Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ቱሪዝም ማለት ቅንጡ ሆቴሎችን ማከራየት ሳይሆን ያሉንን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ትሩፋቶችን ማሳየት ነው›› ሔኖክ ሥዩም፣ የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት

ባለፉት 15 ዓመታት የቱሪዝምና የባህል ዘርፉ ላይ የተለያዩ ተግባቦት ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በፋና ሬዲዮ ላይም የኢትዮጵያን ባህልና ዕሴት የሚያስተዋውቅ ኅብር የተባለ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚተላለፍ የ30 ደቂቃ ፕሮግራም አዘጋጅ ነበር፡፡ በየሦስት ወሩ የሚወጣ ‹‹ቱባ›› የሚባል መጽሔት በማዘጋጀት ለአንባቢያን ተደራሽ አድርጓል፡፡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ሥዩም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡ የማኅበሩን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ለምን ዓላማና ግብ ተቋቋመ? የአባላቱ ስብስብ ከየት ከየት ነው? እንዴትስ ተደራጀ? ከሌሎች የጋዜጠኞች ማኅበር ለየት ማለት ለምን አስፈለገ?

አቶ ሔኖክ፡የኢትዮጵያ የቱሪዝምና የጋዜጠኞች ማኅበር የዛሬ 13 ዓመት ገደማ አካባቢ በተለያየ መልኩ የቱሪዝም ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ዘገባዎችን የሚሠሩ ጋዜጠኞች ተሰብስበው በጋራ ለመሥራትና ለመመካከር እንዲሁም ዕድሜያቸውን ለማሳደግ የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡ በወቅቱ የማኅበራት የመደራጀት መብትና ሕጋዊ ሰውነት የማግኘቱ ነገር በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሙያው ሰዎችን  አቀራራቢ በመሆኑ፣ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ግንኙነት በመፍጠርና በጋራ ችግሮችን በመፍታት ሰፊ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በወቅቱም የባህልና ቱሪዝም እንደሌሎች አገሮች የጉዞና የጉብኝት ጋዜጠኞች ተሰብስበው እንዲሠሩና ማኅበር እንዲያቋቁሙ ፍላጎቱ ስለነበራቸው ማኅበሩን ለማቋቋም ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ በዓለም ላይም አብዛኛውን አገሮች የተጓዦች ማኅበር ስለነበራቸው በማኅበራቸው በኩል የዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ይታደማሉ፣ ምክክሮችን ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆነን፣ በክሮሽያ በተዘጋጀው የዓለም የቱሪዝም ሚዲያ ጉባዔ ላይ ከማኅበሩ የተመረጡ ጉባዔውን ሊካፈሉ ችለዋል፡፡ ከአምስት ወይም ከስድስት ወር በኋላም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ጋዜጠኞችም ዓመታዊ የቱሪዝም ሚዲያ ጉባዔ ሚኒስትር ዴኤታዋ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ቢሾፍቱ ላይ የመጀመርያውን የቱሪዝም ሚዲያ ጉባዔ ለማካሄድ ተችሏል፡፡ ከዚያ በኋላም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚዲያ ፎረም ተቋቁሟል፡፡ የሚዲያ ፎረሙም ከመንግሥትም፣ ከግልም እንዲሁም ከሚዲያ ያልሆኑ ተቋማት በመሆኑ ሕጋዊ የሆነ ሰውነት ለማግኘት ተቸግረን ነበር፡፡ በዚህም ሒደት በተደጋጋሚ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄዎችን አቅርበናል፡፡ ነገር ግን የአደረጃጀትና የፖሊሲው መመርያው ፈቃድ ስላልሰጠን ፈቃድ ማግኘት አልቻልንም፡፡ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አማካይነት ፈቃድ በማግኘቱ ሊቋቋም ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል አባላት አላችሁ?

አቶ ሔኖክ፡- ከአባላት ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ብዙ የሚባሉ ጋዜጠኞች አባል ሆነው ነበር፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአገር ውጭ በመሰደድ፣ ዘርፉን ለመደገፍ በሚደረገው ርብርብ ወቅት እልሃቸውን በመጨረስ የተዉትም በመኖራቸው የአባላቱ ቁጥር አነስተኛ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ 35 ያህል አባላት አሉን፡፡ በአጭር ጊዜም ይህንን ቁጥር በማሳደግና አብዛኛው የመገናኛ ብዙኃን ራሱን የቻለ የቱሪዝም ጋዜጠኞች እንዲኖራቸው የምንሠራ ይሆናል፡፡ ማኅበሩም በዋናነት የተመሠረተው የጋዜጠኛውን አቅም፣ ክህሎትና ዕውቀት ለማሳደግ ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዕውቀት ጋር ተያይዞ ያለውን ውስንነት ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎችን የምንሠራ ይሆናል፡፡ ከቱሪዝሙም የምናገኘውን ጥቅም በማሳደግና ማኅበረሰቡም ስለአገሩ በቂ ዕውቀት እንዲኖረው ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡– የቱሪዝም ሆነ የባህል ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ እንዴት ትገልጸዋለህ? ብዙ ምቾት እንደሌለውና ትኩረት እንዳልተሰጠው ይነገራል፡፡ ተግዳሮቱን እንዴት ትገልጸዋለህ?

አቶ ሔኖክ፡- በእርግጥ ተግዳሮቱ በጣም ከባድ ነው፡፡ ተግዳሮቱንም በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛ ከውጭ ሴክተሩ የሚመለከተውና የሚመራው ተቋም በቂ የሆነ የፋይናንስ፣ የሎጀስቲክና የሞራል ድጋፍ አለማድረጉ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃኑ ጉዳዩን እንደ ተራ ጉዳይ ስለሚያዩትና ከሆነ ይሠራል ካልሆነ አይሠራም የሚል አቋም ስላላቸው ነው፡፡ ይኼም ጋዜጠኛው በሚያገለግልበት ተቋም በኩል ጥሩ ድጋፍ ስለማያገኝ በዘርፉ ላይ ትልቅ ችግር እየሆነ ይገኛል፡፡ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎች በዋናነት የሚያነሱት ነገር የቱሪዝም ዘርፉ ምንም ዓይነት ገንዘብ አያመጣም የሚል እንደሆነና ቀለል ያሉ የመዝናኛና የስፖርት አየር ሰዓቶች በቀላሉ ብር እንደሚያስገኙ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃኖች የቱሪዝም ዘርፍ ላይ እየሠሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ በፊትም ዋልታና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለዘርፉ የአየር ሰዓት በመስጠትና ማኅበረሰቡ ስለአገሩ እንዲያውቅ በማድረግ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህንን ተሞክሮ ለሌሎች የመገናኛ ብዙኃኖች በማሳየትና እነዚህም ተቋሞች እንደከዚህ ቀደሙ ለማኅበረሰቡ በማስተላለፍ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በዓለም አቀፉም ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ሚዲያዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– ሙያው ካለበት ችግር ለማውጣት ማኅበሩ ምን ለመሥራት አስቧል?

አቶ ሔኖክ፡እውነት ለመናገር በአሁኑ ወቅት ሙያውን ወዶ የሚሠራ ሰው በርካታ ነው ለማለት ይቸግራል፡፡ ነገር ግን ማኅበራችን ጋዜጠኛው አቅም እንዲኖረው ለማድረግ ሰፊ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡ አቅም ኖሮት ራሱን በዕውቀት ካበለፀገና በኢኮኖሚ ካሳደገ በሚሠራው ሥራ ስኬታማ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ኢንዱስትሪ ውስጥ ጋዜጠኞቹ የራሳቸውን አሻራ ያኖራሉ የሚል እምነት አለን፡፡ በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ባህልና ሌሎች ዕሴቶች ላይ ብዙ አልሠራንም፡፡ ይኼንንም ታሳቢ በማድረግ ጋዜጠኛው አቅም ኖሮት እንዲሠራ ምቹ መንገዶችን ለመፍጠር እንቅስቃሴዎችን እያደረግን እንገኛለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ማኅበራት ስለሚገኙ ከነሱ ጋር በቅንጅት በመሥራት አገር ውስጥ በብዙ ቋንቋዎች ስለቱሪዝም የሚሠሩ ጋዜጠኞችን  ቁጥር ለማብዛት ሰፊ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ ይኼም በአጭር ጊዜ ውስጥ የምንሠራው ሥራ ይሆናል፡፡ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ሙሉ ጊዜውን ስለኢትዮጵያ ባህል፣ ቅርስ፣ ተፈጥሮ፣ የቱሪዝም ሀብቶች የሚሠራ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ለማቋቋም ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይኼም በሌሎች አገሮች ተሞክሮ መሠረት ውጤታማ እንድንሆን ያስችላል፡፡ የምንፈልገውን የቱሪዝም ዕድገትና ብልፅግና ዕውን እንዲሆን ለማስቻል ዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡– ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ወስዶ በቅንጅት ለመሥራት ማኅበራችሁ ምን ዓይነት እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል?

አቶ ሔኖክ፡ የቱሪዝም ዘርፍን ከሚመሩ ተቋሞች ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አለን፡፡ የተለያዩ ድጋፎችንም እያደረጉልን ይገኛል፡፡ የመንግሥት አሠራር በፈቀደ ሁኔታዎች ላይ ከእኛ ጋር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በፊትም የዓለም የጉዞ ፀሐፊዎች ወደ ኢትዮጵያ ተጋብዘው በመጡ ጊዜ የማኅበራችን አባላት የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ በአጭር ጊዜም ጋዜጠኞችን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ ልምድ ቀስመው እንዲመጡ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በፊትም የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በተናጠል በሰጠን ዕድል መሠረት የተለያዩ አገሮች ላይ ሄደው የተለያዩ ተሞክሮዎችን ቀስመው የመጡ ጋዜጠኞችም ነበሩ፡፡ በማኅበሩም ሆነ በአጋር ተቋማት በሚመጡ ዕድሎች በመጠቀም ተሞክሯችንን የምናሰፋ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በቱሪዝም ላይ እንዲሠሩና ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቀናል፡፡

ሪፖርተር፡– መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር አብራችሁ ትሠራላችሁ፡፡ የጋዜጠኝነት ነፃነታችሁን እንዴት ትጠብቃላችሁ?

አቶ ሔኖክ፡- ከዚህ በኋላ የጋዜጠኝነት ነፃነት ጉዳይ የምንደራደርበት አይደለም፡፡ ጤነኛ የሆነ አስፈጻሚ አካል ካለ በመካከላችን የምኞትና የግብ ልዩነት አለ ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ ኢትዮጵያ በቱሪዝም በልፅጋ ማየት የሚፈልግ የመንግሥት የሥራ ኃላፊና በዘርፉ ላይ በሚሠራ ጋዜጠኛ መካከል የጥቅም የመንፈስም ግጭት ይኖራል የሚል  እምነት የለንም፡፡ ተቋማዊ በሆነው ግንኙነታችን ከመርህና ከጥቅም ጋር ብዙ የሚያጋጨን አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የጋራ ሥራና የጋራ ግብ በመሆኑ ነው፡፡ ግለሰቦች ወይም ደግሞ ኃላፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ እንደ ጋዜጠኛም እንደ ዜጋም መንግሥት እንዲያርምና ጠንካራ የሆነ የቁጥጥር ሥራ እንዲሠራ ጫና የምንፈጥር ይሆናል፡፡ በመካከላችንም የግብ ልዩነት ይኖራል ብለን ስለማናስብ የሙያ ነፃነታችንን ይጋፋል የሚል ሥጋት የለንም፡፡

ሪፖርተር፡– ብዙ ጊዜ ባህልና ቱሪዝም ይባላል፡፡ ግን ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ስሙ ጎልቶ የሚነሳው ቱሪዝም ነው፡፡ ቅርስን ጨምሮ እኩል ትኩረት እንዲያገኝ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ሔኖክ፡- የኢትዮጵያ የቱሪዝም መሠረት በዋናነት ባህሏ፣ ቅርሷና ተፈጥሮዋ በመሆኑ እነዚህ ነገሮች ካልተጠበቁና ካልተሠራባቸው ቱሪዝሙ መኖሩ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ የኢትዮጵያ የባህል ዕሴቶች ካላደጉ ከቱሪዝም የምናገኘው አየር ላይ የሚቀር ይሆናል፡፡ ተቋማቱ የተለያዩና ምንም የሚያገናኛቸው ነገር ባይኖር እንኳን የኢትዮጵያ ቱሪዝም የተመሠረተው በነዚህ ነገር ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተራሮቿ፣ ወንዞቿ፣ ቅርሶቿ፣ ባህላዊ ምግቦቿና በሌሎች ነገሮቿ የታወቀች በመሆኗ እነዚህን በመያዝና በማሳደግ እንዲሁም ለዓለም ለማስተዋወቅ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ቱሪዝም ማለት ቅንጡ የሚባሉ ሆቴሎችን ማከራየት ሳይሆን፣ ያሉንን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ትሩፋቶች የምናሳይበት እንደሆነም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንፈጥራለን፡፡ ዘርፉ እየተተወ ነው የሚለውን ለመለወጥ ዕድሎችን እንፈጥራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ በይፋ መመሥረቱን ባበሰራችሁበት ዕለት ሽልማትና ዕውቅና ሰጥታችኋል? ለምን? ለወደፊቱስ ይቀጥላል?

አቶ ሔኖክ፡- ከምንሠራቸው ነገር አንዱና ዋነኛ በየዓመቱ ዕውቅና እና ሽልማት መስጠት ነው፡፡ ከዚህ በፊትም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሽልማት ወስዷል፡፡ ሽልማቱንም የወሰዱት የኤዥያ ፓስፊክ ትራቭል ጸሐፊዎች አሶሴሽን ሽልማት ባበረከተላቸው መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ በዓለም እንደዚህ ዓይነት ማኅበራት ዕውቅናና ሽልማት ይሰጣሉ፡፡ እኛም ይኼንን በመመርኮዝ ከዚህ በኋላ ሽልማት የምንሰጥ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ የቱሪዝምና ባህል ልማት ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና እንሰጣለን፣ በአደባባይም እናመሠግናለን፡፡ ከዚህ ባሻገር ለመጀመርያ ጊዜ ማኅበራችን መመሥረቱን ይፋ ባደረግንበት ወቅት ክብርት ወ/ሮ ታደለች ዳሌቾን በኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚዲያ ታሪክ ቱሪዝም ላይ የሚሠራ ጋዜጠኛ እንዲፈጠርና አቅሙን እንዲያሳድግ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው የሕይወት ዘመን ዕውቅና ሰጥተናቸዋል፡፡ ለሳቸው የተሰጠው ሽልማትም ለ11 ዓመታት ገደማ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ለዘርፉ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ከተመሠረተ ቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ከእዚያ በፊት ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ሠርታችኋል፡፡ በወቅቱ ምን ዓይነት ችግር አጋጥሟችኋል?

አቶ ሔኖክ፡- ተቋማችን ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ ብንፈልግም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ዕውቅና ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ከድጋፍም አኳያ ምንም ዓይነት ዕገዛ ሲደረግልን አልነበረም፡፡ በተለይም ዘርፉን እየመራ የነበረው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተገቢውን ድጋፍ አላደረገልንም፡፡ በየጊዜውም ከሚመደቡና ከሚነሱ ኃላፊዎች ጋርም ግብ ግብ በመፍጠር ኃላፊነት የተሞላው አሠራር እንዲሠሩ ተጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ በዘርፉ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ ከውጭ አገር አንድ ጊዜ ለሚመጡ ጋዜጠኞች የሚደረግ አቀባበልና መስተንግዶ ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ለሁለትና ሦስት ዓመታት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ቢሆንም ይህ ተደርጎ አያውቅም፡፡ ሚኒስቴሩም በዘርፉ ላይ ምን እየሠራ ነው የሚለውን ለመናገር የሚቸግር ነው፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት ጋዜጠኛው ምን እየሠራ ነው? ምንስ  እያደረገ ነው? የሚለውን  ተጠይቀንም አናውቅም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...