Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበ‹‹ዲሽታ ጊና›› ወደ አሪዎች ትውፊት

በ‹‹ዲሽታ ጊና›› ወደ አሪዎች ትውፊት

ቀን:

መሰንበቻውን በተለያዩ ሚዲያዎች በስፋት ተደራሽ የሆነው ‹‹ዲሽታ ጊና›› የተሰኘው የድምፃዊ ታሪኩ ጋንኪሲ ሥራ ነው፡፡ ድምፃዊው‹‹መዝሙር›› ብለው ይሻለኛል ያለው  ዘፈኑ ከአሪ ብሔረሰብ ባህል በፈለቀ የዳንኪራ ጥበብ የታጀበ ነው፡፡

ለሙዚቃው ከተዘጋጀለት ክሊፕ ሌላ በሌሎች አገሮች የተሠሩ የዳንኪራዊ ዘፈኖች ክሊፖችን በመጥለፍ በዲሽታ ጊና ‹‹ሲያስጨፍሩ›› በማኅበራዊ ሚዲያ ታይተዋል፡፡ ዘፈኑ የብዙዎችንም ቀልብ መግዛቱን ከሚሰነዘሩት አስተያየቶች መረዳት ይቻላል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙት ብሔረሰቦች አንዱ የሆነው አሪ፣ የራሱ የሆነ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር አለው፡፡ አቆጣጠሩ የጨረቃን የዑደት መንገድ ነው፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ ወር፣ መጀመሪያ ቀን በክብረ በዓል የሚደምቀው ዕለቱ መጠርያው ‹‹ዲሽታ ጊና›› እንደሚባል በዞኑ ባህላዊ ቅርሶች ላይ ዳሰሳ ያደረገው የቅርስ ባለሥልጣን ድርሳን ያስረዳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ድምፃዊው ታሪኩ የብሔረሰቡን ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ ‹‹ሰምና ወርቅ›› በሆነው ድርሰቱ በኢትዮጵያውያን መካከል ፍቅርና አንድነት፣ ሰላምም እንዲሰፍን ያስገነዝባል፡፡ ‹‹አዳም ወንድሜ ሔዋን እህቴ›› እያለ፡፡ ሲሻገርም ሥራ እንጂ ‹‹ዘር አያፀድቅም›› እያለ፡፡

የአሪ ብሔረሰብ ማን ነው?

በሀገሬ ሚዲያ ተዘጋጅቶ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል ባሳተመው መጽሐፍ እንደተገለጸው፣ የደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የአሪ ብሔረሰብ በዋናነት በሰሜን አሪና በደቡብ አሪ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖር ሲሆን፣ የተቀረው ግን ከጎፋ፣ ከኦይዳ፣ ከበናና ከማሌ ብሔረሰቦች ጋር ተሰባጥሮ ይኖራል፡፡ እንዲሁም የብሔረሰቡ አባላት በሚኖሩባቸው የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ውስጥ የባስኬት፣ የጎፋ፣ የወላይታ፣ የኮንሶ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጋሞና የትግራይ ማኅበረሰቦች ከብሔረሰቡ ጋር በስብጥር ይኖራሉ፡፡

የመልከዓ ምድር አቀማመጡን በተመለከተ ብሔረሰቡ የሚኖርበት ደጋማው ክፍል እንደ ሰንሰለት በተያያዙ የበርካን፣ የቶልታ፣ የሸንጋማ፣ የባኮና የሴኔጋል ተራሮችና ኮረብታዎች የተከበበ ሲሆን፣ ቆላማው ክፍል ደግሞ ለጥ ያለ ሜዳ ነው፡፡

የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥና አሰፋፈርን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ በዋናነት የሚጠቀሰው አስተያየት ‹‹ነባር ሕዝብ›› ነው የሚል ሲሆን ለዚሁም የብሔረሰቡን መጠሪያ ትርጓሜ በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡ ይኸውም ‹‹አዕሪ›› የሚለው ስም በሒደት ወደ አሪ ቢለወጥም ትርጉሙ ‹‹መወለድ ወይም መፈጠር›› ማለት ስለሆነ ብሔረሰቡ ‹‹እዚሁ የተፈጠረ ነው›› በማለት መረጃ ሰጪዎች ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

የአሪ ብሔረሰብ አፍ መፍቻ ቋንቋ ‹‹አሪኛ›› ሲሆን ቋንቋው በኦማዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ውስጥ ይመደባል፡፡ ቋንቋው ከበና፣ ከሐመር፣ ከካራና ከዲሜ ብሔረሰቦች ጋር ይቀራረባል፡፡ የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ አማርኛ፣ በንኛ፣ ሐመርኛ፣ ባስኬቶኛና ጎፍኛ ይናገራሉ፡፡ ብሔረሰቡ በዋነኛነት የሚተዳደረው በእርሻ ሥራ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን የቀንድና የጋማ ከብቶችን ያረባል፡፡ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ እንሰት፣ ቦይናና ጎደሬ በዋነኛነት ያመርታል፡፡

በ‹‹ዲሽታ ጊና›› ወደ አሪዎች ትውፊት

 

የአሪ የወራት አሰያየምና የዓመት አከፋፈል ሥርዓት

የቅርስ ባለሥልጣን የባህልና የሥነ ሰብዕ ባለሙያዎች እነ ኤፍሬም አማረና እታገኝ አስረስ ባካሄዱት የመስክ ጥናት የአሪን የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ተንትነውታል፡፡

እንደ አጥኚዎቹ አገላለጽ፣ አሪዎች ጊዜያትንና ወሮችን ከአካባቢ የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ለሥራም ሆነ ለማኅበራዊ ሕይወታቸው መግባባቢያና መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡

በአሪ ብሔረሰብ አንድ ቀን ‹‹ሰጻ›› ማለት ንጊ ላይ ዶሮ ሲጮህ ጀምሮ እስከሚቀጥለው ንጊ ድረስ ያለውን ሰዓት ይወክላል፡፡ አንድ ወር የሚይዛቸው ቀኖች በጨረቃ /አርፊ/ መውጣትና መግባት ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ጨረቃ ስትወጣ ‹‹ስትወለድ›› የወር መጀመርያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ከብሔረሰቡ ባህልና የተፈጥሮ ዕውቀት ጋር በማያያዝ አንድን ዓመት በአሥራ ሁለት ወራት ተከፋፍለው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ የዘመን መለወጫ የሚጀምረው በ‹‹ተማ›› ወር ነው፡፡ በዚህ ወር እህልና ሳር ስለሚደርስ እንዲሁም በአካባቢው ስለሚለመልም የአዲስ ዓመት መግቢያ ወር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በብሔረሰቡ ባህል መሠረት የእህል ጎድሚዎች የዘመን መለወጫ ሥርዓት እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡

የአሪ ብሔረሰብ የሚጠቀምባቸው ወራት ተማ፣ በግሳ፣ ሶምዛ፣ ሎንጋ፣ ቶራ፣ ማከን፣ አይዲ፣ ዶላ፣ ላ፣ ተብዛ፣ ዜታ እና ሰግላ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ወር የራሱ የሆነ አባባልና ትርጉም ያለው ነው፡፡

የቁጥር ሥርዓት

ሌላው አጥኚዎቹ የተመለከቱት የአኃዝ ሥርዓት ነው፡፡ እንደነሱ ማብራሪያ፣ የአሪዎች መቁጠርያ ከአንድ እስከ አሥር ያሉ ቁጥሮች ናቸው፡፡ የተወሰኑት ቁጥሮች ስያሜ ከአጎራባች የኦሞቲክ ብሔረቦች ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ እነሱም 1 ኦላካ፣ 2 ቀስተን፣ 3 መካን፣ 4 ኦይዲ፣5 ዶ፣ 6 ላ፣ 7 ተብዛ፣ 8 ቀስተን ተመር፣ 9 ኦልካን ተመርና 10 ተማ ናቸው፡፡ ከአሥራ አንድ እስከ አሥራ ዘጠኝ ድረስ ያሉት ቁጥሮች የሚራቡት ተማ የሚለውን ቃል ከፊት በማስቀደም ከአንድ እስከ ዘጠኝ ያሉትን ቁጥሮች በማስከተል ነው፡፡

በብሔረሰቡ አሰያየም ‹‹ቦንዳ›› ማለት ሃያ ማለት ሲሆን፣ ከሃያ በኋላ ያለው የቁጥር አረባብ የተለየ ሥርዓትን ይከተላል፡፡ አንድ ሰው ማለት አሥር የእጅና አሥር የእግር በድምሩ ሃያ ጣቶች የሚወክል በመሆኑ፣ ከሃያ በኋላ ያሉ ቁጥሮች በሰው ውክልና ላይ በማራባት ይቀጥላል፡፡ በመሆኑም ሠላሳ ለማለት አንድ ሰው ላይ ግማሽ የጨመረ ብለው በቃላት ይጠሩታል፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ የሰውን ውክልና በመጥራት ከአንድ እስከ ዘጠኝ ያሉ ቁጥሮች ጨምረው የፈለጉትን ቁጥሮች በቃላት ይጠራሉ፡፡

አንድ መቶ ለማለት ‹‹አሥር የበላ›› ብለው ይጠራሉ፡፡ ከሃያ በኋላ ያሉት ቁጥሮች ረዥምና ለመጥራት አስቸጋሪ የሚሆኑት በሰው ውክልና ላይ በተመሠረተ ቃላት የሚገለጽ በመሆኑ ነው፡፡

ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት

የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል ጥናት እንደሚገልጸው፣ የአሪ ብሔረሰብ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር በዋነኛነት የሚመራው በንጉሥ ‹‹ባቢ›› ሲሆን በንጉሥ ሥር ደግሞ ‹‹ዚስ፣ ጎድሚና ፆይኪ›› የተሰኙ ተዋረዳዊ የሆኑ የሥልጣን እርከን ያላቸው ክፍሎች አሉ፡፡ በብሔረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ ሕዝቡ እጅ መንሻ በመያዝ ንጉሡ ጋር ይሄዳል፡፡ ንጉሡም ሕዝቡ ወደ ተለያዩ ‹‹ጎድሚዎች›› በመሄድ ችግሩን እንዲቀርፍ ወይም እንዲፈታ ትዕዛዝ ያስተላልፋል፡፡

የኅብረተሰቡ ችግር ፈቺ ተደርገው የሚወሰዱት ጎድሚዎች የተለያዩ መንፈሳዊ ሥራዎችን የሚሠሩ በመሆናቸው ከዱር እንስሳት፣ ከጦርነት፣ ከዝናብ፣ ከወፍ በሽታና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መንፈሳዊ ሥራዎችን በመሥራት የተከፋፈሉ በመሆኑ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ባህላዊ ሥርዓት በመፈጸም ችግሩ እንዲቃለል ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ እያንዳንዱ ጎድሚም የራሱን ባህላዊ ሥርዓት ያከናውናል እንጂ በሌላ ጎድሚ ሥራ ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡

‹‹ዚስ›› ደግሞ የንጉሡ ትዕዛዝ ለሕዝቡ የማድረስና የሕዝቡንም ስሜት ለንጉሡ የመናገር ሥራ ከመሥራቱም በተጨማሪ ጎስድሜዎችንና የጦር አበጋዝ የሆኑትን ‹‹ዶማንጎ›› እና ‹‹ኮሰማንጎ›› የተባሉ አካላትን የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው ይነገራል፡፡ ‹‹ፆይኪ›› ደግሞ በዚስ ሲታዘዝ ለጦርነት፣ ለሥራ ወይም ለስብሰባ ጥሩንባ በመንፋት ሕዝቡን የመቀስቀስ ሥራ ይሠራል፡፡

እነ እሸቱ እውነቱ፣ ሜሮን ታምሩ ባዘጋጁት ጥናት መሠረት፣ በባህላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ረገድ በቤተሰብ ደረጃ ያሉ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ‹‹ቶይዲ›› በመባል የሚታወቁ ክፍሎች አሉ፡፡ ቶይዲ የቤተሰብ ጉዳይ ፈጻሚ እንደመሆኑ መጠን አዲስ ለሚወለዱ ሕፃናት ለወንድ ከአራት ወር፣ ለሴት ደግሞ ከሦስት ወር በኋላ በቤተሰብ የባህላዊ ሥርዓት መፈጸሚያ ቦታ ላይ እህል ያቀምሳል፡፡ እንዲሁም በቤተሰብ መካከል ችግር ሲፈጠር የማስታረቅ ሥራ ይሠራል፡፡ አዲስ ከብት ሲገዛ ደግሞ ‹‹ቦሌ›› የተሰኘውን አፈር በመቅመስና በመመረቅ ከሌሎች ከብቶች ጋር እንዲቀላቀል ከማድረጉም በተጨማሪ ላም ስትወልድ የተጠራቀመውን ‹‹እንገር›› ከቀመሰ በኋላ ቤተሰቡ እንዲጠጣ ያደርጋል፡፡ ቶይዲ ሳይመርቀው ከከብቶች ጋር የተቀላቀለ ከብት ካለም ባለንብረቱ ከብቱን ከቤት እንዲያስወጣ ዕገዳ ይጥላል፡፡

በ‹‹ዲሽታ ጊና›› ወደ አሪዎች ትውፊት

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...