Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአገራዊ ውይይቶች ከተፅዕኖ ነፃ ባለመሆናቸው መስማማት ያቃታቸው ሐሳቦች መበራከታቸው ተነገረ

  አገራዊ ውይይቶች ከተፅዕኖ ነፃ ባለመሆናቸው መስማማት ያቃታቸው ሐሳቦች መበራከታቸው ተነገረ

  ቀን:

  በኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት ስለአገራዊ አንድነትና ብሔራዊ ዕርቅ በቁጥር በዛ ያሉ ሐሳቦች ቢሰነዘሩም፣ የሚነሱ ሐሳቦችንና አመንጪዎችን ወደ አንድ አምጥቶ ሊያወያይ የሚችል ነፃ የውይይት መድረክ ባለመፈጠሩ ምክንያትና ተቀራርቦ መነጋገር ባለመቻሉ፣ የተቃርኖ ሐሳቦች እየበዙ መምጣታቸውን ምሁራን ገለጹ፡፡

  በ2012 ዓ.ም. የተመሠረተውና የስምንት ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ማይንድ ኢትዮጵያ የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት፣ ሁሉን አቀፍና አካታች በሆነ የምክክር መድረክ ላይ እያከናወናቸው ያሉትን ሥራዎች አስመልክቶ፣ ሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡

  የድርጅቱ መሥራችና የአካባቢ ተቆርቋሪ ባለሙያ ንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ አሁን ድረስ እየታዩ ላሉት ወጣ ገባ የሆኑ አገራዊ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት የመሪዎች ችግር ሳይሆን፣ ምሁራንና የሐሳብ አመንጪዎችን በአንድ አገናኝቶ በገለልተኛ መድረክ፣ ስለአገራዊ ጉዳይ ደፍረው የሚናገሩበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መቀራረብና መደማመጥ የሚችሉበት የውይይት መድረክ አለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያላት ብቸኛውና ዋነኛው የለውጥ መንገድ ውይይት ብቻ እንደሆነ፣ በዚህ ረገድ ረዥም ርቀትን ሊያስኬድ የሚችል የሰጥቶ መቀበል አካሄድ መፍጠር  ለዘላቂ ሰላምና አገራዊ መግባባት ያለው ሚና ትልቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

  ሁሉም በሚያስበው ልክ የምትታደስና ምቹ የሆነች አገር ለመገንባት የራሱ የሆነ ቀመር በማዘጋጀት፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ድምፅ መስማት የሚቻልበት መድረክ ሊፈጠር እንደሚገባ ንጉሡ (ዶ/ር) አክለው ተናግረዋል፡፡

  በዚህም ከተለያዩ ውይይቶች የሚገኙና የሚመነጩ አገራዊ ሐሳቦችን መንግሥት እንዲቀበላቸውና ተግባራዊነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ፣ የችግሩ ቁልፍ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

  ማይንድ ኢትዮጵያ የስምንት ድርጅቶች ጥምረት ዴስቲኒ ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጥምረት፣ የሐሳብ ማዕድ፣ ጀስቲስ ፎር ኦል፣ ኢንሼቲቭ ፎርቼንጅ፣ የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያንስ ፎር ኢንክሉሲቭ ዲያሎግና የሰላም ሚኒስቴር በመያዝ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረኮች ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

  በሚቀጥሉት ጊዜያት ሊደረጉ የታሰቡ ምክክሮችን ጨምሮ ባለፉት ጥቂት ወራት ገዥውን ፓርቲና በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በማካሄድ፣ በአጭርና በረዥም ጊዜ ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ አጀንዳዎች እየተለዩ መሆኑን ንጉሡ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

  ማይንድ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተወከሉ 1,000 ተሳታፊዎችን የያዘና ረዥም ጊዜ የሚቆይ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

  ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ የምክክር መድረኮች ከውይይት ያላለፈ ተጨባጭ ለውጥን ማምጣት የተሳናቸው በመሆኑ፣ በሚቀጥሉት ጊዜያት በማይንድ ኢትዮጵያ ሊካሄዱ የታሰቡ የውይይት መድረኮች እስካሁን ከተደረጉት ውይይቶች በተለየ መልኩ አጀንዳውን ከሕዝቡና ከሚወያየው አካል ተመርጠው የሚዘጋጁና ለውጥን መሠረት ያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img