ለወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ክስ በቀረበባቸው የሕወሓት አመራሮች ላይ ምስክር ለመሆን ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር የገቡትን ስምምነት በማፍረሳቸው በሕግ አግባብ ያገኙት የምስክርነት ጥበቃ እንዲቋረጥና በተጠረጠሩበት ወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው ዓቃቤ ሕግ ወሰነ።
ሪፖርተር ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምንጮቹ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ወ/ሮ ኬሪያ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር ስምምነት አድርገው በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 መሠረት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተወስኖ በዚሁ አግባብ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር ተለቀው ነበር።
ይኼንንም ተከትሎ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ተጠርጣሪዋ ምስክር ለመሆን ፍቃደኛ ሆነው በገቡት ስምምነት መሠረት ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን በነፃ ፈቃዳቸው በጽሑፍና በቪድዮ ካሜራ እየተቀረጹ ማስመዝገባቸውን ምንጫችን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ምስክሯ በገቡት ስምምነት መሠረት ለምርመራ ቡድኑ በፈቃዳቸው የሰጡትን ምስክርነት ለፍርድ ቤት እንዲሰጡ ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ምስክር ለመሆን ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 11 መሠረት የጥበቃ ተጠቃሚ የሆነ ሰው ስምምነቱን በማክበር በፍርድ ቤት ምስክር የመሆን ግዴታን የሚጥል በመሆኑ እንዲሁም በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 11 ሥር ተደንግጎ እንደሚገኘው የጥበቃ ተጠቃሚው ግዴታውን ሳያከብር የቀረ እንደሆነ የጥበቃ ስምምነት ውሉ እንደሚቋረጥ የተደነገገ በመሆኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከምስክሯ ጋር የነበረውን የምስክር ጥበቃ ስምምነት ማቋረጡን ምንጫችን ገልጸዋል።
‹‹ወ/ሮ ኬርያ ምስክር ለመሆን ስምምነት ገብተው ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው የጥበቃ ተጠቃሚ ከሆኑ በኋላ ሐሳባቸውን በመቀየር ስምምነቱን ስለጣሱ የምስክርነት ጥበቃው ተቋርጧል፣ ተጠርጣሪዋ ምስክር የመሆን ሐሳባቸውን የተው በመሆኑም መጀመርያ በተጠረጠሩበት ወንጀል ክስ የሚቀርብባቸው ይሆናል፤›› ብለዋል።
በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ወይም ክስ ቀርቦበት በክስ ክርክር ሒደት ላይ ያለ ሰው ስለቀረበው ክስና ሁኔታዎች ጉዳይ የሚታመን ዝርዝር መግለጫና ጥቆማ ከሰጠ ከተጠርጣሪው ወይም ከተከሳሹ ጋር በመስማማት ክሱን መተው ወይም ምስክር በማድረግ የሕዝብን ጥቅም ማስከበር በሕግ የተፈቀደ አሠራር መሆኑን የገለጹት ምንጫችን ይህ አሠራርም የቆየና በተለያዩ አገሮች የሕግ ሥርዓት የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ መሠረት የምስክር ጥበቃ የተሰጣቸው ወ/ሮ ኬሪያ በርካታ ጠቃሚ መረጃና ማስረጃዎችን እጃቸውን ከሰጡበት ቀን ጀምሮ በፍላጎታቸው ለምርመራ ቡድኑ መስጠታቸውን፣ ምስክር ለመሆን መስማማታቸውን እንዲሁም በራሳቸው ፍላጎት እጅ መስጠታቸውን ከግምት በማስገባት የምስክርነት ጥበቃ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።