Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእነ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) አራት አዋጆች ላይ የሕገ መንግሥት ጥያቄ አቀረቡ

እነ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) አራት አዋጆች ላይ የሕገ መንግሥት ጥያቄ አቀረቡ

ቀን:

በተጠረጠሩባቸው የተለያዩ ወንጀሎች ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ስብሃት ነጋ፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር)ን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎች፣ ለተጠረጠሩባቸው የወንጀል ድርጊቶች በተጠቀሱባቸው አራት አዋጆች ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመራላቸው  ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛና ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት አቤቱታ እንደገለጹት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ክስ መሰል ማመልከቻ ጽፏል፡፡ በማመልከቻው ላይ የተዘረዘረው ክስ ተጣሰ ለተባለው ወንጀል የሕግ ድንጋጌ ሳይጠቀስ ነው፡፡ የሕግ ድንጋጌው ባይጠቀስም ፍርድ ቤቱ ሲመለከተው መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ መሰል ማመልከቻ ያቀረበው ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በዝግ ችሎት እንዲሰሙ የሰጠውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ ነገር ግን ምስክሮቹ ከመስማታቸው በፊት፣ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ማግኘት የሚገባቸውና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ አራት አዋጆች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84 (2) እና በአዋጅ ቁጥር 798/2006 አንቀጽ 3 (2ሀ) እና 4 (2) ድንጋጌዎች መሠረት፣ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ እንዲልክላቸው በአቤቱታቸው አብራርተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መቼ እንደሆነ ባልተጠቀሰበት ሁኔታ በሽብር ወንጀል መጠርጠራቸውን መግለጹን ጠቁመው፣ ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 እንደነበር በማስታወስ፣ ከመጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ አዋጁ ሙሉ በሙሉ ተሸሮ በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 መተካቱን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (1) ድንጋጌ፣ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ እንደማይሠራ ቢደነግግም፣ በአንቀጽ 22 (2) ድንጋጌ ላይ ደግሞ ‹‹ለተከሳሽ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ ይሠራል›› ስለሚል፣ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በየትኛው የሽብርተኝነት ወንጀል ሕግ (አዋጅ) እንደተከሰሱ ሳያመላክት፣ በሽብር ወንጀል መጠርጠራቸውን መጥቀሱ፣ ተፈጻሚነት ያለው አዋጅ (ሕግ) የትኛው አዋጅ እንደሆነ ለማወቅ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው አብራርተዋል፡፡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 25 (3) እና አንቀጽ 61 ድንጋጌ አንፃርም ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ጉዳዩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (1፣ 2 እና 4) ድንጋጌዎች፣ የተከሰሱ ሰዎች መብቶችን በተመለከተ ቀዳሚ ምርመራ በሚያደርገው ፍርድ ቤት፣ በተከሳሾቹ ላይ ተፈጻሚነት ላቸውም የሚል አቋም የያዙ በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም አስተያየት ለመስጠትና አስገዳጅ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን ባላቸው ጉባዔውና ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሊያገኙ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ያቀረቡበት አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4 (1ቀ እና በ) ሥር ተደንግገው የሚገኙ የምስክሮች ጥበቃ አዋጅን ነው፡፡ በአዋጁ የተከራካሪዎችን የግል ሕይወት፣ የሕዝብን ሞራልና የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ፣ ምስክርነት በዝግ ችሎት ሊሰማ እንደሚችል ጠቁመው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የምስክርን ግላዊ ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ክርክር ከሕዝብ ዝግ በሆነ ችሎት ስለሚደረግበት ሁኔታ የደነገገው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4 (1) ድንጋጌ ደግሞ ለምስክር ግላዊ ደኅንነት ሲባል ብቻ ምስክርነት በዝግ ችሎት ሊሰማ እንደሚችል መደንገጉን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (1) ውጪ በልዩ ሁኔታ ላይ በመመሥረት በተጠርጣሪቹ ላይ የሚሰጠው ምስክርነት ለማናቸውም ሚዲያና ታዳሚ ዝግ በሆነ ችሎት እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደውን በግልጽ ችሎት የመስማት መብት የሚነፍግ መሆኑንና ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ በተቃራኒ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሊሰጥበት እንደሚገባና ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲመራላቸው ጠይቀዋል፡፡

በትግራይ ክልል የምርጫ አዋጅ፣ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅና የትግራይ ክልል መንግሥት ስለተመጣጣኝ ውክልና ድንጋጌ አሻሽሎ ያወጣው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት አዋጅ ቁጥር 45/94፣ ከፌዴራል ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን መሆን አለመሆኑን በሚመለከትም የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥላቸው ሰፋ ያለ ትንታኔ በመስጠት አቤቱታቸቸውን አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ትናንት ግንቦት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አከራክሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...