Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገት‹‹አንገትሽ ራስሽን ችሎ ልየውና…››

‹‹አንገትሽ ራስሽን ችሎ ልየውና…››

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በአሁኑ የኢትዮጵያ እውነታ ውስጥ ሦስት ዝንባሌዎች ይታያሉ፡፡ 50 ዓመታት ያህል አቀንቃኝ ባላጣውና ከዚያም በኋላ ከ1983 ዓ.ም. ወደዚህ የኢትዮጵያ ኑሮ በተደረገው ብሔርተኛነት ውስጥ እስረኛ ሆኖ ሰንሰለት እያንቃጨሉ መንኳተት አንዱ ነው፡፡ አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት በዚያው የእስረኝነት ግቢ ውስጥ በሚደረግ መወራጨትና ፅንፈኛ ብሔርተኝነትን በሚጠቅም ጅል ተላታሚነት አማካይነት፣ ራስን በራስ በማጥፋት ጎዳና መንጎድ ሁለተኛው ዝንባሌ ነው፡፡ ሦስተኛው ዝንባሌ ከሁለቱ ራስን ነጥሎ የእስረኝነትን ስንሰለት የመጣል እንቅስቃሴ ነው፡፡

ካቴናና ሰንሰለት

- Advertisement -

አዕምሮ በአተያይና በአስተሳሰብ ተከታትፎ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ያህል ተሟሽቷል፡፡ በዚሁ ሙሽት መሠረት ወገኔ ባይነትና መሬቴ ባይነት በጎሳ፣ በብሔረሰብና በጎጥ ጎማምዶናል፡፡ የዚሁ የመጎማመድ መዋቅር በሆኑት በየብሔር ፓርቲ መቧደን፣ ባለቤትና ባይተዋር በሚል አዚም እየተመሩ በክልል ደረጃ፣ በዞን፣ በልዩ ዞንና በወረዳ መሬት መቃረጥ፣ እዚያ ቅርጫና ቅርጨኛነት ውስጥ ሆኖ ያለውን ሕገ መንግሥትና አሸናሸን በጭፍኑ ማምለክ፣ የአንድ አገር ልጅነትን በዘነጋ ይዞታዬ ባይነት መንቀብቀብ፣ መሬት ቀረኝ/ተነካብኝ ባይ ደም አፋሳሽና አፈናቃይ ግጭት መፍጠር፣ በየአቅጣጫው ያለውን ቅርጨኛነት አመጣሽ የሆነውን መጠማመድና ግጭት፣ ግድያና መፈናቀል እያዩም ቢሆን እዚያው የቅርጫ አተያይና ድርጅታዊ አቦዳደን ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹ማንነቴ ይታወቅልኝ›› (ይዞታዬ ይሠፈርልኝ)፣ የተሠፈረልኝ ይዞታ የዞንነት/የልዩ ዞንነትና የክልልነት ደረጃ ይሾምልኝ የሚል ጥያቄና እንቅስቃሴ ውስጥ መማሰን፣ ጥያቄውን በይፋ ባያነሱም ውስጥ ውስጡን መቋመጥ፣ ግለሰቦችን የአንዱ ወይም የሌላው ጎሳ/ብሔረሰብ ናሙና አድርጎ መመልከት፣ እነዚህ በመደበኛነት የታወቁት የክፍልፋይነት ካቴና መገለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መገለጫዎች አንድ ላይ ተደምረው ሲታዩ ኢትዮጵያ ጠቅላላ የክፍልፋይ አተያይና መዋቅሮች፣ ፍላጎቶችና ንቁሪያዎች እስረኛ ነች ማለት ይቻላል፡፡

ከላይ ለማስቀመጥ የሞከርኩት ጭማቂውን እንጂ፣ እስረኝነት የሚገለጥባቸው መልኮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ በብሔርተኛ ፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት ውስጥ ሆነው ክፍልፋይነት በሚፈጥረው አዙሪት ውስጥ እየተዳፉ፣ በቁጣና በበቀል መጦፍና ወደ ግጭት መሄድ፣ መግደል መገደል፣ አልቅሶ መቅበርና ማቅ መልበስ በውስጣችን ከራርሟል፡፡ ነገር ግን እያለቀስንና እየበገንንም ከመሀላችን ከብሔርተኛ እስረኝነት ለመላቀቅ የማይሹ (ክፍልፋይነት የሚጥማቸው) ጥቂት አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም የክፍልፋይነት እስረኛ መሆናቸውንም አያቁትም፡፡ በብሔር ማሰብን፣ በየብሔር ተለይቶ መደራጀትንና የመሬት ቅርጨኛነትን እየተቃወሙ እዚያው ካቴና ውስጥ ሲልወሰወሱ ይገኛሉ፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረትም ሆነ ማኅበራዊ ዝውውርና መላላስ በተትረፈረፈበት የታሪክ ጉዟችን መሠረት፣ በኢትዮጵያ ያለ መሬት ሁሉ የብሔር ቅርጫ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ መሬቱ የኢትዮጵያ መላው ሕዝብ ሀብት ስለመሆኑ በአንድ ወገን እየተከራከሩ፣ በሌላ ጎን አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች ነች የሚሉ አሉ፡፡ ‹‹የክልሎች አወቃቀር ብሔርንና ቋንቋን ብቻ ሳይሆን፣ ለአስተዳደር አመቺነትንና የዕድገት አቅምን ሁሉ መመዘኛ ማድረግ አለበት›› ያለ አንደበት፣ በሌላ ጎን ‹‹ይህ መሬት ከእኛ አስተዳደራዊ አካባቢ ውጪ በሌላ አስተዳደር ውስጥ ገብቶ አያውቅም›› የሚል ክርክር ሲያቀርብም እናገኛለን፡፡

ኢትዮጵያዊነትን በረዥም ጥንተ ታሪክ ውስጥ የተገነባ ማንነት፣ (ብሔረሰባዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዥንጉርጉርነት ያለው አንድ ዘርነት) አድርገን አንረዳውም፡፡ ማንነት ወይም ‹‹ዘር›› እያልን የምንጠራው ብሔር/ብሔረሰብነትን ነው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔረሰብ ገጽታን ውሉ ያደረገ መገዳደልና መፈናቀል ሲከሰት፣ ኢትዮጵያዊ በገዛ ዘመዱና ዘሩ ላይ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑ አይታሰበንም፡፡ እከሌ ብሔር/ብሔረሰብ በዘሩ እየተጠቃ ነው እንላለን፡፡ ቋንቋን ዋና ያደረገ የዝምድና (የወገን) መለኪያችን ምን ያህል ግልብ እንደሆነ ለመረዳት፣ ከሚሴ ሰሜን ሸዋ አካባቢ የታየው ብዙ ሰው የሞተበት፣ ብዙ ሺዎች የተፈናቀሉበትና እሳት እንደ ልቡ የነደደበት ግጭት ምርጥ ምሳሌ ነው፡፡

በዚያ አካባቢ ላለ የኦሮሞ ሕዝብ በየትኛውም አካባቢ ካለ ኦሮሞነት ይበልጥ አብሮት ያለው አማራነት (በባህልም፣ በሥነ ልቦናም በመወላለድ ተወራራሽነትም) የበለጠ ቅርብ ዘመዱ ነው፡፡ ኦሮሞነት አማራነት የሚሆንበት፣ አማራነት ኦሮሞነት የሚሆንበት የተዋልዶ መስተጋብር ለረዥም ጊዜያት ሲካሄድ ኖሯል፡፡ ያንን ሒደት ዛሬም ማንም ሊገታው አይችልም፡፡ ሙስሊምነትና ክርስቲያንነትም እንደዚያው የአንድ ቤት ትዳር ድረስ እየገባ ሲያዘማምድ ኖሯል፡፡ ተላልሶ ከመኖር ባሻገርም፣ ከክርስትና ወደ እስልምና ከእስልምና ወደ ክርስትና ማለፍ እንግዳ አይደለም፡፡

በብሔርተኛ የቋንቋ መሥፈርት ዝምድና ተለክቶ ‹‹የኦሮሞ ልዩ ዞን›› የሚል መዋቅር በተፈጠረ ጊዜ፣ በኦሮሞነትም በአማራነትም መለካት (መደልደል) በሚጠባቸው ዝንቅ ዘመዳሞች መሀል አጥር ነበር የተፈጠረው፡፡ አጥሩና ብሔርተኛ ‹‹ንቃቱ›› የኦሮሞ ልዩ ዞንን የኦሮሚያ የሩቅ ዓምባ አስመሰለው ለወሎ፣ ለሸዋ ኦሮሚኛ ተናጋሪ በዝምድና ቅርበት የባሌና የወለጋ፣ ወዘተ ኦሮሞ የሚበልጥ አስመስለው፡፡ የአካባቢው አማርኛ ተናጋሪም ከተጋባው/ከተዋለደውና በትውልድ ሐረግ ከተሰናሰለው የአጠገቡ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ዘመዱ ይልቅ፣ ከጎጃሜነትና ከጎንደሬነት ጋር ያለው ዝምድና እንደሚበልጥ አድርጎ ‹‹እንዲረዳ›› ተደረገ፡፡ የዚህ ዓይነቱን የቦዘ ‹‹ንቃት›› የተላላሱ የትግሬ አማራ፣ የአማራ አፋር፣ የአፋር ኦሮሞ፣ የአፋር ሶማሌ፣ የጉራጌ ኦሮሞ፣ የኦሮሞ ሶማሌ፣ ወዘተ ዝንቅ (ባለድርብ ገጽ) ማኅበረሰቦችን ያሳሳተና ያላተመ ነው፡፡

ጥቃትና መፈናቀል ሲፈጸምም ጩኸትና ውግዘቱ ሁሉ በአያሌው ቋንቋን ባንጠለጠለ ወገንተኝነት ሠፈር የለየ ወጥመድ ውስጥ መግባቱም ሌላ የእስረኝነት መገለጫ ነው፡፡ ይህ እስረኝነት የኢትዮጵያ መላ ሕዝብ ሉዓላዊነት የሚወከልበት ፌዴራል ፓርላማ ድረስ የዘለቀ ነው (በቅርቡ ከአማራ ክልል የኦሮሞ አካባቢ የተወከሉ ተወካዮች ኦሮሞ ተጠቃህ ተነስ ከማለት ያልራቀ ወገንተኛ ንግግር እንደተናገሩ ያስታውሷል)፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማ አባልነት ባህርይ ለየመጡበት አካባቢያዊ ጉዳዮች ተወካይ ከማሰባሰብ ይልቅ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ጥቅል ልዕልና ከየአካባቢዎች አውጣጥቶ መወከል ሆኖ ሳለ፣ ያሉት የዛሬ ‹‹ተወካዮችም›› ፓርቲያዊ አመጣጥ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ውህድ አመለካከት የመሸጋገር ተሃድሶ ውስጥ ካለው ብልፅግና ጋር የተያያዘ ሆኖ ሳለ፣ ግርሻው የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ድረስ ሊከሰት የቻለው በግለሰባዊ ድክመት ብቻ አይደለም፡፡

ኅብረ ብሔራዊ ውህድ አመለካከትና ፓርቲያዊ አደረጃጀት ውስጥ የገባው ብልፅግና ፓርቲ የፓርቲ ቅርንጫፎቹን ሲያዋቅር፣ ነባሩን ብሔርተኛ አወቃቀር ከመከተል አላመለጠምና ሁለት ፈተናዎች ውስጥ ይገባል፡፡ ‹‹የኦሮሚያ ብልፅግና››፣ ‹‹የአማራ ብልፅግና››፣ ወዘተ እያለ ቅርንጫፎችን ሲፈጥር፣ የክልሎቹ አወቃቀር ትልልቅ ብሔረሰብነትን ወይም ‹‹የባለቤትነትን መብት›› መሠረት ያደረጉ እንደ መሆናቸው የፓርቲ አባልነት የድጋፍ ክምችታቸው ለየክልሉ መታወቂያ ከሆኑት ብሔረሰብ/ብሔረሰቦች ጋር ይያያዛል፡፡

ዋና ብሔረሰብን/ብሔረሰቦችን መሠረት ያደረገው መዋቅርና የአባልነት ነባር ክምችቱ በራሱ በዚያ ግቢ ውስጥ እንዲያስቡ ይጫናቸዋል፡፡ በባይተዋርነት ሲንጓለሉ የቆዩ ወገኖችን፣ ገና በውህድነት ጅምራቸው የማግበስበስ ሩጫ ውስጥ ቢገቡ ያልተጣጣሙ አስተሳሰቦችን አንድ ፓርቲያዊ ትልም ላይ የማገናኘቱ ሥራ አንድ ፈተና ነው፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ባለቤትና መጤ›› የሚል አስተሳሰብ የፀናባቸው በፓርቲው ውስጥና ከፓርቲው ውጪ የሆኑ ብሔርተኞች ‹‹ብልፅግና የመጤ/የነፍጠኛ ጎሬ እየሆነ ነው›› ለሚል ማወናበድ ምርጥ ፍትፍት ያገኛሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የዚህ ዓይነቱ አወናባጅነት መንገድ ካገኘ ደግሞ፣ የፓርቲ መሰነጣጠቅና ጎጣዊ መከፋፈል ከመፍጠር በበለጠ፣ ትልቅና የበለፀገች አገር በመገንባት ዕድላችን ላይ እጅግ ውድ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ይህንን መሰሉን ቀውስ አምልጦ ፅንፈኞችን ለማክሰም፣ ከሁሉ በፊት በዚህ ምርጫ የኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ አሸናፊነትን ማሳካት፣ ተከትሎም ለተዋደደና ለተከባበረ የሕዝቦች ግንኙነትም ሆነ ለግስጋሴ በብሔር ከተደራጀ አንጓላይ ገዥነት ይልቅ፣ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲና አመራር እንደሚስማማ በተግባር ማስመስከር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን በማረጋገጥ የስኬት ሒደት ውስጥ የየክልል ፓርቲንም ሆነ የአገራዊ ፓርቲ ቅርንጫፎችን ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር ማሳደግ ቀላል ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይባርቅ ሆኖ እስኪሟላ ድረስ፣ የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ለራሱ ለአባላቱም ከበፊቱ ‹ኦዴፓ› ብዙ ልዩ ሆኖ ላይታይ ይችላል፡፡ የአማራ ብልፅግናም ከበፊቱ ‹አዴፓ› ብዙ ርቆ ላይታይ ይችላል፡፡ በሌሎችም አካባቢዎች እንደዚያው፡፡ ከውስጥ ላሉት ልዩነቱ ጎልቶ ካልታየ ከፓርቲው ውጪ የሆኑ ሰዎች በፊት በነበረ አደረጃጀትና በአሁኑ የብልፅግና አደረጃጀት ውስጥ ያለ ልዩነትን ማጤን ቢያስቸግራቸው አይገርምም፡፡ ‹‹ብልፅግና የሚል ስም ተጨመረ እንጂ ዛሬም እንደ ትናንቱ ያሉት የየብሔር ድርጅቶች ናቸው…›› የሚለው አስተያየት አንዱ መነሻ፣ ልዩነታቸው ኅብረ ብሔራዊ ጥንቅርን ተመርኩዞና ማኅበረሰቦችን አዋድዶ ሲያተም በአግባቡ ለመታየት አለመቻሉ ነው፡፡

ሌላው መነሻ የብልፅግና ፓርቲን ኅብረ ብሔራዊ ሽግግር አዋድቆ እዚያው የብሔርተኛ ጎሬ ውስጥ የመክተት የፖለቲካ ንግድ ነው፡፡ እነዚህ ለኢትዮጵያ እናስባለን ባይ ነጋዴዎች በብልፅግና በኩል ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለውን ዕድል ከማደናቀፍ በቀር፣ በነቀፋቸው የፖለቲካ አትራፊ የሚሆኑበትም ሆነ ኢትዮጵያን አትራፊ የሚያደርጉበት ነገር የላቸውም፡፡ የዚህ ዓይነት የፖለቲካ ባህርይ የዜሮ ባለሀብትነት ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሳዛኝ የኪሳራ ባለሀብትነት የእስረኝነት ዕዳችን ሌላ መልክ ነው፡፡

የብልፅግና ፓርቲ በተለይ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፎቹ ውስጥ አሁን የሚንገላታባቸው የብሔርተኛነትና የኅብረ ብሔራዊነት አጣቢቂኞችና ፍትጊያዎች፣ ከሌሎቹ ክልሎች ሁሉ የከበዱ ናቸው፡፡ ይህ ፈተና የእነሱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም የወደፊት ዕጣ ፈተና ነው፡፡

የአማራ ብልፅግና ቢወድም ባይወድም አማራ ውስጥ ብዙ ሕዝብ የተዋደቀለት የወልቃይትንና የራያን የአማራ ክልል አካልነት ከመደገፍ ውጪ አማራጭ የለውም፡፡ አጣብቂኝ! በአማራ ክልል በሚደርሱ ግጭቶች ውስጥ ተቀዳሚ ወገናዊነቱ ለ‹‹አማራ›› እንዲሆን፣ መጠሪያ ስሙም አገሪቱ ላይ ገና እየሠራ ያለው ብሔርተኛ አስተሳሰብና አወቃቀር ቀይዶ ይዞታል፡፡ ‹‹ኦነግ ሸኔ በሚል የዳቦ ስም ኦሮሞ (በአማራ ክልል ውስጥ) በአማራ ልዩ ኃይል ተጨፈጨፈ›› የሚል ፖለቲካ የተሠራው፣ በዚሁ የተዋሀደ ኅብረ ብሔራዊ አመለካከት መጓደል ምክንያት ነበር፡፡ እነ አጣዬ ላይ የተደራጀ ጥቃት ሲከፈትና ክልሉ ከአቅሙ በላይ ሲሆን፣ ሕዝብ አነቃንቆ ከመተጋተግ ይልቅ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ኃይል እንዲገባ መጥራቱ ደግሞ ከኅብረ ብሔራዊ ኃላፊነት የፈለቀ (የእርስ በርስ መጨፋጨፍን በር እንዳይከፈት ያደረገ) አስተዋይ ምርጫ ነበር፡፡ ይህን ተረድቶ ዋጋ የሰጠው ግን የለም፡፡ የአማራ ብልፅግና አማራን ከጥቃት የማያድን የእንጨት ምንቸት ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ባልታረመ ንግግርና ቀረርቷቸው አማራ በየቦታው እንዲጠቃ ሰበብ የሚሆኑት ብሔርተኛ ጀብደኞች ግን እንደ ሀቀኛ የአማራ ጠበቆች ይቆጠራሉ፡፡

የኦሮሞ ፅንፈኞች በኦሮሚያ ውስጥ የመንግሥት ሹሞችን፣ ሠራተኞችንና ካድሬዎችን ጨምሮ አማራ የተባለ መናጢ ገበሬን መግደልና ማፈናቀልን ሥራዬ ብለው የያዙበትና ጥቃታቸውን አማራ ክልል ድረስ ያዘለቁበት ዋና ዓላማ፣ አማራ እንዳይሆን ሆኖ ቅስሙ እንዲሰበር ወይም ‹‹አሁንስ በዛ!›› ብሎ እንዲያብድና በኦሮሚኛ ተናጋሪ ዘመዶቹ ላይ በቀል እንዲከፍት ነው፡፡ ይህ ተከፈተ ማለት ‹‹ኦሮሞ ተጨፈጨፈ›› የሚል የፅንፈኞች ጩኸትና አማራን የማስጨፍጨፍ ትርዒታቸው ደራ ማለት ነው፡፡ ይህንን አዙሪት ለመግታት የኦሮሚያ የብልፅግና ቅርንጫፍ ሲሞክር ‹‹የኦሮሞ አስጨፍጫፊ! የነፍጠኛ ቅጥረኛ!…›› ተብሎ ይጠመዳል፡፡ አማራ ክልል ውስጥ ያለው የብልፅግና ቅርንጫፍም አዙሪቱን ሲቃረን ‹‹የአማራ አስጨፍጫፊ! የእነ ዓብይ ቅጥረኛ!…›› ተብሎ መጠመድ ይቀበለዋል፡፡ ከሁለት በኩል የሚመጣው የመጠመድ ጥፊና የፍጅት አዙሪቱ በጣምራ ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ በአንጃ የሚታመስበትንና መንግሥቱ የሚከነበልበትን፣ ኢትዮጵያ የምትሰናበትበትን ውጤት ይደግሳል፡፡ ይህ ሁሉ በአጣብቂኞች እየተጠቀሙ የማዳፋት ሥሌት በፅንፈኞቹ ዓላማ ውስጥ ስለመኖሩ፣ መፋጀት እንዳይመጣ በሚሠጉ ወገኖች ዘንድ በሰፊው የተጤነ አይመስልም፡፡ ተጤነ ቢባልም በፖለቲከኞች ደረጃ እንኳ የሚገባውን ያህል ጥንቃቄ ሲደረግ እያየን አይደለም፡፡

ከዚህ የአጣብቂኝ ፈተና አኳያ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ድጋፋቸው በየትኛውም ወገን ባሉ ፅንፈኞች ሳይሰለብ ከፊታችን ባለው ምርጫ አሸንፎ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት፣ በቀጭን ገመድ ላይ የመሄድ ያህል ከባድ ነው፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በፓርላማ ስለወቅታዊ ጉዳዮች ከተወካዮች ለቀረቡ ጥያቄዎች ዶ/ር ዓብይ አህመድ ማብራሪያ በሰጠባት ቀን፣ በአማራ ክልል ውስጥ ከኦሮሞ ልዩ ዞን ጋር ስለተያያዘው ግጭት ከሁለት በኩል የቀረቡ ቅሬታዎችን በተመለከተ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ መልስ ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ፣ ይፈጥረው የነበረው አውሎ ንፋስ፣ ‹‹ኦሮሞን የከዳ የነፍጠኛ አገልጋይ መሆኑ በይፋ ተረጋገጠ…›› ወይም፣ ‹‹ዓብይ የሚመራው መንግሥት አማራ ጠልና ለኦሮሞ የሚያዳላ ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ ምን ይምጣ!…›› የሚል በሆነ ነበር፡፡ በዱሮ አቋም ረዥም እንቅልፍ (ሃይበርኔሽን) ውስጥ ካሉት የኦነግ አንጃዎች አንዱ በተዓምር ከእንቅልፉ ነቅቶ የኦሮሚያ ብልፅግናን ልቀላቀል ቢልና ቢቀላቀል ‹‹ለውጡ በብሔርተኛ ተጠልፏል›› ሲሉ የነበሩ ወገኖች፣ በሽፍንፍን የነበረው ሽርክና ወደ ቅልቅል ተሸጋገረ ለማለት ይመቻቸዋል፡፡ ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያሳረፈ ፓርቲም አገርን ለማዳን ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ግንባር መፍጠር ይገባል ቢልና ንግግር ቢሞካከር፣ ብሔርተኞች ፈንጠዝያ ውስጥ ይገባሉ፡፡ እንዲህ ያለ አውሎ ንፋስ እንዲፈጠር የሚሹት ቡድኖች ጆሮና ልባቸው ሁሌም ንቁ ነው፡፡ የሆነች ቅንጣት አግኝተው ይቅርና ያልሆነውን የሆነ ለማስመሰል 24 ሰዓት ይተጋሉ፡፡

በአጣዬና በአካባቢዎቹ ላይ የደረሰውን በግድያ፣ በቃጠሎና በማፈናቀል የደመቀ ጥቃትን በተመለከተ የሐዘን ስብራትን የሚገልጽ ይፋ ንግግርና መግለጫ ከማድረግ ዶ/ር ዓብይን የሸበበው፣ ይኼው ጣምራ ወጥመድ ይሆን ይሆናል፡፡ የመሪ ንግግር ድፍን ሐዘን ብቻ አይሆንም፣ የሆነ ማብራሪያ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ እዚያ ውስጥ ደግሞ አደገኛ የሽቦ ላይ ዕርምጃ አለች፡፡ የሐዘን ቀን ማወጅና ባንዲራ ዝቅ ማድረግ የሚሉ ነገርማ የሚፈጥረው ንፋስ እስከ መፈጥፈጥ ሊወስድ ይችላል፡፡ በሌላ ጎን፣ ‹‹መንግሥት/ዓብይ እንዴት የሐዘን መግለጫ አይሰጥም? ሕዝብን መጠበቅ ኃላፊነቱ ሆኖ እንዴት ይቅርታ አይጠይቅም? … ባንዲራ ዝቅ ማድረግና የሐዘን ቀን ማወጅ ለደረሰው የሕዝብ ጥቃት የሚያንስ ሆኖ ነው!?… ወዘተ›› የሚሉት ትዝብታዊ ቅሬታዎች የአንጀት የመሆናቸውን ያህል፣ ዓብይንና የፌዴራል መንግሥቱን በአድሏዊነትና በአማራ ጠልነት የማስጠርጠርና የማስጠመድ ፖለቲካዊ ሾኬም አለባቸው፡፡ ሾኬውም ሆነ የመሪ ዝምታው የብሔርተኛ ክፍልፋይነት እስረኛ የመሆን ገጽታዎች ናቸው፡፡

በተቀረ ዝምታን ምንም ዓይነት ሰበብ ተገቢ ሊያደርገው ባይችልም፣ በቅን አዕምሮ ለመረዳት ለፈቀደ ሰው ግን እስካሁን ስለዶ/ር ዓብይ የምናውቀው፣ ቢያንስ በጋብቻው አማካይነት የሚፈልቀው ብሔረሰብ ያልለየ የበጎ አድራጎት ተግባር ለምስክርነት አያንስም፡፡ በአስከፊው ጥቃት ውስጥ ‹‹የመንግሥት እጅ አለበት›› የሚለው ጥርጣሬም ስንዝር አያራምድም፣ አማራነትን ያካተተ ኢትዮጵያ አቀፍ ፓርቲ የያዘውን የመንግሥት ሥልጣን፣ በስንት አጣብቂኝ ውስጥ ምርጫ አሸንፎ ለማስቀጠል እየለፋ ሳለ፣ ግዙፍ የድጋፍ ኪሳራ የሚያስከትል ጥይት በራሱ ላይ ይተኩሳል ብሎ ማመንም፣ ማሳመንም የማይመስል ነው፡፡ በፓርቲውና በመንግሥት ውስጥ በሁለት ቢላ የሚበሉ ሳይኖሩ አይቀሩም የሚል ጥርጣሬን ግን ፍሬ ፈርስኪ አድርጎ መናቅ የዋህነት ነው፡፡ ዓብይ አህመድና የብልፅግና ፓርቲ አጣብቂኝ በበረታበት ጎዳና ውስጥ፣ የኅብረ ብሔራዊነቱንም የብሔርተኛነቱንም አዎንታዊ ሰበዞች አዋደው፣ የትኞቹንም ፅንፈኞች አልፎ ለመሄድ በሚያደርጉት ትግል ውስጥ ኅብረ ብሔራዊነትንና ብሔርተኝነትን የማምታታት ድጥና ፈተና እንደሚኖርበትም ግልጽ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም ያለችበት ከባድ ፈተና በቀጭን ሽቦ ላይ የመሄድ ያህል ጠንቃቃነትን መጠየቁን በደንብ ያስተዋለ ሰው፣ ዓብይ አህመድና የብልፅግ ፓርቲ ድጋፋቸውን በንፋስ ሳያስወስዱ ይህንን ምርጫ ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ሁለገብ ትግል በግለሰብና በቡድን የሥልጣን ጥማት አቅልሎ አይተረጉመውም፡፡

‹‹የሥልጣን ጉዳይ እንጂ ኢትዮጵያን ከማዳን ጋር ምን ሲያገናኘው!›› ብሎ የሚል የፖለቲካ ሊቅ ካለ፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ አሳማኝ ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባዋል፡፡ አንደኛ ከብልፅግና ውጪ በአሁኑ ደረጃ ያሉት ቡድኖች ከሞላ ጎደል ከቁጥቋጦነት ያላለፉ መሆናቸውን፣ ከብልፅግና ውጪ ፓርቲ ለመባል የሚበቃ ከአንድ ጣት ቁጥር እጅግም አለመዝለሉን (እዚያም ላይ ሁሉን ማኅበረሰብ አካላይ ተቀባይነት በማግኘት ረገድ የድርጅታዊ ሥርጭት ማነስ ያለ የመሆኑን ግምገማ) ፉርሽ የሚያደርግ ነገር ሊሰጠን ይገባል፡፡ ሁለተኛ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ብሔር ከፅንፍ ተፅዕኖ እያመለጠ ነው፡፡ ይህ ጉዞ ለኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚና ብርቱ ሰላምን ተቆናጦ የመቀጠል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዕድል በአሁኑ ደረጃ እየፈካ ያለው በብልፅግና ፓርቲ በኩል ብቻ ነው፡፡ ይህንን የምለው ብልፅግና የየክልል ብሔር ፓርቲዎችን አዋህዶ የፈጠረውን አቅም ብቻ መመዘኛ በማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በምርጫ ዘመቻውና ክርክሩ አገርንና ኦሮሞን የቀዘፈ (ቢያንስ በየቅጣጫው የርቀት ድጋፍ እያፈሰ ያለ) ተቀናቃኝ ፓርቲ አለማየቴንም ሚዛን ውስጥ አስገብቼ ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ መመረጥ አለመመረጥ ከኢትዮጵያ ዕጣ ጋር የተያያዘ ነው የሚያሰኘውም አንዱ ዋና ሰበዝ ይህ ነው፡፡ በአሁኑ ደረጃ ሌላ ፓርቲ ምርጫውን ቢያሸንፍ የኦሮሞን ትግል የፅንፈኞች የኋሊት ጉተታ አይገዳደረው ይሆን? የኢትዮጵያ መንገጫገጭስ ከምናልባትነት አልፎ አይደቀን ይሆን? ይህ ሥጋት በማስፈራሪያ ብልፅግናን የመጥቀም ብልጣ ብልጣነት ሳይሆን ኢትዮጵያን የማዳን ተግባር ሰቅዞ እንቅልፍ የነሳው የፖለቲካ ቡድን ሁሉ ለራሱ ሊያቀርብ የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ምናልባት ሊሆን የሚችል ሥጋት ከሆነ፣ ከዚሁ ምናልባት ጋር ተጓትቶ ከፓርቲና ከብሔር ወገናዊነት የመላቀቅና ለአገርና ለሙያ የመታመን ዕነፃ ውስጥ የገቡት የፀጥታ አውታራት በጅምር ደረጃቸው መደናገር ሊያገኛቸው ቢችልስ ብሎ ማሰብም አብሮ ብቅ ይላል፡፡ ይህንን ሥጋት ፉርሽ የሚያደርግ መልስ የሚኖረው የፖለቲካ ሊቅ የሚኖር አይመስለኝም፡፡

ብዙኃኑ በየአቅጣጫው የመረጠውና ኢትዮጵያን አስተባብሮ በድል የሚመራ መንግሥት የመቀዳጀቱ ፈተና በምርጫ ዓውድ በመፎካከር ውስጥ ብቻ ያለ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ከምርጫ ተሳትፎ ውጪ ምርጫውን ከሲታ አድርጎ የማዋደቅም ዝንባሌ ውስጥ ለውስጥ ሲላወስ ታዝበናል፡፡ በዚህ ዝንባሌ ውስጥ ተወዳድሮ የማሸነፍ ተስፋ የተመናመነ የሆነበትን የፖለቲካ ኪሳራ፣ ‹‹በአባላቶቼ ላይ የደረሰው እስራትና አፈና ለመወዳደር አያስችለኝም›› በሚል ምክንያት ሸፍኖ ማፈግፈግም አለ፡፡

በሌላ በኩል በሕግ ሰበብ ምርጫ ቦርድ ከምርጫ ውድድር ውጪ እንዳደረገ አድርጎ ማቅረብም ማፈግፈጊያ ሆኖ ሠርቷል፡፡ የዳውድ ኢብሳ አንጃ ከእነ ቀጄላ መርዳሳ አንጃ ጋር አንድ ላይ በጠቅላላ ጉባዔ አልቀመጥም ማለቱ፣ የኦነግን ስም እንደያዙ በድርጅት ለመቀጠል ባያስችል እንኳ፣ ስምን ቀየር አድርጎ የመወዳደር መንገድ ዝግ አልነበረም፡፡ ቀጄላ መርዳሳ በሰጧቸው የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቆች እንደተረዳነው ግን፣ የእነ ቀጄላ ቡድን ይህንን ማድረግ አልፈለገም፡፡ ምክንያቱም የኦነግን የትግል ቅርስና ዝና ለዳውድ ኢብሳ አሳልፎ መስጠት ስላልፈለገ፡፡ ከመጠሪያ ስምና ከዝና ውጪ በብሔር ትግላቸው በቅርስነት ጠብቀው ያቆዩትና ዛሬም የሚታገሉለት ዋና ዓላማ ደግሞ፣ ‹‹ኦሮሞ የራሱን ዕድል በራሱ ይወስን›› የሚል ነው፡፡ ኦሮሞ የኢትዮጵያ እምብርትና ወጋግራ መሆኑን አጢኖ በሁለገብ የኢኮኖሚ ዘርፎች የዳበረች ኢትዮጵያን የመገንባት ትግልን እየመራ ባለበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ‹‹ኦሮሞ ቢሻው በኢትዮጵያ ውስጥ፣ ቢሻው ከኢትዮጵያ ውጪ የመሆን የፖለቲካ ዕድሉን ይወስን›› የሚል ትርጉም ያለውን አሮጌ አቋም እያድበሰበሱ ዛሬም ሙጥኝ ማለት አረጋዊ እስረኛ መሆን ነው፡፡ ራስን በራስ ማሰር በቀጥታ ችግር አይሆን ይሆናል፡፡ የቡድን አሸናፊነትን ዕድል ባለማየትም ሆነ ማክተሚያ ባጣ ጥቃት ተስፋ ቆርጦ ምርጫውን ከማኩረፍ ባሻገር ሌሎች ለምርጫ እንዳይመዘገቡ ውስጥ ለውስጥ መጫን ግን መብት ነኪ ችግርነቱ አከራካሪ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር በማስፈራራት መልክ ተሞካክሮ ነበር (አድራጊው ባይታወቅም)፡፡ እንዲህ ያለውም ድርጊት ጫና አድራጊውንና ጫና የተሞከረበትን ሁሉ የሚነካ የካቴና ፈርጅ ነው፡፡

የእስረኝነቱ ብዛት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተነክቶ ሊፈነዳ የሚችለውን የተቀጣጣይ ፈንጂ ብዛትም ይጠቁማል፡፡ ከፊታችን ያለውን ምርጫ ለማሰናከል ከኩርፊያ አልፎ ትርምስንና ግጭቶችን ማባዛትም እንደ ታክቲክ ይሠራበታል፡፡ የዓብይን መንግሥት ከምንም የማያድን አድርጎ ተስፋ በቆረጠ ቁጣ ለማወራረድ ብዙ ነገር ተሠርቷል፡፡ ኦሮሞንና አማራን ለማላተም ከጭፍን ግድያ አንስቶ ብሔር ዘላፊ መፈክርን በብሶተኛ አፍ የማጉረስም ሸር ይሠራል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ትግል የኋሊት (ወደ ፅንፈኛ ብሔርተኝነት) ለመመለስ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም፡፡ ኢትዮጵያን አርዶ ቁራጭ አገሮች የመፍጠር ዕብደት ውስጥ ከተገባ ከራርሟል፡፡ እነዚህን በመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሳይነጋገሩ መደገፍ እንዳለ ሁሉ ሥውር ዳንቴልም አለ፡፡ መጋቢትን ይዞ እስከ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም. ተሻግሮ በነበረው የአማራ ክልል ቀውስ ውስጥ ብዙ ሥሌቶች ተሳትፈው ነበር፡፡ የመሬት ሽሚያ፣ ‹‹አማራ›› ክልልን የማመስና የመቦዳደስ፣ አማራና ኦሮሞን የማባላትና በግርግር ወደ ሱዳን የመሹለክ ሙከራ ሁሉ ነበር፡፡ ይህንን ለመረዳት ከመንግሥት ሚስጥራዊ መረጃ ማግኘትን አይጠይቅም፡፡

ራያና ወልቃይት ከሕወሓት መዳፍ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የቃላት ምልልስ ማገላበጥ፣ በ2013 ዓ.ም. መጋቢት መጨረሻና ሚያዝያ መጀመርያ ውስጥ በትግራይ ከአገር አራጁ የሕወሓት ቡድን ትራፊዎች ጋር ይካሄድ ከነበረው ባለ ብዙ ግንባር ውጊያ ጋር የሰሜን ሸዋው ቀውስ መግረር፣ መገጣጠሙንና ለቅማንት እታገላለሁ ባዩ የሕወሓት አሻንጉሊት ቡድን በዚያ ወቅት መፈራገጡን አንድ ላይ አገናዝቦ ማስተዋል በቂ ነው፡፡

‹‹የሚሴርብን የሴራ ብዛት፣ እግዚዎ!›› እያልን በሌሎች ላይ ጣት በመጠቆም፣ ዘልዛላ ጥፋተኝነታችንን ግን ልንደብቅ አንችልም፡፡ ተንኮለኞች ተደፍቶ ባገኙት ገመናችን ሠሩበት እንጂ መተት አልደገሙብንም፡፡ የኢትዮጵያ ኑሮ (በተለይ አወቅን፣ ተማርን በሚሉት ጥራዝ ነጠቅ ግሪሳዎች አካባቢ) ለአመል የነገር መረቅ የሚበቃው ከንቱ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የተለያየ የብሔረሰብ/የቋንቋ ባለታርጋ ሆኖ በማኅበራዊ ሚዲያ መወራከብ ተቅማጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኖ ድንገተኛ ጥልና ስድድብ ውስጥ መግባት እንኳ በሰላማችን ላይ ማጥወልወል የሚያደርስ ሆኗል፡፡ ውርክቡና ፀቡ የብሔርተኛ ወገንተኛነት አዚም ውስጥ የገባ ከሆነማ ጦሱ ብዙ ነው፡፡ ኑሯችን ይህንን ያህል ቆፍቋፋ መሆኑ እየታወቀ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲወራከቡ የነበሩ አወቅን ባይ የኦሮሚያና የአማራ ብልፅግና ሰዎች፣ በቴሌቪዥን ወገንተኛ ቃላት ሲወራወሩ የሰማናቸው የዚህና የዚያ ተቆርቋሪ ነን/ተወካይ ነን/ አስተዳዳሪ ነን ባይ ሰዎች ሁሉ ከከሚሴ እስከ አጣዬ ድረስ መለስ ቀለስ ሲል በቆየውና በኋላ እንዳይሆን በከፋው ቀውስ ውስጥ ድርሻ አላዋጣንም ሊሉ አይችሉም፡፡ ሁሉን ዕዳ በሸኔ/ባልታወቀ ታጣቂ ላይ ሲደፈድፉ የነበሩትም ሆኑ፣ ‹‹የተደራጀ የታጠቀ ኃይል አልመጣም የእርስ በርስ ግጭት ነው›› ብለው ሲያስተባብሉ የተሰሙት ሙሉውን እውነት አልነገሩንም፡፡ አግባብ ያላቸው መንግሥታዊ አካላት መዘዞችን ገና በጢሳቸው ደረጃ ለይተው የማክሸፊያ ሥራ አለመሥራታቸውም ያንገበግባል፡፡ መደረግ የሚገባው ሳይደረግ ቀርቶ፣ ጨለማ ልልበስ ያላለ ከበባ፣ ሥልታዊ የቦታ አያያዝና አጠቃቅ በተሳላበት መልክ፣ ቤት ከማቃጠል በፊት ንብረት ዘርፎ መጫን በተከናወነበት አኳኋን ከተሞችና መንደሮች ስለመውደማቸው መስማት ጆሮ ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ሙልጩን የቀረ ሰው የሚያደርገው ቢጠፋው፣ ‹‹ምን መንግሥት አለ!›› ብሎ ቢያማርር፣ መንግሥትን አስጠቃኝ ብሎ ቢጠረጥር ምን ሊገርም! ከሌላ የቀውስ ሥፍራ ሸሽቶ መጥቶ ሥራ ብጤ ከማቋቋሙ አመድ የሆነበት ሰውም፣ ‹‹ከዚህ ወዲያ ወዴት ልሽሽ›› የሚል ግራ መጋባት ውስጥ መውደቅ ያንሰው እንደሆን እንጂ አይበዛበትም፡፡ አንድ እናት፣ ‹‹የተረፍነው በሞቱት ቀናን! የሞቱት ተገላገሉ…›› በሚል ንግግራቸው ሁሉንም ጨርሰውታል፡፡ ግራ አጋቢውን ጭንቅ በደንብ ገልጸውታል፡፡ ተገን አልባነት ውስጥ መግባታቸውን ነግረውናል፡፡ በዚህም ስሜታቸው ክንድ ምላስ የምንዘረጋና ሃምሳና ስልሳ ፓርቲ ነን እያልን የምንጋፋ ቦትላኪዎች፣ ለሕዝብ ዋይታ መፍትሔና መፅናኛ መሆን ያቃተው የሞት ሞት ውስጥ መሆናችንን ነግረውናል፡፡ ‹‹በሞቱት ቀናን!›› በሚል ንግግራቸው ውስጥ የተንፀባረቀው ጥልቅ ሐዘንና ጭንቅ፣ አፈር ልሰው የተነሱትን እሳቸውን ይቅርና ከሩቅ ምላስ የምንዘረጋውንም ይቧጥጣል፡፡

ትልቁ ጥያቄ ግን ስሜቱ ቢጋባብንና ስሜቱን ብናራግብ፣ ስሜት ብቻውን መፍትሔ ይሆናል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በተቀዳሚ ደረጃ፣ ወደ ፈጣን ዕርዳታና መልሶ ወደ ማቋቋም ይወስደናል፡፡ ይህ በራሱ አዛላቂ ዕፎይታን ይዞ አይመጣም፡፡ ስለነገ እርግጠኛ ያለመሆን ሥጋት እንደምን ይቋረጣል? እየገደሉ መቅበር፣ እያፈናቀሉ ማቋቋም፣ አቋቁሞ መለስ ሲሉ ማፈናቀል እንደምን ይቋረጣል? የሚሉ ጥያቄዎች ሲወዘውዙን ይቆያሉ፡፡ ለጥያቄዎቹ መልስ የመፈለግ ጥረት ደግሞ ተባብሮ መፍትሔ ወደ መሆን አካባቢ ይመራናል፡፡ በመፍትሔዎች ሠፈር ውስጥ ስናማትር፣ ከፊታችን ያለውን ምርጫ ያለ ማኩረፍና ተጋግዞ የተዋጣ እንዲሆን የማድረግ ጉልህ ተግባር ተገሽሮ እናገኛለን፡፡ እዚያ ተግባር ውስጥ ደግሞ ሬት ሬት የሚል ጣዕም ሊኖራት የሚችል ነገር አለች፡፡ አገርን እንደ ተያያዘች ጠብቆ ወደፊት ለመውሰድ፣ በፓርቲ ደረጃ አቅም የሚሆነን የቱ ነው ብሎ ለማማረጥ ወዲህም ወዲያም ቢሉ አማራጭ ማጣት፣ ማለትም በቅሬታዎች ለሚርኮመኮሙበት ፓርቲ የምርጫ ድምፅን የመስጠት አጣብቂኝ፡፡ እኔ እዚህ ውስጥ ነኝ፡፡ የእኔ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሆኑ በርካታ ግለሰቦች (የፖለቲካ ቡድኖችም) እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡ በአሁኑ ደረጃ የገጠመንን አማራጭ የማጣት ሬት ወደ ጣፋጭነት ልንቀይረው የምንችለው፣ በቅሬታዎች ቆንጥር ውስጥ ያለውን ብሩህ ተስፋ በማስተዋልና ተባብሮ ለአገርና ለሕዝብ በመሥራት ነው፡፡

(ይህ ጽሑፍ ለኦሮሞና ለትግሬ ዘመዶቹ ታሪካዊ ጠላት እንደ ሆነ ተሥሎ ለ30 ዓመታት ያህል በጦስ ዶሮነት ሲጠቃ ለኖረው፣ ቻይነቱንም ለሰጠው አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ መታሰቢያ ይሁን፡፡)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...