Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዕድልና ዕዳ ያለበት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዕድልና ዕዳ ያለበት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ

ቀን:

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተደረጉት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች  ጅምራቸው ጥሩ የሆነ ውጤት ያስገኘ ቢሆንም፣ በሌላ መንገድ አገሪቱ ዕድልም ዕዳም ያለበት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የሰላም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ሒደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር በተሰኙ ርዕሰ ጉዳዮች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙበት ለአራት ቀናት የሚቆይ አገራዊ የምክክር መድረክ ሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል በተከፈተበት ወቅት ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያ ካሚል፣ ‹‹አገር በተወሰነ አካል ፍላጎትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብቻ ማቆም እንደማይቻል ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ አውነታ ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ አክለውም፣ ‹‹ዘላቂ የሰላም ግንባታ ሥራችን ከግለሰብ የሚጀምር፣ በቤተሰብ የሚመነዘር፣ በኅብረተሰብ ደረጃ የሚተገበር፣ የእሱም ድምር ውጤት አገራዊ ቅርስ ሆኖ የሚያዝ እንደሆነ ይታመናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ላለፉት ሦስት ዓመታት ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው የተባሉትን ጉዳዮች በጥናት በመለየት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሰላም ሚኒስቴር የሐሳብ ማሰባሰቢያ መድረኮችን ቅደም ተከተል በማውጣት ሲያከናውን እንደቆየ ያስረዱት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ምናልባት አንዳንዶቹ ጉዳዮች ውጤታቸውን ለማየት ጊዜ የሚጠይቁ ይሆናሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በባህሪያቸው ባጠረ ጊዜ ውጤት ማየት የሚያስችሉ ሆነዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ጅምራቸው ጥሩ ውጤት ያስገኘ ቢሆንም፣ በሌላ መንገድ ዕድልም ዕዳም ያለበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ የዞሩ ድምሮቻችንን ጨምሮ አዳዲስ አዳጊ ፍላጎቶችን ታክለውበት ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችም አጋጥመዋል ብለዋል፡፡

የተግዳሮቱን መንስዔና ምንጩን አውቆ በቀጣይነት ሥረ ነገሩን ለመመልከት ዕድል የሚሰጥ ሆኖ ስለተገኘ፣ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት በማየት ዓለም አቀፋዊ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ጋር በማናበብ ሌሎች አገሮች ምን ዕድሎችንና ዕዳዎችን አስተናግደዋል? የሚሉ ጉዳዮችን አንጥሮ ለማውጣት በማሰብ የምክክር መርሐ ግብሩ እንደተዘጋጀ አስታውቀዋል፡፡

በመክፈቻው ዕለት ‹‹ኢትዮጵያ በሽግግር ጎዳና›› ያለፉትን ሦስት ዓመታት አገሪቱ እያለፈችበት ያለው ሽግግር ያሉት ባህሪያት፣ ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ሽግግሮች በምን ይለያል? እንዲሁም እየተደረገ የሚገኘው ሽግግር፣ ከሽግግር ጥናት አንፃር እንዴት ይታያል? የሚለውን የተመለከተ ጥናት በሚኒስትሯ አማካሪ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ቀርቧል፡፡

የሽግግር ጥናት ከአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የሚደረግ የሽግግር ሒደት ላይ የሚያተኩር ጥናት እንደሆነ ያስረዱት አብዲ (ዶ/ር)፣ ፖለቲካዊ ሽግግር ደግሞ እየሞተ ባለውና በሚወለደው ሥርዓት መካከል ያለ የእንጥልጥል ጊዜ እንደሆነ፣ ይህም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ወጥና ቀጥተኛ ያልሆነ፣ ክፍት፣ ሒደታዊ፣ በማያቋርጥ መንገድ የሚያድግና እንዲሁም በተለያየ ሁኔታ የሚተነተን የወል ባህሪያት ያሉት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

መከፈት የሚለው ወይም የፖለቲካ ሊበራላይዜሽን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከታዩት ጉዳዮች አንዱ መሆኑን፣ በዚህም አፋኝና ጨቋኝ የነበሩ ሒደቶችን መናድና ማፍረስ የሚሉት ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን እነዚህን ሒደቶች መሸከም የሚችል የዴሞክራሲ መዋቅሮችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ አንፃር የአምባገነንና የከፊል አምባገነን ሥርዓት የማፍረስ ሒደትን ተከትሎ የሚመጣ ከፍተኛ የሕዝብ ጉጉትና ተስፋ፣ ወይም ወዲያው ሁሉም የትሩፋቱ ውጤት እንዲደርሰው የመፈለግ ዝንባሌ መኖሩን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ብዙ ጊዜ ተቋማት እየተሻሻሉና እየተቀየሩ ስለሚሄዱ በአንድ ጊዜ የፀና መሠረት እንደማይኖራቸው በዚህም ብዙውን ጊዜ ነገሮች እርግጠኝነት የሚባለው ነገር አይታይባቸውም የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከዘውዳዊ ወደ አብዮታዊ፣ ከአብዮታዊ ወደ ከፊል አምባገናነዊ ዓይነት የተለያዩ የመንግሥት አማራጮችን እንደተጠቀመች ያስታወሱት አብዲ (ዶ/ር)፣ አማራጮቹ ደም መፋሰስና ለአገሪቱ መጥፎ ምሥል ጥለው ያለፉ ሒደቶች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሰላም ትፈልጋለች በሚለው ጥናት ውስጥ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ ያሉት የሚኒስትሯ አማካሪ፣ የመጀመርያው ከግጭት ነፃ መሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አብዛኘውን ጊዜ ግጭትን የሚወልዱ ነገሮች መዋቅራዊ ከሆኑ ችግሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ፣ እነሱን ማስተካከልና ሦስተኛው የሰዎች ውስጠ ሰላም ላይ መሥራት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

በምክክሩ የሁለተኛው ቀን መድረክ የሽግግር ተሞክሮዎችና ንፅፅራዊ ትንታኔ የሚል የውይይት መነሻ ሐሳብ ከስትራቴጂ ጉዳዮች ተቋም ተመራማሪ በሆኑት ሔኖክ ጌታቸው (ዶ/ር) ቀርቧል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ ካለበት የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ሌላ የፖለቲካ ሥርዓት ለመግባት ሽግግር ያደርጋል ያሉት ሔኖክ (ዶ/ር)፣ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ የፖለቲካ ሽግግር ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ ሽግግር ውስብስብና ከአገር አገር መለያ ባህሪዎቹ፣ ምክንያቶቹ፣ እንዲሁም ውጤቶቹ የሚለያዩ እንደሆነ ያስረዱት ተመራማሪው፣ የፖለቲካ ሽግግር እርግጠኛ መሆን የማይቻልና ሁሌም ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር የማያመራ በመሆኑ፣  ሒደቱ ተቀልብሶ ወደ አምባገነን ሥርዓት ወይም ቅይጥ አምባገነን ሥርዓት ሊያመራ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር የተለያየ መልክ የያዘና የተለያዩ ተዋንያን ሚና የሚጫወቱበት  መሆኑን፣ ለዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር አንድ ዓይነት ሞዴል እንደሌለው ያስረዱት ሔኖክ (ዶ/ር)፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከስኬታማ አገሮች ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡

በብዙ ስኬታማ አገሮች የሚታየው ተቃዋሚ ኃይሎች በትብብር እንደሚሠሩና አንድ ሆነው የሚያጋጥማቸውን ፈተና እንደሚወጡ፣ ከተከፋፈሉ ተስፋን እንደሚያቀጭጩ፣ ያለፈ ቁጭትና በደል ላይ አለማተኮር፣ በሽግግር ጊዜ ማስተዳደር ክህሎትና ቁርጠኝነት እንደ መጠየቁ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣ የደኅንነት ተቋማት ከበፊት ሚናቸው ተላቀው እንዴት የኅብረተሰቡ ጠባቂ ይሆናሉ የሚለው ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...