Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሚዲያዎች ግልጽ በሆነ ፖሊሲ ሳይገሩ በመቆየታቸው ለተለያዩ ተፅዕኖዎች መዳረጋቸው ተገለጸ

ሚዲያዎች ግልጽ በሆነ ፖሊሲ ሳይገሩ በመቆየታቸው ለተለያዩ ተፅዕኖዎች መዳረጋቸው ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚዲያዎች ባለፉት ዓመታት ግልጽ በሆነ ፖሊሲ ሳይገሩ በመቆየታቸውና ዘርፉን የሚመለከቱ ዕርምጃዎች በወቅቱ ባለመወሰዳቸው ምክንያት፣ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ሲላጉ መቆየታቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ‹‹መገናኛ ብዙኃን ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለአገር ግንባታ›› በሚል ርዕስ ከሰላም ሚኒስቴርና ከፍሬደሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግ ጋር በመተባበር፣ ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል አገራዊ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትርና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ሚዲያው ባለፉት ዓመታት ግልጽ በሆነ ፖሊሲ መመራትና መገራት ያልቻለበት ሁኔታ እንደነበረ አስታውሰው፣ ማደግና መዳበር በነበረበት ደረጃ ሳይደርስ መቆየቱንና በዚህም የግልና የመንግሥት ተብሎ ለግሉም ሆነ ለመንግሥት መሆን ያልቻለበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

የሚዲያ ዘርፉን ለማሳደግ ያስችላሉ የተባሉና ሊወሰዱ ይገቡ የነበሩ በርካታ ዕርምጃዎች በወቅቱ ባለመወሰዳቸው፣ ሚዲያው በተለያዩ ተፅዕኖዎች ሲላጋ እንደቆየ ያስረዱት ሚኒስትሯ፣ በዚህ ወቅት ያለው የሚዲያዎች ገጽታ የዚያ ሁሉ ድምር ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአራተኛ መንግሥትነት የተፈረጀ አካልን በአጭር ጊዜ በሁለት እግሩ ማቆም እጅግ ከባድ እንደሆነ ያስረዱት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ በርካታ የከራረሙ የማስፈጸም አቅም ችግሮች ስላሉ እነዚህ ችግሮች የሰው ኃይል አቅም ብቃት፣ የተቋማቱን የግብዓት አቅርቦትና ያልተቋረጠ የተወዳደሪነት አቅሞች ጨምሮ ሚዲያዎች ተልዕኳቸውን እንዳይወጡ ሲያደናቅፏቸው እንደቆዩ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ሚዲያዎች ‹‹አገልግሎቶቻቸውን ለማዳረስ አገርና ተከታታይ ሕዝብ ያስፈልጋቸዋል›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ከወቅቱ ጋር እንንፈስ ለማለት ሳይሆን የግድ የሚሉና የማይታለፉ ጉዳዮች ላይ ግን መቆም እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢ  መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በመድረኩ ላይ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ንግግር፣ ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት በአገር ደረጃ የመነጋገር ባህል አልዳበረም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁሌም ንግግርና መልዕክቶች ይተላለፉ የነበረው ከአንድ ዓይነት አቅጣጫ፣ ማለትም ከላይ ወደ ታች ሲወርድ ብቻ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ሚዲያ በአንድ አገር ውስጥ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው ያሉት መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ በአሉታዊ ተፅዕኖው ምክንያት እንደ ቦሲኒያና ሩዋንዳ ባሉ አገሮች የደረሰውን የዜጎች ዕልቂት መመልከት በቂ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹መገናኛ ብዙኃን በአንድ አገር ግጭት አፈታት ላይ የሚያደርጉትን በጎ አበርክቶት ከግምት ውስጥ እናስገባለን፤›› ያሉት የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢው፣ በየክልሉና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች በራሳቸው ቋንቋ በሚያስተላልፏቸው መልካም መልዕክቶችና ዕውቀቶች፣ ግጭቶችን በተሻለ መንገድ መፍታት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት ንጉሤ ተፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ውይይቱ ከመደረጉ በፊት ከሚዲያ ጋር በተገናኘ ተሳትፎ ያላቸውን የተወሰኑ ግለሰቦችን በመምረጥ የተወሰኑ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው እንደነበረ አስረድተው፣ ተሳታፊዎች ከሰጡዋቸው ምላሾች መካከል፣ ‹‹ሚዲያዎቻችን የአገራዊ አንድነታችን ምሰሶ የሆኑትን የኅብረተሰባችንን እሴቶች የሚሸረሽሩ ያልሆኑ ትርክቶች፣ የፈጠራ ወሬዎችና ደካማ አስተሳሰቦች በማጋለጥ ለኅብረተሰቡ ያልተዛባ መረጃ በመስጠት፣ አስተሳሰቡን በማቃናትና ከአደጋ እንዲጠበቅ የማድረግ ሙያዊ ኃላፊነትንና የአገር አደራን በብቃት እየተወጡ አይመስልም፤›› የሚል ምላሽ እንደተገኘ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ውጥረትና ፈተና አኳያ ሰላምንና አገራዊ አንድነትን በተመለከተ ሚዲያው ትኩረት በመስጠትና ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ የሚመጥን ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል የሚለው ምላሽ ሌላው በመላሾች የቀረበ ሐሳብ እንደሆነ ያስረዱት ንጉሤ (ዶ/ር)፣ ከሰላምና ከአገራዊ አንድነት የሚበልጥ ምንም ዓይነት አጀንዳ ባለመኖሩ፣ ሚዲያዎች በእነዚህ ተቀዳሚ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ተገቢውን አመራርና ክትትል፣ እንዲሁም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚል ምላሽ እንደተገኘም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...