Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት ለወቅታዊው የዋጋ ንረት መፍትሔ ይስጠን

ወቅታዊውን የዋጋ ንረት በተመለከተ የሚሰሙ ድምፆች በርክተዋል፡፡ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ይኼ ነው የሚባል መፍትሔ አላገኘም፡፡ በመሆኑም የገበያው የዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ ግሏል፡፡ ቀነሰ የሚባል ምርት ወይም ሸቀጣ ሸቀጥ ማግኘት ዘበት ሆኗል፡፡ እንዲያውም በቀናት ልዩነት ውስጥ ዋጋቸው የሚጨምር ምርቶች እየበዙ ነው፡፡ ከውጭ ይመጣል የሚባለውም ምርት ሆነ በአገር ውስጥ በቀላሉ ይገኛሉ የተባሉ ምርቶችን ተመጣጣኝ በሚባል ዋጋ ማግኘት ዘበት ሆኗል፡፡ ይህም የአገሪቱን የዋጋ ንረት አሁንም ከፍ እያለ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡

ከሁሉም በላይ የዋጋ ንረት በእጅጉ ከፍ ካለባቸው ምርቶች ውስጥ ምግብ ነክ በዋናነት ይቀመጣል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የአገሪቱን ወርኃዊና ዓመታዊ የዋጋ ንረት የሚመለክቱ አኃዛዊው መረጃዎች የሚያመለክቱትም፣ የምግብ የዋጋ ንረት ከሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች በተለየ ዋጋው መሰቀሉን ነው፡፡

ከምግብ ነክ ምርቶች ውስጥ ዋጋቸው የናረው በአብዛኛው በአገር ውስጥ የሚመረቱ ሆነው መገኘታቸው ጉዳዩን በተለየ እንዲታይ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ከውጭ የሚገቡ ምግብ ነክ ምርቶች አሁን ካለው የምንዛሪ ዋጋ ከፍ እያለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የዋጋ ለውጥ ቢደረግባቸው በተወሰነ ደረጃ የሚያግባባን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከውጭ የምናስመጣውና እዚሁ የምናመርታቸው ምርቶች ሳይቀሩ ከዚህ ቀደም ከሚታወቀው የዋጋ ጭማሪ በተለየ ከፍተኛ ዋጋ እየታከለባቸው ባልተቋረጠ የዋጋ ጭማሪ መቀጠላቸው እየታየ መፍትሔ አለመበጀቱ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በተለይ የዋጋ አጨማመሩ መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑና ለኑሮ ውድነት እንደ አንድ ምክንያት የሚቆጠረው የዋጋ ጭማሪ ምክንያቱ ምንድነው ብሎ ለመፈተሽና ለችግሩ መፍትሔ ለማበጀት አለመድከሙ ወይም ነገሩ እንደቀላል ታይቶ መታለፉ ሸማቹን እየተገዳደረ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪዎችም በተለያዩ አቅርቦቶች ላይ እየታዩ እንዲቀጥሉ በር ከፍቷል ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ ቀደም ይህ ነው በማይባል ምክንያት በተለያዩ ሰብል ምርቶችና ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶች ላይ እየተደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ አንድ ቦታ ላይ እንዲቆም ወይም ምርቶች ትክክለኛ የገበያ ዋጋ እንዲይዙ ባለመደረጉ ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

መንግሥት ይህንን ሥር እየሰደደ የመጣ የዋጋ ንረት ለመቀነስ ብሎም በዘፈቀደ የቀጠለውን የገበያ ሥርዓት መስመር ለማስያዝ እየተገበርኩ ነው ያለው አካሄድ ውጤት አለማምጣቱን ገበያው ያሳያል፡፡ ስለዚህ ለዋጋ ንረቱ መባባስ የመንግሥት መፍትሔ ውጤታማ አለመሆኑን ያሳያል፡፡

የጤፍ ዋጋ በዚህ ሁለትና ሦስት ዓመት በአንድ ኩንታል እስከ 1,500 ብር ጭማሪ በማሳየቱ አምስት ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ደረቅ እንጀራ እስከ 10 ብር እንዲሸጥ አስገድዷል፡፡ የዳቦ ነገርም በተመሳሳይ የሚሠራ ሲሆን ዋጋ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን በሦስት ብር የሚሸጠው አንድ ዳቦ መጠን ወርዶ ወርዶ አንድ ጉርሻ እስከ መሆን ደርሷል፡፡

ከሰሞኑ በገበያ ውስጥ የምናየው የተለየ ነገር ከትንሳዔ በዓል በኋላ የሥጋ ዋጋ እስከ ዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋ መጨመሩን ነው፡፡ በበዓል ሰበብ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ቀላል እንደማይሆን ቀድሞም ተሠግቶ የነበረ ሲሆን፣ የተፈራውም እየሆነ ነው፡፡

በተከታታይ ጤፍ ሲጨምር፣ ዘይት ዋጋው ጨመረ ሲባል በርበሬ ተወደደ እየተባለ ምግብ ቤቶች ያደረጉት የዋጋ ጭማሪም ታይቷል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ በየምግብ ቤቱ ሲገባ በሥጋ ጨመረ ሰበብ የተጨመረው ዋጋ ‹ኧረ ጎበዝ! ወዴት እየሄድን ነው› ያስብላል፡፡ የግብዓት ወጪ መጨመር ለዋጋ መጨመር ምክንያት መሆኑ ባይቀርም፣ እኛ አገር የግብይት ባህልና ዋጋ ጭማሪ የሚሠላው በዘፈቀደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪው የተጋነነ ሆኗል፡፡ በሥጋ ጨመረ ሰበብ በአንድ በርገር ላይ 50 ብር መጨመር የጤና አይሆንም፣ አስገራሚው ደግሞ ሥጋ ስለመጨመረ በሥጋ የሚዘጋጁ ምግቦች እሺ ይሁን ብንል፣ ሥጋ የሌለበት ፒዛም፣ ሽሮም፣ ሻይም ዋጋቸው መለወጡ ለምን? ያስብላል፡፡ እንዲህ ያሉ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመመለስ እጅግ ከባድ እንደሆነ የሚታመን ቢሆንም፣ ይህ ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበት ካልቻለ እየተፈጠረ ያለው የዋጋ ንረትን ለመቋቋም ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል፡፡

በተለይ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምግብ ነክ ምርቶች እንዲህ ለመወደዳቸው ምክንያት የሆኑ ነገሮች በአብዛኛው ሰው ሠራሽ በመሆናቸው ለዚሁ መፍትሔ መፈለግ ግድ ይላል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በተለይ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ያለውን የምርት አቅርቦት ማሳደግ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል የመጀመርያው ዕርምጃ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ የወሳኝ ምርቶችን ዋጋ ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር መዘርጋትና ቁጥጥር ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ አሁንም ሸማቹ የበለጠ እየተጎዳ፣ ገበያውም ቅጥ እያጣ ይጓዛልና የመፍትሔ ያለህ! እንላለን፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት