Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእነ አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ላይ ሆነው ዕጩ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸው ውሳኔ...

እነ አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ላይ ሆነው ዕጩ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸው ውሳኔ ተሰጠ

ቀን:

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸው በጠፋ፣ አካላቸው በጎደለና በወደመ ንብረት ተጠርጥረው የተከሰሱት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብና ሥዩም፣ ወ/ሮ አስካለ ደምሌ በእስር ላይ ሆነው ዕጩ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸው ውሳኔ በሰበር ችሎት ተሰጠ፡፡

ውሳኔውን የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡

በተከሳሾቹ ላይ የተሰጠው ውሳኔ በከፍተኛ አመራርነት ይመሩት የነበረው ባልደራስ ለእውነተኛ ፓርቲ (ባልደራስ) በዕጩነት እንዲመዘገቡለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ጥያቄ፣ ‹‹በሕግ ከለላ ሥር ስለሆኑ በዕጩነት መመዝገብ አይችሉም፤›› በማለት ቦርዱ ውድቅ በማድረጉ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ያደረገው ክርክር ተቀባይነት በማግኘቱ ነው፡፡

የፓርቲው የሕግና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ዓለም አቀፍ ሕግጋትም ሆኑ የምርጫ ሕጉ በሕግ ከለላ ሥር ያሉ ሰዎች በዕጩነት እንዳይመዘገቡ የሚከለክል ድንጋጌ የለም፡፡ በመሆኑም ፓርቲው አራቱን ከፍተኛ አመራሮች እንዲመዘገቡ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቢቀርብም፣ በሕግ ክልከላ ያልተጣለበትን መብት በመጣስ እንደማይመዘገቡ ውሳኔ ላይ በመድረሱ፣ በይግባኝ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሄዳቸውን አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ድንጋጌ ላይ ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ አንድ ዜጋ የመምረጥ መብቱ በሕግና በፍርድ ቤት ውሳኔ ካልተገፈፈ በስተቀር በዕጩነት መቅረብ እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ፓርቲው ይህንንም የመከራከሪያ ሐሳብ አድርጎ ቢከራከርም፣ ቦርዱ ሊቀበለው እንዳልቻለ አቶ ሔኖክ ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን በይግባኝ ያየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በማፅናት፣ የፓርቲውን መከራከሪያ ሐሳብ ውድቅ እንዳደረገውም አስታውሰዋል፡፡   

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች፣ በሕገ መንግሥቱ የተከሰሱ ሰዎችን ንፁህ ሆነው የመገመት መብት (Presumption of Innocence) የሚጎዳና ሕጉን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ በመሆኑ፣ አራቱም ተከሳሾች ላይ የተሰጠው ውሳኔ ተሽሮ በዕጩነት እንዲመዘገቡ እንዲወሰንለት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ማቅረቡን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ ለሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ፣ ፓርቲው በዕጩነት እንዲመዘገቡ ያቀረባቸው ግለሰቦች ዋስትና ተከልክለው በእስር ላይ መሆናቸውን፣ በምርጫ ቅስቀሳና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ በመገኘት ከሚመርጣቸው ሕዝብ ጋር ሊገናኙ አለመቻላቸውን በመገንዘብ፣ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍ እንዳልሆነ ማስረዳቱንና የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔም የመጨረሻ መሆኑን በመግለጽ መከራከሩን አቶ ሔኖክ ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾቹ በእስር ላይ እያሉ ቢመረጡ እንኳን የመረጣቸውን ሕዝብ ማገልገል ስለማይችሉ፣ ይግባኝ መባሉ ተገቢ እንዳልሆነም መከራከሩን አክለዋል፡፡

ፓርቲው በበኩሉ ባደረገው ክርክር ቦርዱ ተከሳሾቹ ተመዝግበው ቢመረጡ እንኳን በእስር ቤት ሆነው የመረጣቸውን ሕዝብ ማገልገል እንደማይችሉ መናገሩ፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጋፋት መሆኑን እንዳስረዳ አቶ ሔኖክ ገልጸዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ሰበር ሰሚ ችሎት፣ የዜጎች መምረጥም ሆነ መመረጥ መብት የሚነፈገው በፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም በሕግ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም እነ አቶ እስክንድር (አራት ሰዎች) በሕግ የተላለፈባቸው ውሳኔ ስለሌለ በዕጩነት መመዝገብ እንደሚችሉ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል፡፡

የሕግ መሠረት በሌለበት ሁኔታ ምርጫ ቦርድ የፓርቲ አባላትን በዕጩነት መወዳደር እንዳይችሉ ማድረግ እንደማይችል በመግለጽ፣ በፓርቲው ዕጩዎች ላይ የተሰጠውን ውሳኔ መሻሩን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ባልደራስ አራቱን ዕጩዎቹን ማስዝገብ እንደሚችልና ቦርዱም እንዲመዘግብ ትዕዛዝ መስጠቱን አክለዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...