Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

  የጉራጌዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓት

በሲሳይ ዓለሙ

በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙት ግድያዎች፣ መፈናቀሎችና አልፎ አልፎ በማኅበራዊ ትሥሥር ድረ ገጾች ላይ በሚለጠፉ የጎሳና የብሔር መልክ ያላቸው የጥላቻ ንግግሮች በተደጋጋሚ ከሰማሁና ከተመለከትኩ በኋላ በጣም ተጨንቄ ለአንድ የአገር ሽማግሌ እንዲህ ስል ጠየቅኳቸው፡፡ …አባባ አልኳቸው፣ እንባ ያቀረሩ የዓይኖቼን ብሌኖች በስስት እየተመለከቱ፣ እንደ ሲባጎ ተወጥሮ ንዴቴን ያሳበቀብኝ የግንባሬን ደም ሥር ትኩር ብለው እያዩ፣ ‹‹አቤት ልጄ›› አሉኝ! በዝግታ፡፡ እንደው እንደዚህ ዓይነት ጠብ ድሮ እናንተ እንደኛ ወጣት በነበራችሁ ጊዜ አሁን በአገራችን እንደተከሰተው ዓይነት ምክንያቱ እንኳን ይህ ነው በማይባል ፀብ፣ ክርክር፣ ዘረኝነት፣ ግድያ ነበረ እንዴ? ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ ከጉረሮዬ የሚወጣው ትንፋሽ ቆረጥ ቆረጥ እያለ፡፡

በግራ እጃቸው የያዙት የነፍሳት ማባረሪያ ጭራቸውን እያወዛወዙ፣ በቀኝ እጃቸውን ፀጉሬን ከዳበሱኝ በኋላ… አይይይ ልጄ… እንኳንስ ሰው ለሰው ይቅርና እግርና እግር ይጋጭ የለም፡፡ ፀብማ ነበረ አሉኝ፡፡ ግን እውነት እልሃለሁ ልጄ እንደ አሁኑ ዓይነት የዘር፣ የብሔርና የጎሳ ግጭት ግን ዓይቼም ሰምቼም አላውቅም አሉኝ፡፡  ከጥቂት መብሰልሰል በኋላ ልጄ አንዴ ሆኗል እናንተ ወጣቶች በየአካባቢያችሁ ያለውን የግጭት አፈታትና የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ላይ አተኩራችሁ ልትሠሩ ይገባል፡፡ አገራችሁን ኢትዮጵያ ጠብቋት ብለውኝ በነበርኩበት ጥለውኝ ሄዱ፡፡

ለጥቂት ደቂቃዎች በሐሳብ ዳገት ቁልቁለቱን ወጥቼ ከወረድኩ በኋላ ትዝ ያለኝንና በአካባቢዬ የተመለከትኩትን መጠነኛ የሆነ ግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓት እንዲህ አካፍላችኋለሁ፡፡

ጉራጌዎች አያንዳንዱ ተግባራቸው፣ ወግና ልማዳቸው፣ ሐዘንም ደስታቸው፣ የግጭት አፈታታቸው፣ የአረማመድና የአበላል ሥነ ሥርዓታቸው የጉራጌ ሽማግሌዎች ተሰባስበው አርቅቀው፣ ቃለ መሃላ በፈጸሙባቸው የጆካ ቂጫ፣ ሴራና የጎርደነ ባህላዊ መተዳደሪያቸው ላይ ባስቀመጡት ሕግና ደንብ መሠረት ነው የሚመሩት፡፡ መላው ቤተ ጉራጌ የእነዚህ ደንብና ሕጎች ያለማቅማማት ተገዥ ነው፡፡

በጎረቤት ወይም በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ሁለት ሰዎች መካከል ጥል ከተፈጠረ በኋላ ባለመግባባቱ ወይም በግጭቱ ወቅት በሚፈጠር ጩኸት ወይም ጫጫታ ሰምተው የመጡ የአገር ሽማግሌዎች መጀመርያ የሚያደርጉት ነገር አንተም ተው አንቺም ተይ በማለት ጉዳዩን እንዲረግ በማድረግብ ነው፡፡ መጀመርያ ግጭቱን የፈጠሩ ሰዎች እንዲረጋጉ ከተደረገ በኋላ ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን ወዲያው ለመፍታትና ለማስታረቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ግጭቱን ወይም ጥሉ ትንሽ ከበድ ያለ ከሆነ ተጨማሪ የአገር ሽማግሌዎች ተካተውበት ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ ለመፍታት በማግሥቱ ጠዋት ወይም በሌላ ጊዜ ቀነ ቀጠሮ ይይዛሉ፡፡

ጥሉን የፈጠሩ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጉዳያቸውን በቀነ ቀጠሮው መሠረት ሽማግሌዎቹ በዝርዝር ተመልክተው እስኪፈቱት ድረስ በመሃል ምንም ዓይነት የጥላቻ ንግግር እንዳያካሄዱ፣ ጥልም ሆነ ግጭት እንዳያስነሱ ሽማግሌዎቹ ከበድ ካለ ማስጠንቀቂያ ጋር ‹‹ኸተራት›› ይሰጣሉ፡፡

ኸተራት ማለት ጉዳዩን በሽማግሌዎች እስኪታይ ድረስ በመሀል ምንም ዓይነት ጥልም ሆነ ዘለፋ እንዳይካሄድ የሚደነግግ ባህላዊ ሕግ ነው፡፡ ይህን ኸተራት የጣሰ አካል ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ይወሰንበታል፡፡ ቅጣቱ ከማንኛውም ዓይነት የማኅበራዊ ጉዳዮች እስከ ማገድና ማግለል ሊደርስ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ጉራጌዎች ለኸተራት ልዩ ሥፍራ የሚሰጡት፡፡

በቀነ ቀጠሮው መሠረት በአካባቢው የሚኖሩ ሽማግሌዎች ጉዳዩን ለመፍታት እንደአየሩ ፀባይ ሞቃትና ነፋሻማ ከሆነ ዋርካ ሥር የብርድና የዝናብ ወቅት ከሆነ ደግሞ እልፍኝ ውስጥ ይሰባሰባሉ፡፡ ነጭ ሀጫ በረዶ የመሰለውን ጋቢያቸውን ትከሻቸው ላይ ግራና ቀኝ ያጣፉ፣ ባርኔጣቸውን በራስ ቅላቸው ላይ ያደረጉ የአገር ሽማግሌዎች ምርኩዛቸውን ወይም ከዘራቸውን መሬት ላይ ጋደም አድርገው መደዳ በተሰደሩ መቀመጫዎች ወይም በርጭማዎች ቁጭ ይላሉ፡፡

ጉዳዩን እንዲያስተባብር የተመደበው ሽማግሌ ለሽማግሌዎቹ እንዲናገር ፈቃድ ጠይቆ ጥሉን ለፈጠሩ ሰዎች ጉዳያቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው በኩል እንዲፈቱትና በይቅር ለእግዚአብሔር እንዲያወርዱና ሰላም እንዲያሰፍኑ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ባለ ጉዳዮቹ አይ ጉዳዬን ሽማግሌ ይመልከትልኝ ካጠፋሁም እቀጣለሁ፣ ካጠፋብኝም ይቀጣልኝ የሚሉ ከሆነ ደግሞ ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን በጥልቀት ተመልክተው በአጥፊው ግለሰብ ላይ አስተማሪና አስፈላጊ የሆነ ቅጣት ለመቅጣት ጉዳዩን ከሥር መሠረቱን ማድመጥና መመልከት ይጀምራሉ፡፡

መጀመርያ ግጭቱን የፈጠሩ ሰዎች የሚበየንባቸውን ቅጣት ለመክፈል ቃማ   (ዋስ) እንዲጠሩ ከተደረጉ በኋላ፣ ለቅጣቱ የሚውል ሽማግሌዎቹ በወሰኑት መሠረት የገንዘብም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ተመጣጣኝ የሆነ ንብረት ባለጉዳዮቹ ዋስ እንዲሆናቸው ለጠሩት ሰው ያስይዛሉ፡፡

ተራ በተራ በሽማግሌዎቹ ፊት ተነስተው በመቆም የፀባቸውን መንስዔ ምን እንደሆነና ተበደልኩበት ያሉት ጉዳይ ለተሰበሰቡ ሽማግሌዎች በጥልቀትና በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡  ሽማግሌዎቹም ግራ ቀኝ ክርክሩን አድምጠው የጠቡን መንስዔ መስቀለኛ በሆኑ ጥያቄዎች መርምረው ከተረዱ በኋላ ተጨማሪ የምስክሮች ቃል አድምጠው የቅጣት ብይን ለማስተላለፍ ግጭቱን የፈጠሩ ሰዎች ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከቦታው ገለል እንዲሉ ይደረጋል፡፡

ሽማግሌዎቹ የጥፋት ብይኑን ለማስተላለፍ እውነት እንደ ፀሐይ ትብራ እንደ ጨረቃም ትድመቅ በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን ካካሄዱ ኋላ ጥፋቱን ማን ላይ እንደሆነ በአንድ ድምፅ ይወስናሉ፡፡ ለደቂቃዎች ከቦታው ገለል እንዲሉ የተደረጉ ባለጉዳዮች እንዲቀርቡ ከተደረገ በኋላ ከታላቅ ተግሳጽና ምክር ጋር ለአጥፊው ወገን የጥፋቱን ሁኔታ በዝርዝር በተመደቡ ሽማግሌዎች አማካይነት ይነገረዋል፡፡ በውሳኔው አጥፊው ወገን ቅሬታም ሆነ አስተያየት እንዲያቀርብ ዕድል ይመቻችለታል፡፡ ያቀረበው ቅሬታ አሳማኝ ከሆነ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲታይለት ይደረጋል፡፡ ካልሆነም ደግሞ አጥፊው ወገን ዳግም እንደዚህ ዓይነት ጥል ያለ አግባብ በሠፈሩና ከማንኛውም ዓይነት  ግለሰብ ጋር እንዳይፈጠር ከማስጠንቀቂያ ጋር ቅጣቱን እንዲከፍል ይደረጋል፡፡

እንደየ ሁኔታው ሽማግሌዎቹ የቅጣት ማቅለያ ካለ ያደርጋሉ፡፡ በቅጣት የሚገኝ ገንዘብም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት ንብረት ሽማግሌዎቹ በሚወስኑት ውሳኔ መሠረት ዕድራቸው ወይም የጋራ በሆኑ የማኅበራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡

በማንኛውም ዓይነት በጥልም ሆነ ባለመግባባት ወቅት የሰው ነፍስ ከጠፋ ጉራጌዎች እስከ ሰባት ዓመት የሚውስድ ባህላዊ የዕርቅ ሥነ ሥርዓት አላቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡                                        

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles