወደ ቀን በሸማቹና በአምራቹ ምክንያታዊነት (Rationality) በመዳበርና በመሻሻል ፋንታ በሸማቹና በአምራቹ ምክንያተ ቢስነት (Irrationality) ቀጭጮ፣ ሸማቹንም አምራቹንም ግራ አጋብቶ እንዳይናበቡና ለተወሰኑ ቀናት እንኳ በጋራ ቋሚ የገበያ ማጣሪያ ዋጋ (Market Clearing Price) ፈጥረው እንዳይገበያዩ ማድረጉን፣ በነበሩት የሦስትና የአምስት ደቂቃዎች ላብራራ ሞክሬያለሁ፡፡
ለሙግቴ እንደ ቁልፍ ቃላት አድርጌ የመረጥኳቸውም አዛዥ፣ ታዛዥና አጋዥ የተሰኙ ቃላትን ነው፡፡ ኢኮኖሚ መነሻ ሀብትን በምርት ዓይነት ደልድሎ ምርት ማምረትና የተመረተውንም መከፋፈል ስለሆነ፣ በሀብት ድልድሉና በሚመረተው ምርት ዓይነት ምርጫ የአዛዥነት ሚና ያለው ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ ለአምራቹ የሚከፍለውና በተለምዶም “ደንበኛ ንጉሥ ነው” የተባለው ሸማቹ ሲሆን፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር በሚወሰነው ዋጋ የሸማቹን ትዕዛዝ ተቀብሎ የሚሰማራበትን የሥራ ዘርፍ መርጦ፣ የሚያመርተውና የሸማቹን ገንዘብ የራሱ ለማድረግ እርስ በራሱ የሚወዳደረው አምራቹ ትዕዛዝ ተቀባይ እንደሆነ ገልጬ፣ የመንግሥት በግል ኢኮኖሚው ውስጥ የቁጥጥርም ሆነ የድጋፍ አገልግሎት ለሸማቹም ሆነ ለአምራቹ የአቅም ግንባታ የአጋዥነት ሚና ብቻ እንደሆነ ገልጬያለሁ፡፡
በተነፃፃሪነት ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ በሶሻሊዝም መርህ መንግሥት ገበያውን የማቀጨጭ ተልዕኮውን መፈጸም ሳይጀምር በፊት፣ ሸማቹም አምራቹም እንደ ዛሬው ምክንያተ ቢስ (Irrational) ባልነበሩበትና የዳበረ የገበያ ሥርዓት በነበረበት የንጉሡ ዘመን ዓመታት በዓይኔ ዓይቼ እንደማውቀው፣ የሸቀጦች ዋጋ በየቀኑና በየሳምንታቱ ከመለዋወጥና ከመዋዠቅ ይልቅ ለወራት የረጉ እንደነበሩ፣ ለአብነት ያህልም በንጉሡ ዘመን ለረጅም ጊዜ በአሥራ አምስት ሳንቲም ምሳ ይበላ እንደነበርና በደርግ ጊዜም ዋጋው በአንድ ብርና በሁለት ብር መካከል እንደነበረ በምሳሌዎች ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡
የምርጫ ሙግቶቹ እንደ አቅራቢው ዝግጅትና ዋና ነጥቦችን መርጦ የማቅረብ ችሎታ፣ መድረክ ላይ ቀርቦ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ አቅምና የተሰጠው ጊዜ በቂነት የሚወስኑ ሲሆኑ፣ የብልፅግና የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምም ሆነ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ምንም ያህል የረቀቁና ሳይንሳዊ ሊሆኑ ቢችሉም፣ መንግሥት በአጋዥነት ሚና ሳይሆን በአዛዥነት መንፈስ ውስጥ ሆኖ ያዘጋጃቸው ስለሆኑ፣ ሸማቾችም ሆኑ አምራቾች እንደ ሶሻሊዝሙ ዘመን የመንግሥትን ትዕዛዝ ተቀብሎ ለመፈጸም የሥነ ልቦናም ሆነ የአካላዊ ዝግጅት ስላላደረጉባቸው፣ ወይም የአዛዥና የታዛዥነት ምክንያታዊ (Rational) የገበያ መስተጋብር ሚናቸው በቀጨጨበት ሁኔታ መተግበር ስለማይቻል፣ ውጤታቸው ከቀድሞዎቹ የዕድገትና ትራንስፎረሜሽን ዕቅዶች የተለዩ እንደማይሆኑ በግርድፉና በጥቅሉ አሳስቤያለሁ፡፡
የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ ስለሆንኩኝ በገበያና በዕቅድ መካከል ስላለው ፉክክርና መደጋገፍ እረዳለሁ፡፡ በካፒታሊዝም ገበያው ከዕቅድ በላይ አቅም እንዳለው በሶሻሊዝም ዕቅድ ከገበያው በላይ አቅም እንዳለው አውቃለሁ፡፡ መንግሥት ምን ለማን እንዴት ይመረት በሚለው የገበያ ኢኮኖሚ መርህ የሀብት ድልድል፣ ምርት አፈጣጠርና የተመረተውን በመከፋፈል አዛዥና ታዛዥ የሆኑትን ሸማቹንና አምራቹን በአጋዥነት ተሳትፎው ከቀኝ ዘመም የሊበራል ፖለቲካል ኢኮኖሚ አንስቶ፣ እስከ ግራ ዘመሙ የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ድረስ ራሱ እንደ ሸማች ወይም እንደ አምራች ከሚቆጠርበት መንግሥታዊ አገልግሎቶች በቀር፣ በግሉ ኢኮኖሚ ምክንያተ ቢስነትን የመቆጣጠርና የማጥፋት የአጋዥነት ዕቅድ ብቻ ሊያወጣ እንደሚገባው እገነዘባለሁ፡፡
አንድ ኢኮኖሚ የሚያድገው በራሱ ከገበያው ውስጥ በሚያገኘው ውስጣዊ የዕድገት ምክንያቶች ሲሆን፣ ውጪያዊ የዕድገት ምክንያት የሆነው የመንግሥት ዕገዛ ጠቀሜታው በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ሰዎችም ጥቅሉን ኢኮኖሚ ሲያቅዱ ዕድገትን በቀዳሚነት የውስጥ ኃይላት ተፅዕኖ ውጤት አድርገው መመልከት እንደሚገባቸውና የመንግሥትን ዕገዛ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ አድርገው መውሰድ እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ መንግሥት አንደኛውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከሸማቹና ከአምራቹ በመንጠቅና ራሱን ዋናው የዕድገት መሠረት አድርጎ መቁጠር ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ መገንዘብ አለባቸው፡፡
የትኛውም ፓርቲ በሕዝብ ድምፅ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ የሚሠራው ሥራ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም የማይፃረርና የደከመው ኢኮኖሚያችን እንዲያንሰራራ የሚያግዝ መሆን እንዳለበት በምርጫ ወቅት ከመሞገት ባሻገር፣ የተመረጠው ፓርቲ ስህተቱን እንዲያርም በሙያ ምክር መርዳት የየትኛውም ፓርቲ አባል ከሆነ ባለሙያ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከብልፅግና ጋር ተከራክሮ አካሄዱን ለማረም ሦስት ወራትም መከራከር ይቻላል፡፡ አልበርት አንስታይን እንዳለው ተመሳሳይ ሥራ እየሠሩ የተለየ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡ ብልፅግና በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተለየ ሥራ እንደሠራ የሚቆጥረው በፊት ከነበሩት መንግሥታት በወረሰው የአዛዥነት መንፈስ ውስጥ ሆኖ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመለወጥ ከመንግሥት የልማት ፋይናንስ በመቀነስ ለግሉ ኢኮኖሚ በቂ የልማት ፋይናንስ እለቅለታለሁ በማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ራሱ ከአዛዥነት መንፈስ አለመላቀቅ እንጂ፣ የገበያውን የሀብት ደልዳይነት ሚና ማን ለብልፅግና ሰጥቶት ነው መጥኖ ሰጪና መጥኖ ከልካይ የሚሆነው፡፡
ከ1967 እስከ 2013 ዓ.ም. ለአርባ ስድስት ዓመታት የሀብት መደልደል ሚናውን በመንግሥት ተነጥቆ በሸማቹና በአምራቹ ምክንያተ ቢስነት የሀብት ሽሚያ የቀጨጨውን ገበያ፣ በአንድ ጊዜ ሚናውን መልሶ መስጠት አስቸጋሪ እንደሆነ የገበያው ጉድለት ለረጅም ጊዜ እንደሚቀጥልም እረዳለሁ፡፡ ሆኖም ረጅም ጉዞ በአንድ ዕርምጃ ይጀመራል እንዲሉ ገበያው አንድ ርምጃውን ሳይጀምር በብልፅግና የአዛዥነት ሚና በተነደፈ የሪፎርም ፕሮግራምና የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ የተለየ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡ የዕዝ ኢኮኖሚ አስተዳደር የሸማቹንም የአምራቹንም ምክንያተ ቢስነት ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ ይህ ከራሳችን ስህተቶች ልንማር የሚገባን ጉዳይ እንጂ ከሰው የተቀዳ አይደለም ይህ በእውነተኛ ችግሮቻችን ላይ የተመሠረተው አካሄድ ነው፣ አገር በቀል አካሄድና አገር በቀል ሪፎርም ሊሆን የሚችለው፡፡
ለምሳሌ ከማኅበረሰባችን ውስጥ ምክንያተ ቢስነት የሚያጠቃው ወጣቱን ነው ወይስ አረጋውያኑን? ወንዱን ነው ወይስ ሴቷን? ሀብታሙን ነው ወይስ ደሃውን? ከተሜውን ነው ወይስ ገጠሬውን? የሸማችነት ምክንያተ ቢስነት ይብሳል? ወይስ የአምራችነት ምክንያተ ቢስነት? ምክንያቶቹ ምንድናቸው ብለን ልናጠና እንችላለን፡፡ ኢኮኖሚያዊ ምክንያተ ቢስነት መላውን ዓለምና የዓለም ሎሬት ኢኮኖሚስቶችን የጥናት ውጤቶች የተፈታተነ ችግር ቢሆንም፣ የኢትዮጵያው ምክንያተ ቢስነት የራሱ የሆኑ ባህሪያት አሉት፡፡ ባህሪያቱን አጥንቶ በአስተሳሰብ ለውጥ ስብከት ሳይሆን፣ ገቢና ወጪን በሚቆጣጠር ተጨባጭ መንግሥታዊ የቁጥጥር፣ የድጋፍና የተግባር ዕርምጃ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 25 እናት ፓርቲን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡