Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በ3.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሁለት ወራት አስገነባሁ ያለውን የሞጁላር መረጃ ማዕከል ሥራ አስጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም በ3.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሁለት ወራት ውስጥ ማስገንባቱን የገለጸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኔትወርክ መሠረተ ልማት የሚያፋጥን ዘመናዊ የ‹‹ሞጁላር መረጃ ማዕከል››፣ ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ሥራ አስጀመረ፡፡

ማዕከሉ በከፍተኛ ደረጃ የኃይል ፍጆታን የሚቀንስ፣ በቀላሉ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችልና ፈጣን የሲስተም ተከላ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ማዕከሉን መርቀው በይፋ ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት፣ ‹‹እየጨመረ ላለው የግልና የመንግሥት ተቋማት የመረጃ ክምችትና ሥርጭት፣ ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ ማዕከል መገንባት አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር ይህንን ፍላጎት ማስተናገድ እንዳልቻለ አስታውሰው፣ ማዕከሉን መገንባት እንዳስፈለገም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹን መሠረት አድርጎ ማዕከሉን መገንባቱን፣ ማዕከሉ ኩባንያው ለሚሰጠው ለሁሉም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኔትወርክ መሠረተ ልማቶች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም የኃይል ፍጆታው ያነሰና ለጥገና የሚወጣውን ወጪ 35 በመቶ እንደሚቀንስም አክለዋል፡፡

በቅርቡ የተዋወቀው ‹ቴሌ ብር› የተሰኘው አገልግሎት በዚህ ማዕከል ለሥራ እንደሚበቃ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ መሰል ማዕከላት በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገነቡም አስረድተዋል፡፡ ማዕከሉ ለኩባንያው ትልቅ አቅም የሚፈጥርና በቀጣይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሚረዳ እንደሆነ ጠቁመው፣ በቀጣይ በነባሩ የመረጃ ማዕከል ላይ ያሉ ደንበኞችም በዚህ ሲስተም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል፡፡

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ወራት እንደፈጀና ለዚህም 3.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል፡፡

የሞጁላር መረጃ ማዕከል ክላውድ ሲስተምን ማጎልበት፣ ቨርቹዋል ማድረግ፣ የዳታ ማዕከልን የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃት ማሳደግ፣ እንዲሁም የመረጃ ማዕከላትን አሠራር ማዘመን፣ ፈጣንና ውጤታማነትን ማሻሻል፣ የኃይል ፍጆታን መቀነስ ከጠቀሜታዎቹ መካከል መሆናቸው ታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች