Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በማይክሮ ሎት ሥርዓት ሊገበያይ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግና አርሶ አደሩን በቀጥታ ተጠቃሚ ለማድረግ የማይክሮ ሎት የግብይት ሥርዓት ዘርግቶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን መጨረሱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የማይክሮ ሎት የግብይት ሥርዓት ከሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

በይፋ የሚጀመረው የግብይት ሥርዓት ለባለ ልዩ ጣዕም ዓለም አቀፍ ውድድር (Cup of Excellence) ቀርበው በብሔራዊ ደረጃ አሸናፊ የሆኑትን አርሶ አደሮች ቡና ለማገበያየት እንደሆነና ይህም በዘርፉ ላይ መነሳሳትን ሊፈጥር እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬከተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በቅርቡ የሚጀመረው የቡና ግብይት ሥርዓት ከቀደመው የተለየና ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

የማይክሮ ሎት አሠራር በተለይም መጠናቸው ዝቅተኛም ቢሆንም፣ በከፍተኛ ጥራት ተዘጋጅተውና በላቦራቶሪ ምርመራ ከ85 በመቶና ከዚህ በላይ የጥራት ደረጃ ውጤት የተሰጣቸው፣ የምርት ዱካቸው የሚታወቁ ቡናዎች የሚገበያዩበት አዲስ የአሠራር ሥርዓት ሲሆን፣ ሽያጫቸውም እጀግ አማላይ በሆነና አርሶ አደሩንም ሆነ አቅራቢውን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር ነው፡፡

 አሠራሩ የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ቡናዎችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ በዋጋ የመደራደር አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመርና የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ ለማድረግ ሚና እንደሚኖረውና አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ በማድረግ ገቢውን ከማሳደግ በተጨማሪ በርካታና አዳዲስ የውጭ ቡና ገዥ ድርጅቶችን ትኩረት እንደሚስብ ታምኖበታል፡፡

ከኢትዮጵያ ምርት ገበያና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራ ሲሆን፣ በተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት የሚመራና አቅራቢም ሳይጉላላ ፈጣን አገልግሎት የሚያገኝበት፣ በአነስተኛ መጠን ተዘጋጅተው ለገበያው የሚቀርቡት ቡናዎች በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀው በዚህ የግብይት ሥርዓት (Micro Lot Coffee Trading Platform) የሚስተናገዱበት አማራጭ ነው፡፡

የግብይት አማራጩ ለመጀመርያ ጊዜ የሚጀመረው ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው የባለ ልዩ የቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር ላይ ተሳትፈው በብሔራዊ ደረጃ አሸናፊ ተብለው የተለዩትን አርሶ አደሮች ቡና በማገበያየት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ኢትዮጵያ ከቡና የወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግና አርሶ አደሩም የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ በማሰብ በተዘረጋው የግብይት ማዕቀፍ በአነስተኛ መጠን ተመርተው የሚቀርቡ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና በልዩ ሁኔታ የማይክሮ ሎት ግብይት ሥርዓት በመዘርጋት ለማገበያየት ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ አስረድተዋል፡፡

ይህ ዓይነት ግብይት ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለውን ቡና ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል አርሶ አደሩን ገቢ ከፍ ለማድረግ፣ ከፍተኛ ጥራት ያለውን ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብና የአገራችንን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጸኦ ይኖረዋል፡፡

ለዚህ ግብይት የሚቀርብ ቡና የተመሰከረላቸው ቡና ቀማሾች በሚሳተፉበት የላቦራቶሪ ምርመራ ደረጃ ይሰጠዋል፡፡ ምርቱ የሚቀመጠው ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ደረጃውን በጠበቀ ማከማቻ ሲሆን፣ ከሁሉም ንግድ ባንኮች ጋር በመረጃ መረብ በተያያዘው የክፍያና ርክክብ ሥርዓት በግብይት ማግሥት አርሶ አደሮች ክፍያቸውን፣ ገዥዎችም ምርታቸውን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ልዩ ግብይት በከፍተኛ ዋጋ የሚከናወን ስለሆነ በአስተማማኝ የገበያ መረጃ ሥርዓት ሁሉም የግብይት ተዋንያን ወቅታዊ መረጃ የሚያገኙም ይሆናል፡፡

ሥርዓቱ ለባለ ልዩ ጣዕም ቡና ግብይት የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ተገበያዮች የሚመጡበት፣ የወጪ ንግዳችንን የሚያጠናክር፣ የኢትዮጵያን ቡና ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድሎች የሚያሰፋ ይሆናል ተብሏል፡፡

ምርት ገበያ በመጀመርያው ዙር በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ሒደት ያለፉትን ቡናዎች መረጃ ከአዘጋጆቹ በመውሰድ የማገበያየት፣ ክፍያውን የማስፈጸምና የገበያ መረጃ የማሠራጨት ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ ግብይቱ በየዕለቱ ከሰዓት በፊት በድምፅ ማስተጋቢያ የግብይት መድረክ (Open Outcry) ላይ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት የምርቱ ባለቤት ወይም ሕጋዊ ተወካይ በግንባር ተገኝተው መሸጥ ያለባቸው ሲሆን፣ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ላኪዎችና፣ ቡና ቆዪዎች በነፃ የገበያ ውድድር መግዛት ይችላሉ፡፡

ለዚህ እንዲረዳ የቅድመ ግብይት መረጃ ለሁሉም ተገበያዮች በተለያዩ መንገዶች ይሠራጫል፡፡ ግብይቱ ከተጠናቀቀም በኋላ የገበያ መረጃው በይፋ ይገለጻል፡፡

በተለመደው ሥርዓት ገዥዎች አስቀድመው ለዚህ ተብሎ በልዩ ሁኔታ በምርት ገበያው በተከፈተው የባንክ አካውንት ለግብይቱ የሚያበቃቸውን በቂ ገንዘብ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምርቱን ከገዙ በኋላ በሰባት ቀን ጊዜ ውስጥ ካለበት መጋዘን መረከብ ይገባቸዋል፡፡

ምርቱን የሚያስረክቡት የቡናና ሻይ ባለሥልጣንና የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሲሆኑ፣ ገዥው ምርቱን በሰባት ቀን ውስጥ እንደተረከበ ምርት ገበያው ለሻጩ ገንዘቡን ይከፍላል፡፡ በዚህ ውስጥ ገዥው ምርቱን ካልወሰደ በስምንተኛው ቀን ክፍያው ለሻጩ ይተላለፋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይህን የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ብሔራዊ አሸናፊዎች ለማበረታታትና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማገበያየቱ ሒደት ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ አይኖርም፡፡

አርሶ አደሩ የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ቡናን ጥራቱን ጠብቆ እንዲያመርት፣ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ እጅግ ልዩ ጥራት ያላቸውን ቡና እንዲገዙና በምርትና ግብይት ሥርዓት ውስጥ አገርን ሊለውጥ የሚችል ተግባር እንዲኖርም አቶ ወንድም አገኘሁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎቸ ማኅበር፣ ከፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫሊዩ ቼይን አክቲቪቲና ከአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ጋር በመሆን የ2013 ዓ.ም. ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር የኢትዮጵያ ምርጥ 30 አሸናፊ ቡናዎችን ይፋ ተደርጓል፡፡ 30ዎቹ ቡናዎች በውድድሩ 87 ነጥብና ከዚያም በላይ በማምጣት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም አምስት ቡናዎች ከ90 በላይ ውጤት በማስመዝገብ ፕሬዚደንሽዋል አዋርድ በመባል የሚታወቀውን ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊ ቡናም ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ድረ ገጽ ላይ በቀጥታ ለ24 ሰዓታት በሚቆይ ጨረታ ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡

137 ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ድረ ገጽ ለ24 ሰዓታት በሚካሄድ ጨረታ ለመሳተፍ ተመዝግበዋል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ በተካሄደው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ለዘርፉ በርካታ ጥቅሞችን ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሸናፊ ቡናዎችም ለጥራታቸው ከፍተኛ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጥ ቡናም ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በሚዘጋጃቸው ስመ ጥር የሆኑ የውድድር መድረኮች ላይ በስፋት የመተዋወቅ ዕድል ያገኛል፡፡ ይህ የቀጥታ ግብይት ቀጣይነት ያለው ትስስር ከመፍጠር በተጨማሪ የቡና አብቃይ ገበሬዎችንና የቡና ገዥዎችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ውድድሩ የቡና ኢንዱስትሪው የተለዩ የቡና ጣዕሞችን በተሻለ ሁኔታ መለየት እንዲችል ዕገዛ ያደርጋል፡፡

ዓምና በተደረገው ውድድር አሸናፊው ቡና በቀጥታ ጨረታ በኪሎ 407 የአሜሪካን ዶላር በመሸጥ የኢትዮጵያን የቡና ዋጋ ሪከርድ መስበሩ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች