መንግሥት ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ባወጣው ጨረታ ለመወዳደር ፍላጎት የነበረው ግዙፉ የፈረንሣይ ኩባንያ፣ በመጨረሻው ሰዓት በጨረታው ላለመሳተፍ የወሰነው፣ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ በሚወጣው ጨረታ ለመሳተፍ በመፈለጉ እንደሆነ ተጠቆመ።
መንግሥት ባወጣው ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ጨረታ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን ከገለጹ 12 ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የፈረንሣዩ ኩባንያ፣ ለሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃዶች በወጣው ጨረታ ላይ ብቁ ተወዳዳሪ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ሐሳቡን እንደቀየረ ለማወቅ ተችሏል።
ለሁለቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃዶች በሚወጣው ጨረታ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን ካሳወቁት ኩባንያዎች መካከል ሁለት ኩባንያዎች ብቻ በጨረታው የተካፈሉ ሲሆን፣ እነዚህም ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ በሚል ጥላ ሥር እንደ አንድ ድርጅት የተወዳደሩት ኩባንያዎችና የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ናቸው።
ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ በተሰኘው ጥምረት ውስጥ የተካተቱት ድርጅቶች፣ ቮዳ ፎን፣ ፎዳ ኮም፣ ሳፋሪ ኮም፣ ሶሚቶም የተባለ የጃፓን ኩባንያና እነዚህ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሚያስችላቸውን ፋይናንስ ያቀረቡት የእንግሊዝና የአሜሪካ መንግሥት የተቋማት (ሲዲሲና አይኤፍዴሲ) ናቸው።
ከቻይና መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያገኝ የሚነገርለት የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ለብቻው የተወዳደረ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) ሰሞኑን በተካሄደው የባለድርሻ አካላት ግምገማ ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከላይ የተገለጹት ኩባንያዎች ለሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች የቀረቡ ብቸኛ ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ፣ ከፈረንሣዩ ኦሬንጅ በስተቀር ሌሎቹ ፍላጎታቸውን የገለጹ ኩባንያዎች፣ የጨረታውን መሥፈርት እንደማያሟሉ ተገንዝበው ሳይሳተፉ መቅረታቸው ተነግሯል።
የፈረንሣዩ ኦሬንጅ ኩባንያ ግን ለሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች ከቀረቡት ሁለቱ ኩባንያዎች የተሻለ አቅምና የጨረታውን መሥፈርቶች በማሟላት ረገድም ከሁለቱ ኩባንያዎች የተሻለ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ላይ ላለመሳተፍ መወሰኑ ታውቋል። ኦሬንጅ የተባለው ኩባንያ ለውድድር ከቀረቡት ሁለቱ ኩባንያዎች በተሻለ ሁኔታ ዓመታዊ የገቢ መጠንና ልምድ ቢኖረውም የኢትዮ ቴሌኮም የ40 በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ሲቀርብ ለመሳተፍ በመምረጥ ለአዲሶቹ የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ከመሳተፍ መቆጠቡን ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) ገልጸዋል።
ኦሬንጅ ቴሌኮም ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮ ቴሌኮምን በማኔጅመንት ኮንትራት ለሁለት ዓመታት በማስተዳደር ተቋሙ አሁን ለደረሰበት የለውጥ ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ቢሮውን የከፈተ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የአይሲቲ ማዕከልም የምርመርና የሥልጠና ማዕከል አቋቁሟል።
እንደምንጮቹ ገለጻ ከሆነ ለአንደኛው የቴሌኮም ፈቃድ የተወዳደረው ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ የተባለው የኩባንያዎች ስብስብ ያቀረበው የክፍያ መጠን ኤምቲኤን የተባለው ኩባንያ ካቀረበው የክፍያ መጠን በእጅጉ የሚበልጥ በመሆኑ፣ መንግሥት ዝቅተኛ ክፍያ የቀረበበትን የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ሊሰርዘው እንደሚችል ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ጨረታው ቻይናን ከኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለማስወጣት አሜሪካ ከፍተኛ ጥረት ያደረገችበት አስብሎታል። ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ ለተባለው ስብስብ የአሜሪካ መንግሥት 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ያቀረበ ሲሆን፣ ከብድሩ ጋር ተያይዞ በተቀመጠው ግዴታ ምክንያት ጥምረቱ ከቻይና ኩባንያዎች የቴሌኮም መሣሪያዎችን መግዛት አይችልም።
የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ጨረታ እንደሚወጣም ታውቋል።