Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በኮንዶሚኒየምና በመንግሥት በቀበሌ ቤቶች ላይ ያቀረበው ሪፖርት

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በኮንዶሚኒየምና በመንግሥት በቀበሌ ቤቶች ላይ ያቀረበው ሪፖርት

ቀን:

‹‹… እኛም እንናገር ሕዝብም አይደናገር …››

በዳዊት ዮሐንስ

ያሳለፍነው ጥር ወር 2013 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሕገወጥ የመሬት ወረራ የኮንዶሚኒየም ቤትና የመንግሥት የቀበሌ ቤት ላይ ‹‹በገለልተኛ›› ወገን ‹‹ሳይንሳዊ›› በሆነ መንገድ የተጠናውን ጥናት ያቀረቡበት፣ ሕዝቡም ከተለያየ አቅጣጫ የራሱን ግምትና ግንዛቤ ሲወረውር የሰነበተበት እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡… ግለቱ ግን እስካሁን አለመብረዱን ከአንዳንድ ከሚወጡ መረጃዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡

የከንቲባዋ የወቅቱ ደመ ሞቃት ንግግር በሕገወጥ የተያዙ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶችን በአስቸኳይ አስለቅቀው በቤት ዕጦት ለተራቡና ለተጎዱ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች አድላለሁ በማለታቸው፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከፊሉ በሞቅታ ሲያጨበጭብ ከፊሉ ደግሞ በተስፋ የሚታደሉ ከሕገወጦች የተነጠቁ ቤቶችን በጉጉት እየጠበቀ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሕገወጥ የተያዙ የቀበሌ ቤቶች ተለቀው ለተጠቃሚ እየተላለፉ ነው የሚሉ ዜናዎች በመስማት ላይ በመሆናቸው ከንቲባዋን፣ ‹‹በዚህ አስቸጋሪና ውስብስብ ጊዜ ድንገት የተገኙ ጀግኒት›› አሰኝቷቸዋል፡፡ ዕውን እየሰማንና እያየን ያለነው ጉዳይ ከተጨባጭ ማስረጃዎች አንፃር ሲታይ ትክክለኛነቱ ምን ያህል እውነት ነው የሚለውን ሐሳብ ለማጣራት ለማረጋገጥ የሞከረ አካል ግን እስካሁን አላገኘሁም፣ አልሰማሁም፡፡

ይህ ሀተታ ዕውን ከባለሙያ ዕይታ አንፃር በተለይ በተለይ በኮንዶሚኒየም ቤቶችና በመንግሥት የቀበሌ ቤቶች ላይ ተፈጸሙ የተባሉት ሕገወጥ ተግባራት ተፈጽመዋልን? ምክትል ከንቲባዋ ዕርምጃ ወስደን ለአዲስ አበባ ሕዝብ እናከፋፍላለን ያሉት የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት መሬት ሲወረድ ይገኛልን? ካልሆነ ከእነዚህ ሁሉ የቁጥር ‹‹ማማለያዎች›› ጀርባ ያለው ምክንያትና ውጤታቸው ምንድነው? የሚሉ ጥቄዎችን በማንሳትና በመተንተን የቀረበ የባለሙያ ማብራሪያ ሲሆን እውነታውን እንወቅ እንረዳ በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው፡፡ የጽሑፉ ዓላማ ዘወትር ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት በጥናትና በሪፖርት ሰበብ የሚደረድሩት የቁጥር ጋጋታ ሕዝብን እያምታታ እያደነጋገረና ተስፋ እያስቆጠረ በመሆኑ፣ ለዚህም በመስኩ ልምድና ዕውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎች እውነቱንና ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በድፍረት ለሕዝብ ያቅርቡ የሚል አለው፡፡ ይህ ጽሑፍ ከኮንዶሚኒየም ቤትና ከቀበሌ ቤት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በጥልቀት ሲመለከት፣ የመሬት ጥናት ውጤት በዚህ ጽሑፍ ያልተካተተ መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተጠኑና የተገኙ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት ግኝቶችና ዕርምጃዎች እነሆ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

በጊዜው በሕገወጥ መንገድ ተይዘው መረጃቸው ለሕዝብ ይፋ የተደረጉትና እወቁልን የተባሉት ሕገወጥ ቤቶች፣ በተቀናጀና በተጠና ሁኔታ ይህን ጽሑፍ እስካቀርብ ድረስ በአራት ዋና ዋና አካላት ማብራርያና ገለጻ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

1. የመጀመርያው በምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባዋም 21,695 የኮንዶሚኒየም ቤቶች በሕገወጥ የተያዙ፣ 15,891 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መረጃ ያልቀረበባቸው፣ 4,530 ለረዥም ጊዜ ዝግ የሆኑ፣ 850 ከመጀመርያውም ዝግ የሆኑና የተቀመጡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲሆኑ፣ 10,565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባትና በሌሎች ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገወጥ መንገድ የተያዙና 7,723 ቤቶች ውል በሌላቸው ሰዎች የተያዙ፣ 2,207 ቤቶች ወደ ግል የዞሩ 265 ቤቶች በሦስተኛ ወገን የተያዙ፣ 164 ቤቶች ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው ወይም የራሳቸው ቤት እያላቸው ከሕጉ ውጭ የቀበሌ ቤት የያዙ እንደሆነ፣ በምክትል ከንቲባዋ ተብራርቷል፡፡ (27 January 2021 ሪፖርተር ጋዜጣ)

ለዚህም እንደ ዋቢ በገለልተኝነት ያጠናውን የአዲስ አበባ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲን ጠቅሰዋል፣ አመሥግነዋልም፡፡ በጥናቱም እንደሚተማመኑበትና ትክክል እንደሆነ በአደባባይ መስክረዋል፡፡

2. ቀጥሎ በጥናቱ ላይ ማብራርያና ገለጻ የሰጠው ጥናቱን በ ‹‹ገለልተኝነት››  ያጠናው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገብረ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ጥናቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንደተጠና፣ ብዙ የተደከመበትና ብዙ የተለፋበት መሆኑን፣ እንዲሁም በጥናቱ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ወጣቶች ከፊሉ ታመው ከፊሉ አልጋ ቁራኛ እንደሆኑ፣ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ቀን ከሌሊት መጠናቱን ገልጸው፣ ለዚህም የከንቲባዋንና የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነትና አልበገር ባይነት አመሥግነው አልፈዋል፡፡ በጥናቱም ወቅት አንዳንድ ‹‹አካላት›› ችግሩ እንዳይጋለጥ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር፣ እነዚህንም ‹‹አካላት›› እስከ ሕግ ተቋም እንዳደረሱ አልሸሸጉም፡፡

3. በሦስተኛነት ስለጥናቱ አስተማማኝነት ማብራሪያ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ናቸው፡፡ አቶ ዣንጥራር ሚዲያዎችን ጠርተው ገለጻ አድርገው ከጋዜጠኞቹም ጥያቄ ቀርቦላቸው የጥናቱን አጀማመር መነሻ ታሪክ አካሄድና ውጤት አብራርተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውን የዚህ ጥናት መነሻቸውና ለውጤቱ መድረሻቸው ኢዜማ የተባለው ፓርቲ እንዳልሆነና ጥቆማውን በተመለከተ ከኢዜማ ብቻ ሳይሆን፣ ከማንኛውም አካል ጥቆማ ለመቀበል በራቸው ክፍት መሆኑን፣ የኢዜማንም ጥቆማ የሚጥሉት እንዳልሆና እንደተጠቀሙበት አብራርተዋል፡፡ 

4. በመጨረሻ በጥናቱ ላይ ማብራርያ የሰጡትና ለጥናቱ ተፈጻሚነት ቆርጠው እንደሚሠሩ፣ እንዲሁም ከውጤት በኋላ የተለቀቀውን ቤት ‹‹ለደሃው የአዲስ አበባ ሕዝብ›› የተለቀቀውን ኮንዶሚኒየም ቤት ላጣው፣ ለተስፈኛውና ለመከረኛው የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢ እንደሚያድሉ የተናገሩት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡

የአራቱም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሿሚዎችና ባለሥልጣናት ማብራሪያ (መግለጫ) የሚያሳየን፣ ጥናቱ በከተማው ምክትል ከንቲባ ታምኖበት እንደተጠና፣ ዩኒቨርሲቲው ያጠናው ውጤታማ ብቻ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊና የጥናት ሕግና ሥርዓትን የተከተለ እንደሆነ፣ የጥናቱ ውጤቶች (ከላይ የተገለጹት) ቁጥሮች ትክክልና መሬት ላይ ሲወረድ በእርግጠኝነት የሚገኙ እንደሆነ፣ በዚህም ጥናት የተገኙ ቤቶች ለደሃውና ለተስፈኛው የአዲስ አበባ ሕዝብ በተለይ (ለ1997 ዓ.ም. ቤት ተመዝጋቢ) እንደሚከፋፈል፣ ይህንን ሥርዓት አልበኝነትና በሕገወጡ ሥራ ላይ የተሳተፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ቅጣታቸውን እንደሚያገኙ ተስማምተዋል፣ አረጋግጠዋል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከላይ የተገለጸው በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የቀረበው ጥናት ሳይንሳዊ ነው አይደለም የሚለው ውዝግብ ውስጥ ባይገባም፣ የጥናቱን ውጤት መሬት ላይ ስንወርድ አናገኘውም ይላል፡፡ በተለይ በቀበሌ ቤቶች ላይ የተደረገው ጥናት ዩኒቨርሲቲው ያገኘው አዲስ ግኝት ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት በሁሉም የወረዳና የክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ተቋማት ተጠንቶ ለአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ የተላከ፣ ኤጀንሲውም ውጤቱን በወቅቱ ለነበሩት የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የበላይ ኃላፊዎች የላከና ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን ከማጥናቱ በፊት በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቢሮዎች ውስጥ የሚገኝ፣ በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማም ሆነ በምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጽሕፈት ቤቶች የሚገኙ የየክፍላተ ከተሞች የጥናት ውጤቶች አሉ፡፡ ዛሬ አዲስ ነገር አዲስ ጥናት ሆኖ በዩኒቨርሲቲው ተጠንቶ ከቀረበልን የጥናት ውጤት በፊት፣ በየዓመቱ የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽንና የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ያጨናነቁ የተጠረዙ የጥናት ውጤቶች አሉ፡፡ በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዩኒቨርሲቲውና የከተማ አስተዳደሩ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የአዲስ አበባን ሕዝብ እያጓጉት ወይም እያሳሳቱት ነው የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ ለዚህም የሚሆን በቂ ማብራርያና ገለጻ ከማስረጃዎችና ከቁጥሮች ጋር ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ለግልጽነት እንዲያግዘንም የኮንዶሚኒየም ቤቶችና የመንግሥት የቀበሌ ቤቶች በተናጠል ይታያሉ፡፡

 በእኔ አተያይ ዩኒቨርሲቲው የሠራው (የሚሠራው) አዲስ ጥናት ወይም አዲስ ፈጠራ ሳይሆን፣ በመሬት ላይ ያለን የማይንቀሳቀስ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ በመንግሥት ተቋም ካለ መረጃ ጋር በማመሳከር ውጤቱን ማወዳደርና ማሳወቅ፣ ያሉትንም ክፍተቶች ከእነ መፍትሔ ሐሳብ ጋር ጥናቱን አጥናልኝ ላለው አካል ማቅረብ ነው፡፡ አካሄዱና አፈጻጸሙ ይህ መሆን ሲኖርበት የዩኒቨርሲቲው አካሄድ ግን ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

 ጉዳዩን ግልጽና ቀለል ለማድረግ በአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ያለውን የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት መረጃ፣ በክፍለ ከተማ የሚገኘውን የቀበሌና የኮንዶሚኒየም ቤቶች መረጃ በተለይ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ አጠቃላይ ፋይል ተደራጅቶ የሚገኘው በክፍለ ከተማ ስለሆነ፣ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ የሚገኘውን የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት መረጃ በተለይ የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ የነዋሪው ፋይል የሚገኘው በወረዳ ደረጃ ስለሆነ፣ የኮምፒዩተር መረጃ (Soft Copy) እና የወረቀት መረጃ (Hard Copy) በመያዝ እነዚህ መረጃዎች መሬት ላይ አሉ ወይስ የሉም የሚል ጥናት ማድረግ ነው፡፡

በጊዜው ግን የተደረገው ጥናት የኮንዶሚኒየም ቤትን በተመለከተ ቀጥታ ከአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን የቁጥር መረጃ ተወስዶ፣ የአሥሩም ክፍላተ ከተሞ የቤቶች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽሐፈት ቤቶችን (የግለሰቦች ፋይልና መረጃ የሚገኝበትን ክፍለ ከተማንና የወረዳ ቤቶች ተቋማትን) ዘሎ፣ ቀጥታ ቤቶቹ የሚገኙበት መስክ ላይ (ወረዳ ቤቶች) በመውረድ መረጃ እንዲወሰድ መደረጉ ትልቅ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን፣ በመጨረሻም ምክትል ከንቲባዋን ላልተገባ ወይም ለተዛባ ሪፖርት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

 ጉዳዩን እንዲሁ ከጥሬ ሀቅ አንፃር ስናየው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ውስጥ ምንም የኮንዶሚኒየም ቤትና የቀበሌ ቤት ፋይል የለም (አናገኝም)፡፡ ቢሮ ውስጥ የሚገኘው ቁጥር ነው፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች መረጃ ብቻ፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ፋይልና ሙሉ መረጃ ያለው ክፍለ ከተማ ነው፡፡ የቀበሌ ቤት ፋይልና ሙሉ መረጃ ያለው ወረዳ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለምን የክፍለ ከተማና የወረዳ የቤቶች ተቋማት በሌሉበት ወይም ባልተሳተፉበት ሁኔታ መረጃውን ለማጥናት፣ ለማጠናቀርና ሰንዶም ሪፖርት ለማድረግ እንደፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን ሲጀምር ምናልባት የክፍለ ከተማና የወረዳ ባለሙያዎች ለሚደረገው ጥናት እንቅፋት ይሆናሉ፣ ወይም የሠሩትን ሕገወጥ ሥራ (ወንጀል) ለመሸፋፈን ይሞክራሉ ብሎ ቅድመ ጥናት ሠርቶ ይሆን…?    

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በተወሰኑ ክፍላተ ከተሞች የጥናቱን አካሄድና የመጨረሻ ውጤት ለማየት እንደሞከረው የየክፍላተ ከተሞችና የየወረዳዎች የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶችን የሚያስተዳድረው የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ ዩኒቨርሲቲው ጥናት እያጠና እንደሆነ እንኳን አያውቁም፡፡ ወይም በጥናቱ እንዲሳተፉ አልተደረጉም ወይም እንዲያማክሩ አልተጠየቁም፡፡ እርግጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃም ሆነ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ጥናቱን እንደ ገለልተኛ ወገን ለማጥናት ስለተፈለገ፣ በተለይ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቤቶች አስተዳደር ተቋም እንዳይሳተፉ ተፈልጎ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ለዓመታት የተደራጀ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት መረጃ በጥራት ተሠርቷል፣ አልተሠራም ሌላ ጉዳይ ሆኖ መናቅ (መተው) የለበትም፡፡ ምናልባት የመንግሥት ተቋማቱ በዩኒቨርሲቲው ተቀባይነት ወይም አመኔታ ባያገኙም፣ በቤቶቹ ላይ ከዚህ በፊት የሠሩት በቂ ጥናት አለና  ዩኒቨርሲቲው መነሻና ማወዳደሪያ ቢያደርገው መልካም ነበር፡፡ በአጠቃላይ በኮንዶሚኒየምና በቀበሌ ቤት ቆጠራ ላይ የነበሩ ክንውኖችና የዩኒቨርሲቲውን ጥናት ውስንነት ከዚህ በታች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ከዚህ በፊት በመንግሥት የተደረጉ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት ቆጠራዎች

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በጥናቱ ያካተተው የጊዜ ማዕቀፍ ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. የ13 ዓመት የቀበሌና የኮንዶሚኒየም ታሪክ እንዳጠና ይናገር እንጂ፣ ከዚህ በፊት በቢሮ ደረጃ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶችን ትክክለኛነት ወይም ውጤታማ አለመሆናቸውን በግልጽ አላስቀመጠም፡፡ ለዚህም እንደ ዋና ማሳያ የሚቆጠሩ የቀበሌ ቤትና የኮንዶሚኒየም ቤት ቆጠራ መደረጋቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለዚህ መነሻ የሚሆነው የመንግሥት ቤቶች መመርያ በወጣና በተሻሻለ ቁጥር አንድ የማይቀር የመመርያው ክፍል ቢኖር፣ ‹‹ቢሮው በክፍለ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ ጊዜ መንግሥታዊ ባልሆኑ፣ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች የተገነቡና የከተማው አስተዳደር የሚያስተዳድራቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚገባ ቤቶችን ቢያንስ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ቆጠራ ያካሂዳል፤›› የሚል ሲሆን፣ ይህንም አሁን በሥራ ላይ ያለው የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር መመርያ 5/2011 አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ ቁጥር አንድ ላይ በማስፈር አረጋግጦታል፡፡ ይህንም መሠረት በማድረግ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት ቆጠራ ከተካሄደባቸው ጊዜያት መካከል፡-

1. በ2008 ዓ.ም.  እስከ 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ባሉት አሥር ክፍላተ ከተሞች የኮንዶሚኒየም ቤትና የቀበሌ ቤት ቆጠራ ተደርጓል፡፡

 • በግኝቱም ምን ያህል ቤቶች በሕገወጥ እንደተያዙ፣ ምን ያህል ሕገወጥ የቀበሌ ቤት ግንባታ እንደተካሄደ፣ ምን ያህል የመንግሥት ቤት ከግል ቤት ጋር እንደተደባለቀ፣ ምን ያህል የቀበሌ ቤት ለሌላ ሦስተኛ ወገን እንደተከራየ፣ የተቀጠሉ ቤቶች፣ የተደባለቁ ቤቶች፣ ያለ ምንም ውል በቀበሌ ቤት ለረዥም ዓመት ነዋሪዎች እንዳሉ… በብዙ ርዕሶች ተጠንቶ በወቅቱ ለነበረው ለአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ጥናቱ ሲገባ የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሪፖርቱን አንዳስገባ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምስክር ነው፡፡
 • የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተም ምን ያክል የኮንዶሚኒየም ቤቶች ክፍት እንደሆኑ (ለተጠቃሚ ያልተላፉ)፣ ምን ያህሉ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንዳሉ፣ ምን ያህል ሳይት የፍሳሽ ችግር እንዳለባቸው፣ ምን ያህሉ ኮሚናል ተሠርቶላቸዋል ተብሎ እዳልተሠራላቸው፣ ምን ያሉ በሕገወጥ እንደተያዙ…  በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በብዙ ርዕሶች ተከፋፍሎ ተጠንቶ በወቅቱ ለነበረው ለአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ጥናቱ ሲገባ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲም ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሪፖርቱን እንዳስገባ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምስክር ነው፡፡

2ኛ. አገራዊ ለውጡ በመቀጣጠል ላይ ሳለ በ2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከንቲባ ልዩ ትዕዛዝ ከየክፍላተ ከተማው የተለየ ቡድን ተቋቁሞ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በር ለበር እየዞረ በመቁጠር ኦዲት ለማድረግ ተችሏል፡፡

 • ለዚህም እንደ ማሳያ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ‹‹እስከነ ነፍሳቸው›› ጠፍተው የአዲስ አበባ ሕዝብ ተቋሙን መዘባበቻ ያደረገበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም፡፡

3. ከለውጡ በኋላ 2010 ዓ.ም. ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከመጡ በኋላ በተመሳሳይ የኮንዶሚኒየም ቤትና የቀበሌ ቤት ቆጠራ (ኦዲት) ተደርጓል፡፡

 • በተለይ በሕገወጥ መንገድ ተይዘው የተለቀቁ ቤቶችን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በየክፍላተ ከተማው ዞረው ቤቶችን ለድሆች ሲያከፋፍሉ ማየታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነበር፣

4. ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ወደ አዲስ አበባ በምክትል ከንቲባነት ከመጡ በኋላ በተለይ ‹‹ሕገወጥ የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በማስለቀቅ ለሥራ አጥነት ለተዳረጉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለመስጠት›› በሚል ርዕስ፣ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ከነሐሴ 2012  እስከ  ኅዳር 2013 ዓ.ም. የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በየክፍላተ ከተማውና በየቀበሌው ቆጠራ በማድረግ ውጤቱ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

5. ይህ ቆጠራ በአዲስ አበባ ከተማ ከተደረጉት የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት ቆጠራዎች ውስጥ በጽሕፈት ቤት ደረጃ መዋቅር ተሠርቶለት የተካሄደ ነው፡፡ ውጤቱም የማይናቅ ሆኖ ‹‹የሽግግር ጽሕፈት ቤት›› ተብሎ ተቋቁሞ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲን ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ያሸጋገረ የቆጠራ መረጃ ነው፡፡ (ይፋ ያልሆነ የቆጠራ መረጃ ከዚህ ጥናት ጋር ተያይዟል)

 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር የመንግሥት ተቋማትን እንደገና ለማደራጀት ባወጣው ደንብ ደንብ ቁጥር 64/2011 በይፋ ከፀደቀ በኋላ፣ አንዳንድ መዋቅራቸው ከተሻሻለላቸው ተቋማት አንዱ የአዲስ አበባ ቤቶች ነው፡፡ ተቋሙ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሥር ሆኖ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲነት ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንነት ሲሸጋገር የኤጀንሲውን አጠቃላይ የሰው ኃይል፣ የተቋም ንብረት፣ ፋይናንስ (ዕዳን ጨምሮ) የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶችና መሰል ንብረቶችን ቆጥሮ ርክክብ የሚያደርግ ‹‹የሽግግር ጽሕፈት ቤት›› ተቋቁሞ ሥራውን አጥንቶና አጠናቆ፣ አጠቃላይ ንብረቱን በወቅቱ በነበሩት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ዳምጠው አማካይነት ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ርክክብ ተፈጽሟል፡፡ (የቆጠራ ውጤቱ ቅጽ ከዚህ ጥናት ጋር ተያይዟል – ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ መረጃ)

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የጥናት እጥረቶች ምን ነበሩ?

 1. ዩኒቨርሲቲው የሚያጠናው (ያጠናው ጥናት) የመነሻ ድምዳሜ ስህተት መሆኑ፣

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ስለኮንዶሚኒየም ቤቶችና የቀበሌ ቤቶች ያደረገው ጥናት ውጤቱን ማሳየት ሲገባው፣ ጥናቱ ገና ሳይካሄድ የጥናቱ መነሻ ላይ ድምዳሜ ይዞ ወይም ውጤቱን ቅድሚያ ተንብዮና ወስኖ የጥናት ጉዞ ጀመረ፡፡ የጥናቱ መነሻ ላይ ውጤቱን ማወቁን የሚያሳዩ ግልጽ ምልክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፣

 • ጥናቱን ለማድረግ በተለይ በአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች በአሠራርም ሆነ በውጤት የተበላሹ ስለሆነ፣ ይህን የተበላሸ ውጤት አጥንተን ለአዲስ አበባ ሕዝብ እናሳያለን፣ ሊወሰድ የሚገባውንም ዕርምጃ እንጠቁማለን የሚል መነሻ ይዞ ተነስቷል፣
 • በአዲስ አበባ ውስጥ የከፋ የመሬት፣ የኮንዶሚኒየም ቤት፣ እንዲሁም የቀበሌ ቤት በሕገወጥና ያላግባብ ተይዟል የሚል ድምዳሜ ነበረው፣
 • ለዚህም ዋናዎቹ የወረዳ ባለሙያዎች፣  የክፍለ ከተማ ባለሙያዎች፣ የከተማ ባለሙያዎችና አመራሮች እንደሆኑ የመነሻ ድምዳሜ ይዞ ተነስቷል፣
 • ለዚህም ከዚህ በፊት የነበሩ ጥናቶች እንደ መነሻና እንደ ግብዓት መጠቀም ሲገባው ከዚህ ይልቅ እኔ ያጠናሁት ብቻ ትክክል ይሆናል የሚል ግምታዊ ምልከታ ይዞ ወደ ጥናቱ ገብቷል፣

2. ዩኒቨርሲቲው የሚያጠናው (ያጠናው ጥናት) ከዚህ በፊት የተጠኑት ጥናቶችን መነሻ አለማድረጉ ወይም ውጤቱን ከዚህ በፊት ከተጠኑ ጥናቶች ጋር አወዳድሮ አለማቅረቡ፣

3. ለዩኒቨርሲቲው ጥናት አጋዥ (አጋር) የሆኑና እንደ ማዕከላዊ የመረጃ ምንጭ የነበሩ ተቋማትን ማግለል፣

 • የኮንዶሚኒየም ቤት አጠቃላይ የግለሰቦች ፋይል መረጃ የሚገኘው በክፍላተ ከተሞች ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ሆኖ እያለ፣ ከክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ቅጽር ጽሕፈት ቤቶች (ባለሙያዎች) በጥናቱ ውስጥ እንዲካተቱ አልተደረገም፣
 • የቀበሌ ቤትን በተመለከተ የግለሰቦች መረጃ የሚገኘው በየወረዳው ቤቶች አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሆኖ፣ በጥናቱ ውስጥ በአጋዥነት ወይም በአጋርነት እንዲሳተፉ አልተደረገም፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እጥረቶች ምን ነበሩ?

1. የዩኒቨርሲቲውን ጥናት ሙሉ በሙሉ እውነት ነው ብሎ መቀበል        

 • የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣  የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ እንዲሁም የቀድሞ የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ስፖንሰር ያደረጉት ኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤቶች ቆጠራ ተደርጓል፡፡ ውጤቱም እዚያው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ይገኛል፣ ይህን ለዓመታት የተሠራ ጥናት እንደ ግብዓት ተጠቅሞ በተጨማሪ ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ጋር አዋህዶ ውጤቱን ከማስቀመጥ ይልቅ፣ ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ዩኒቨርሲቲውን ጥናት ምሉዕ አድርጎ መውሰዱ፣
 1. የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና በሥሩ የሚገኙ ተቋማትን ጥናት አለመቀበል
 • ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት ዓመታት በሥሩ ያዋቀራቸው ተቋማት እንዳሉ ዕሙን ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤትን የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሆኖ፣ በሥሩም የተለያዩ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንና የክፍላተ ከተማና የወረዳ ቤቶች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲኖሩ፣ እነዚህ ተቋማትና በሥራቸው ያሉ ባለሙያዎች በሥራ ላይ እያሉ እነሱ ያጠኑትን የጥናት ውጤት ትክክል ወይም ስህተት ሳይል ችግርና ክፍተታቸውን ሳያሳይ፣ ወይም ጥናቱ ውዳቂ ነው ብሎ ሳይጥል የተቋማቱን ሥራዎች ገለል አድርጎ፣ አዲስ ተቋም ገለልተኛ ነው ብሎ ወስዶ ሳይገመግም ሳያወዳድርና ሳያነፃፅር መቀበልና የራስን ተቋም ማናናቅ በእርግጠኝነት ታይቷል፣
 • አብዛኛውን ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የሚሾሙ የመንግሥት ተሿሚዎች ተግተው በመሥራት ውጤትን ከማሳየት ይልቅ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች ትክክል እንዳልየሩ ለማሳየት አዲስ የተሳሳተ ጥናት ይዞ መቅረብ የዓመታት ልምዳቸው ነው፡፡

4. የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት ጥናት ውጤት በከፊል

4.1. የኮንዶሚኒየም ቤት

የጥናት ውጤቱ በአጭሩ (ክብርት ምክትል ከንቲባ ካቀረቡት ሪፖርት የተወሰደ)

 • 21,695 በሕገወጥ የተያዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣
 • 15,891 መረጃ ያልቀረበባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣
 • 4,530 ለረዥም ጊዜ ዝግ የሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣
 • 850 ከመጀመርያውኑ ዝግ ሆነው የተቀመጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣
 • 424 በሕገወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው የተገኙ፣ እንዲሁም
 • በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው 132,678 የባለዕጣዎች ዝርዝር ውስጥ 18,424 ቤቶች የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው መሆኑ በጥናቱ የተለየ ቢሆንም፣

የክብርት ምክትል ከንቲባዋ የጥናት ውጤቱ በየክፍላተ ከተማውና ወረዳው ዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድበት፣ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አማካይነት ታኅሳስ ወር መጨረሻ 2013 ዓ.ም. ለአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የተሠራጨው ደብዳቤ ባጭሩ ይህን ይመስላል፡-

‹‹እርስዎ የያዙትና በ ———— ክ/ከተማ በ ———— ሳይት በ ————– ብሎክ በ ——— የቤት ቁጥር የሚገኘው ቤት በሕገወጥ መንገድ እንደያዙት በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት በተደረገው ጥናት በመረጋገጡና ይህንኑ ተከትሎ የከተማው አስተዳደር በሕገወጥ መልኩ የተያዙ ቤቶችን በማስለቀቅ፣ በ1997 ዓ.ም. ተመዝግበውና እየቆጠቡ ላሉ ነዋሪዎች ቤቶቹ በዕጣ ለማስተላለፍ የተወሰነ በመሆኑ፣ ይህ ደብዳቤ በደረሰዎት በሁለት ሳምንት (አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ) ቤቱን በመልቀቅ ለወረዳው እንዲያስረክቡ በጥብቅ እያሳሰብን፣ ይህንን የመንግሥት ጥያቄ የማይቀበሉ ከሆነ ግን በሕጋዊና አስተዳደራዊ መንገድ ቤቱን የምንረከብ መሆኑን እናውቃለን፤›› በማለት ያስቀምጣል (አንድ ናሙና ደብዳቤ ከጥናቱ ጋር ተያይዟል)

ከላይ የተቀመጠው ደብዳቤ ሕገወጥ በተባሉት የኮንዶሚኒየም ባለቤቶች በር ላይ እንዲለጠፍ ተደርጓል፡፡ በቤት ውስጥ ላሉ የኮንዶሚኒየም ባለቤቶች ወይም ተከራዮች ደብዳቤው በእጃቸው እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ በተጓዳኝ እነዚህ ሕገወጥ የተባሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በየክፍለ ከተማው ቤቶች ልማት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሚያገለግሉ ባለሙያዎች ዘንድ ሕጋዊ ናቸው አይደሉም የሚለው መረጃ እንዲመረመር ተደርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው አጥንቼ ደርሼበታለሁ ያለው መረጃ፣ መረጃውንም መሠረት በማድረግ ምክትል ከንቲባዋ ለአዲስ አበባና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ ያደረጉት መረጃና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የተፈረደባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ለየክፍለ ከተማ አመራሮች ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ነው የዩኒቨርሲቲው ጥናትና ውጤት ትክክል እንዳልሆነ፣ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች የተረጋገጠው፡፡ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናው ሕገወጥ ሳይሆኑ አብዛኛዎቹ የኮንዶሚኒየም ባለቤቶች ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሕጋዊ መንገድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የኮንዶሚኒየም ቤቱን በዕጣ ወይም በሌላ መሰል ሕጋዊ መንገድ ያገኙ ተጠቃሚዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተጠናውና ሕገወጥ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተገኝተዋል ተብለው ለ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢ በዕጣ ይተላለፋል ተብለው በክብርት ምክትል ከንቲባ የተነገሩ፣ ነገር ግን በየክፍላተ ከተሞቹ ሲጣራ ወይም ሲረጋገጥ ሕገወጥ ያልሆኑ፣ መረጃቸው ትክክል የሆነና ካርታና ውል ያላቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዝርዝር ከየክፍላተ ከተሞቹ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች የተገኘ፡-   

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን

ማስገንዘቢያ

 • ከላይ ከአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በተገኘው ውጤት መሠረት ዩኒቨርሲቲው አጥንቼ ደርሼባቸዋለሁ ያለውና ምክትል ከንቲባዋ አስለቅቄ ለ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢ አድላለሁ ያሉት ሕገወጥ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምንም እንዳልተገኙና ጥናቱና ሪፖርቱ ትክክል እንዳልሆነ ያሳያል፣
 • ከላይ የቀረበው የየክፍለ ከተሞቹ ቁጥር ቢቻል በሕጋዊ ደብዳቤ ቢረጋገጥ መረጃውን ይበልጥ ታማኝ ሊደርገው ይችላል፣
 • ከዚህ የምንረዳው የዩኒቨርሲቲው ጥናትም ሆነ የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ውሳኔውን ለሕዝብ ይፋ የማድረጉ ውጤት፣ በጣም ግብታዊና የአዲስ አበባን ሕዝብ ለስህተት ዜና የዳረገ ሆኗል፡፡

  የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጥናት ተቀባይነት አግኝቶ ለሕዝብ ይፋ የሆነው በጥር 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባዋም ሆኑ ሌሎች የከተማው አመራሮች በሕገወጥ የተያዙትን ቤቶች አስለቅቀን ለ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች እናድላለን ብለው የገቡት ቃል አሁን ይህ ጥናት እስከ ቀረበበት ሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ አንድም የኮንዶሚኒየም ቤት አስለቅቀናል/አግኝተናል ተብሎ ለአዲስ አበባ ሕዝብ የቀረበ ሪፖርት የለም፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት እንደ ቀበሌ ቤት ጉራንጉር ውስጥ ያለና ለውሸት ቁጥር ስለማይመች፣ ወደፊት የሚነገር ቁጥር ካለ መጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው ተጠንቶ ተረጋግጧል የተባለው በሕገወጥ የተያዙ የኮንዶሚኒየም ቤት ግኝቶች በየክፍለ ከተማው ቤቶች ልማትና አስተዳደር  ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በኩል ግኝቱ ዜሮ “0”  ስለሆነ፣ ምክትል ከንቲባዋ (የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አመራሮች) ከጥናቱ በኋላ መሬት ላይ ያገኙትን ውጤት በግልጽ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ይፋ አድርገው ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ የተገኙት 138 የ10/90 የኮንዶሚኒየም ቤቶች በክፍለ ከተማው የሚታወቁ፣ በተለያየ ጊዜ ለኮርፖሬሽኑ ለችግረኛ እንዲተላለፉ ቀርበው ኮርፖሬሽኑ ጆሮ ዳባ ልበስ ያላቸው፣ ከዩኒቨርሲቲው ጥናትና ሪፖርት በፊት ባለቤት የነበራቸው ወይም ያልተላለፉ፣ ወይም ባለቤት ኖሯቸው በተለየ ምክንያት ተለቀው ክፍት የሆኑ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ ቢኖር ከ20/80 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ምንም ዓይነት በሕገወት መንገድ እንዳልተገኘ ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር በተለይ ቤቶቹ ይታደለዋል የተባለው ተስፈኛ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢ በሌላ ጉዳይ ባይክሱትም በይቅርታ ልቡን ሊያራሩት ይገባል፡፡   

  4.1. መንግሥት የሚያስተዳድረው የቀበሌ ቤት

  የቀበሌ ቤትን በተመለከተ በምክትል ከንቲባዋ ለሕዝብ ይፋ የተደረገው ውጤት፡-

 • 10,565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባትና በሌሎች ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ፣
 • 7,723 ቤቶች ውል በሌላቸው ሰዎች የተያዙ፣
 • 2,207 ቤቶች ወደ ግል የዞሩ፣
 • 265 ቤቶች በሦስተኛ ወገን የተያዙ፣
 • 164 ቤቶች ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው ወይም የራሳቸው ቤት እያላቸው ከሕጉ ውጭ የቀበሌ ቤትን የያዙ፣
 • መንግሥት የሚያስተዳድራቸውን የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናው የተጋነነ ባይሆንም፣ ከላይ ባቀረብኩት በተራ ቁጥር አንድ ላይ አምስት ጊዜ በተደረጉ ቆጠራዎች በቀበሌ ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት በሕገወጥ እንደተያዙ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ዕርምጃ መውሰድ ያለመውሰድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሥልጣንና ኃላፊነት ሆኖ እያለ፣ ለዓመታት ሕገወጥ ቤቶች (የቀበሌ ቤቶች ችግር) ተብሎ የተሰጣቸውን ሪፖርት መልሰው ለኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ሰጥተው፣ ‹‹በገለልተኛ›› ወገን የተጠና ብለው ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ከሰሞኑ በምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሕገወጥ ተይዘው የነበሩ ቤቶች ተለቀው ለችግረኛ እየታደሉ እንደሆነ እተነገረ ነው፡፡ ሐሳቡና ድርጊቱ እውነት ከሆነ መልካም ነው፡፡ በድጋሚ መግለጽ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር የቀበሌ ቤት ባህሪ ዥንጉርጉርና ከዚህ በፊት ተጠንቶ የተቀመጠ ስለሆነ አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከሦስት ወራት ወይም ከስድስት ወራት በኋላ የቀበሌ ቤት ይቆጠር (ኦዲት ይደረግ) ቢባል ተጨማሪ ሕገወጥ የቀበሌ ቤቶች እንደሚገኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን በዚህ አጋጣሚ ሁለት ለአዲስ አበባ ሕዝብ ቁምነገር የሆነ ክስተቶችን ልጥቀስ፡፡

  1. በየካቲት ወር 2013 ዓ.ም. ምክትል ከንቲባዋ በአራዳ ክፍለ ከተማ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ካጠናውና ሕገወጥ ሆነው ተለቀው ለችግረኞች ተሰጡ ከተባሉት ውስጥ፣ በተለይ በተለምዶ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ የተሰጡ ቤቶች ታሪኩ ሌላ ነው፡፡ ይኸውም ዶሮ ማነቂያ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች ከአንድ ዓመት በፊት አካባቢው ለልማት ስለሚፈለግ በዚያ የሚኖሩ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ከፊሉ የቀበሌ ቤት፣ ከፊሉ ኮንዶሚኒየም ቤት መርጠው በአካባቢው የቀበሌ ቤቶች ታሽገው ለማንም ሳይሰጡ ተቀምጠው ነበር፡፡ ልማቱ በመጓተቱ ወይም በመቅረቱ እነዚህ ቤቶች ለዓመት ማንም ስለሌባቸው እንዲሁ ተቀምጠው ነበር፡፡ ምክትል ከንቲባዋ እንግዲህ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አጥንቶ ተለቀቁ ተብለው የተሰጡት እነዚህ ቤቶች ናቸው፣

  2. በየካቲት ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ የትንሣዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ምክትል ከንቲባዋ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ 134 ቤቶች በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ሕገወጥ መንገድ የተጠኑ የተባሉ ቤቶች እንደተሰጡ ተደርጎ፣ በየሚዲያው ሲነገር መሰንበታችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ታሪኩ ሌላ ነው፡፡ ይኸውም ከ134 ውስጥ 26 ቤቶች በሕገወጥ ተይዘው የነበሩና የተለቀቁ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም አብዛኛው ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ጋር የተገናኙ አይደሉም፡፡ 108 ቤቶች ግን ‹‹የረዥም ዓመት በሚል የፀደቁ ናቸው፡፡ ይህም 1008ም በቤቱ ውስጥ ከዘጠኝ ዓመት በላይ የኖሩና ረዥም ዓመት በቀበሌ ቤት ውስጥ ስለኖሩ በክፍለ ከተማው ካቢኔ ቀርቦ የፀደቀላቸው ቤቶች እንጂ ቤቶቹ በሕገወጥ የተያዙና የተለቀቁ ሳይሆኑ ለዓመታት በቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች የፀደቀላቸው ቤቶች ናቸው፡፡ በዚህም ክፍለ ከተማውና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕዝቡ ይህን ግልጽ ማድረግ አለባቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኮንዶሚኒየምና የቀበሌ ቤት የጥናት ውጤት ላይ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ባምንም፣ ከቀበሌ ቤት ባህሪይ አንፃር አሁንም የቀበሌ ቤቶች ድጋሚ ቢቆጠሩ (ኦዲት ቢደረጉ) በእርግጠኝነት አዲስ ሕገወጥ የቀበሌ ቤቶች እንደሚኙ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

  ማጠቃለያ 

  በ2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ትልቅ የመነጋሪያ ወሬ ሆኖ የነበረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካይነት ተወክሎ፣ በአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየምና ቀበሌ ቤቶች ላይ ጥናት ሲያደርግ የነበረው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ያቀረበው የጥናት ውጤት ነበር፡፡ ጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል ተቀባይነት አግኝቶ፣ ከምክትል ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ጀምሮ የተለያዩ የከተማዋ ባለሥልጣናት በአገር ደረጃና በአዲስ አበባ በሚገኙ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ርዕሰ አንቀጽ ሆኖ ሲዘገብና ሲወራ እንደነበር የሁሉም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር፡፡ በተለይ ከ21,000 በላይ በሕገወጥ የተያዙ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለምስኪኑ ተስፈኛው የ1997 ዓ.ም. የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢ በዕጣ እንደሚተላለፍ የተነገረ ቢሆንም፣ እስከዚህ የጥናት ሪፖርት ቀን ድረስ ምንም ዓይነት ሕገወጥ ኮንዶሚኒየም ቤት ተለቀቀ ሲባል አልተሰማም፡፡ ደግሞም ለማንም አልተሰጠም፡፡ በሌላ ጎኑ የየክፍለ ከተሞች ሪፖርት በየወረዳው ምንም ዓይነት በሕገወጥ የተያዘ ኮንዶሚኒየም ቤት እንደሌለ ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ቆጠራዎች (ኦዲት) ተደርገዋል፡፡ በተለይ በ2009 ዓ.ም. በአሥሩም ክፍላተ ከተሞችና በሥራቸው የሚገኙ ወረዳዎች የቆጠሩት የቆጠራ ውጤት እዚያው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ ያንን ተግባራዊ ማድረግ ሲገባ ግብታዊ የሆነና ትክክለኛ ጥናት ሳይደረግ የተሰበሰበውን መረጃ እንደ ትክክለኛ መረጃ ቆጥሮ የከተማ አስተዳደሩ የተሳሰተ መረጃ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ (በ2009 ዓ.ም. የተደረገው ቆጠራ አይደለም ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቀርቶ ሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ተልኮ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ለጠቅላይ ሚኒስቴር ሪፖርቱን /የተገኙ ችግሮችን/ ገልጾ ልኮ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ለቀረቡለት ጥያቄዎች በቀን መስከረም 26/2010 በቁጥር መ30 – 878/3 ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ምላሽ የሰጠበት ደብዳቤ በእጄ አለ)፡፡

  ከዚህ አንፃር የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ያቀረበው ጥናትና ያቀረበው ሪፖርት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ትክክል አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንም ለማረጋገጥ የእኔ ግርድፍ የጥናት ውጤት ዩኒቨርሲቲው አጠናሁ ካለው ውጤት ጋር ተመሳክሮ ውጤቴ ለአዲስ አበባ ሕዝብ መቅረብ አለበት፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አጥንቼ አገኘሁት ያለው ሕገወጥ የቀበሌ ቤቶችና የሕገወጥ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ትክለኛ ካለመሆኑም በላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን (የምክትል ከንቲባዋ ጽሕፈት ቤትን) ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ለአዲስ አበባ ሕዝብ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ ይህንም ሕዝቡ ሚዲያውና የሚመለከታቸው አካላት ማወቅ አለባቸው፡፡ አውቀውም ወደፊት ለሕዝቡ፣ ማንኛውንም ዓይነት የሐሰት ሪፖርት እንዳያቀርቡ ማስጠንቀቂያ እንዲሆናቸውና ውይይት እንዲደረግበት ይህን የጥናት ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን አቅርቤያለሁ፡፡   

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...