Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የዘመናችን ወጣቶች በብዙ ነገሮች ዕድለኞች ናቸው እላለሁ፡፡ የመጀመሪያው ቴክኖሎጂ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተራቀቀበት ዘመን ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እኔና ብዙዎቹ የዕድሜ እኩዮቼ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ብርቃችን ነበር፡፡ የዚህ ዘመን ወጣቶች የሕይወታቸውን አቅጣጫ ለማስተካከል የሚረዱ በርካታ አማራጮች አሉዋቸው፡፡ የእኛ የወጣትነት ዘመን ያለፈው በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር፣ በሶማሊያ ጦርነት፣ በሰሜን የአገራችን ክፍል በተደረጉ ጦርነቶችና ዕልቂት ነው፡፡ ከብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ለመሸሽ አልጋ ሥርና ቁም ሳጥን ውስጥ ተደብቀን ያሳለፍናቸው ጊዜያት አይረሱም፡፡ እንደኛ በለስ ያልቀናቸው ደግሞ በየዓውደ ግንባሩ ቀርተዋል፡፡ እስር ቤት ተወርውረው የተደበደቡ፣ አካላቸው የጎደለና የተገደሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ከዚያ የመከራ ዘመን ጋር ሳስተያየው የዘመኑ ወጣትነት ከእኛ የሰቆቃ ወጣትነት ጋር አይነፃፀርም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በመላው አገሪቱ በተከፈቱ የመንግሥትም ሆነ የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ መማር የዚህ ዘመን ወርቃማ ዕድል ነው፡፡ ያኔ ዩኒቨርሲቲ መግባት የመንግሥተ ሰማያት ያህል የራቀ ነበር፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ዕጦት፣ ሥራ አጥነትና ተስፋ ቢስነት ከወረረው የዘመናችን ወጣትነት የአሁኑ ደማቅ ብርሃን የተላበሰና በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ አሁን ዓለም ጠባብ መንደር እስክትመስል ድረስ የዘመኑ ወጣት የዘመኑን ዕውቀት በቀላሉ መግብየት እየቻለ ነው፡፡ በአጠቃላይ እኔ በበኩሌ ምናለበት የዚህ ዘመን ሰው በሆንኩ ብዬ እቀናለሁ፡፡ የሰቆቃው ዘመን ወጣት በመሆኔ ያጣሁዋቸው በርካታ ዕድሎች አሁንም ይቆጩኛል፣ ያንገበግቡኛል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዘመኑ ወጣቶች ላይ በማያቸው አልባሌ ድርጊቶች እበሳጫለሁ፡፡ ብዙዎቹ ማለት ይቻላል ንባብ አይወዱም፡፡ ለአገር ፍቅርና ለታሪካችን ያላቸው ዕውቀት ያሳዝነኛል፡፡ ከፋሽንና ተያያዥ ጉዳዮች በተጨማሪ ለፌስቡክና ለዩቲዩብ የአሉባልታ ወሬ፣ ለጫት፣ ለሺሻ፣ ለትንባሆ፣ ለመጠጥና ለተለያዩ ሱሶች ያላቸው ቅርበት ያናድደኛል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ወጣቶቻችን በሙሉ በዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የእነዚህ ሱሶች ሰለባዎች መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ በየዕለቱ በዓይናችን የምናየው ነውና፡፡ የዘመኑን መልካም ዕድል ለመጠቀም ከሚማስኑ ጥቂት ብልህ ወጣቶች በስተቀር፣ ብዙዎቹ አቋራጭ መንገድ ፈላጊና በማይጨበጥ ምኞት የሚሰቃዩ ድኩማን ናቸው፡፡

ለምሳሌ የእህቴ ልጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አመሏ በመለዋወጡ ምክንያት ምክር ለመስጠት የቤተሰብ ጉባዔ ተቀመጥን፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላ የጫትና የመጠጥ ሱሰኛ መሆኗን ስትነግረን ድንጋጤያችን የጨው ዓምድ ነው ያደረገን፡፡ እኛ ዩኒቨርሲቲ ልከን በከፍተኛ ጉጉት ትልቅ ውጤት ስንጠብቅ ልጃችን ጫት እየቃመችና ጂን እየጠጣች ችግር ውስጥ ገብታ ነበር፡፡ እሷን ለመታደግ አሉ የተባሉ የሥነ ልቦናና የሕክምና ባለሙያዎችን በራፍ እያንኳኳን ነው፡፡ እኛስ ለጊዜው አቅም ስላለን ይህንን ርብርብ እያደረግን ነው፡፡ ሌላው እንዴት ያደርገዋል? እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ቦሌ መድኃኔዓለም ሸገር ሕንፃ ጀርባ መንደር ያለውን ጉድ የሚያውቅ ምን እያልኩ እንደሆነ ይገባዋል፡፡ ታዳጊ ወጣቶች ከመጠጥ፣ ከጫትና ከትምባሆ አልፈው የአደገኛ ዕፆች ተጠቃሚ ሆነው ከልካይ የጠፋ ይመስል፣ ዝምታ ሰፍኖ ትውልድ እየጠፋ ነው፡፡

ልብ ብላችሁ በአዲስ አበባ ታዋቂ የሚባሉ መሸታ ቤቶችን ተመልከቱ፡፡ በተለይ የዘመኑ ወጣት ሀብታሞች ውስኪና ቮድካ የሚጠጡባቸው ‹‹ምርጥ›› ቤቶች ብትሄዱ ዕብደት ይቃጣችኋል፡፡ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ልጆቻችን አልኮል እየተጋቱ በላይ በላዩ ትምባሆ ሲምጉበት ማየት ወላጅ ለሆኑ ሰዎች ያሰቅቃል፡፡ ከጫት መልስ መጠጥና ትንባሆ ተደባልቀው በመጨረሻ ውጤቱ ምን ይሆን ትላላችሁ፡፡ ትምህርት ቤት ወይም ጥናት ላይ መገኘት የሚገባቸው ታዳጊዎች ጠንካራ አልኮል እየተጋቱና ዕፅ እየወሰዱ ከዚያም ጥንቃቄ ወደ ጎደለው አደገኛ ወሲብ ሲነዱ ማሰብ በራሱ ያሳብዳል፡፡

የድሮ ወጣቶች ያን ያህል ቅንጦት ባልነበረበት ዘመን ሻይ ቤት ሄደው ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ቤሳ ሳንቲም ለማግኘት ስንት መከራ እንደነበረባቸው የምናውቀው እንረዳዋለን፡፡ ዛሬ ያለ ዕድሜያቸው በየመጠጥ ቤቱና በየሱስ ቤቱ ተሠልፈው የምናያቸው ወጣቶቻችን ገንዘቡን ከየት እንደሚያገኙት እናውቃለን፡፡ በተለይ የሀብታም ነጋዴ ልጆች አያያዝ መረን ከመለቀቁ የተነሳ ከተማችን የወጣት ሰካራሞች መናኸሪያ ሆናለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወጣት ሥራ አጦች በመብዛታቸው ምክንያት አዲስ አበባ አደገኛ ዘራፊዎች እንደ እንጉዳይ ፈልተውባታል፡፡

በቀደም ዕለት ምሽት ከውጭ አገር ከመጣ ዘመዴ ጋር ወደ አንደኛው ታዋቂ የከተማችን ውስኪ ቤት ጎራ አልን፡፡ በበኩሌ እንዲህ መሰል ሥፍራዎች ባልገኝ ደስ ይለኛል፡፡ ይህ ዘመዴ የቀጠራቸው ሰዎች ስለነበሩ በይሉኝታ አብሬው ሄድኩ፡፡ ገና ከደጅ ከመኪና ማቆሚያው ጀምሮ በተደረደሩት ዘመናዊ የቤት መኪናዎች እየተደመምኩ ወደ ውስጥ ስንገባ፣ በዘመኑ አጠራር ‹‹ጂ ኤይት›› የሚባሉ ወጣቶች ቤቱን ሞልተውታል፡፡ ከእነሱ ጋር የተሠለፉት ታዳጊ ቆነጃጅት ብዛት ያስደነግጣል፡፡ ካፌ ውስጥ ጁስ እየጠጡ መዝናናት የሚገባቸው እነዚህ ልጆች ደብል ብላክ ሌብል፣ ጎልድ ሌብል፣ ግሪን ሌብል፣ ቮድካና መሰል ጠንካራ አልኮሎችን እየተጋቱ ወጣ ገባ እያሉ ያጨሳሉ፡፡ የእኔ ልብ ለእነሱ ይመታ ጀመር፡፡

በጣም መገረሜንና መሳቀቄን ያየው ዘመዴ፣ ‹‹ይኼንን ዘመን ከራስህ ጋር አታነፃፅር፡፡ የእነዚህን ወጣት ሀብታሞች አባቶች ብትጠይቃቸው እነሱም አይገረሙም…›› አለኝ፡፡ ተናድጄ ስለነበር፣ ‹‹እንዴት?›› ብዬ አፈጠጥኩበት፡፡ ‹‹አየህ የእነሱን አባቶች ልጆቻችሁ ከእናንተ በላይ ይዝናናሉ እናንተ ግን ስትዝናኑ አትታዩም ብትላቸው፣ መልሳቸው ምን ይመስልሃል?›› በማለት መልሶ ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ምን ብለው ይመልሳሉ?›› ብዬ እንደገና ጥያቄ ሳቀርብለት፣ ‹‹እኛ የደሃ ልጆች ነበርን፣ እነሱ ግን የሀብታም ልጆች ናቸው ይሉሃል…›› ሲለኝ የሞራል ዝቅጠት ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ መምከን ምን ያህል እንደተንሰራፋ ገባኝ፡፡

በቀደም ዕለት ሁለት መጻሕፍት አዟሪዎች መጻሕፍት እንድገዛቸው ጠየቁኝ፡፡ እስቲ ከእነዚህ ወጣቶች ጋር እያወራሁ የሚረቡ መጻሕፍት ካሉም እገዛለሁ ብዬ ወግ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ለመሆኑ መጻሕፍት የሚገዙዋችሁ ደንበኞቻችሁ በየትኛው ዕድሜ ይገኛሉ…›› የሚል ጥያቄ ሳቀርብላቸው አንደኛው በፍጥነት፣ ‹‹ዕድሜያቸው ገፋ ያሉና ከጎልማሳነት የላቁ ናቸው በብዛት የሚገዙን እንጂ፣ ብዙዎቹ ወጣቶችማ ዞር ብለው አያዩንም፡፡ የሴቶች ነገርማ አይነሳ…›› አለኝ፡፡ ሁለተኛውም በበኩሉ፣ ‹‹በጣም ብዙ ወጣቶችና ሴቶች እንዲገዙኝ ጠጋ ስላቸው የእኔ ቢጤ የሚለምናቸው ይመስል ፊታቸውን ያዞራሉ…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹የዘመኑ ወጣት የፌስቡክ አሽሙርና አሉባልታ እንጂ ቁምነገር አዘል መጻሕፍት ማንበብ አይፈልግም…›› እያለ አንደኛው ሲነግረኝ በጣም አዘንኩ፡፡ ጎበዝ ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል፡፡

(ኤልያስ ደምሴ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...