Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኢትዮጵያ ለቴሌ ብር የከፈለችውን ዋጋ ኢትዮ ቴሌኮም በአገልግሎቱ ሊክስ ይገባል!

በየትኛውም የአገልግሎት ዘርፍ የዘመነ አሠራር ያስፈልገናል፡፡ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶችን ማስፋትም የግድ ነው፡፡ ከተለመዱና ኋላቀር ከሆኑ አሠራሮች ተላቀን አኗኗርን የሚያቀልና ጊዜን የሚቆጥቡ አሠራሮችን ከቴክኖሎጂው ጋር አዋዝቶ ኅብረተሰቡ እንዲገለገልበት ማስቻል ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ዜጎችም ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎትን መቀበልና በዚሁ መንገድ መጓዝ ግድ እያለ በመሆኑ ራስን ከዚሁ ጋር ማላመድና በአግባቡ መተግበር የግድ ይላቸዋል፡፡

ከሰሞኑ ኢትዮ ቴሌኮም ይፋ ያደረገው የቴሌ ብር አገልግሎት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የሞባይል ባንክ አገልግሎት በቅርብ በኢትዮጵያ በተለዩ ባንኮች የተተገበረ ቢሆንም፣ ቴሌ አገልግሎቱን ለየት ባለ መልኩ ይዞ ብቅ ማለቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚደርስ ከመሆኑ አንፃር በተለየ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡

የአገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ የተሰጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ማንቀሳቀስ ማስቻሉ በዋናነት የሚጠቀስ መገለጫው ነው፡፡ ዜጎች የገንዘብ እንቅስቃሴያቸውንና ግብይታቸውን የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም በቀላሉ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው፡፡

ገንዘብ ለመላላክ፣ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመክፈል፣ ከውጭ የሚመጣ ገንዘብን ለመቀበል ሁሉ ይህ የቴሌ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡

የአገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ ጥቅሙ የጎላ ስለመሆኑም በሰፊው ተብራርቷል፡፡ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ከመፍጠር ባሻገር የኢትዮ ቴሌኮምን ገቢ ሁለት ሦስት እጅ ያህል የሚያሳድግ መሆኑም አገራዊ ፋይዳውን ያጎላዋል፡፡ እሰየው ነው፡፡ እንዲህ ያሉ መልካም ነገሮች ይብዙልን፡፡

በትሪሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚንቀሳቀስበት የሚጠበቀው ‹‹ቴሌ ብር›› አገራዊ ፋይዳው ከዚህም በላይ እንደሚሆን የታመነ ሲሆን፣ እንደ አገር ግን ዋጋ የተከፈለበት ፕሮጀክት ስለመሆኑም ‹‹በቴሌ ብር›› የማስጀመሪያ ሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ መናገራቸው ልብ ይሏል፡፡

የቴሌ ብር ሥርዓት መጀመር የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር አንዱ ምክንያት ከ‹‹ቴሌ ብር›› አገልግሎት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስመልክተውናል፡፡ በውጭ ሚዲያዎች በተለያየ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲበረታ ያደረገ ከመሆኑ አንፃር ዋጋ የተከፈለበት ፕሮጀክት እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡

ይህንኑ ምልከታቸውን ‹‹ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የቴሌኮም ገበያውን ከፍታለሁ እያለች በሌላ በኩል ደግሞ ዋናውን ሁለት ሦስተኛ ትርፍ የሚያስገኘውን የሞባይል ባንኪንግ ዘርፍ ለራሷ ቴሌኮም ሰጠች በሚል ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

ይህንን ጉዳይ አያንዳንዱ በግልጽ የሚናገረው ሲሆን፣ አንዳንዱ ደግሞ ይህንን ትቶ በሌላ መንገድ ዱላውን እያሳረፈ መሆኑን በመግለጽ ይህ ዱላ እንዲያርፍብን የፈቀድንበት ዋናው ምክንያትም ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በቀጥታ በመያያዙ እንደሆነ በዕለቱ ተናግረዋል፡፡

አሁን ለሁለት የቴሌኮም አገልጋዮች ፍቃድ ሲሰጥ የሞባይል ባንኪንግ ያለመካተቱን ተናግረዋል፡፡ ይህን በማድረጋችን የኢትዮጵያ መንግሥት በትንሹ 500 ሚሊዮን ዶላር ያጣል፡፡ ይህን የተደረገው ኢትዮጵያ ልምድ አካብታ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል ነው፡፡ ምክንያቱም ከዓመት በኋላ ዘርፉ ለሌሎች ክፍት ይደረጋል፡፡

ስለዚህ ቴሌ ብር በተለየ ሊታይ የሚችለበት ሁኔታን የፈጠረ ነው ማለት ነው፡፡ በመንግሥት ፖሊሲ የሞባይል ባንኪንግን ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ እንዲሠራው መደረጉ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ቴሌ ይህንን አገልግሎት በብቸኝነት የሚሠራው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡

ቴሌ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ተወዳዳሪዎች ይመጡበታልና ይህንን መስዋዕትነት የተከፈለበትን ፕሮጀክት በአግባቡ በመተግበር ዳር የማድረስ ኃላፊነቱ እንዲህ በዋዛ የሚታይ አይሆንም፡፡ እንደ አገር በቀል ኩባንያ የሚጠበቀውን ተወዳዳሪነት አሸንፎ በመውጣት በዘርፉ ውጤታማ ካልሆነ አገር ሁለት ጉዳት እንድትጎዳ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ አገልግሎት አሰጣጡን በብቸኝነት ገበያውን ይዞ ሲጓዝ እንደነበረው ሳይሆን፣ ከወዲሁ መትጋት ግድ ይለዋል፡፡ ጊዜው የተሻለ አገልጋይ የሚፈልግበት በመሆኑ መትጋት ተገቢ ነው፡፡ እንደ አጀማመሩ አካሄዱንም አጨራረሱንም ባወጣው ዕቅድ መሠረት ማስፈጸም አለበት፡፡ በተለይ በተለይ እንደቀድሞ ኔትዎርክ እየተቆራረጠ ደንበኞችን በማማረር የሚሆን ነገር የለም፡፡ ቴሌ ብር አጠቃላይ አገልግሎቱ ከገንዘብ ዝውውር ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ኔትዎርክ ተቋረጠ ተብሎ ዝም የሚባል አይደለምና ቅድሚያ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችንም ማረም ይገባል፡፡

በዚህ በቴሌ አዲስ አገልግሎት ጉዳይ ላይ ግን አንድ የተለየ ነገር ሊታሰብ ይችላል፡፡ ፕሮጀክቱ አገርን ዋጋ እንዳስከፈለ ሁሉ አገር ቤትም የራሱ የሆነ አበርክቶ ሊኖረው ይገባል የሚለውን ሐሳብ ያጭራል፡፡ ይህም እንደ ሸማች ተገልጋይ የተሻለ አገልግሎት ለሚሰጥ ጎንበስ ማለት ተገቢ ቢሆንም፣ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን የጀመረው አገልግሎትና አግልግሎቱን ለመጀመር አገር እየከፈለች ያለችው መስዋዕትነት ሲታሰብ ደግሞ ይህ ፕሮጀክት ነገ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በአገሩ ሜዳ ላይ የሚጠብቀው ውድድር የቱንም ያህል ቢሆን ዜጎች ለተቋሙ እንዲያደሉ ማድረግ ግድ ሊል መቻሉ ነው፡፡ ልክ እንደ አየር መንገድ ቴሌን እንደ አገር ኩባንያነት እንድናየው ከተፈለገ እሱን መምረጥ ያሻል፡፡

ቴሌ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ኩራታችን ነው ብለን፣ የትኛውም ተወዳዳሪ ቢመጣበት የምጠቀመው በአገሬ ኩባንያ ነው እንዲሉ ከተፈለገ ግን ኢትዮ ቴሌኮም ዛሬ ላይ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ማድረግ ይጠይቀዋል፡፡ ዜጎች በአገሬ ኩባንያ እኮራለሁ እንዲሉና ከሞባይል ባንኪንግ የሚገኘውን የሚያደስጎመዥ ትርፍ እዚሁ ለአገሬው ለማስቀረት ዜጎች የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በመንግሥት ፖሊሲ ያገኘውን የአጭር ጊዜ ዕድል በመጠቀም ደንበኞቹን እስከወዲያኛው ለማሻገር የአገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማድረግ ይህ ጊዜ ወሳኝ ነው፡፡ ያለተወዳዳሪ ለዘመናት ሲጓዝ ከነበረበት ዘመን አሠራሩ ተላቅቆ ኃላፊነቱ ድርብ መሆኑን በመረዳት ጠንክሮ ይሥራ፡፡ ያኔ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች አንፃር ተቀራራቢ የሆነ አገልግሎት ቢሰጥ እንኳን ዜጎች ከእርሱ ጋር ይሆናሉ፡፡ ካልሆነ ይህ ያለአግባብ መስዋዕትነት የተከፈለበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ አየር መንገዳችን ዛሬ ላለበት ደረጃ የደረሰው ዜጎች የኩራታቸው ምልክት በማድረጋቸው ጭምር ነው፡፡ ከሌሎች አየር መንገዶች የበለጠ ዋጋ እየጠየቀ እንኳን አየር መንገዱን በመምረጥ መብረራቸው ለአየር መንገድ ስኬት አንዱ መሆኑን ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ ቴሌ አገር የከፈለውን መስዋዕነት ጠንካራ ተወዳዳሪ በመሆንና የተሻለ አገልግሎት በመስጠት እንዲክሰንም ይጠበቃል፡፡ በጥረቱ ልክ እንደ አገር ኩባንያ ሊታገዝ የሚችለውም ይህንን በማድረግ ነው፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት