Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዓለም ከኮቪድ-19 ጋር የገጠመው ጦርነት

ዓለም ከኮቪድ-19 ጋር የገጠመው ጦርነት

ቀን:

ከተከሰተ ከዓመት በላይ ያስጠቆረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዛሬም በደቂቃ ዘጠኝ በየዕለቱ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየነጠቀ ይገኛል፡፡ የአገሮችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁነትን የፈተነው ይበልጡኑ ደግሞ የጤና ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለው ወረርሽኝ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ገድሏል፡፡

አገሮች ይህ መድኃኒት ያልተገለኘትን ወረርሽኝ ለመዋጋት ከቅድመ መከላከል ጀምሮ እስከ የአስቸኳይ ጊዜ ክትባት ቢዘልቁም፣ ቫይረሱን መቋቋም አልተቻለም፡፡

በየጊዜው ዓይነቱን እየቀያየረ፣ የመጀመርያ ዙር አጥቅቶ ከጨረሰ በኋላ ሁለተኛ ዙር እየደገመ አገሮችን አስጨንቋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ዓይነቱን መቀያየሩና ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛውን ያልደረሱት ክትባቶች ዓይነቱን ቀይሮ የሚመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ ይከላከሉ አይከላከሉ በጥናት አለመረጋገጡ፣ የወረርሽኙ ባህሪ የጤናውን ሥርዓት አብዝቶ የሚፈትንና ከየትኛውም አገር አቅም በላይ መሆኑ ከተከሰተ ከዓመት በኋላም የዓለም አጀንዳነቱን እንደያዘ ቀጥሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም (ተመድ) ዓለም ከኮቪድ-19 ጋር ጦርነት ላይ ነው ብሏል፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ እንዳሉት፣ አገሮች ኮቪድን ለመከላከል ‹‹የጦርነት ጊዜ ሎጂክ›› መጠቀም አለባቸው፡፡

ዓለም ከኮቪድ-19 ጋር የገጠመው ጦርነት

 

የገንዘብ አቅም፣ ጊዜንና የሞት መጠንን በቀነሰ መልኩ በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን አዋጭ የጦርነት ሥልት ዓይነት በመጠቀም የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ እያደረሰ ያለውን ከባድ ጉዳት በአጭር ጊዜ መመከት ይገባል እንደ ጉተሬስ፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል ወሳኝ የሆነውን መሣሪያ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም አገሮች ማዳረስ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔን በሳምንቱ መጀመርያ የከፈቱት ጉተሬስ፣ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸውንና ግማሽ ቢሊዮን ያህል ሥራዎች መክሰማቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በጣም ተጋላጭ የሆኑት በጉልህ ይጎዳሉ፣ አሁን ላይ ያለው አደጋ ወረርሽኙን ለመግታት ባለሁለት ፍጥነት የዓለም ምላሽ መኖሩ ነው›› ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ጸሐፊው፣ አሁን ላይ የዕርምት ዕርምጃ መወሰድ ካልጀመረ ሀብታም አገሮች በርካታ ሕዝባቸውን በመከተብ ኢኮኖሚያቸውን ክፍት ሲያደርጉ፣ ደሃ አገሮች ለቫይረስ ድግግሞሽና ለተለያዩ ዓይነት ቫይረሶች እየተጋለጡ ለከባድ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡

ይህ ግን ደሀ አገሮችን ብቻ ጎድቶ አይቀርም፡፡ ቫይረሱ በአንድ ጊዜ አንድ አገር ብቻ አጥቅቶ የማይቀር በመሆኑም፣ ተፅዕኖው ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ የአንዱ ኢኮኖሚ መጎዳትም የሌላውን ይጎዳል፡፡ ይህንን እውነታ በመጋፈጥ ‹‹ዓለም ከቫይረሱ ጋር ጦርነት ላይ ናት›› ብለዋል፡፡

ጉተሬስ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ ደሃ አገሮች ቫይረሱን ሊዋጉ የሚችሉበት የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ አቅም ላይ አልደረሱም፡፡ የቡድን ሃያ አገሮች ከዓመት በፊት በነበራቸው ውይይት የክትባት ተደራሽነት ላይ ባደረጉት ምክክር ደሃ አገሮች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ማመቻቸት ላይ ከስምምነት ደርሰው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ በቅጡ አልተተገበረም፡፡

የዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎች የፈጠሩት ዓለም አቀፍ የክትባት ፕሮግራም ኮቫክስም፣ ክትባቱ ለአገሮች በፍትሐዊነት ተደራሽ እንዲሆን ዓላማ አስቀምጦ ቢንቀሳቀስም፣ የኮቪድ-19 ክትባት አቅርቦት ጉልህ እጥረት ገጥሞታል፡፡ ይህም በደሃ አገሮች ክትባቶች እንዲዘገዩ ምክንያት ሆኗል፡፡

እስካሁንም ለደሃ አገሮች የተከፋፈለው ክትባት ከታዘዘው 0.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው፡፡ በደሃ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች ደግሞ የዓለምን አሥር በመቶ ይሸፍናሉ፡፡

ይህም ሆኖ ግን ቫይረሱን መከላከል ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ ራሱን ከመቀያየሩ ባለፈም፣ ሌላ ቫይረስ ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት አለና፡፡

አሁን ያለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል እንዳለ ሆኖ፣ የሚቀጥለውን ወረርሽኝ ለመከላከል ራስን ማዘጋጀትና የዓለም ጤና ሥርዓትን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓለም አሁን ያለውን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልገዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ ለወረርሽኝ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አለበት፡፡ ዘላቂና ሊፈጠሩ ለሚችሉ ችግሮች የሚውል ሀብት መያዝና የሚጠበቅበትን መሥራትም ይጠበቅበታል›› ብለዋል፡፡

በዓለም የጤና ጉባዔ ላይ ለኮቪድ-19 አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ባለፈው ሳምንት  የመከሩት የቡድን ሃያ አባል አገሮች ከዓመት በፊት የገቡትን ቃል መተግበሪያ ጊዜውም አሁን ነው ተብሏል፡፡

ወረርሽኙን የማስቆም አቅም በቡድን ሃያ አገሮች እጅ ላይ ነው የሚለው የዓለም ጤና ድርጅትም፣ አገሮቹ ወረርሽኙን ለመከላከል፣ የመመርመር አቅምን ለማጠናከር፣ ክብካቤና ክትባቱም ለሁሉም በፍትሐዊ መንገድ እንዲዳረስ ለማስቻል የጀመሩትን ሥራ ማጠናከር ይገባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...