Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ የተመሠረተ የማድረግ ሒደት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከዚሁ ጋር ተያይዘው ያሉ ለዘመናት ያልተፈቱ ችግሮች ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ኢኮኖሚያዊ ስንክሳሮች መካከል  ይጠቀሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ብቻ ሳይሆን የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከማስተዳደር አንፃር ያለው ክፍተትም የችግሩ አካል ነው፡፡ ጥቁር ገበያ ጎልቶ መውጣትና ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ አሻቅቦ መገኘቱ እንዲሁም የጥቁር ገበያው ጉልበት መታየት ሁኔታውን አብሶታል፡፡ ያለውን እጥረት ተከትሎ የሚታየው ሕገወጥ ሥራም የውጭ ምንዛሪ ሥርዓቱ ጤናማ እንዳይሆን አድርጓል፡፡

እንደ አገር ችግር ሆኖ የቆየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አጠቃላይ የግብይት ሒደቱን መስመር ለማስያዝ በሚል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተደጋጋሚ የሚወጡ መመርያዎች ምናልባት በጊዜያዊነት መፍትሔ ሆነው ይሆናል እንጂ፣ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የመመርያዎቹ መለዋወጥ የሚያሳውም ችግር መኖሩን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በገበያ መወሰን አለበት የሚል ሆኗል፡፡

በዚሁ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በገበያ ላይ ወደተመሠረተ ሥርዓት ለመግባት የሦስት ዓመታት ዕቀድ ተይዞ እየተሠራበት እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ግን ይበልጡኑ ለዋጋ ንረት ምክንያት ይሆናል በሚል በተለያዩ ወገኖች አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚል አመለካከትን ማሳደሩ አልቀረም፡፡

በቅርቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከተሰጡ አስተያየቶች መገንዘብ የሚቻለው የብር የምንዛሪ ዋጋ በገበያ መወሰን የዋጋ ንረትን ያስከትላል የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህ ማለት የምንዛሪ ዋጋ በገበያ ዋጋ ይመራ ማለት የብር የመግዛት አቅምን በማዳም የምንዛሪ ዋጋ አሁን ካለው የበለጠ እንዲሆን ማድረጉ ስለማይቀር የኑሮ ውድነትን ያስከትላል የሚል ነው፡፡

የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ ግን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት የሰጡትና አሁን እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በቅርብ የሚከታተሉ አንድ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ሥርዓት ያልነበረው፣ በገበያ የማይመራ ስለነበር ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ የምንዛሪ ዋጋው እንደቀደመው የሚቀጥል ከሆነ፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ እየሳረፈ ያለው ተፅዕኖም ሄዶ ሄዶ አደጋውን የከፋ ስለሚያደርገው ገበያውን ነፃ ማድረግና የምንዛሪ ዋጋውም ትክክለኛውን መንገድ እንዲከተል የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ተገቢ ነው፡፡   

የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ መወሰን አስፈላጊነት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንደሰጡት ባለሙያው፣ የምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት ስለማይመጣጠን አማራጩ የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ ነው፡፡

አሁን ከአቅርቦቱ በላይ ፍላጎት ያለ በመሆኑን በመጥቀስም ይህንን ለማስተካከል የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በገበያ ሥርዓት እንዲራመድ ማድረጉ የግድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው እስካሁን የተመጣበትን አሠራር ማስቀጠል ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን በመገንዘብ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት እንደሚታየውም የምንዛሪ ዋጋው የቱንም ያህል ቢሆን ሰው እየገዛ መሆኑ መታሰብ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ አንድ ዶላር 27 ብር እያለ እጥረት ነበር፡፡ ግን አሁንም 41 ብርም ሆኖ እጥረት አለ›› ያሉት እኚሁ ባለሙያ፣  41 ሆኖም ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ መኖራቸው በዶላሩ አስመጥተውበት እዚህ ቢሸጡ የሚያዋጣው እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡ አሁን ያለው የምንዛሪ ዋጋው ያለውን ፍላጎትና አቅርቦት የሚመጥን ባለመሆኑ ይህንን ማመጣጠን ያስፈልጋል፡፡

በእጥረቱ ሳቢያ አንዳንዶች በመደበኛ ገበያውና የጥቁር ገበያን እያደበላለቁ የሚጫወቱት አደገኛ አካሄድም ሊገታ የሚችለው ገበያውን ነፃ ማድረግ እንደሆነም ከባለሙያው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ለመድኃኒት ማስመጫ ዶላር እየጠፋ መኪኖች ይገባሉ፡፡ ሱፐር ማርኬቶች ሙሉ ናቸው፡፡ ይህ ያለው ዶላር በትክክለኛው እየሄደ አይደለም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ስላሉ ዶላር ትክክለኛ ዋጋውን አይመጥንም፡፡ ከፍላጎት አንፃር ያለውን ችግር ለመቅረፍ አሁንም ገበያውን ነፃ ማድረግ ጥሩ አማራጭ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡   

እስካሁን ያለው አሠራር ከአቅርቦት አንፃር ሲታይ ደግሞ ዕቃ ወደ ውጭ የሚልኩ ኤክስፖርተሮች ለሚልኩት ዕቃ ትክክለኛ ዋጋቸውን ስለማያገኙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዋና ገበያው ወጥተው ወደ ጥቁር ገበያ መሸጥ መጀመራቸውም ሌላው ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡  በጥቁር ገበያ ከተሸጠ ደግሞ ምንም ሲስተምና ቁጥጥር ስለማይኖር የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እያደገ ይሄዳል፡፡

ስለዚህ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አሠራሩ ችግር ውስጥ ሆኖ መቆየቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸውን እንደ ማኑፋክቸሪንግ ያሉ ዘርፎች ውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም አሁን ያለው አሠራር ኤክስፖርተሮችና ከውጭ የሚልኩ ሰዎች (ሬሚታንስ) ለሚያመጡት ዶላር ትክክለኛውን ዋጋ እንዳያገኙ ማድረጉ ነው፡፡ ይህ ማለት መንግሥትን ወይም ነጋዴውን እንዳይደጉሙ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፣ ማግኘት የሚገባቸው 50 ብር ሆኖ 41 ብር ሲሰጣቸው የዘጠኝ ብር ያህል አስመጪዎችን ይደጉማሉ ማለት ነው በማለት አሉ ያሉትን ችግር በተለያየ መንገድ ገልጸዋል፡፡  

የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ሲመራ ወደ ውጭ ዕቃ የሚልኩና ሬሚታንስ የሚልኩት ወደ መደበኛው ምንዛሪ እንዲመጡና በጥቁር ገበያና በመደበኛው የባንክ ምንዛሪ ዋጋ መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ይህም የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ያስችላል በማለት ውሳኔው የሚያስገኘውን ጥቅም ተናግረዋል፡፡ ሌላው የውጭ ምንዛሪው የበለጠ ገበያ መር በሆነና ቁጥጥሩ ለቀቅ በተደረገ ቁጥር ማኑፋክቸሪንግ ውስጥ የተሰማሩ ኩባንያዎችም የሚፈልጉትን ውጭ ምንዛሪ አደራድረው ማግኘት የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ አሁን በሠልፍና በኮታ ወይም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተብሎ እየተለየ የውጭ ምንዛሪ የማደሉ አሠራር እየቀነሰ፣ ከዚያም እየቀረ እንዲሄድ ማስቻሉንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ዋጋ ይሁን የሚለው ሲተገበር ከመንግሥት አንፃርም የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ አብዛኛው በራሱ በሚያገኘው ዶላር ላይ የተመሠረተ የሚደርገው ሲሆን ተጨማሪ ከፈለገም ገበያ ውስጥ ተወዳድሮ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

የውጭ ምንዛሪን በገበያ እንዲሆን በመንግሥት የተወሰነው ውሳኔ እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚፈጸም ቢሆንም፣ ውሳኔውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን ወሳኝ የሚባሉ ጉዳዮችን ማሟላት ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ከማድረግ በፊት ግን በብርቱ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ  የተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የውጭ ምንዛሪን በማሳደግና የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በማስተካከል ሥራ ላይ ያለ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን 3.5 ቢሊዮን ዶላር ማድረሱ እንደ አንድ ማሳያ ይወሰዳል፡፡

ይህንን ክምችት በየዓመቱ እያሳደጉ በመሄድ ወደሚፈለገው ግብ መድረስ ይቻላል፡፡ ሌላው እንዲህ ያለው ዕርምጃ ሲወሰድ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑ ነው፡፡ በገበያ እንዲመራ እየተደረገ ጥቁር ገበያ አብሮ እየጨመረ ከሆነ ይህ ፖሊሲ አልሠራም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በ20 በመቶ ዲቫልዩ ተደርጎ የዋጋ ንረትም 20 በመቶ ከጨመረ ኤክስፖርተሩ ምርቱን እዚህ ቢሸጠው ይሻለዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ወደ ውጭ ለመላክ አይገፋፋም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለ የዋጋ ንረት እንዳይኖር የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ይጠይቃል፡፡

የብዙዎች ሥጋት ግን የምንዛሪ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረቱን ያብሰዋል የሚል ነው፡፡ ባለሙያው ግን ይህንን ሥጋት፣ ‹‹የዋጋ ንረትን ስንመለከት አሁን የዋጋ ንረትን የሚያሽከረክረው የምግብ ዋጋ ነው፡፡ በጣም የናረው የምግብ ዋጋ ነው፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ እህልና እንደ ሥጋ ያሉ ምርቶችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ደግሞ ከውጭ የሚመጡ አይደሉም፤›› ይላሉ፡፡

ምግብ ነክ ያልሆኑት ነገሮች ድርሻቸው 50 በመቶ አይሞላም፡፡ ስለዚህ በዋናነት የዋጋ ንረቱን እያባባሰ ያለው የምግብ ዋጋ በመሆኑ የምግብ ዋጋ ላይ ያለውን የዋጋ ንረት መቀነስ ላይ በእጅጉ መሠራት አለበት፡፡ እስካሁን ያለውም ሁኔታ ሲታይ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታየው የዋጋ ንረት ምክንያቶች በአቅርቦት ችግር ነው፡፡ የአቅርቦት ችግሩ ደግሞ በተለይ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የመሳሰሉ ችግሮች የፈጠሩት የዋጋ ንረት ጭምር በመሆኑ ይህ ሁኔታ ከተስተካከለ ሥጋቱ እንደማይኖር ይጠቅሳሉ፡፡

አሁን መንግሥት በአብዛኛው የገንዘብ ልቀት ቢቀንስም አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ የማድረጉን ሥራ ከዋጋ ንረት ቁጥጥር ጋር አብሮ መሄድ አለበት የሚባለውም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡

ስለዚህ እንደ ባለሙያ ምልከታ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መጨመር ለዋጋ ዕድገት ምክንያት መሆኑ ባይቀርም፣ አብዛኛው የዋጋ ንረቱ ያለው ምግብ ነክ የሆኑ ዕቃዎችና ምርቶች ላይ በመሆኑ ይህንን ከተቆጣጠረ የተፈራው ነገር እንደማይኖር ነው፡፡ ምናልባት በሽግግር ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ ገበያው ከተረጋጋ በኋላ ሁሉም ዕቃ ትክክለኛውን ዋጋ ካገናኘ የዋጋ ንረቱ እየጠፋ ይመጣል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን አቅርቦት ላይ መሥራቱ ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ግን አቅርቦት ላይ እንዳይሠራ በሰው ሠራሽ ዋጋ የተያዘ በመሆኑ ወደ አቅርቦት ሥራ ለመግባት የሚገፋፋ የለም፡፡ አገሪቱ ደግሞ በሌላት ገንዘብ ልትኖር ስለማትችል የውጭ ምንዛሪ ለውጡ የአቅርቦት ዘርፉንም ሊያሳድገው ይችላል የሚለውንም ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ በጥቅል ሲታይ አሁን ላይ የምንዛሪ ዋጋው 27 ብር ሆኖ ይቀጥል ቢባል አይሠራም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ወደ ጥቁር ገበያ ይሄድና በ27 ብር የሚገዛው በጣም ጥቂት የገበያ ክፍል ስለሚሆን እንደ አገር ትልቅ ጉዳት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ የውጭ ምንዛሪ ወጪዎችን ያዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪን በገበያ ዋጋ እንዲመራ ለማድረግ የሦስት ዓመታት ግብ ተቀምጦ በዚያ መሠረት እየሄደ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች