‹‹የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት በምርጫ›› በሚል ስያሜ 176 የሲቪል ማኅበራት የመሠረቱት ድርጅት፣ በቀጣዩ ወር ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፣ ከ3,000 በላይ የሠለጠኑ የምርጫ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ዝግጅት እያደረግኩ ነው አለ፡፡
የሲቪል ማኅበራቱ ጥምረት በምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ግጭቶች አስመልክቶ፣ ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል፡፡
ላለፉት ሳምንታት ሲካሄድ የነበረውን የመራጮች ምዝገባ ለመታዘብ፣ 144 ታዛቢዎችን አሠልጥኖ አሠማርቶ እንደነበር ኅብረቱ ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ታዛቢዎችን ለመላክ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የታዛቢዎች የምስክር ወረቀትና መታወቂያ በምርጫ ቦርድ በኩል በወቅቱ ባለመድረሱ ከታሰበው ጊዜ በላይ እንደዘገየ የጥምረቱ ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡
የታዛቢዎች የምስክር ወረቀት ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም፣ እስካሁን 1,300 ያህል የመራጮች የምዝገባ ጣቢያዎችን መታዘብ እንደተቻለ የተናገሩት፣ በጥምረቱ የምርጫ ታዘቢዎች ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ ናቸው፡፡
ጥምረቱ በመራጮች ምዝገባ ወቅት የተገኙና ያጋጠሙ ክስተቶችን አስመልክቶ፣ በመጪው ሳምንት መግለጫ እንደሚሰጥ አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማኅበራቱ ጥምረት ቢያንስ በ5,000 የምርጫ ጣቢያዎች የሚታዘቡ ግለሰቦች ምልመላ አጠናቆ፣ ምርጫ ቦርድ የምስክር ወረቀት እስኪያዘጋጅ እየጠበቀ መሆኑን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ይካሄዳል በተባለው ምርጫ በመራጭነት የተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 36.2 ሚሊዮን መድረሱን ቦርዱ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡
ይህ ቁጥር ቀሪ ሁለት ተጨማሪ ቀናትን ስለማያካትት የተመዝጋቢዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጥምረት ጠቅላላ ምርጫን፣ ፍትሐዊነቱንና ተዓማኒነቱን ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ ለመታዘብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አቶ ቢኒያም አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን ምርጫን ለመታዘብ ፍላጎት ካላቸው የአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻዎቻቸውን ካስገቡ 111 ድርጅቶች ውስጥ፣ የተመረጡ 36 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች 134,109 ታዛቢዎችን ማቅረባቸውን ቀደም ሲል ያስታወቀው ቢሆንም ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ደግሞ ዘጠኝ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን በተጨማሪነት መምረጡን አስታውቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት 60 አባላት ያሉት የታዛቢ ቡድን እንደሚያሰማራም ተሰምቷል፡፡