ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ
በትግራይ ክልል ከወራት በፊት በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦችን ጨምሮ በርካታ የስፖርት መሠረተ ልማት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በክልሉ ከስድስት ወራት በላይ በዘለቀው ቀውስ ምክንያት በክልሉ ሊከናወኑ የታቀዱ ስፖርታዊ ክንውኖች ተቋርጠው ቢቆዩም፣ ከሰሞኑ ግን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ክለቦቹ በጀታቸውን ሠርተው እንዲያቀርቡ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡
ትግራይ በተለይ በአትሌቲክሱ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ታላላቅ አትሌቶች ያፈራ ክልል መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእግር ኳሱም ቢሆን በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ሲወዳደሩ የምናውቃቸው የ2011 ውድድር ዓመት የሊጉን አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታን ጨምሮ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ስሁል ሽረ ሲጠቀሱ፣ በከፍተኛው (ሱፐር) ሊግና ብሔራዊ ሊግ እንዲሁም በዲቪዚዮን ደረጃ ሲወዳደሩ የሚታወቁ በርካታ ቡድኖች ቢኖሩም፣ በችግሩ ምክንያት ከ2013ቱ የውድድር ዓመት ተሳትፎ ውጪ ሆነው አሳልፈዋል፡፡
ችግሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በክልሉ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ ሲወዳደሩ የነበሩት ሦስቱ ክለቦች መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ስሁል ሽረ በቀውሱ ምክንያት ከውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር ውጪ ሆነው እንዲቆዩ፣ ውል ያላቸው ተጨዋቾቻቸውን በሚመለከት ለዚህ ዓመት ብቻ ወደ ፈለጉበት ክለብ ሄደው መጫወት እንደሚችሉ መወሰኑ ይታወቃል፡፡
ከሰሞኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር መጠናቀቁን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ቡድኖች ለሚቀጥለው ዓመት መርሐ ግብር የሚያስፈልጋቸውን ቅድመ ሁኔታ እንዲያሟሉና ምዝገባ እንዲያደርጉ በደብዳቤ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡ ጥያቄው የትግራይ ክለቦችን ጭምር እንሚያካትት ታውቋል፡፡
የትግራይ ስፖርትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ እንደሚሳተፉ የሚጠበቁት ሦስቱ ክለቦች በጀታቸውን ሠርተው እንዲያቀርቡ የተጠየቁት ይህንኑ መነሻ አድርገው ሳይሆን እንዳልቀረ የሚናገሩ አሉ፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በ2014 ዓ.ም. የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ቁጥር ወደ 16 በማሳደግ እንደሚያወዳድር ቀደም ብሎ አሳውቋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ደብዳቤ የትግራይ ክለቦች በቀጣዩ የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊግ የማይሳተፉ ከሆነ በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉት ሦስቱ ቡድኖች ከወዲሁ ለመለየት ይቻል ዘንድ ያለመ ስለመሆኑ ጭምር ይነገራል፡፡ እንደ ፌዴሬሽን ምንጮች ከሆነ የትግራይ ክለቦች በተቀመጠላቸው ጊዜ ሰሌዳ መሠረት መጥተው እንዲመዘገቡ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጉዳዩ እየተነጋገረ ይገኛል፡፡
ከወራት በፊት ስፖርት ኮሚሽን በጦርነቱ ምክንያት የወደመውን የትግራይ ስፖርት መሠረተ ልማት ወደ ነበረበት ለመመለስ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ በማቋቋም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎችን በማከናወን ለክልሉ ዕገዛ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዚሁ ተብሎ ለተቋቋመው ግብረ ኃይል 300 ሺሕ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ብሔራዊ ፈዴሬሽኑ ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ለሚያከናውኑት የወጣቶች ሥልጠና ለእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር 300 ሺሕ ብር ድጋፍ ሲያደርግ፣ በትግራይ ክልል የነበረው ሁኔታ ምንም እንኳ ያንን ለማድረግ ባይፈቅድም የገንዘብ ድጋፉ ግን ለክልሉ መስጠቱን ጭምር የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የትግራይን ስፖርት ወደ ነበረበት ለመመለስ ከስፖርት ኮሚሽን ጀምሮ በተዋረድ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩ አሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ የትግራይ ክለቦች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቁመና እንዲመለሱ በተለይ በስፖርት ኮሚሽን የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ እንደሚነገረው ከሆነ በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉት የክልሉ ክለቦች በ2014 ውድድር ዓመት የማይሳተፉ ከሆነ፣ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ የሚሆነው ከፕሪሚር ሊጉ የወረዱትን ሦስቱ ክለቦች በከፍተኛው ሊግ ከሦስቱም ምድብ ሁለተኛ ሆነው ካጠናቀቁት ሦስቱ ክለቦች ጋር በማወዳደር የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን ሦስቱን ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማሳደግ ውድድሩን ለማስቀጠል ዕቅድ እንዳለው ይታወቃል፡፡