በሽቴፋን አወር
ካለፈው ክረምት አንስቶ የጀርመን አምባሳደር ሆኜ ቆይታዬን ስጀምር፣ አገሪቱ እጅግ ከባድ የሰብዓዊ ችግሮች እያየች የነበረችበት ሁኔታ ነበር። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የበረሃ አንበጣና ጎርፍ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎችና ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን ጨምረው ነበር። በትግራይ የተከሰተው ግጭትም በነበሩት ተግዳሮቶች ላይ ተጨማሪ ጫና ሆኗል። በትግራይ በትንሹ 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ይታመናል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት የላቸውም። እየተቃረበ ያለ የረሃብ አደጋን የሚያሳዩ ምልክቶች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። በትግራይ ያሉ አርሶ አደሮች ከክረምቱ መግቢያ በፊት ማሳቸውን ማረስ ካልጀመሩ፣ ክልሉ እ.ኤ.አ. 1980ዎቹን የሚያስታውስ የረሃብ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።
ይህ ቀውስ ከጀመረ አንስቶ፣ ጀርመን ከአውሮፓ ኅብረትና ከሌሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለጋሾችና አጋሮች ጋር በመሆን ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትና የሲቪሎች ጥበቃ እንዲኖር ስትጠይቅ ቆይታለች። ይህን መጠየቃችንም የሚቀጥል ይሆናል። ያም ሆኖ በተመሳሳይ ጊዜ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራችንን በፍጥነት፣ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረናል። እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2020 ጀርመን ለቀውሱ ምላሽ የሚሆን ስድስት ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ፈንድ መድባለች። በተጨማሪም ለዚሁ ዓላማ የሚውል ተጨማሪ አሥር ሚሊዮን ዶላር መድበናል። ባለፈው ዓመት ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ፈንድ ከቀረቡ ልገሳዎች ውስጥ ትልቁ ድርሻ የእኛ ነበር። በአጠቃላይ ጀርመን እ.ኤ.አ. በ2020 ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ለተከናወኑ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ያወጣች ሲሆን፣ ይህንንም ድጋፋችንን በዚህ ዓመት ይበልጥ ማሳደግ ዕቅዳችን ነው።
ግባችን ግልጽ ነው፡፡ በትግራይ እንዲሁም ከዚያ ባሻገር ያሉ ሥቃዮችን ማብረድ፣ እንዲሁም ማንም ሰው ወደኋላ ሳይቀር ሕይወትን ማዳን ነው። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ አሁንም ተለዋዋጭና ከባድ ነው። ነገር ግን የሰብዓዊ ዕርዳታ አጋሮችን ጨምሮ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም፣ እንዲሁም በተለያዩ አገሮች እጅግ አስቸጋሪ በሚባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚችሉ አስመስክረዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት በመተባበርና አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ በማቅረብ፣ ለጥበቃቸው የምንችለውን ሁሉ በማድረግና ዕርዳታ የሚሹትን ሁሉ መድረስ እንዲችሉ በማገዝ፣ እነዚህን ድርጅቶች በተሻለ ልንደግፋቸው እንችላለን።
በዚህ አጋጣሚ መንግሥት ላደረጋቸው ከፍተኛ ሥራዎችና ለደረሰበት ሒደት፣ ለምሳሌ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ መክፈት፣ ተፈጽመዋል ስለተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም የጦር ወንጀሎች ገለልተኛ ምርመራን መፍቀድ፣ እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች ለቀው እንዲወጡ ስለተደረገው ስምምነት ዕውቅና መስጠት እፈልጋለሁ። ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሬት ላይ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እየተሻሻለ እንዳልሆነ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እየባሰም ነው። ስለዚህ እንቅስቃሴዎቻችንን በጥምረት ማሳደግ፣ እንዲሁም በሚሊተሪና በሲቪል መካከል ያለውን ቅንጅት ማሻሻል ይኖርብናል። መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና ሠራተኞቻቸው ላይ የተቃጡ ጥቃቶች መመርመር አለባቸው።
እ.ኤ.አ. በ2021 የምናደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ ከትግራይ ውጪ ያሉ ሰዎችንም ተደራሽ የሚሆን ይሆናል። ይህንንም የምናደርገው አጋሮቻችን ከፍተኛውን ዕርዳታ የሚሹ ሰዎች ባሉበት ሥፍራዎች በጀት መድበው ሥራዎችን ይሠሩ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት ነው። ወደ 20 ከሚጠጉ የተለያዩ የመንግሥታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት እንሠራለን፡፡ የምናተኩርባቸው ሴክተሮች ምግብ፣ ጤና ጥበቃ፣ መጠለያ እንዲሁም ውኃና ንፅህናን ያካትታሉ።
ለምሳሌ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሚያከናውናቸው የምግብ ድጋፍ ሥራዎች የምናግዝ ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅትን ደግሞ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት እናግዛለን፡፡ በተጨማሪም የሴቭ ዘ ችልድረን ሕፃናትን የመጠበቅ ሥራዎች፣ እንዲሁም የጀርመኑን ቬልት ሃንገር ሂልፈ (Welthungerhilfe) የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍና የንፁህ ውኃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለሰብዓዊ ዕርዳታዎች እ.ኤ.አ. በ2021 የበጀት ዓመት በመመደብ ጀርመን ከዓለም ሁለተኛዋ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ለጋሽ ነች። የገንዘቡ መጠን ባለፉት አምስት ዓመታት ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል። በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ በግጭት፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ አልያም በወረርሽኞች የሚጠቁ ሰዎችን እየረዳን ያለን ሲሆን፣ ይህን ጥረታችንንም የውጭ ፖሊሲያችንና የዓለም አቀፍ ኃላፊነታችን ወሳኝ አካል አድርገን እናየዋለን።
በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢሆን የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚቀርበው የሰብዓዊነት፣ ኢ–ጣልቃ ገብነት፣ ገለልተኛነትና የነፃነት መርሆችን መሠረት ባደረገ መንገድ ነው። በዚህ ረገድ አንድ ቁልፍ መርህ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው የትም ይሁኑ የት፣ ዕርዳታ መድረስ ያለበት እጅግ በጣም ለሚያስፈልጋቸው ነው የሚለው ነው። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው በአገር ውስጥ ከተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ጋር ተያይዞ ትልቅ ተግዳሮት ነው። ነገር ግን እነዚህ መሪ መርሆች በአገሪቱ ውስጥ፣ በተለይም በትግራይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለማስተናገድ ቁልፍ ናቸው ብዬ በፅኑ አምናለሁ። ለድርጊት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለዚህም ጀርመን ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በቅርብ ትብብር ድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ ናት።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡