ብልፅግናና ኢዜማ ከፍተኛውን ድርሻ አግኝተዋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እንዲሆን የሚያሠራጨውን ገንዘብ ሁለተኛ ዙር እያከፋፈለ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ በጠቅላላ ከ98.6 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነው ድጋፍ የተቀረውን 77.8 ሚሊዮን ብር ለ46 የፖለቲካ ፓርቲዎች እያሠራጨ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ቦርዱ ዓርብ ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፣ ገንዘቡን ያከፋፈለው ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ያካሄደውን ውይይትና ምክክርን መሠረት ባስቀመጣቸው መሥፈርቶች አማካይነት ነው፡፡
ለፓርቲዎቹ የተደረገው አጠቃላይ የገንዘብ ክፍፍልና ቀመር እኩል ዕውቅና ላላቸው፣ ፓርቲው ባቀረበው አጠቃላይ ዕጩ ብዛት፣ የሴት ዕጩ ብዛት፣ የአካል ጉዳተኛ ዕጩ ብዛትና ፓርቲው ባለው የሴት ሥራ አስፈጻሚዎች ብዛት መሥፈርቶች መሆኑን በመረጃው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጡት መሥፈርቶች አማካይነት በሠራው የማከፋፈያ ቀመር መሠረት ብልፅግና ፓርቲ (ብልፅግና) ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ በማግኘት ከፍተኛውን ድጋፍ ሲያገኝ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ከ10.8 ሚሊዮን ብር በላይ በማግኘት ሁለተኛውን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘ ፓርቲ ሆኗል፡፡ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ፣ እናት ፓርቲ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ሲያገኙ፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች ከ2.7 ሚሊዮን ብር እስከ 70 ሺሕ ብር የሚደርስ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡
ቦርዱ ከመንግሥት የተገኘውን የድጋፍ ገንዘብ በሁለት ዙር ያከፋፈለ ሲሆን፣ ድጋፉ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለሚያወጡት ወጪ የሚውል ነው፡፡ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚደረግ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዕጩዎች ምዝገባና በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አለመጠበቅ ሳቢያ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ከአሁን ቀደም ለሪፖርተር ያስታወቁ ቢሆንም፣ ቦርዱ ግን ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ታውቋል፡፡ ለዚህም ቦርዱ በራሱ ያለበትን የገንዘብ እጥረት በምክንያትነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለተራዘመው ምርጫ የተለያዩ ወጪዎች መሸፈኛ እንዲሆን ቦርዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1.1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መጠየቁም ይታወሳል፡፡