ኢትዮጵያ ከውጭ ከመጡ ጠላቶችና በአገር ውስጥ በተደረጉ ጦርነቶች መሬት ውስጥ ተቀብረው የቆዩ ፈንጂዎችን፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ለማፅዳት ዓለም አቀፍ ትብብር እየጠየቀች መሆኑ ተገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ በካናዳ እ.ኤ.አ. በ2004 የፈረመችውን የፀረ ሰው ፈንጂ ማውደም ስምምነትን በተያዘለት እ.ኤ.አ. በ2020 አስወግዳ ባለማጠናቀቋ፣ ሁለተኛ የማራዘሚያ ጊዜ በኖርዌ ኦስሎ እ.ኤ.አ. 2020 እንደገና ለአምስት ዓመት ጠይቃ እስከ 2025 እንደተራዘመላት፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የፈንጂ ማምከን ቢሮ ኃላፊ ኮለኔል አበራ አዘናው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በአምስት ዓመታት ውስጥ አፅድታ እንድትጨርስ በስምምነቱ መሠረት ፈቃድ የተሰጣት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ያሏት የፈንጂ ማምከኛ መሣሪያዎች ኋላ ቀር በመሆናቸውና በፋይናንስ ችግር ሳቢያ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ትብብር መጠየቋ ተገልጿል፡፡
የድጋፍ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የፈንጂ ማምከን ቢሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርንና ሌሎች አካላትን ጨምሮ ከኤምባሲዎችና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍና ትብብር ለማግኘት ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ዝግ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የፈንጂ ማምከን ቢሮ ኃላፊው አገሪቱ ምንም እንኳ በትግራይ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በጋምቤላ ክልሎች መሬት ውስጥ የተቀበሩ ወይም ተከማችተው የሚገኙ ፀረ ሰው ፈንጂዎች እንዳሉ ቢታመንም የፈንጂዎቹ ትክክለኛ መገኛ ቦታ አይታወቅም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፀረ ሰው ፈንጂዎችን ማምረት፣ መጠቀም፣ ማከማቸትና ማስተላለፍን ለመከላከልና ጨርሶ ለማውደም የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት በ1997 ዓ.ም. አፅድቃለች፡፡
የፀረ ሰው ፈንጂዎች በኢትዮጵያና በጣሊያን ጦርነት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኤርትራ ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች መሬት ውስጥ ተቀብረው የቀሩ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ በነበሩ ግጭቶች በተመሳሳይ የተቀበሩና ተፈልገው ያልወጡ ፈንጂዎች እንደሚኖሩ ኮሎኔል አበራ አስረድተዋል፡፡
‹‹የፈንጂ ማማከን ባለሙያዎች ቢኖሩንም ገንዘብና ዘመናዊ የፈንጂ መመርመርያና ማምከኛ መሣርያዎች አለመኖራቸው ከመሬት ውስጥ የማፅዳት ሥራውን አዘግይቶብናል፤›› ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በስድስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ስፋት ውስጥ በ35 አካባቢዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ፈንጂዎች እንዳሉ፣ በአንድ ቢሊዮን ካሬ ሜትር ውስጥ በ226 አካባቢዎች ደግሞ የፈንጂዎች መኖር ሥጋት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አህመዲን እንደሚናገሩት፣ ከ15 ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት ከአሥር ሺሕ በላይ የፈንጂ ተጠቂዎች እንዳሉ የተገለጸ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ መረጃ የለም፡፡
በዚህም መንግሥት የዓለም አቀፍ ተቋማትን የፈንጂ ተጎጂዎችን መረጃ ለማጠናቀር የሚያግዘውን ድጋፍ ለማግኘት፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ካሉ ፈንጂዎች በከፍተኛ ደረጃ ከተቀረበባቸው አገሮች ውስጥ የምትመደብ እንደሆነች፣ ቢያንስ የሁለት ሚሊዮን ዜጎች ሥጋት መሆኑን የተገኘ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡