ሰላም! ሰላም! እንዴት ከረማችሁ ወገኖቼ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በየደረስኩበት ከእንጀራዬ ጎን ለጎን የአገሬን ውሎና አዳር እከታተላለሁ፡፡ እናንተስ እንደ እኔ ናችሁ ወይስ ነገር ዓለሙን ትታችሁ ትባዝናላችሁ? በቀደም አንዱ፣ ‹‹ዓይኔ አላርፍ ብሎ እዚያም እዚህም ሳይ፣ አየሁት ቂጣዬን ከምጣዱ ላይ…›› እያለ ሲያንጎራጉር፣ ‹‹የሰው ልጅ ባህሪው የሚወሰነው አካባቢውን ለመቋቋም በሚያደርገው ተጋድሎ መሆኑን ያወቅኩት በልጅነቴ ነበር…›› አለ ብሎ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለሌኒን ወዳጅ ማክሲም ጎርኪ ወዲያውኑ ነገረኝ። እኔስ ማነኝ ብዬ ተራዬን የሚከተለውን አልኩ። ‹‹የሰውን ልጅ ባህሪ ለማወቅ የሚሳነው ሚሊዮን ለማካበት በሚያደርገው ተጋድሎ መሆኑን የተረዳሁት በዚህ ዘመን ነው…›› አይደለም እንዴ? ወዳጅንም ጠላትንም፣ ሰይጣንንም አምላክንም ገንዘብ ተክቶታል። መቼም ይኼን አለ ተብዬ በመጭው ትውልድ ለመዘከር ሌኒንን ማጫወት አይጠበቅብኝም። ሚሊዮን ማጫወት ከቻልኩ እንኳን መጪው ትውልድ ጨረቃና ከዋክብትም ይንጫጩልኛል። ምነው ጫጫታ በዛባችሁ? እውነት ነው የቀን አበል ከሌለው እንኳን ጫጫታ ዝምታም ያሰድዳል። ድሮ ነው አሉ ሰው ከሞተ በኋላ ምን ይሆናል ሲባል፣ ወይ ይፀድቃል ወይ ይኮነናል ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮስ አትሉኝም? አሁንማ ከሞት በኋላ ሳይሆን ከሞት በፊት ስላለው ሕይወት ነው ትኩረት የሚሰጠው፡፡ ‹ይሞታል ወይ ታዲያ…› ያለው ዘፋኙ ወዶ እኮ አይደለም!
የድሮ ሰው ሳይቸግረው በትንቢት አምናለሁ ማለቱ በሰው ልጅ አምናለሁ ለማለት እኮ ነው። የሚረባውን ይልቅ የዛሬን ጠይቁኝ። ዛሬስ? ዛሬማ አዳሜ እምነቱ ሚሊዮን አልፎ ቢሊዮን ሆኗል። ትሪሊዮን ዕዳ ታቅፎ የምን ሞት ነው? የዘንድሮ ሰው ድንገት ቀና ብሎ ወደ ሰማይ አንጋጦ ዓይኑ ኮከብ ሲያይ ምን ትዝ የሚለው ይመስላችኋል? ኧረ ምንድነው ነቃ በሉ እንጂ? ‹አካውንቱን!› ነው አትሉም እንዴ። ነው እናንተም ብር ቆጠራ ላይ ናችሁ? መቼም ኮከብ አትቆጥሩም በዚህ ገንዘብ ናላ ባዞረበት ዘመን። እናላችሁ ‹ሀብትን ደግፌ ድህነትን ነቅፌ› ዛሬ በፊታችሁ ስቆም አቋሜን በአጭሩ ላስጨብጣችሁ፡፡ አጭር ዓረፍተ ነገር አስከትዬ ልመሠርትም እወዳለሁ። እርሱም አጥብቀው ከያዙት ሰውም ገንዘብ ነው የሚል ነው። አለ አይደል ሠርቶ ማግኘት ፀጋ ቢሆንም አንዳንዴ የማየው የፍቅር መቀዝቀዝ፣ መራራቅና መናናቅ የዋሁን ልቤን አደብዝዞት ያድራል። ለአንድ ደላላ ልብ ግድ ባይኖራችሁም፣ ለአንድ ምስኪን ሰው መቼም ርኅራኄ አታጡም። ከተሳሳትኩ በ‹ጥልቀት ለመታደስ› ዝግጁ ነኝ። ወይ መታደስ!
የገንዘብን ነገር ካነሳን አይቀር የኑሮን ነገር መበርበር ግድ ነውና ሰሞኑን አንድ ቤት መግዛት የፈለገ ዳያስፖራ አጋጠሞኝ ነበር። ያው የዘንድሮ ሻጭና ገዥ ታሪክ ለእናንተ ምኑም አይነገርም። ብቻ ራሱ ሰርቆ በሰው ላይ ላትርፍ የሚለው በዝቶ ናላዬን ሲያዞረው ይውላል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከዳያስፖራው ጋር ስንጫወት ድንገት ውሎ አድሮ አትርፎ ለመሸጥ ካሰበ በማለት፣ ‹‹ተመልሰህ ትሄዳለህ?›› ብዬ ጠየቅኩት። ‹‹ፎር ጉድ ነኝ!›› አለኝ። ሰዋሰውን እርሱት። ይኼ እንግሊዝኛና መቶ ብር ዘንድሮ የሚገባበት አጥቷል። ‹‹ኧረ?›› ስለው ቅስሜ እየተሰበረ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ምን ተብሎ ይኬዳል? አገሬን መለወጥ አለብኝ። የመጣሁት ወገኔን ለመቀየር ነው…›› ብሎ ብዙ አወራኝ። እንግዲህ ካወራው የማስታውሰውን ነግሬያችኋለሁ። ቀሪውን ለመስማት ትዝ ያለኝን ታዋቂ ታሪክ መርሳት ነበረብኝ፡፡ ለማንኛውም ከተማውን ሳካልል ዕድሜያቸውን አሜሪካ ጨርሰው የመጡ አዛውንት ዳያስፖራዎች በዝተውብኛል፡፡ ባለፈው ሰሞን ሰሚት አካባቢ አንድ ካፌ ጎራ ብል ዋሽንግተን ዲሲ የገባሁ መስሎኝ፣ በውኔ ነው በሕልሜ ብዬ መወዛገቤን አልረሳውም፡፡ አይ አሜሪካ እግዜሩ ይይልሽ፡፡ ሰዎቹን እንደ ሸንኮራ መጥጣ ከጨረሰች በኋላ እኮ ነው የላከችልን፡፡ ይህ አልበቃ ብሏት ልታተራምሰን እንቅልፍ አጥታ ታድራለች፡፡ አዲሷ የእጅ አዙር ቅኝ ገዥ ልትሆን እኮ ነው፡፡ ‹‹ዳውን ዳውን ኒዮ ኮሎኒያሊስት ያንኪ!›› እንበል መሰል፡፡ አዲዮስ አሜሪካ!
አንዴ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዘመኑ የመረጃ እንጂ የዕውቀት ስላልሆነ ወሬ ስትጀምር ‘ታዋቂ’ ብለህ አትጀምር…›› ያለኝ እዚህ በቀይ እስክሪቢቶ አስምሩበት። ቀይ እስኪሪቢቶ ያላችሁን ብቻ ይመለከታልና ወሬ ሳላበዛ ታሪኩን በአጭሩ ላስታውሳችሁ። ሰውዬው ናቸው አሉ መጀመሪያ ዓለምን ለመቀየር አስበው ተነሱ። አልሆን ሲላቸው ወደ አገር ወረዱ። ከዚያ እናንተም እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ወደ ታች መውረድ ነው። የዴሞክራሲ ጥማት ገደለን እያሉ ሀተታ የማዳመጥ ብቃት ያነሳቸው ስላሉ ብዬ ነው ‘ስኪፕ’ ያደረግኩት። መጨረሻ ላይ ሰውዬው የአልጋ ቁራኛ ሲሆኑ ነገሩ መሆን የነበረበት የተገላቢጦሽ ነበር። መጀመሪያ ራስን መለወጥ። ከዚያ ሁሉ ይከተላል። አዛውንቱ ባሻዬ ይኼን ታሪክ ደጋግሜ ሳጫውታቸው፣ ‹‹የለም መጀመሪያ ጽድቁንና ሰማዩን መፈለግ ነው። ከዚያ ነው ሁሉ የሚከተለው…›› እያሉ ወሽመጤን ይቆርጡታል። ወሽመጤ ርዝመቱ አይገርምም ግን? እናም ትናንት ከሁለት መቶ ምናምን ዓመታት በኋላ የተፈጠረች አገር እንደ ሠፈር ጎረምሳ አላስቆም አላስተኛ ስትለን፣ እኛ ደግሞ ፊት እየሰጠን አንገታችንን በትዝብት መወዝወዛችን ያናድደኛል፡፡ አሜሪካ መጀመሪያ ትራምፕና ቢጤዎቹ ያተራመሱትን ቤቷን ሳታፀዳ አትምጪብን ማለት ምን ያቅታል? አሜሪካ ለወፈፈችው እኛ ምን ተዳችን ነውና ነው የምንተራመሰው? አሁንስ በዛ!
ህልምና ወሽመጥ ባይረዝም ኖሮ የአዳም ዘር መቀጠሉን እጠራጠራለሁ። ብቻ እንደማየውና እንደምሰማው ከሆነ በህልም ፍቅር ጭልጥ ብሎ በእንቅልፍ የቀረው በዝቷል። የጤና ያደርግልህ እንዳትሉት እንቅልፉ እንጂ ህልሙ የጤና የሆነ ቸግሯል። አንድ ደቀ መዝሙር ነው አሉ። መምህሩ ከሚሰጡት ጥበብና ትምህርት ይልቅ በስማቸው ይመካ ነበር። እና ተኝቶ በህልሙ፣ መምህሩ በመልዕክት ታጅበው በአክሊል በክብር ደምቀው አየር ላይ እየተንሳፈፉ ሲያስተምሩት ያያል። ጠዋት ተነስቶ ተጣድፎ ሄዶ ህልሙን ሲግራቸው፣ ‹‹እስኪ ድገመውና ና…›› አሉት። ቀኑን ተኛ፣ ማታውን አልነቃም። ህልሙ አልተደገመም። አዝኖ ወደ መምህሩ ሲጓዝ መምህሩ ሞተው ፍትኃት እየተደረገላቸው ደረሰ። በዚያች 24 ሰዓት በህልም ሲፈልጋቸው በገሃድ ካጣቸው መምህሩ የቀረበት ትምህርት አያስቆጭም? ብለን እንዳንቆጭ ደግሞ የእኛው እንቅልፍ ቁጭት አያሳልፍም። እናም ከገሃዱ ዓለም እውነታ ራሳቸውን ጋርደው በራሳቸው የህልም ዓለም ሊያኖሩን ከሚፈልጉ ጋር አንጓተት፡፡ በሕይወት ሳሉ ጉራቸው አልቻል፣ ትዕቢታቸው ከሚታገሱት በላይ፣ ድርጊታቸው የሚያንገፈግፍ የነበሩት አሁን አፈር ሆነው እያየን የምን ማላዘን ነው? እነሱን ከመቀመቅ አውጥተው ሊያስፎክሩብን የሚጃጃሉትን በአንድ ልብ መክረንና ዘክረን ዞር በሉ ማለት እኮ ቀላሉ ግዳጃችን ነበር፡፡ ኧረ በቃ!
ወደ ጉዳዬ ስመለስ ከታች መጀመር ያለበት ከላይ ይጀምራል ምን ማለት መሰላችሁ? ተምሮ ተመርቆ ቀበሌ ወርዶ መልካም አስተዳደር ማስፈን ያለበት ብርቱ ንቁ ወጣት፣ በ26 ዓመቴ ፕሮፌሰር ተብዬ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ካላሰለቸኋችሁ ባዩ፣ ‘እኔና ትውልዴ ይህችን አገር ካልተረከብን ቁልቁለቱ ይቀጥላል’ የሚላችሁ ዓይነቱን ማለቴ ነው። ይኼን ምን ትሉታላችሁ መሰላችሁ? ‘ልረከብ ማለትህ ብቻ በቂ ነው?’ ነዋ። ልንጠቅስ ቢልስ ኖሮ? ሆ!ሆ! ‘ለሰበበኛ መረቅ አታብዛበት’ ማለት እኮ ይኼን ነው። አቤት ግን ይኼኔ ይኼ ተረት በእንግሊዝኛ ቢሆን ኖሮ እኮ ቃሉ አይገደፍም ነበር። እንደ ወረደ መናገርና ማሰብ ስንፈራ፣ ይኼው ከዘመን ዘመን የሚወራረድብንን የአስተሳሰብ ህፀፅ ሳናውቀው ሳንደግፈው አረጀን። ማምሻም ዕድሜ ነው ግድ የለም። ግን ነገር ግን ለማይረባ ዕድሜ ማምሸትም ሆነ ማንጋት ፋይዳ የለውም፡፡ ፋይዳ ያለው ግን ደረትን ነፋ አድርጎ በነፃነት የሚያኖር ተግባር ማከናወን ነው፡፡ ሺሕ ዓመት አይኖር!
በቀደም እኔም ድለላዬን በጊዜ አጠናቅቄ በስንት ዘመኔ መክሰስ ልበላ ወደ ቤቴ አዘገምኩ። ጎበዝ መክሰስ መብላት ማቆማችንን ልብ ብላችሁታል? ምን ነበረበት ስሪ ዲ፣ ሰቭን ዲ ቴክኖሎጂ በማስገባት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብለን ስንኩራራ ዓለም ከሚስቅብን፣ በቀን ሦስቴ የሚያበላ ጎተራ ባይኖራቸውም በቀን አራቴ የመብላት መርሐ ግብር አላቸው ብሎ ማስተዛዘኛ ቢነገረን? የምር! አንዱን ሳነሳ አንዱን ስጥል የማልረግጠው የለም። ላጫውታችሁ የፈለግኩት ምን መሰላችሁ? መክሰስ ልበላ ከቤቴ ስደርስ መብራት ጠፋ። የዘመኑ ሰው ፍቅርና መብራት ተመልሶ እስኪበራ ከመጠበቅ መቼስ ለህዳሴው ግድብ በሰላም መጠናቀቅ መጸለይ፣ ፍቅር ላጡት ምሕረት መለመን ነጥብ ያሰጣል። ወዲያው እጥፍ ብዬ (ፍሬቻ ያላበራሁት መብራት ስለሌለ ነው እንዳለው አሽከርካሪ) ባሻዬ ዘንድ ሄድኩ። ስደርስ በረንዳቸው ላይ በጋቢ ተጀቡነው ሬዲዮናቸውን እየጎረጎሩ ደረስኩ። ሳያቸው አንዱንም አያዳምጡም። ወደ ቀኝ ወደ ግራ ጣቢያ ማሽከርከሪያውን ይጫወቱበታል። ‹‹ባሻዬ ለምን አንዱን አይተውትም? እናዳምጠው እንጂ…›› እያልኩ ዱካ አውጥቼ አጠገባቸው ስቀመጥ፣ ‹‹የሚደመጥ ሲኖር እኮ ነው…›› አሉኝ። ‹‹ተው እንጂ ባሻዬ የሚደመጥ አይጠፋም፣ ዋናው ጆሮ ነው…›› አልኳቸው። እንዳሻህ ብለው አንዱ ጣቢያ ላይ ለቀቁት። እንዲህ ነው እንጂ ውሳኔ!
ባለጣቢያው አዘጋጁ ነው። ‘ይኼን ፕሮግራም ስፖንሰር ያደረጉላችሁ…’ ብሎ ሰባት ደቂቃ ስፖንሰሮቹን በግጥም በዜማ አሞካሸ። ምን ያበደ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ይሆን እያልኩ መቁነጥነጥ ስጀምር ወዲያው እጥፍ ብሎ ‘አንድ ወንድ ለወሲብ ብቻ ሲፈልግሽ የሚያሳይሽ አሥር ምልክቶችን ማስታወቂያ በኋላ እንነግርሻለን’ ብሎ ጠፋ። ያው እሱ ያስተዋወቀን ስፖንሰሮች አንድ በአንድ በበጀታቸው ያሠሯቸውን ማስታወቂያዎች አስደመጡን። አሥራ ምናምን ደቂቃዎች ላይመጡ ሄዱ። ፕሮግራሙ ሲመለስ ባልደረባውን አስተዋውቆ አሥሩን ዘረዘረ። አሁን ይኼ ለሴት ይነገራል? በአፍንጫቸው አይደለም እንዴ አነፍንፈው የሚያውቁት? ዕድሜ ለተፈጥሮ ፀጋቸው። አልኩ ባይ ሁላ…›› ብለው ባሻዬ ሬዲዮኑን ዘጉት። ወዲያው ወደ እኔ ዞረው፣ ‹‹አጅሬ በገዛ ሬዲዮንህ የማድመጥ መብት አለህ። በሰው ጆሮ አስታኮ መስማት ግን ዕድሜ ለመብታችን ድሮ ቀረ…›› ሲሉኝ ከት ብዬ ሳቅኩ። በሰው አፍ ለፍላፊው፣ በሰው ወርቅ ደማቂው፣ በሰው ጆሮ አድማጩ በዝቶ ቢያቅራቸው ነዋ። አሥር እውነቶች ግን የሚያልቁት መቼ ነው? መራራ እውነት ሲታከልባቸው እንዳትሉኝ ብቻ፡፡ ሀቅ ነው!
በሉ እንሰነባበት። ሆድ ስለባሰኝ ወደ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወልኩ። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተገናኝተን አንድ አንድ ስንል አመሸን። ደመናው ነው መሰል ይወብቃል። ‹‹የዘንድሮ ወበቅ ከአምናው ባሰ…›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ይኼን ሲል አንዱ ከሩቅ ሰምቶት፣ ‹‹ወበቅ ምን አለን? ከሕግ በላይ ሆኖ የሚያወራው፣ አላስቆም አላስቀምጥ ያለን ወሬኛ አይብስም እንዴ?›› አለው። ‹‹ነገር መጣልህ…›› አልኩና የካፖርቴን ቁልፎች ቆልፌ ጠንቀቅ ብዬ ተቀመጥኩ። ተጠንቅቀንም መዳናችንን እርግጠኛ አይደለንም እንዳትሉ ብቻ። ‹‹እና ምን ይሻላል?›› አለው አንዱ ተናግሮ አናጋሪ ወዲያ የተቀመጠ። ‹‹ማጥራት ነዋ፣ ማፅዳት ነው መፍትሔው። ሳይታክቱ መጥረግ…›› አለው። ወይ መጥረግ፣ ዘንድሮም እርስ በርስ ለመጨራረስ በር የሚከፍቱ መፈክሮችን ስንሰማ ያቅራል፡፡ ታሪካዊ ጠላት በአራቱም ማዕዘናት ግብረ አበሮቹን አሠልፎ አገራችንን መተንፈሻ አሳጥቷል፣ አጅሬው ምን እንዳልተፈጠረ የለመደውን እርግማን ይዞ መጥረግ ነው ይላል፡፡ መፈክር ሰለቸን!
በደርግ ዘመን ነው አሉ አንድ አዛውንት ቀበሌ ስብሰባ ተጠርተው አዳራሹ በሰው ጢም ብሎ ደረሱ፡፡ ገብተው አንድ ጥግ ላይ ተጨናንቀው ተቀመጡ፡፡ ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እስከ አገር ቤት ቡችሎቻቸው የተባሉ ወገኖች ድረስ በየተራ ይወገዛሉ፡፡ አዛውንቱ ትክዝ ብለው ተቀምጠው ሳሉ መድረኩን ከሚመሩት አንደኛው ካድሬ ወደ እሳቸው እየጠቆመ፣ ‹‹አባት ምነው የከፋዎት ይመስላሉ?›› ብሎ በሚያስገመግም ድምፁ ይጠይቃቸዋል፡፡ ድሮ ወፍጮ ቤት ኩንታል ጤፍ ሲያሸክሙት የኖሩት ወጠምሻ ካድሬ የቀሉ ዓይኖቹን ሲያጉረጠርጥባቸው ነገር ፍለጋ መሆኑ ስለገባቸው፣ ‹‹ኧረ ጓድ ምንም አልከፋኝም፣ ይህ ሁሉ መፈክር ሲዘንብ አንድ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው…›› አሉት፡፡ እሱም ምን ሊሉ ነው ብሎ፣ ‹‹ትዝ ያለዎትን ይንገሩን እስቲ…›› ሲላቸው፣ ‹‹ይኼ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም እኮ እንዲህ በሀብቱ ተመክቶ የተነሳብን አሽከሮቹ አድርጎን የፈለገውን ሊያሸክመን በመፈለጉ ነው… ሰው መሆናችንን ተጠራጥሮ ነው…›› ሲሉት የድሮው ኩንታል ተሸካሚ የዘመኑ ድልብ ካድሬ ቅኔው ሳይገባው ከመጠን በላይ እያሽካካ ሲስቅ፣ ድሮ የሚያውቁት በሙሉ በድንቁርናው እየተገረሙ ከእሱ በላይ በሳቅ አዳራሹን አናጉት፡፡ አሁንም ነገር ሳይገባቸው እንደገባቸው የሚያስመስሉ ካሉ፣ ዘፋኙ እንዳለው መጀመሪያ ሰው ይሁኑ፡፡ ከምንም ነገር በፊት ሰው መሆን ይቅደም፡፡ እስቲ ሰው ሰው እንሽተት፣ ሰው ነን እንበል፡፡ እኔ በበኩሌ ከምንም ነገር በፊት የማስቀድመው ሰው መሆኔን ነው! መልካም ሰንበት!