Friday, June 2, 2023

የምርጫው መራዘም የፈጠራቸው አዳዲስና ነባር ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ እንዲራዘም ከመወሰኑ አስቀድሞ፣ በርካታ ውዝግቦችንና ክርክሮችን ሲያስተናግድ የነበረ ሒደት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ከምርጫው መራዘም አስቀድሞ ፅንፍ የያዘ የፖለቲካ ምኅዳር ባለበትና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሊያባራ ያልቻለ የንፁኃን ዕልቂት ያስከተለ የፀጥታ ችግር ሳለ ምርጫ ማካሄድ የሚያዋጣ ጉዞ አይደለም ሲሉ የነበሩ ምርጫውን ማድረግ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ መስጠት የሚችል ቅቡል መንግሥት ከመመሥረት ይልቅ አባባሽ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዚህ ሥጋት ተግባራዊ ማሳያ ሊሆን በሚችል ሁናቴ በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት፣ እንዲሁም በብልፅግና ፓርቲና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል በተለይ የምርጫውን ሒደት አስመልክቶ ሲታይ የነበረው ውዝግብ እየጎላ መጥቶ አንዱ ለሌላው ዕውቅና መንፈጉ ነው፡፡ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ምርጫውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊያራዝም መወሰኑን በመቃወም፣ ክልላዊ ምርጫ በማድረግ ‹ቅቡልነት ያለው› መንግሥት አቋቁሜያለሁ ማለቱን ተከትሎ የተፈጠረው ውዝግብም እየተባባሰ መጥቶ ወደ ጦርነት አድጓል፡፡ ይኼም ጦርነት እስካሁን ከሰብዓዊ ቀውሱ በተጨማሪ አገሪቱን በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በንብረት፣ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ ዘርፎች ዋጋ ያስከፈለና እያስከፈለም ያለ ነው፡፡

ነገር ግን ምርጫው ባልተጠበቀው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሳቢያ ከመራዘሙ አስቀድሞ ይፋ ተደርጎ የነበረው የምርጫ ሰሌዳ የድምፅ መስጫው ቀን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲሆን በማድረጉ ምክንያት፣ በተለያዩ አካላት ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ ይታወሳል፡፡ አገሪቱ ባለባት የፖለቲካ ምስቅልቅል ሳቢያ ምርጫን ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት ብሔራዊ ውይይት ይቅደም እያሉ ሲከራከሩ ከነበሩትና አሁን ከፈረሱት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና ከኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ሥጋቶች በተጨማሪ፣ ምርጫው የሚደረግበት ጊዜ የክረምት ወቅት በመሆኑ ሳቢያ የምርጫ ዝግጅቶችን ለማከናወንም ሆነ የምርጫ ቀን ድምፅ ለመስጠት አዳጋች ይሆናል ሲሉ ሞግተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ በአንዳንድ ሥፍራዎች በሥራ ላይ ስለሚሆንና በመሠረተ ልማት ዕጦት ሳቢያም ከምርጫ ጣቢያዎች ከመድረስ ስለሚቸገር፣ በነሐሴ ምርጫ ማድረግ አዋጪ አይደለም ሲሉ ነበር፡፡ ይኼ ሥጋት ለመራጮች ብቻም ሳይሆን ለቦርዱም የሚሠራ ሲሆን፣ በክረምት የሚሞሉ ወንዞችን ለመሻገርና ጭቃማ የገጠር መንገዶችን አልፎ የምርጫ ቁሳቁስ ለማሠራጨትና ለማስመረጥ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ዕሙን ነው፡፡

በዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫ ቦርድም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ ዓመት የዝግጅትና የዕፎይታ ጊዜ ማግኘት ችለዋል፡፡

ምርጫው መራዘሙን ተከትሎ የቫይረሱን ባህሪ ተከታትለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ክብካቤ ኢንስቲትዩት ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡ ምርጫው እንዲከናወን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቫይረሱ ባህሪን በተሻለ ተረድቻለሁ በማለት ለመከላከል የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች ከተደረጉ፣ ምርጫውን ማከናወን ይቻላል የሚል ምክረ ሐሳብ በማቅረቡ ቦርዱ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት እንዲያደርግ የታዘዘው በመስከረም ወር አጋማሽ 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ታኅሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲሱን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ሲያደርግ፣ በዕለቱ የታደሙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በሁለት ጉዳዮች ሳቢያ ያስጨበጨበ ነበር፡፡ የመጀመርያው ምክንያት ምርጫው አስቀድሞ የነበረው መርሐ ግብር በዝናብ ወቅት በመሆኑ ሳቢያ፣ ለምርጫ ዝግጅትና ሒደት አዳጋች ይሆናል በሚል ሲሰማ ለነበረው ሥጋት ምላሽ የሰጠ፣ ካሁን ቀደም ሲደረጉ የነበሩ ምርጫዎች ሲደረጉበት ወደነበረው ግንቦት ወር የመጣ በመሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ወቅት በታየው የፊርማ ማጣራት ውጣ ውረድ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዕጩዎቻቸው የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንዳይጠበቅባቸው ቦርዱ ለፓርላማው ጥያቄ ማቅረቡ መገለጹ ነበር፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ቀን እንዲሆን የተቆረጠለት ስድስተኛው ምርጫ ከፍ ያለ የመራጮች ቁጥር ሊኖርበት እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ ቦርዱም 50 ሚሊዮን መራጮችን በመመዝገብ ካሁን ቀደም ከነበረው የመራጮች ብዛት ከፍ ያለ ሕዝብ እንዲመርጥ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበር፡፡

ሆኖም በምርጫ መርሐ ግብሩ ላይ የተመለከቱት ተግባራት በጊዜያቸው እንዳይከናወኑ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲገጥሙ ቆይተው፣ በስተመጨረሻም የድምፅ መስጫ ቀን እንዲራዘም አድርገዋል፡፡ የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያዎችን ለማደራጀት የሚያስችል ትብብር ከክልሎች ማግኘት ባለመቻሉ፣ እነዚህ ጽሕፈት ቤቶች በጊዜያቸው እንዲቋቋሙ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በተጨማሪም በዚህ መዘግየት ምክንያት የዕጩዎች ምዝገባ በሁለት መርሐ ግብሮች በ22 ቀናት እንዲከናወኑ ተደርጓል፡፡

ከክልሎችም ሆነ ከፌዴራል መንግሥቱ ወገን ለቦርዱ መደረግ የነበረባቸው ትብብሮች ባለመደረጋቸው ሳቢያ፣ ቦርዱ እየተቸገረ እንዳለና ይኼንን በተመለከተም ቅሬታ እንዳላቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ካሁን ቀደም ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀው ነበር፡፡ ስለዚህም ከዚህ ምርጫ ሒደት መወሰድ ያለበት ትምህርት ክልሎችም ሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግሥት አደረጃጀቶች የምርጫ ዝግጅት በቦርዱ ሲጀመር አብረው መጀመር እንዳለባቸው፣ ይኼንንም ማድረግ እንዲቻል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ሊያስፈልግ እንደሚችል ጠቁመው ነበር፡፡

በዚህ እየተገፋፉ በቆዩ የምርጫ ሰሌዳ ተግባራትና የመራጮች ምዝገባም በተደጋጋሚ በመራዘሙ ምክንያትና በፀጥታ ችግሮች ሳቢያ እስከ ዓርብ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ የነበረባቸው አካባቢዎች ነበሩ፡፡ ከፀጥታ ችግር ውጪ አነስተኛ የመራጮች ቁጥር በታየባቸው የምርጫ ክልሎች ሁለት ጊዜ የመራጮች ምዝገባን በማራዘም መራጮች እንዲመዘገቡ ለማድረግ ታቅዶ ነበር፡፡ ሆኖም በ46,088 ጣቢያዎች በተደረገ የመራጮች ምዝገባ 36,345,444 መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በጊዜያዊነት ይፋ ካደረገው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሆኖም እስካሁን የመራጮች ምዝገባ ያልጀመሩና ዘግይተው ለመመዝገብ የተገደዱ የምርጫ ክልሎች በመኖራቸው ምክንያት፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ እንዲሰጥበት በተወሰነው ምርጫ ላይ አይሳተፉም፡፡ እነዚህም አራቱ የወለጋ ዞኖች (ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋና ሆሮጉዱሩ ወለጋ)፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከማሺና መተከል ዞኖች፣ እንዲሁም የአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ሲሆኑ፣ እስካሁን በፀጥታ ችግሮች ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ አልጀመሩም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአፋር ክልልና የሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተው ነው የመራጮች ምዝገባ እያከናወኑ ያሉት፡፡ እንዲሁም በሶማሌ ክልል የሚገኙ ሰባት የምርጫ ክልሎች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ቅሬታዎች የቀረቡባቸው በመሆናቸው ምክንያት፣ ሲያከናውኑ የነበሩትን የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ አቋርጠው የቦርዱን ውሳኔ እንዲጠብቁ ተደርገዋል፡፡

ምንም እንኳን ቦርዱ ምርጫውን በሁለት ሳምንታት ለማራዘም ያለውን ዕቅድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርግ በጭብጨባ የታጀበ ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ይፋ ባደረገው የምርጫ መርሐ ግብር ተገዝቶ ሊያከናውናቸው ባልቻላቸው ተግባራት ሳቢያ የገንዘብና የምርጫ ዘመቻ መዛባት ችግር እንደ ገጠማቸው የሚናገሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልታጡም፡፡ የኢዜማ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዘላለም ወርቃገኘው ባለፈው ሳምንት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በምርጫው ይደረጋሉ ተብለው የታቀዱ ተግባራት ጊዜውን ጠብቀው ባለመከናወናቸው ምክንያት፣ የምርጫ ዘመቻ መርሐ ግብራቸውን በማዛባት የገንዘብ ብክነት እንዲኖር አድርጓል ብለው ነበር፡፡

ነገር ግን ከሐሙስ ግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. መግለጫ ጎን ለሪፖርተር የተናገሩት የምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ፣ ፓርቲዎች እንዲህ ያለ ቅሬታ አላቀረቡም ብለዋል፡፡ በምርጫ ሰሌዳው መዛባት ሳቢያ ለሚያጋጥማቸው ተጨማሪ ወጪ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሰጠው ገንዘብ ላይም ተጨማሪ ድጎማ ለማድረግ በጀት የለም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ቦርዱ በተቀረው ጊዜ 106,345 የምርጫ አስፈጻሚዎችን በመቅጠር በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚሠሩ አስፈጻሚዎች ቁጥር ወደ አምስት እንዲያድግ እንደሚደረግ ሶልያና የተናገሩ ሲሆን፣ ይህም እስካሁን የመራጮች ምዝገባ ሲያካሂድ የነበሩትን አጠቃላይ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ቁጥር ከ138,655 ወደ 245,000 ያደርሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ኅትመት ተጠናቅቆ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባና ሥርጫቱም በአራት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያስታወቁት አማካሪዋ፣ ለዚህም የሚያግዝ የትራንስፖርት ዕቅድ አዘጋጅተው ለመንግሥት ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እንደ አስፈላጊነቱ የአየር፣ የየብስ፣ የውኃ ላይና የጋማ ከብት የትራንስፖርት ዘዴዎች በመጠቀም የምርጫ ቀን ቁሳቁሶች እንደሚሠራጩ አገልጸዋል፡፡

ይሁንና የዝናብ ወቅት እያየለ የሚመጣበት ጊዜ ላይ ምርጫ ማድረጉ ራሱን የቻለ አዳጋች ሁኔታ እንደሚፈጥር አልሸሸጉም፡፡

‹‹ክረምት ለእኛ ትልቁ ተግዳሮት ነው፡፡ ካሁን ቀደም በተሰረዘው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይም ሲነሳ የነበረ ጉዳይ ነው፤›› በማለት፣ በቦርዱ ላይ ተጨማሪ ጫናዎች ይኖራሉ ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚከሰት መሆኑንና ይኼም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው በኦሮሚያ ክልል ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃምና የባህር ዳር ዙሪያ፣ በደቡብ ክልል፣ በሲዳማ ክልል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ፣ በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍና የመሳሰሉ ተፅዕኖዎች ይኖራሉ ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -