Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበፈረንጅ ድጋፍ ሾልኮ የወጣውና አደባባይ የተሰጣው የቅዱስነታቸው ገመና

በፈረንጅ ድጋፍ ሾልኮ የወጣውና አደባባይ የተሰጣው የቅዱስነታቸው ገመና

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ሰሞኑን በትግራይ ሚዲያ ሐውስና ቢጤዎቹ በሆኑት ጽንፈኛ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት አማካይነት በሰፊው ሲሠራጭና ከፍተኛ አቧራ ሲያስነሳ የሰነበተው የአባ ማትያስ ዋልታ ረገጥ ኑዛዜ፣ እንደ ገና እየታደሰ መነጋገሪያነቱን ቀጥሏል፡፡ ‘ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም’ እንዲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ መደበኛውን መንገድ በመስበርና አስቀድሞ ከሚታወቀው የግንኙነት መስመራቸው በማጋደል ወደ አደባባይ ብቅ ብለው፣ ‘ዘር ከልጓም ሳይስባቸው’ አልቀረም በሚያስብል ሲቃ ያረገዘ ቅላፄ ድምፅ ወገኔ ነህ በሚሉት የትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም ላይ መሆኑን እስኪያቅረን ድረስ ነገሩን፡፡

በእርግጥ አባ በሕወሓት ላይ በተወሰደው የመልሶ ማጥቃት ዕርምጃ በኋላ ያለ ቅጥ ተስፋፍቶ የተራገበላቸውን ሐረግ የገደል ማሚቱ ያህል ደግመው ከማስተጋባታቸው በስተቀር፣ በጠባዩ ውስብስብ የሆነው የዘር ማጥፋት ወንጀል ራሱ ምን ያህል ከባድና በተፈጸመበት አገር ብቻ ሳይሆን፣ የትም ቦታ ይፈጸም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣ እንደሆነ በውል ለይተው መረዳታቸውን ይህ ጸሐፊ አጥብቆ ይጠራጠራል፡፡

“ያ ሕዝብ” (የትግራይን ሕዝብ ማለታቸው ነው)፣ ጨርሶ “ከምድረ ገጽ ይጠፋ ዘንድ ለምን እንደተፈለገ እኔ አላውቅም” በማለት አስደንጋጭ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እምብዛም ያልቸገራቸው አባ ማትያስ፣ እሳቸው በግል ደፋር የነበሩ ቢሆንም ይህችን አውጥቶ ለመናገር እንኳ በየትኛው ኃይል እንደሆነ ፍንጭ ባይሰጡንም አፈና ሲፈጸምባቸው እንደከረመ ገልጸው፣ ወገኖቻቸው ይህንኑ ጥረታቸውን በክሬዲት መልክ እንዲይዙላቸው መማፀናቸውን በሚያሳብቅ ድምፀት “የራሴን ችግር የማውቀው ራሴ ነኝ” ሲሉ በአንክሮ አድምጠናቸዋል፡፡

አንዳንድ የዋሃን ወገኖች ታዲያ ደጋግሜ ብሞክርም “መናገር አልተፈቀደልኝም” የሚለውንና ሰሞኑን በቪዲዮ ተለቅቆ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚንሸራሸረውን ይህንኑ የአባ ማትያስ መልዕክት፣ “ረገጥከኝ፣ መተንፈስ አልቻልኩም” ከሚለውና አሳዛኝ ሲቃ ከተቀላቀለበት የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ የፃዕረ ሞት ድምፅ ጋር ያነፃፅሩት ይዘዋል፡፡ ይህ እንኳ በእውነት ተገቢ ንፅፅር ነው ብዬ በበኩሌ አላምንም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን የእምነት አጥር እንኳ ያን ያህል ሳይገድበን ብፁዕነታቸውን የሁላችንም የመንፈስ አባት እንደሆኑ አድርገን ነው የምንቆጥራቸው፣ የምንተማመንባቸውም፡፡ በእርግጥ ይህንን የምናደርገው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከዓመታት በፊት አክሱም ፅዮን ላይ በአካል ተገኝተው፣ ለያኔው የሕወሓት ፊታውራሪ ለደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) አክሊል እንደ ደፉለትና ‘ሺሕ ዓመት ንገሥ’ ብለው እንደባረኩት ፈፅሞ ሳንዘነጋው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሌላው ቀርቶ ቀደም ባለው ጊዜ እኮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ከተዋቀሩት 14 መምርያዎች ውስጥ 12 የሚሆኑት፣ እሳቸው ከበቀሉበት ብሔር ተመርጠው በተሰባሰቡ የመንደር አሽከሮች የተያዙ እንደነበሩ ማስታወስ ይሳናቸዋል ተብሎ አይታመንም፡፡ ይህንንም ያልተቀደሰ ፕሮጀክት ጀምረውላቸው ያለፉት በዘር የሚሻረኳቸው አባ ጳውሎስ እንደነበሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

እንግዲህ ይህንን ሁሉ ማስታወሱ የማይገዳቸው ከሆነ ዛሬ ላይ ብቅ ብለው “አፈና ተፈጸመብኝ” በማለት፣ የዓለሙን ኅብረተሰብ አንጀት ለማራራት ዴኒስ ዋድሌ የተባለን አንድ አውሮፓዊ ወዳጃቸውን ወደ ቢሯቸው በሚስጥር ከጠሩ በኋላ፣ ድምፅና ምሥላቸውን ቀርፆ ለጠላት ሚዲያ በማቀበል ረገድ እንዲተባበራቸው የጠየቁበትና ያስፈጸሙበት ኩነት ግብዝነታቸውን ያሳያል፡፡ በተለይ በቪዲዮ የተሠራጨው የቅዱስ ፓትርያርኩ መልዕክት ማዕከላዊ ይዘቱ በጥልቀት ሲመረመር፣ ከመንፈሳዊነታቸው ይልቅ ፖለቲከኝነታቸውን የሚያሳብቅ መስሎ ታይቷል፡፡

ብፁዕ አባታችን ተፈጥሯዊ የሆነው ሐሳብን የመግለጽ ነፃነታቸው በተደጋጋሚ እንደ ተጣሰ አደባባይ ወጥተው በምሬት ነግረውናል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ተወዳጅ መብት ያላግባብ ተጠቅመው የነዙት መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ፣ ከተከበረው መንበረ ፕትርክናቸው ወርደው ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ለሕወሓት ማደራቸውን አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በመሠረቱ አባ በጎውን ማወደስና ክፉውን ማውገዝ ወይም መገዘት ይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለአንድ ብሔር ወግነው የቆሙ በሚያስመስላቸው አኳኋን (ያውም ሽብርተኛው ሕወሓት በግብረ በላዎቹ አማካይነት በሚዘውረው የውጭ ሚዲያ በኩል ተጋንኖ ከሚቀርብላቸው ውጪ እምብዛም ባላረጋገጡት ጉዳይ)፣ ያን ያህል ሽንጣቸውን ገትረው እንዲሟገቱ ጨርሶ አይፈቀድላቸውም፡፡

አቡነ ማትያስ ለእርስ በርስ ፍቅር፣ ለአገር ሰላም፣ ለዜጎች ደኅንነትና ለማኅበረሰቦች አንድነት ዘወትር መፀለይና ምዕመናንን ሳይታክቱ ማስተማር መደበኛ ሥራቸው ነውና ይህንን ለመፈጸም ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ከሃይማኖታዊ ተግባራቸው ዕላፊ በመሄድ እንደ ወያኔ ያለ ሕገወጥና አረመኔ ቡድን በአንድ አገር ሉዓላዊነትና በመከላከያ ሠራዊቷ ላይ የለየለት ክህደት በመፈጸም ከፍ ያለ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ፣ ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ከተወሰደ አፀፋዊ የመከላከል ዕርምጃ ጋር ተያይዞ በተጓዳኝ ያጋጠመን ሰብዓዊ ጥፋትም ሆነ የሀብት ውድመት፣ ሆን ተብሎ በአንድ ብሔር ላይ የተነጣጠረ የጅምላ ጥቃት አስመስለው ሊያቀርቡና ዓለምን በሐሰት ሊያሳምኑ በድፍረት የተጓዙበት ርቀት አስተዛዛቢ ሆኖ ተመዝግቦባቸዋል፡፡

አባ በሁላችንም ዘንድ የተከበሩ የአንድ ገናና ሃይማኖት ቁንጮ መሪ ስለሆኑ፣ ዓለማዊውን መንግሥትም ቢሆን ሲያጠፋ ቢገስፁና የተሳሳተ መስመር ተከትሎ ከሆነም አገሪቱን ላላስፈላጊ ኪሳራ ከመዳረጉ በፊት ወደ ቀልቡ እንዲመለስ አባታዊ ምክራቸውን ቢለግሱት እኮ እናደፋፍራቸዋለን እንጂ አናሸማቅቃቸውም፡፡

በዕውን የሆነው ግን ይህ አይደለም፡፡ ‘ከምን ጋር የዋለች ጊደር’ እንዲሉ ከመንበረ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤታቸው አንድ ማይል እንኳ ፈቀቅ ሳይሉ የመልሶ ማጥቃት ዕርምጃው ካስደነገጣቸው ዋሾ የሕወሓት አፈ ቀላጤዎች የሰበሰቡትን ያልተጣራ እንቶ ፈንቶ መረጃ፣ ከአንድ መንፈሳዊ አባት በማይጠበቅ ድምፀት በህቡዕ አስቀርፀው በአደባባይ ለቀቁልን እንጂ፡፡

ከዚህ ጋር አብሮ ሳይወሳ መታለፍ የሌለበት ሌላም ቁምነገር አለ፡፡ አስደማሚው መግለጫ አፈትልኮ በወጣና አየር ላይ በዋለ ማግሥት፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አባ ማትያስን በእንግድነት ጠርቷቸው ነበር ይባላል፡፡ እሳቸውም የኋላ ኋላ ዙሩ እየከረረ የሄደ እንደሆነ ጥላ ከለላ ሳይሆነኝ አይቀርም ብለው፣ ወደ ገመቱት ወደ እዚያው የኃያሏ አገር ኤምባሲ ተቻኩለው ለማምራት እምብዛም አላቅማሙም ነበር፡፡

እንግዲህ አባ አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ከአንደኛው ወደ ሌላኛዋ ወጥመድ መረማመዳቸው ነው፡፡ እኔ በበኩሌ እንደ አንድ ተራ ምዕመን ይህንን ነጭ አምላኪነታቸውን ፈጽሞ አልወደድኩላቸውም፡፡

ለማናቸውም እዚያ በተገኙበት ወቅት በቅርቡ ሥራዋን የጀመረችው አሜሪካዊቷ እንስት አምባሳደር (ጊታ ፓሲ ትሰኛለች)፣ ተፈጸመብኝ ከሚሉት አፈና ጋር በተያያዘ አንዳች ዓይነት ሥጋት ይሰማቸው እንደሆነ አባን በጠየቀቻቸው ጊዜ በረዥሙ ከተነፈሱ በኋላ፣ “እንቢየው፣ አሻፈረኝ” እንዳሏትና ከዚህ የባሰ ፈተና ቢያጋጥማቸው እንኳ የመንፈስ ልጆቻቸውንና አገራቸውን ጥለው የራሳቸውን የግል ደኅንነት በመሻት ብቻ ለስደት ዝግጁ አለመሆናቸውን እንደተናገሩ በበጎ ጎኑ ተዘግቦላቸው አድምጠናል፡፡

መቼም ይህ እውነት ከሆነ አባታችን ‘ጎሽ፣ ደግ አደረጉ’ ነው የምንለው፡፡ አሜሪካስ ብትሆን እዚህ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረጋትና ነው በሃይማኖታቸውና በአገራቸው ክብር እንዲደራደሩ አባን በግል ጠርታ ያን ያህል የምትወሰውሳቸው? ያንኑ ሽርፍራፊ የንዋይ ድጋፍና ዕርዳታዋን ተመክታ ምን ያህል ጢባጢቤ እንደምትጫወትብን ታያላችሁ? ድህነት የዘለዓለም ደዌ መሆኑን ይህ ብቻ ሊያስገነዝበን ይገባል፡፡

በመሠረቱ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ አዘውትራ ራሷ እንደምትለፍፈው የዓለም ፖሊስ አይደለችም፡፡ ልሁን ብትልና ይህንኑ ከፍታ በአንድ ድምፅ ተስማምተን ብንፈቅድላት እንኳ፣ ገለልተኛና እምነት የሚጣልበት ሕግ አስከባሪ የመሆን አቅምም ሆነ ሞራል የላትም፡፡

‘ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል’ እንዲሉ ብሔራዊ ጥቅሞቿ ይከበሩልኛል ብላ እስካመነች ድረስ የሰውን ቤት ካላፈረሰች በስተቀር፣ ምን ጊዜም ቢሆን አርፋ የማትተኛው ያቺ ግብዝ አገር አጉል ልማድ ሆኖባት እንጂ እንደ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ያልተቀደሰ አቀራረብ፣ አባ ማትያስ በአገራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ያለፈ የባዕድ አገር ጥበቃ አያሻቸውም፡፡

ይልቁንም ታላቁ የሕዝበ ክርስቲያን እረኛ ናቸውና በዋነኝነት ጠባቂያቸው ልዑል እግዚአብሔር ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ግፋ ቢል በመሬት ላይ አባ ለሚያስፈልጋቸው የግል ደኅንነት አጠባበቅ ቀዳሚውንና የአንበሳውን ድርሻ ኃላፊነት የሚወስደው፣ ከእነ ችግሮቹም ቢሆን እሳቸውን ጭምር በሥሩ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ጠንከር አድርገን እንነጋገር ከተባለና በአገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ አተኩሮ እ.ኤ.አ. አፕሪል 18 ቀን 1961 የወጣውን የቪዬና ስምምነት በዝርዝር ከተመለከትን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተጠለለውን ራሱን የአሜሪካን ኤምባሲስ ቢሆን በመጀመርያ ደረጃ የሚጠብቀውና የደኅንነት ከለላ የሚሰጠው ከኢትዮጵያ መንግሥት በስተቀር ሌላ ማን ሆነና ነው?

እርግጥ ነው አሜሪካ በምድራችን ታላቅ፣ ባለፀጋና ኃያል አገር መሆኗ አይካድም፡፡ ይህ ግን እስከ መጨረሻው ጫፍ ድረስ ያላግባብ ተለጥጦ ያች አገር ባፈተታት ጊዜና አጋጣሚ በማይመለከታት ጉዳይ ሁሉ እንደ እርጎ ዝንብ ዘው ብላ በመግባት ራሷን እየነከረች፣ የነፃና ሉዓላዊ መንግሥታትን ሥልጣን በዘፈቀደ እንድትጋፋና ህልውናቸውን እንድትዳፈር ያልተገደበ መብት የሚሰጣት አይሆንም፡፡ እንዲህ ያለውን ያፈነገጠ አሠራር የሚያበረታታ ወይም የሚደግፍ ዓለም አቀፍ የሕግ ሥርዓትም ሆነ የዳበረ ልምድ ጨርሶ የለም፣ አይታወቅምም፡፡

አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...