Thursday, December 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት በዲፕሎማሲ የታሸ ብልኃት ነው!

አገር ችግር ሲገጥማት ትዕግሥት፣ ብስለት፣ ብልኃትና ፅናት መጎናፀፍ ተገቢ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየ ያለው ጣልቃ ገብነትና ሰሞኑን ያስተላለፈው የጭካኔ ውሳኔ በጣም አሳዛኝ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን በሳልና ብልኃተኛ መሆን ይጠቅማል፡፡ ውሳኔው የሁለቱን አገሮች ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ የተሻገረ ግንኙነትን ከማሻከር አልፎ፣ እስከ ወዲያኛው ዓይንህን ለአፈር የሚያሰኝ ጠላትነት እንዳያፈራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ንግግሮችም ሆኑ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በዲፕሎማሲ የተሞረዱና ብልኃት የታከለባቸው መሆን አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጭካኔ ፖሊሲ ለመድፈር የተነሳን የውጭ ኃይል፣ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት በሚመጥኑ በሳል ዕርምጃዎች ማስታገስ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ ከጀግንነታቸው በተጨማሪ ብልህና አስተዋይ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ሕዝባችን በተለያዩ ዘመናት በተነሱ ጨቋኝ ገዥዎች አፈና ውስጥ ሆኖ እንኳን አገሩን ለባዕዳን አሳልፎ ሳይሰጥ፣ በደሉንና መከራውን ችሎ አገሩን በጋራ ከጠላት ሲከላከል ኖሯል፡፡ አሁንም ይህ ዓይነቱ አኩሪ ገድል በዚህ ትውልድ መቀጠል አለበት፡፡ የጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የተከተለው የጭካኔ ፖሊሲ የሁለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሻክር፣ ለአሜሪካም ቢሆን ጥቅሟን የማያስከብርና በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ጂኦ ፖለቲካዊ አሠላለፍ ሊያስከትል እንደሚችል በጥሞና በማስገንዘብ ለማለዘብ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ አሜሪካ የምታራምደው ኃላፊነት የጎደለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በቀጣናው ለረጅም ዓመታት አጋሯ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር እንዳያቆራርጣት በጨዋነት መነገር አለበት፡፡ በቁጣና በደመ ሞቃትነት መፈክር ማስተጋባት ሳይሆን፣ ጥበብ በተካነ ዲፕሎማሲ ውጥረትን ማርገብ ተገቢ ነው፡፡

እስኪ አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሳን እንነጋገርባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ የውጭ ኃይሎች እየተፈተነች መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ምክንያት ግብፅና ሱዳን ግንባር ፈጥረው ፈተና ደቅነዋል፡፡ ሱዳን በግብፅ አይዞሽ ባይነት የኢትዮጵያን ድንበር ወርራ ተጨማሪ መሬት ይዛለች፡፡ በትግራይ ክልል በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት በመድረሱ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በተደጋጋሚ መግለጫ ከማውጣታቸውም በላይ፣ አሜሪካ ከቪዛ ክልከላ እስከ የኢኮኖሚና የወታደራዊ ድጋፍ የዕቀባ ዕርምጃ እንደምትወስድ እያስታወቀች ነው፡፡ አሜሪካ በውስጥ ጉዳይ ቀጥታ ጣልቃ በመግባትም ትዕዛዝ እየሰጠች ነው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ሳቢያ ወዳጇን ግብፅን ለማስደሰት ስትል የኢትዮጵያን እጅ እየጠመዘዘች ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ምክንያታዊ ሆነው የውስጥ ችግሮቻቸውን በመፍታት፣ ፀንቶ የኖረው አንድነት እንዳይናጋ መተባበር የግድ ይላቸዋል፡፡ በተጨማሪም የአሜሪካ የተጣመመ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲስተካከል መረባረብ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ብስለት የጎደላቸው ፖለቲከኞች የሚያራግቡትን አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ዘወር በማድረግ፣ ለአገር የሚጠቅሙ በሳል ኢትዮጵያዊያንን ግንባር ቀደም አድርጎ መነጋገር ይቅደም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በብልኃት የታጀበ ዲፕሎማሲ ነው፡፡

እንደሚታወቀው አጋጣሚውን የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዳይስማሙ ያሴራሉ፡፡ ለዘመናት የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ተጋብተው የተዋለዱትን ኢትዮጵያውያን በማጣላት፣ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመቋቋም አቅም የሌላት ኢትዮጵያ እንድትኖር ይፈልጋሉ፡፡ ከአንድ ማዕድ እየተቋደሱ የሚበሉትን፣ በደስታም ሆነ በመከራ የማይለያዩትን፣ እምነታቸውን ይዘው ለአገራቸው አንድነት በጋራ የሚቆሙትን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞችመለያየት ሐሰተኛ ወሬዎችን በስፋት ያሠራጫሉ፡፡ አገራቸውን ከጠላት ሲጠብቁ የኖሩ በርካታ ትውልዶች በክብር አስረክበው ያለፉዋቸውን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ለመናድ፣ በተለይ ወጣቱን ትውልድ በሥነ ምግባርና በሞራል የዘቀጠ እንዲሆን ገንዘብ አምላኪ ያደርጉታል፡፡ ለዓመታት ሲደረግ የነበረው አሳዛኝ ድርጊት ይኸው ነበር፡፡ በጠላት ፊት ያለ መንበርከክ ትልቅ የሞራል ልዕልና የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንበርከክ የሚችሉት፣ ለዘመናት የገነባውን ኢትዮጵያዊነት በማራከስና ትውልዱንም ተስፋ ቢስ በማድረግ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊያን መንቃት አለባቸው፡፡ በስሜት ከመነዳት በመላቀቅ ምክንያታዊ መሆን የግድ ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም በመመካከር ብልኃት መፈለግ ያዋጣል፡፡

በፖለቲከኞች መካከል ሊኖር የሚገባው ልዩነት ጤናማ ካልሆነ ጦሱ ለአገር ይተርፋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በወገኖቻችን ላይ የደረሱትን አረመኔያዊ የግፍ ግድያዎች በአንድነት ቆሞ ከማውገዝ ይልቅ፣ ለጠላት በር የሚከፍት ድርጊት እየተፈጸመ ለሐዘንም ብሔርና እምነት እንዲመረጥ መደረጉ የሚጎዳው አገርን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን ለማፋጀት የተወጠነው ዕቅድ በፖለቲከኞች ዘንድ በብስለት ሊስተዋል ባለመቻሉ፣ መርጦ ማልቀስና ማዘን ማንኛውም ዓይነት ስያሜ ቢሰጠውም በጊዜ ካልታረመ አደጋ አለው፡፡ አደጋው ኢትዮጵያዊነትን በጠላት ፊት ማንበርከክ ነው፡፡ ከሥልጣን በላይ የሆነችው ታላቅ አገርና ይህ ጨዋ ሕዝብ መከበር አለባቸው፡፡ኢትዮጵያዊነትን ታላቅ ምሥል ለመጣል የሚደረገውን ሴራ ማምከን ተገቢ ነው፡፡ በጠላት ፊት ትዕግሥት ማጣት ፈተና ያመጣል፡፡ አገርንና ሕዝብን ያንበረክካል፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች ዙሪያውን እየከበቡ ሲያስፈራሩና ማዕቀብ ሲጥሉ፣ አንድ መሆን አለመቻል ከባድ ጦስ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ምክንያታዊ ሆነው ሲተባበሩ ማንም አይደፍራቸውም፡፡ እያንዳንዱን ዕርምጃቸውን በጥንቃቄና በብልኃት ሲያደርጉ፣ ከማናቸውም ዓይነት ሴራ አገራቸውን ለመከላከል አያዳግታቸውም፡፡ ጥንቃቄና ብልኃት ሴራዎችን ለመበጣጠስ ያግዛሉ፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ እንድትዳከም ያደረጉ በርካታ አስከፊ ድርጊቶች እንደ ዋዛ መታየት የለባቸውም፣ ትምህርት ሊቀሰምባቸው ይገባል፡፡ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አደገኛ ክስተቶች ሲያጋጥሙ የተጠና አካሄድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለክስተቶቹም የሚሰጣቸው ምላሾች የአገርን ጥቅምና የሕዝቡን ዘለቄታዊ ፍላጎት እንዲያማክሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ቁጣን የሚቀሰቅሱ ችግሮች ሲያጋጥሙ መንግሥት ባለበት ኃላፊነትና ግዴታ መሠረት፣ኢትዮጵያን ጥቅምና ደኅንነት የሚያስከብር ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ የሚያወጣቸው መግለጫዎችም ሆኑ የተለያዩ መልዕክቶቹ በዚህ መንፈስ መቃኘት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ አንጋፋ አገር ስለሆነች፣ በመሪዎችም ሆነ በፖለቲከኞች የሚደረጉ ንግግሮች የአገርን ሉዓላዊነት በጥንካሬ የሚያስከብሩና የማያሳፍሩ መሆን አለባቸው፡፡ በስሜት ከታጀቡ ንግግሮች ይልቅ ብልኃትና ብልጠት የታከለባቸው ንግግሮች ይጠቅማሉ፡፡ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመድፈር እንዳያስቡም ይረዳሉ፡፡ ከዚያ ውጪ የደም ፍላትና የእልህ አቋም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ በዲፕሎማሲ ያልተሞረዱ ዕርምጃዎችና ንግግሮች ፋይዳ የላቸውም፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ሕዝቡን ለጋራ ዓላማ አስተሳስሮ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን እያሰፉ ከመገፋፋት ይልቅ እንደ ቀድሞዎቹ ጀግኖች አባቶችና እናቶች፣ የጋራ የሆነች አገርን ጥቅም የማስቀደም አስፈላጊነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለተወሰነ ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ብቻ በሚደረግ ሽኩቻ፣ የአገርና የሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ ለዘመናት በመከባበርና በመፈቃቀድ ልዩነቶቹን አቻችሎ ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሲገብር ለኖረው ለዚህ አኩሪ ሕዝብ፣ ሰላሙንና አንድነቱን የሚገዘግዙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች መገታት አለባቸው፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን በተጋድሎው በአንድነት ያስተሳሰረ ይኼ ጀግና ሕዝብ፣ በስሜታዊነትና በደም ፍላት በሚቅበዘበዙ ወገኖች ድርጊት መጎዳት የለበትም፡፡ ከአገሩ አንድነትና ህልውና በላይ ምንም የሚበልጥበት ነገር እንደሌለ፣ ታላቁን የዓድዋ ድል ጨምሮ በርካታ ተጋድሎዎቹ ህያው ምስክር ናቸው፡፡ በዘመናት አገርን የመከላከል ተጋድሎዎቹ የሚኮራው ይህ ትውልድ በዚህ ዘመን ጀግንነቱን ከዲፕሎማሲ ጋር እያዛመደ፣ ለዘመናት ሥራ ላይ ያልዋሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን እያለማ፣ ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎቶች በላይ አገሩን እያስቀደመና በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋን እያለመለመ ካጋጠሙት ችግሮች በብልኃት መላቀቅ ግዴታው ነው፡፡ የፖለቲካ ሰዎችም በተገራ አንደበትና ብልኃት በታከለበት አቀራረብ ችግሮችን እየፈቱ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ውጥረት በማርገብ ኢትዮጵያን ከገባችበት አጣብቂኝ የማውጣት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አጋጣሚውን መጪው ምርጫ በሰላም፣ በነፃነትና በፍትሐዊነት እንዲከናወንበት መጠቀም ሌላው ብልኃት ነው፡፡  የጋራ ችግሮችን ለመፍታት የጠራ የጋራ አቋም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም ለውጭ ኃይሎች እንዳትንበረከክ የሚጠቅማት በዲፕሎማሲ የታሸ ብልኃት ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...