Tuesday, January 31, 2023

በምርጫ ሒደቱ ተዓማኒነት ላይ ጥያቄ የሚያጭሩ አሉታዊ ክስተቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በ2013 ዓ.ም. በግንቦት ወር መጨረሻ የሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ሒደት ከተጀመረ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በዚህም ከምርጫ አስፈጻሚዎች እስከ የምርጫ ቁሳቁሶች ዝግጅት ተጠናቆ ምርጫውን ለማካሄድ ቁልፍ የሚባሉት የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ ተጠናቀዋል። 

በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች፣ የምርጫ ቅስቀሳና የምረጡኝ ክርክር በመከናወን ላይ ይገኛል። 

ለመጪው ምርጫ የሚያስፈልጉት የምርጫ ክንውኖች በአመዛኙ የተከናወኑ ቢሆንም፣ ክንውኖቹ የተፈጸሙበት ሒደት ወይም አጠቃላይ የቅድመ ምርጫ ሒደቱ ከምርጫ መመዘኛዎች አንፃር ሲለኩ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቁ መሆናቸው እየተነገረ ነው። 

አንድ ምርጫ ከሚመዘንባቸው አላባዊያን መካከል ነፃና ዴሞክሬሲያዊ ሒደትን የተከተለ መሆኑ፣ ያለ አድልኦ በገለልተኝነት የሚፈጸም መሆኑ፣ ይህንንም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተቋማዊ አደረጃጀቶችና ሥርዓቶች መሟላት ዋነኞቹ ናቸው።

የስድስተኛው አጠቃላይ የምርጫ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያለፈበት ሒደት ከዚህ አኳያ ሲመዘን ቀላል የማይባሉ የምርጫውን ተዓማኒነት የሚሸረሽሩ ክስተቶች በመስተዋላቸው፣ አሁንም ክስተቶቹ ተቀርፈዋል ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል። 

ከእነዚህ ክስተቶች መካከል አንዱ የሆነው ምርጫውን በሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራሱ፣ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተገናኘ ተከስተዋል የተባሉ ያልተገቡ አሠራሮች ይጠቀሳሉ። 

ከተከሰቱት ያልተገቡ አሠራሮች መካከል እጅግ ግዙፍ የሆነ ጥሰት ሳይፈጸም አይቀርም የሚል ግምት እምነት እንዲወሰድ ያደረገው፣ በሶማሌ ክልል በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ተፈጽመዋል የተባሉ የመራጮች ምዝገባን የተመለከቱ ጥሰቶች፣ በተመሳሳይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተፈጽመዋል የተባሉ ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተገናኙ ሳንካዎች ይገኙበታል።

በሶማሌ ክልል በርካታ የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ በገዥው ፓርቲ (ብልፅግና ፓርቲ) ዝቅተኛ ካድሬዎች ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት የተፈጸመበት ከመሆኑ አልፎ፣ የመራጮች ምዝገባ በምርጫ ቦርድ ቁጥጥር ሥር አለመሆኑን የሚገልጽና በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የቪዲዮና የምሥል ማስረጃ ጭምር ያቀረቡበት እንደሆነ ተነግሯል። 

የምርጫ ካርዶች ከምርጫ ጣቢያ ውጪ ለግለሰቦች በገፍ መታደላቸውን፣ ያልተሞሉ የመራጮች ምዝገባ ካርዶች ለዝቅተኛው መንግሥት እርከን (ቀበሌ ወረዳ ሠራተኞች) እና ዕጩዎች መሰጠቱ፣ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች ከመንግሥት አስተዳደር እርከን ሠራተኞችና ዕጩዎች ጋር በዝምድናና በተለያዩ መንገዶች የተያያዙ መሆናቸውና በዚህም በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ ተነስቷል።

በተጨማሪም የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የክልሉ ነዋሪዎች እንዳይመዘገቡ ክልከላ እንደተደረገባቸውና የመራጮች ከወሰዱ ነዋሪዎች እጅ ካርዱ ተመልሶ እየተሰበሰበ መሆኑ፣ የምርጫ ድምፅ መስጫ ሳጥን ‹‹ብሉ ቦክስ›› ምርጫ ጣቢያዎች ሲደርስ በተገቢው መንገድ ያልታሸገ መሆኑ፣ ይህም በመሀል ሳይከፈት እንዳልቀረ በመጠቆም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታ አንስተውበታል።

ቅሬታውን የመረመረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሶማሌ ክልል የምርጫ ምዝገባ ሒደት ላይ ተፈጥሯል የተባለው ሁኔታ በምርጫ ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ የሚፈጥር እንደሆነ በመግለጽ፣ አቤቱታ የቀረበባቸው በሶማሌ ክልል የሚገኙ ሰባት የምርጫ ክልሎች ላይ የሚካሄደው የመራጮች ምዝገባ በጊዜያዊነት እንዲቆም መወሰኑን አስታውቋል። 

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳመለከተው በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ሒደት ላይ የቀረቡት ቅሬታዎች በማስረጃ የተደገፋ መሆናቸውንና በማስረጃዎቹ ላይ ባካሄደው ምርመራም ተፈጸሙ የተባሉት ሕገወጥ አሠራሮች ተፈጽመው ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ መውሰዱን፣ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበውን አቤቱታም ማጣራት ለማስጀመር እንደሚያስችል ገልጿል።

በመሆኑም አቤቱታዎቹን መሠረት በማድረግ በክልሉ ከሚገኙ 23 የምርጫ ክልሎች መካከል፣ በሰባቱ የምርጫ ላይ የሚካሄደው የመራጮች ምዝገባ እንዲታገድ ወስኗል።

በሰባቱ የምርጫ ክልሎች ላይ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ሒደት ለማጣራትም አቤቱታ ካቀረቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ከቦርዱ ሠራተኞችና ከገለልተኛ ባለሙያዎች የተወጣጣ ቡድን እንደሚልክ ገልጿል።

በተመሳሳይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚካሄደው የመራጮች ምዝገባና አጠቃላይ የምርጫ ሒደትን የሚያከናውኑ የምርጫ አስፈጻሚዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በገለልተኝነት ማከናወን የሚገባቸው እንደሆነ እየታወቀ፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት በምርጫ አስፈጻሚዎቹ የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ጣልቃ በመግባት መመርያ ሲሰጡ መቆየታቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

መጪውን ምርጫ ለመታዘብ ወደ ኢትዮጵያ የጋራ ቡድናቸውን ያሰማሩት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ብሔራዊ የዴሞክራሲ ኢንስቲትዩት (NDI) እና ዓለም አቀፍ ሪፐብሊካን ኢንስቲትዮት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ባወጡት እስካሁን ያለውን የምርጫ ሒደት የተመለከተ ሪፖርት ከጠቀሱት ከምርጫ ሒደቱ አሉታዊ ክስተት አንዱ፣ በሶማሌ ክልል በምርጫ አስፈጻሚነት የተመደቡ ግለሰቦች መካከል የገዥው ፓርቲና የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚገኙበት መረጃዎች እንደ ደረሱት አመልክቷል።

የሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሪፖርት በአጠቃላይ የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ፣ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚጭሩ በማለት ከለያቸው ክስተቶች መካከል ሌላው የመራጮች ምዝገባ ህፀፆች ይገኝበታል። 

ይህ የምርጫ ታዛቢ ቡድን እንደገለጸው፣ የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ከፀጥታና ከሎጂስቲክስ ችግሮች ጋር በተገናኘ የተወሳሰበ ችግር ገጥሞት እንደነበርና እስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ድረስ የነበረው የመራጮች ምዝገባ በእጅጉ አነስተኛ መሆኑ፣ በምርጫ አስፈጻሚው ምርጫ ቦርድ ላይ ሥጋት ፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳል።

ነገር ግን ይህንን ተግዳሮት ለመቀየር ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጥምረት ባደረገው እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የፈዴራልና የክልል መንግሥታት ዝቅተኛ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ ለመቀየር የተቀናጀ ጥረት ማድረጋቸውን ይገልጻል። 

ነገር ግን አነስተኛ የነበረውን የመራጭች ምዝገባ ለመቀየር የመንግሥት መዋቅሩ ያደረገው ርብርብ በምርጫው ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው፣ ይህም በምርጫው የሚሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ሥጋት መፍጠሩን ይገልጻል። የመንግሥት መዋቅሩ አነስተኛ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ ለመቀየር ያደረገው ርብርብ በሚፈጥረው ጫና፣ የተመዘገቡ መራጮች የሚሰጡት ድምፅ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚገልጽ ላይሆን እንዲሚችል በሥጋትነት በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ ውስጥ የነበረውን የተመዘገቡ መራጮች አኃዝ የመግለጽ ኃላፊነት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆኖ ሳለ፣ የፌዴሬልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች የመራጮች ምዝገባን የተመለከተ የሚጣረስ አኃዝ ይፋ ማድረጋቸው ተገቢ እንዳልሆነ አመልክቷል።

በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ ሚያዝያ ወር ቀናት የነበረው ዝቅተኛ የመራጮች ምዝገባ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወይም እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ በ20 ሚሊዮን ቁጥር መጨመሩ፣ የተጋነነና የምርጫ ምዝገባ ሒደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲነሳ ማድረጉን ገልጿል።

ይህ በመሆኑም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎችን እምነትን ለማረጋገጥና በአጠቃላይ በዚህ ጉዳይ ላይ የተፈጠረውን ጥርጣሬ ለመቅረፍ፣ የምርጫ ሕጉ ከሚፈቀደው በዘለለ በመሄድ የመራጮች ምዝገባ ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሲቪክ ተቋማት በመስጠት፣ የሕዝብን አመኔታ ከፍ ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫውን ለሚሳተፉ ሰቪክ ተቋማት የመራጮች ምዝገባ መረጃውን በወረዳ፣ በምዝገባ ቀን፣ በዕድሜና በፆታ የሚዘረዝር ኤሌክትሮኒክ ሰነድ እንዲያቀርብ ጥሪ አድርጓል።

የምርጫ ወቅት የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ

መጪው ምርጫ የሚካሄድበት የፀጥታና የደኅንነት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ የሚጠቅሰው የዓለም አቀፍ ታዛቢዎቹ ሪፖርት፣ ለዚህ ሁኔታ ሥር የሰደደው የብሔረሰቦች መካረር፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን፣ እንዲሁም በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በምሥራቅ አማራ ክልል፣ በተጨማሪም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሰቀሱ ግጭቶች ሁኔታውን እንዳወሳሰቡት ይገልጻል።

በእነዚህና ሌሎች አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ለምርጫ የሚወዳደሩ ሁለት ዕጩዎች ጭምር መገደላቸውን፣ ፓርቲዎች ቢሮ ለመክፈትና ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን፣ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮች መቀደዳቸውን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ የወደቁ አካባቢዎች መኖራቸውንም ጠቁሟል።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ዕጩዎች በስፋት መታሰራቸውን የሚመለከቱ ቅሬታዎች እንደ ደረሱት፣ በዚህም የፀጥታ ሁኔታና ጫና ቢያንስ ሁለት ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ለማግለል መገደዳቸውንም ጠቁሟል።

ከምርጫ መመዘኛዎች መካከል አንዱ ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትንና ለፓርቲዎችም በእኩል የተደለደለ የፖለቲካ መጫወቻ ማግኘታቸው እንደሆነ የሚጠቅሰው የምርጫ ታዛቢዎች ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የፀጥታ ሁኔታ ይህ እንደሚጎድለው አመልክቷል።

መጠነ ሰፊ የሆነው ግጭትና አለመረጋጋት ኢትዮጵያዊያን ተረጋግተው በምርጫ ሒደቱ እንዳይሳተፉና በተለይም በድምፅ መስጫው ቀን ድምፃቸውን ለመስጠት እንዳይወጡ ሥጋት የመፍጠር አቅም እንዳለው፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚመጣ የምርጫ ውጤት ቅቡልነትንም ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል አስታውቋል።

በመራጮች ምዝገባ ሒደት የመጀመርያ ወቅት ለነበረው አነስተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ምክንያትም፣ ይኸው የፀጥታ ሥጋት አስተዋጽኦ ማድረጉን ከተለያዩ አካላት መረዳት እንደተቻለ ገልጿል።

በመሆኑም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመናበብ በተቀናጀ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ምርጫ ቦርዱም ፀጥታውና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የሥምሪት ዕቅድ አውጥቶ በመላ አገሪቱ ለመተግበር እንዲችል ትብብር ማድረግ እንሚገባ ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል።

የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን ከወገንተኝነት በፀዳ መንገድ ለመወጣት፣ በምርጫ ሒደቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ላለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝት ለሕዝብ ማሳየት እንዳለባቸው በምክረ ሐሳቡ አክሏል።

የመንግሥት ድጋፍ አነስተኛ መሆን 

የአገሪቱን ምርጫ የሚያስተዳድረው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ካሉት ምርጫዎች በተሻለ ገለልተኝነት ምርጫውን ለማስፈጸም የሚያስችል ቁርጠኝነትና ለዚህም የተሻለ ጥበቃ የሚሰጠው የሕግ ማዕቀፍ ቢኖርም፣ ምርጫውን ለማስፈጸም የነበረው ጊዜና የሰው ኃይሉ ምርጫን በማስፈጸም በተግባር የተረጋገጠ ልምድ አለመኖሩ ሒደቱን ፈታኝ እንደሚያደርገው በርካቶች ይገልጻሉ። 

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ የመንግሥት ድጋፍና ትብብር ቦርዱን የገጠመው ፈተና መሆኑ ደግሞ ሒደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል።

ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢ ተቋማቱ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያወጡት ሪፖርትም ይህንኑ አስቸጋሪ ሁኔታ የጠቀሰ ሲሆን፣ ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት የሚያስችል ትብብር ለማግኘት እንኳን ተቸግሮ እንደነበር ይገልጻል።

አሁንም ቢሆን መንግሥት የምርጫ ጣቢያዎችን በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ ለማቋቋም ትብብር ባለማድረጉ፣ በተለያዩ ግጭቶች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በምርጫው የመሳተፍ ወይም የመምረጥ መብታቸውን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ አስታወቋል።

ለምርጫው ዴሞክራሲያዊ መሆን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ቅንጅትና ድጋፍ በእጅጉ የሚያስፈልግ እንደሆነ የሚገልጸው ይኸው የታዛቢዎቹ ሪፖርት፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ አኳያ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደገጠመው ጠቁሟል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -