Sunday, July 14, 2024

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ባለሀብት ጥሩ ጥቅም ያስገኘ ውለታቸውን እያስታወሱ፣ ከባለሀብቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ብድር ወስደው አይመልሱም። በዚህ ድርጊታቸው የተበሳጨው ባለሀብቱ እንዴት እንደሚያስቆማቸው እያሰላሰለ በነበረበት ቀን ሚኒስትሩ የለመዱትን ሊፈጽሙ ባለሀብቱ ቤት በጠዋት ተገኝተዋል]

 • እንዴ ዛሬ ደግሞ እንዴት ሳይደውሉ መጡ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዲያው ድንገት አስቸኳይ ነገር ገጥሞኝ ላማክርህ ብዬ እንጂ ለመምጣትስ አላሰብኩም ነበር። 
 • ምነው ምን ችግር ገጠመዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አይ ችግር እንኳን አይደለም ቀላል ነው፣ እኔ የምልህ…
 • አቤት?
 • ወደ እዚህ ስመጣ በአንተ ሕንፃ በኩል ነበር ያለፍኩት። መሬቱ ለካ እንደዚህ የተንጣለለ ነው በል። አሁን ተጨማሪ ሕንፃ ከጎኑ ማቆም ይችላል እንዴ? 
 • አይ ክቡር ሚኒስትር ከዚያ ቦታ ከተነሱ በኋላ ሳይጠፋብዎት አይቀርም፡፡ 
 • ምኑ ነው የሚጠፋብኝ?
 • እዚያ እያሉ እኮ አንድ ኪስ ቦታ በአንዴ ዓይተው ምን ሊያቆም እንደሚችል ይገምቱ ነበር፣ ዛሬ ግን
 • ዛሬ ግን ምን?
 • ይኸው ለፓርኪንግ እንኳ የማይሆን ቦታ ሌላ ሕንፃ ያቆማል እያሉኝ ነው። 
 • ዋናው መሬቱን በጥሩ ጊዜ ማግኘትህ ነው፣ እኔ ባልኖር አታገኘውም ነበር። 
 • እሱስ ልክ ነው፣ ውለታዎን መቼም አልረሳውም።
 • ይልቅ ወደ መጣሁበት ጉዳይ ልግባአንድ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ የተወሰነ ብር ብታበድረኝ ብዬ ነው ዛሬ ስበር በጠዋት የመጣሁት። 
 • አይይ… ክቡር ሚኒስትር
 • ቶሎ እመልሳለሁ፣ ደግሞ 600 ሺሕ ብር ብቻ ነው የምፈልገው። 
 • ቢኖረኝ ደስ ባለኝ ግን
 • ግን ምን?
 • አካውንቴ የዶላር ነው።
 • ከባለቤትህ አካውንት ቢሆን ፈልግባክህ፡፡
 • እሷም የብር አካውንት የላትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የእሷም የዶላር ነው?
 • የእሷ እንኳን በናቅፋ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ 
 • በናቅፋ ነው? 
 • በናቅፋ ነው አካውንቷ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይሁና፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር? 
 • ናቅፋ ይሁን ማለቴ ነው፣ ሌላ ምን ይባላል!

[ሚኒስትሩ ጠዋት ወደ ቢሮ እንደገቡ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸውን ከፍተው ወሬዎችን እየተመለከቱ ሳለ የአለቃቸውን ንግግር የያዘ ቪዲዮ በስፋት ሲዘዋወር ተመልክተው፣ ቪዲዮውን ከፍተው መከታተል ጀመሩ። ቪዲዮውን በደስታና በስሜት ተውጠው እንዳገባደዱ የቢሮው በር ተንኳኳ፣ አማካሪያቸው ነበር] 

 • ሰላም አለቃ መግባት ይቻላል? 
 • አንተ ነህ… እንኳን መጣህ፣ አየኸው?
 • ምኑን ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አለቃ ያደረጉትን ንግግር አላየኸውም? ማየት አለብህ፣ ልካቸውን ነው የነገራቸው።
 • ስለምንድን ነው?
 • ብታየው ይሻላል… ምዕራባውያኑን ቀጠቀጡዋቸው ነው የምልህ። 
 • የት መድረክ ላይ ነው? ውጭ ነበሩ እንዴ?
 • ኧረ እዚሁ የአንድ ክልል ፕሮጀክት ሊመርቁ ተገኝተው ነው።
 • የውጭ ዜጎች ነበሩ? 
 • የሉም።
 • በውጭ ቋንቋ ነው ንግግር ያደረጉት?
 • አይደለም፣ በአማርኛ ነው፡፡
 • ታዲያ እንዴት ነው?
 • እንዴት ነው ምን?
 • የቀጠቀጡት?
 • አይሰሙም ብለህ ነው? እመነኝ ይሰማሉ፣ የሚያመልጣቸው ነገር የለም። 
 • በእርግጥ የኤምባሲዎቻቸው ሥራ አንዱ ይህ ነው፣ ግን ምን ብለው ነው የተናገሯቸው?
 • ታሪክ የሌላቸው ጎረምሶች›… ኧረ ምን ያላሉት አለ…
 • ጎረምሶች? 
 • አዎ፣ ምን ያላሉት ነገር አለ… ቆይ ንግግሩን እየሰማሁ በማስታወሻ የያዝኩትን ልንገርህ፡፡ 
 • ማስታወሻ ይዘዋል ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎ፣ ምን አሉ መሰለህ…
 • እሺ?
 • ታሪክ የሌላቸው አገሮች በገንዘባቸው አቅም ሊያዙን አይችሉም። እኛ ኢትዮጵያውያን ያልተገዛን፣ ያልተንበረከክንና የማንበረከክ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። 
 • ኦ… ኦ…  እሺ ሌላስ? 
 • ሌላ… እኛ ኢትዮጵያውያን ነፃ የነበርንና ነፃ ሆነን የምንቀጥል ኩሩ ሕዝቦች መሆናችንን ለእነዚህ ጎረምሶች ማስተማርና ማሳየት አለብንም ብለዋል።
 • እውነት ቢሆንም አደገኛ ንግግር ነው ክቡር ሚኒስትር፣ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል።
 • የምን ጉዳት?
 • ክቡር ሚኒስትር ዲፕሎማሲ የንግግር ጥንቃቄ ይፈልጋል።
 • የምን ጥንቃቄ ነው? እነሱ የሚረጩት ፀበል ነው እንዴ?
 • ለጊዜው ለተጋጨን መንግሥት መልስ ለመስጠት ተብሎ አንድን አገር ታሪክ የለውም ማለት ሕዝብን የሚነካ ንግግር ይመስለኛል። በውጤት ደረጃ ቢለካም ችግሩን ከማወሳሰብና ሌሎች አገሮችም እንዲተባበሩብን ከመጋበዝ ውጪ ፋይዳው አልታየኝም። ከዚህ ቀደምም የውጭ አምባሳደሮች ባሉበት እንዲሁ ተናግረው አስከፍተዋቸው ነበር። 
 • እናንተ አማካሪዎች በውጭ አገር የተማሩ ተብላችሁ በአማካሪነት ብትመደቡም መንበርከክ ያጠቃችኋል። 
 • መንበርከክ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እና ምንድነው?
 • የዲፕሎማሲ መርህን የሳተ ስለሆነ ነው። የተናገሩት እውነት ቢሆንም በዲፕሎማሲ ግንኙነት ግን የንግግር ጥበብ ወሳኝ ነው። በእነሱ ቦታ ሆኖ ለምን እንደሠጉ ማየትን፣ ከዚያም በጨዋና በበሰለ መንገድ የእኛን ፖለቲካዊ ምክንያትና አቋም ማስረዳት እንጂ ቁም ነገሩን ትቶ አላስፈላጊ መካረር ውስጥ የሚከት ንግግር ማድረግ በተለይ የፖለቲካ አቅሙ ውስን ለሆነ አገር ጥሩ አይመስለኝም። 
 • እኔ በዚህ መንገድ አላየሁትም ነበር፣ ለነገሩ እሳቸውም በአማርኛ የተናገሩት ለዚህ ይሆናል። 
 • አይ እነሱማ መስማታቸው አይቀርም። 
 • ቢሰሙትም እንዳሰቡት እንዳልሆነ እናስረዳቸዋለን።
 • ምን ብለን እናስረዳለን?
 • የአገር ውስጥ አንድነት ለመፍጠር ነው እንላለን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...

በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ አጠቃላይ ገበያው እንዳይታመም ትኩረት ይደረግ!

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]

ለምንድነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው? ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም። መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስልዎህ ከሆነ ተሳስተሃል። አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር? ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላነጋግርህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡ እርስዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም፣ ምን ገጠመዎት? እኔማ ምን ይገጥመኛል አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ? ምን? እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል፡፡ ይንገሩኝ...

[ክቡር ሚኒስትሩ በቢሯቸው ሆነው ከአማካሪያቸው ጋር ስለወቅታዊ ጉዳዮች እየተነጋገሩ ነው]

ትናንት የሆነውን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር? አልሰማሁም፣ ምን ሆነ?  ኬንያውያን የአገሪቱን ፓርላማ ጥሰው መግባታቸውን አልሰሙም? ኧረ አልሰማሁም።  የፓርላማውን በር ጥሰው ገብተው አንደኛውን ክፍል በእሳት አያያዙት፡፡  ምንድነው ምክንያቱ?  የአገሪቱ መንግሥት ያቀረበው አዲስ...