Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደቡብ ግሎባል ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ ከወለድ ነፃ አገልግሎትን ተቀላቀሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመጀመር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን ሲገልጽ፣ አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ደግሞ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘቱን አስመልክቶ በወጣው መግለጫ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተቀበለ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሸሪዓ የፋይናንስ መርሆችን በመከተል በአገልግሎት ወቅት ምንም ዓይነት ወለድ መክፈል ሆነ መቀበል የማይፈቅድ ሲሆን፣ በሸሪዓ በተፈቀዱ ሥራዎች ላይ ብቻ የሚሳተፍ የራሱ የሆነ አሠራር ያለው ሆኖ ማንኛውም አገልግሎቱን መጠቀም ለሚፈልግ ደንበኛ የቀረበ አማራጭ የባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ባንኩ በቅርንጫፎች ውስጥ ተለይተው በተሰናዱ መስኮቶች ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቅሷል፡፡

በእነዚህ መስኮቶች የሚፈጸሙ ማናቸውም የገቢና የወጪ ሒሳብ እንቅስቃሴዎች ከመደበኛው የባንክ አሠራር ጋር ሳይቀላቀሉ በተለይ ለዚሁ አገልግሎት ተብሎ በተዘጋጀ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በተመረጡ ቅርንጫፎቹ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስኮቶችን በመመደብ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማና በክልል አንዳንድ ከተሞች ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ስለማቀዱም ገልጿል፡፡

እንደ ባንኩ መግለጫ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡት ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ የተጠቃሚዎችን በተለይም የእስልምና እምነት ተከታዮችን ምቾት የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችል አቅርቦት ያሟሉ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሲጀምር በዋናነት እንደሚተገብራቸው የገለጻቸው የአገልግሎት ዓይነቶቹ የዋዲያና የኢንቨስትመንት ተቀማጭ ሒሳብ  የፋይናንስ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት፣ የውጭ ምንዛሪ  የተለያዩ የባንክ ዋስትናና የገንዘብ ማስተላለፍ (ሐዋላ) አገልግሎት ናቸው፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች በየዘርፋቸው በርካታ ልዩ ልዩ ዓይነት አገልግሎት እንደያዙም ጠቅሷል፡፡

በተያያዘ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ‹‹ታካፉል›› ኢንሹራንስ ለመስጠት ፈቃድ ከጠየቁ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው አዋሽ ኢንሹራንስ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

እንደ ባንክ አገልግሎት ሁሉ የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት የሚያስችለውና ታካፉል የተባለውን አገልግሎት ለመጀመር ፈቃድ ያገኘው አዋሽ ኢንሹራንስ፣ አገልግሎቱን ይህ በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት በተመረጡ ቅርንጫፎች በመስኮት ደረጃ ሥራ ያስጀምራል፡፡

ኩባንያው ታካፉልን መጀመሩ የመድን ሽፋንን ከማስፋት አኳያ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚያመላክተው የአዋሽ ኢንሹራንስ መረጃ፣ በእምነታቸው ምክንያት የመድን አገልግሎት ያላገኙ ወገኖችንም በመድረስ የአገልግሎት ተጠቃሚዎችን እንደሚያሰፋ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመስኮት ደረጃ የታካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎትን ለመጀመር ከስምንት በላይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየጠበቁ መሆኑ ታውቋል፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከ110 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የተከፈለ ካፒታሉ 1.2 ቢሊዮን ብር በላይ፣ የተቀማጭ መጠኑ ከ7.3 ሚሊዮን በላይ፣ የብድር መጠኑ ከ7.2 ቢሊዮን፣ የሀብት መጠኑ ደግሞ 7.8 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት በ50 ቅርንጫፎች አገልግሎቱን እየሰጠ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትልቁን የካፒታል መጠን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የኩባንያው የተፈቀደ ካፒታል 1.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉም ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች