Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝብ ድምፁን በነፃነት የሚሰጥበት ምኅዳር መኖሩ ይረጋገጥ!

ጠቅላላ ምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ መወሰኑን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጨምሮ ለተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል፣ አገር አቀፍ ምርጫው ከአዲስ አበባና ከድሬድዋ ከተማ መስተዳደሮች ምርጫዎች ጋር በተመሳሳይ ቀን ይደረግ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው መስማማታቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡ በምርጫው ላይ ምንም ዓይነት የተዓማኒነት ጥቁር አሻራ መጣል እንደማይፈልግም ገልጿል፡፡ በቅድመ ምርጫ ሒደት እየተሰሙ ያሉ አቤቱታዎችንና ቅሬታዎችን ቀርፎ ምርጫውን ያለ እንከን ማካሄድ ከቻለ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ እንደሚፈጸሙ የሚነገርላቸው ሕገወጥ ድርጊቶች ካልቆሙ፣ ጦሳቸው ለድኅረ ምርጫ ግጭት መቀስቀስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ማሰብ ይገባል፡፡ ዜጎች በመንግሥት የፖሊሲና የስትራቴጂ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ከሚጠቀሙባቸው ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ ድምፃቸው ነው፡፡ መብቱን ተጠቅሞ ድምፁን ለመስጠት የሚዘጋጅ ማንም ዜጋ በምርጫው ዋዜማ የፖለቲካ ፓርቲ ተወዳዳሪዎችን በጥፍራቸው ማስቆም ከቻለ፣ የመንግሥትን አስተዳደር ተረክበው በሚመሩበት ወቅት ደግሞ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር እንዲያሰፍኑ የማስገደድ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥልጡንና ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ዜጎች በነፃነት የሚሰጡት ድምፅ ወሳኝ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምንም እንኳ የዴሞክራሲያዊው ሥርዓት ግንባታ ሙከራ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት በፈተና የታጀቡ አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች ተካሂደው ስድስተኛ የተባለውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን አንድ ወር ይቀራል፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩና የመንግሥት ለውጥ መካሄድ ያለበት በምርጫ መሆን ስላለበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለሕግ የበላይነት መገዛት አለባቸው፡፡ ሕዝብ በነፃነት የማይሳተፍበት ምርጫ ፋይዳ የለውም፡፡ ... 1948 ይፋ በሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት፣ በማንኛውም አገር የሚካሄድ ምርጫ ግልጽና ሕዝብን አሳታፊ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መንገድ የሚከናወን ማንኛውም ምርጫሕዝብ ይሁንታ ያለው መንግሥት ከመመሥረቱም በላይ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የማዕዘን ድንጋይ ይሆናል፡፡ ሁሌም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሚፈለገው የሕዝብ ፈቃደኝነት ሲሆን፣ ይህ ፈቃደኝነት የሚገለጸው በድምፅ ብቻ ነው፡፡ የዜጎች ድምፅ ዋጋ እንዲኖረውና ምርጫው ነፃና ተዓማኒ እንዲሆን ግን፣ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድኅረ ምርጫ ያለው ሒደት ከሕገወጥነት የራቀ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አገር የሚመራው መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዘንድሮን ምርጫ ከሕገወጥ ድርጊቶች ሳያፀዱ ስለተዓማኒነቱ መነጋገር አይቻልም፡፡

ለዚህም ነው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ዜጎች ድምፃቸውን እንዲሰጡ ማንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ ምርጫ ዜጎች በእኩልነት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ወኪሎቻቸውን የሚመርጡበት ሥርዓት እስከሆነ ድረስ፣ ሕዝቡን ለመራጭነት የማንቀሳቀስ ኃላፊነት የአንድ ወገን ሊሆን አይገባውም፡፡ ምርጫው ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲፈለግ ሌሎች አሉ የሚባሉ ችግሮችን ከመፍታት ጎን ለጎን፣ መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የምርጫ ካርዱን እንዲወስድ የማድረግ ኃላፊነት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ነው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ማስታወቂያ ሕዝቡ ወጥቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ከሚያደርገው ጥሪና የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ እያደረጉ ከነበረው ጉትጎታ በስተቀር፣ በአብዛኛው ከብዙዎቹ ፓርቲዎች በኩል ይስተዋል የነበረው የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ምርጫው ሲደርስ የቅስቀሳ ዘመቻ የሚደረገው ለማን ነው? ድምፅ ሊሰጡ ይችላሉ የሚባሉ መራጮች የመራጭነት ካርድ ውሰዱ ብሎ የማያሳስብ ፓርቲ በኋላ የማንን ድምፅ ሊጠብቅ ነው? ይኼ ወደፊት በብርቱ መታሰብ አለበት፡፡ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጥንካሬ የሚለካውም በዚህ ጭምር ነው፡፡ እርግጥ ነው በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ ምክንያት ችግር የገጠማቸው ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማሰማታቸው ይታወቃል፡፡ የገዥው ፓርቲ አመራሮችም እስከ ታችኛው መዋቅራቸው በመውረድ ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው፡፡

እስከ ረቡዕ ግንቦት 4 ቀን 2013 .. ምሽት ድረስ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብለው ሲጠበቁ ከነበሩ መራጮች ውስጥ 36.2 ሚሊዮን መመዝገባቸውን፣ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ቦርዱ የመጨረሻ መረጃውን አጠናቅሮ ሲያጠናቅቅ ይህ ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ግጭቶችና ጥቃቶች ምክንያት የደኅንነት ሥጋት ቢፈጠርምና ምርጫ የማይካሄድባቸው ሥፍራዎች ቢኖሩም፣ በምርጫ ለመፎካከር የቆረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው ሥፍራዎች ዜጎች እንዲመዘገቡ ጫናዎችን ተቋቁመው የማሳመን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንድ ፓርቲ የቻለውን ያህል ዝግጅት አድርጎ ወደ ምርጫው ለመግባት ከቆረጠ፣ መራጩ ሕዝብ የመራጭነት መብቱን እንዲጠቀም ማንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መምረጥ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት አካል ስለሆነ ነው፡፡ ይህም በታላላቅ ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች ሳይቀር ተረጋግጧል፡፡ አብዛኞቹ የመብት ድርጅቶች በጋራ የሚቀበሉት የመንግሥት ሥልጣን ለመረከብ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የዜጎችን የመምረጥ መብት ማክበርና ማረጋገጥ እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ በማናቸውም ሁኔታ ዘርን፣ ፆታን፣ ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ማኅበራዊ መሠረትን ወይም አመለካከትንና ሌሎች ልዩነቶችን በማስመልከት አድልኦ ማድረግ የለባቸውም፡፡ ለዚህም ነው ድምፅ መስጠት ወይም የምርጫ ተሳትፎ ሁለንተናዊ መብት በመሆኑ፣ ይህ መብት ምክንያቶች እየተደረደሩ መደናቀፍ የለበትም የሚባለው፡፡ አለበለዚያ ታጥቦ ጭቃ መሆን አይቀርም፡፡

የዴሞክራሲ መጫወቻ ሜዳው በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትምና የፖለቲካ ምኅዳሩ አሁንም በሚፈለገው መጠን የተከፈተ ባይሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነትና ተቀራርቦ በጋራ ጉዳዮች ላይ መነጋገር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ችግሮችን ተቋቁሞ ይህ እንከን እንዲወገድ ጥረት ማድረግ የግድ ነው፡፡ የፖለቲካ አንዱ መገለጫ ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንደ መሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከግጭትና ከአላስፈላጊ ትንቅንቅ ወጥቶ የዴሞክራሲ ቡቃያ እንዲያብብ ማድረግ የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብን መብት ማክበርና ተሳታፊነቱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ መራጩ ሕዝብ በራሱ ጊዜ ወጥቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ፣ ተፎካካሪ የፓርቲዎች ቅስቀሳ በማድረግ ድምፁን ለማግኘት መረባረብ አለባቸው፡፡ ዓለም አቀፉን ልምድ ስናይ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ሥራቸውን የሚጀምሩት መራጩን ሕዝብ ጎትጉተው ከቤቱ በማስወጣት ካርዱን እንዲይዝ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሒደት መምረጥ የማይፈልገውን፣ ማንን መምረጥ እንደሚፈልግ ግራ የተጋባውንና ስለምርጫ ጥቅም ግንዛቤ የሌለውን በመቀስቀስ የራሳቸው ደጋፊ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡ በተለያዩ አገሮች የምርጫ ፉክክር የሚጦፈው በእንዲህ ዓይነቶቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ነው፡፡ የሕዝቡን የመምረጥ መብት መደገፍ ተገቢ ነው፡፡

ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኛ መሆኑን የሚለፍፍ ማንኛውም ፓርቲ፣ መራጮችን የማንቀሳቀስ ተግባር ውስጥ ሳይገባ የምኞት ውጤት የሚጠብቅ ከሆነ ግራ ያጋባል፡፡ ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ችግር አለብን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መገለጫ የሆነውን ምርጫ ፈጽሞ ሊዘነጉ አይገባም፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ሲፈለግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ዕገዛ ይፈልጋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ተሁኖም ለሰላማዊ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ስኬት የድርሻን መወጣት ካልተቻለ ለአገር አሳሳቢ ነው፡፡ ምርጫና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ አንድ አካል በሆኑበት በዚህ ዘመን፣ ለዴሞክራሲ ሲባል ምርጫ በሕዝብ በጎ ፈቃድ ሊከናወን ይገባል፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር እንደሚደረገው ሁሉ፣ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ታዳጊ አገሮች የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ ነው፡፡ ምርጫ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚከናወነው ወሳኙ ሕዝብ ድምፁን በነፃነት ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡ ይህንን ነፃነቱን ተጠቅሞ ለምርጫ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻለው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲያንቀሳቅሱት ነው፡፡ ሕዝቡ መብቱ ተከብሮ የምርጫ ተዋናይ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥረት ያድርጉ፡፡ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አይኖርም፡፡ አለ ከተባለም ውሸት ነው፡፡ ሕዝብ ድምፁን በነፃነት የሚሰጥበት ምኅዳር መኖሩ እንዲረጋገጥ መረባረብ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...