Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ኢትዮጵያ የማንም ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ መሆን የለባትም!

  ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነት ተጋርጦባታል፡፡ በውስጥ ጉዳይዋ ገብተው መፈትፈት የሚፈልጉ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየፈርጁ የተለያዩ አሉታዊ ሪፖርቶች እያቀረቡባት ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በጦር ወንጀል ጭምር እየወነጀሏት ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ጥቅሟን ብቻ በማስላት ከምትንቀሳቀሰው አሜሪካ በኩል የሚሰማው ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረርና ህልውናዋን ጭምር የሚፈታተን ነው፡፡ የአሜሪካ አዝማሚያ ከቀጥታ ጣልቃ ገብነት አይተናነስም፡፡ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ተገብቶ መመርያ ሲሰጣት እየተሰማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙ ማናቸውም ሰብዓዊነት የጎደላቸው ድርጊቶች በኢትዮጵያዊያን ጭምር መወገዝ አለባቸው፡፡ ብዙኃን ኢትዮጵያዊያንን የማይወክል ጣልቃ ገብነት ግን ተቀባይነት የለውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ስህተታቸውን በፍጥነት በማረም በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ በተለይ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችፋይዳ ቢስ ትንቅንቆች በመላቀቅ፣ አገር ለመታደግ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ገጽታውን ቀይሮ አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ ሲገባ፣ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ከችግሩ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚቻል መተባበር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በውጭ ኃይሎች የምትፈተነው ውስጣዊ ስምምነት ሲጠፋ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከሥልጣንና ከጥቅም የበላይነት ጋር ብቻ እየተቆራኘ የአገር ጉዳይ ሲዘነጋ፣ ለውጭ ጣልቃ ገብነት በቀላሉ መንበርከክ ይከተላል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነትን ይዞ ስምምነት መፍጠር አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት ለማከናወን፣ ምርጫውን በሰላም ለማጠናቀቅ፣ ኢኮኖሚውን ከገባበት ቅርቃር ለማላቀቅና የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል የጋራ ስምምነት መኖር የግድ መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እየተጠናከረ ነው፡፡

  የዓለም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች የሚዘወሩት ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ታሳቢ በማድረግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከኃያላን አገሮች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ስለሆነ፣ ችግር ማጋጠሙ እየታወቀም ቢሆን በብርቱ ጥንቃቄ ጉዳይን መፈጸም ይቻላል፡፡ ከልዕለ ኃያሏ አሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ኅብረትና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ሆድና ጀርባ እያደረጉ ያሉ ወቅታዊ ችግሮች ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ቢሆን እንኳ፣ ይህንን ከባድ ጊዜ በጥበብ ለማለፍ ኢትዮጵያዊያን በአርቆ አሳቢነትና በአስተዋይነት ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ህልውና የሚፃረሩ ድርጊቶች ሲበረክቱ፣ ልዩነቶችን ለጊዜውም ቢሆን ወደ ጎን በማድረግ በአንድነት መቆም የኢትዮጵያዊያን ዘመን አይሽሬ ልምድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር እየተደፈረና በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እየተገባ፣ መለስተኛ ሊባሉ የሚችሉ ልዩነቶችን ማራገብ ቅንጦት ነው፡፡ ሕዝብን በብሔርና በእምነት በመለያየት ማጋጨትም ሆነ የአገርን ሰላምና መረጋጋት መፈታተን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለውጭ ጣልቃ ገብነት ረዳት መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሰላምና በትብብር መፍታት የሚችሉትን መናኛ ቅራኔ፣ ላልተገባ ዓላማ በማዋል አገርን ቀውስ ውስጥ መክተት ለውጭ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ቀዳዳ መፍጠር ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አይመለሱም፡፡ አገር አተራምሰውም ኢትዮጵያውንን እንደ የመናውያንና ሶሪያውያን ለስደት ከመዳረግ ወደኋላ እንደማይሉ፣ ተራ አሉባልታ ሳይሆን ምልክቶቹ በሚገባ እየታዩ ነው፡፡ ስለዚህ የውስጥ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑ ማንም እንደማይበግራቸው የታወቀ ነው፡፡ አንድነታቸው ሲላላ ግን ታሪካዊ ጠላቶች ጎራዴያቸውን ስለው ይነሳሉ፡፡

  ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም በጀግኖች አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ተጋድሎ አገራቸው ታፍራና ተከብራ እዚህ መድረሷን ሲዘክሩ፣ እነሱም በተራቸው የተላለፈላቸውን አደራ የመወጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጨቋኝ ገዥዎች ሥር ጭምር ሆነው አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ሲከላከሉ መኖራቸው የሚታወቅ ስለሆነ፣ በዚህ ዘመን ደግሞ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባት ጠንካራ አገር ለመገንባት መረባረብ ግድ ይላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይስማሙ ሲቀሩ ጦር መማዘዝ የለባቸውም፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳይ ቢያጋጥም እንኳ፣ በባህላዊ የግጭት አፈታት ሥልቶችና በሽምግልና መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ አልሆን ብሎ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ሕዝብን ፈራጅ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያጋጠሙ ደም ያቃቡና የአገር ሀብት ያወደሙ ግጭቶች፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት በመጋበዛቸው ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ፈተና ደቅነዋል፡፡ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገር ህልውናን የሚፈታተኑ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ያለ ማዳላትና አጉል ወገንተኝነት የተፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶችን በጋራ በማውገዝ፣ የአገራቸውን ህልውና ከውጭ ጣልቃ ገብነቶች ለመከላከል ደግሞ በአንድነት መሠለፍ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ የማንም ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ መሆን የለባትምና፡፡

  ኢትዮጵያ የታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ ስለሆነች፣ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዛ እንድትጓዝ የማድረግ ኃላፊነት የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚደረገው ፉክክር ሥልጡን ሆኖ የሁሉንም ተሳትፎ በእኩልነት እንዲያረጋግጥ ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መጪው ምርጫ ከእንከን የፀዳ እንዲሆን አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አደረጃጀቶችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖር የሚያደርግ አንዱ አማራጭ ቢሆንም፣ ውጤቱ ላይ ብቻ በማተኮር አላስፈላጊ ድርጊቶችን መፈጸም በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ መቆመር ነው፡፡ ከእነ ችግሩም ቢሆን የፖለቲካ ምኅዳሩ በአንፃራዊነት የተሻለ ነው ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ወቅት፣ ምርጫውን ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሊያመቻች የሚችል ዕድል መፈጠር የለበትም፡፡ ይህ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር አለበት ተብሎ ሲጠበቅ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አሳፋሪ ድርጊቶች እንዲደገሙ መፈቀድ የለበትም፡፡ በዚህ ዘመን ከመንግሥታት ባልተናነሰ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችም ምርጫን የማበላሸትም ሆነ የማጭበርበር ድርጊት ውስጥ እየገቡ መሆኑን፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር በስፋት እየተወሳ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ጣልቃ መግባት ለሚፈልጉ ኃይሎች መሣሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ኅብረት ጥቅማቸውን አስልተው ሲመጡ፣ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት ለማስከበር ብርቱ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለኢትዮጵያም የሚበጀው ይኸው ነው፡፡

  አዲሱ ትውልድ ለዘመኑ የማይመጥኑ አሮጌ አስተሳሰቦችን ከአጠገቡ ማስወገድ አለበት፡፡ አዲሱ ትውልድ ከመፈክር ተሸካሚነትና ከፕሮፓጋንዳ አስተጋቢነት መላቀቅ ይኖርበታል፡፡ አዲሱ ትውልድ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ሥነ ምግባርና ሞራላዊ እሴቶች ሲላበስ የአገር ፍቅር ስሜት ይሰርፅበታል፡፡ ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚችል ይረዳል፡፡ በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት ይመራል፡፡ ታሪክን ሲመረምር የጎራ አሠላለፍ ውስጥ ሆኖ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ ሥነ ዘዴዎችን ይከተላል፡፡ አገርን ከሚያጠፉ ይልቅ የሚያለሙ ተግባራት ውስጥ ይገኛል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና እንጂ ለጉልበት ሥፍራ አይሰጥም፡፡ በሐሰተኛ ወሬ ሳይደናገር እውነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል፡፡ በተጣራ ማስረጃ እንጂ በግርድፍ መረጃ አይበይንም፡፡ በአጠቃላይ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እንጂ ለአምባገነንነት አያጎበድድም፡፡ ለአገር ታላላቅ ጉዳዮችና ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጣል እንጂ፣ ለግለሰቦች ተክለ ሰብዕና አይዋደቅም፡፡ ይህንን የመሰለ ብቁና ንቁ ትውልድ ማፍራት ይገባል፡፡ ሰብዕናው የተሞረደ ልሂቅ ትውልድ ሲፈጠር የአገር ገጽታ ይለወጣል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሠረቱን መጣል አለባቸው፡፡ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የመከራ ዘመናት ያብቁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ ይከባበሩ፣ ይዋደዱ፡፡ የውጭ ተፅዕኖን በብቃት መመከት የሚቻለው ውስጣዊ ስምምነት በመፍጠር ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ መሆን የለባትም!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

  በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

  ብሔራዊ ባንክ የሀዋላ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ያላቸውን የ 392 ግለሰቦች የባንክ ሂሳብ አገደ ።

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሕገወጥ የሀዋላ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ብሎ...