Tuesday, July 23, 2024

የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት የሴራ ፖለቲካ ሰለባ አይሁን!

በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት በመተማመን ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም መንግሥት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው የግልጽነት መጥፋት ነው፡፡ ግልጽነት ሲጠፋ መተማመን አይኖርም፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሲኖርበት ለሴራ ፖለቲካ ሥፍራ አይኖርም፡፡ በዚህ መሠረት መራመድ ሲቻል መግባባት አያቅትም፡፡ አገር የፀና መሠረት ሊኖራት የሚችለው የአገረ መንግሥት ግንባታው (Nation Building) በተሳካ መንገድ መከናወን ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ ደግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ያማከለ ሲሆን፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሕግ የበላይነት ነው፡፡ ሕግ ሲከበር ደግሞ ሕዝብና መንግሥት በሥርዓት ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ አሁን እያስቸገረ ያለው የፓርቲና የመንግሥት ሚና መደበላለቅ ነው፡፡ በዚህ መሀል የተለየ ዓላማና ፍላጎት የሚወክሉ ኃይሎች ሕገወጥነትን ያበረታታሉ፣ ማናለብኝነት ይንሰራፋል፣ መብትና ነፃነት ይደፈጠጣሉ፣ በሥልጣን መባለግ ነውር መሆኑ ቀርቶ ዝርፊያ ይስፋፋል፣ ለሥርዓተ አልበኝነት መበራከት በር የሚከፍተው የሴራ ፖለቲካ የበላይነቱን ይይዛል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ እየሆኑ አገር የአጥፊዎች መጫወቻ ትሆናለች፡፡

አገሪቱን በሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት መካከል መከባበር ከሌለ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ውስጥ ባሉ የተለያዩ መዋቅሮች መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት በሕግ የተገደበ ከመሆኑ አንፃር፣ በግለሰብ ኃላፊዎች መካከል ያለው ግንኙነት ሕግን ብቻ የተከተለ መሆን አለበት፡፡ አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽ መሆንና ተጠያቂነትን ጭምር ያካተተ ሲሆን፣ ሴረኝነትና ነውረኛ ድርጊቶች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ የሴራ ፖለቲካ የበላይነቱን ሲይዝ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ቅሬታ ይከሰታል፡፡ ይህ ደግሞ የሥልጣን ባለቤት በሆነው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ መጠራጠርና አመኔታ ማጣት ያስከትላል፡፡ ሕዝብ መንግሥት እንደማያከብረውና ሥፍራ እንደማይሰጠው እንዲሰማው ያደርጋል፡፡ ሊኖር የሚገባውን በጎ ግንኙነት እያበላሸ ለሁከትና ለትርምስ በር ይከፍታል፡፡ የውጭ ኃይሎች በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገቡ ያሉት በፖለቲካው ጎራ ውስጥ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈል ስለበዛ ነው፡፡ አንድነት ሲገዘገዝ አገር የጠላት ቀላል ዒላማ ትሆናለች፡፡ የሴራ ፖለቲካ ውጤቱ ይኼ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ብልፅግናም ሆነ የሚመራው መንግሥት ከበፊቱ ኢሕአዴግ ስብስብ የሚለዩበትን ተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ ሕዝብ ደኅንነቴ እያሳሰበኝ ነው፣ የአገሪቱ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ ነው፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሚያስቆም ጠፋ፣ በአጠቃላይ ለመጪው ትውልድ የምናስረክባት አገር ህልውና ጉዳይ ያሳስበናል እያለ ነው፡፡ ሕዝብ የሚያቀርበው ጥያቄ ሌላ የመንግሥት ምላሽ ሌላ እየሆነ መደናገር በዝቷል፡፡ ሕዝብ ሕመሜ ይኼ ነው ብሎ በግልጽ ሲያቀርብ ለሕመሙ መፈወሻ ተብሎ የሚቀርበው መድኃኒት በፍፁም አልገናኝ ብሏል፡፡ መንግሥት ከበፊት ጀምሮ በሚታወቅበት የመሸፋፈን ጎጂ ልማድ አማካይነት በርካታ ነገሮች እየተድበሰበሱ እየታለፉ፣ ጊዜያቸው ደርሶ ሲፈነዱ ለአገር መከራ እየሆኑ ነው፡፡ ሴረኞች የፖለቲካ ምኅዳሩን ላልተገባ ዓላማ ሲጠቀሙበት፣ ሕዝብ በገዛ ጉዳዩ ባይተዋር ተደርጎ የተናቀ ይመስለዋል፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች ጥቃቶች እየተፈጸሙ በማንነቱ ምክንያት ብቻ ሲገደልና ሲፈናቀል፣ የሴራ ፖለቲካውን ጥልቀት ያመላክታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያለው ትውልድ ቀደም ባሉት ዓመታት ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ሥልቶች የሚታለል አይደለም፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባፈራቸው መሣሪያዎች አማካይነት በቀላሉ መረጃዎችን ያገኛል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በተለያዩ ይዘቶችና ቅርፆች ስለሚደርሱትና የተለያዩ ትንታኔዎችን ስለሚያገኝ፣ ለተለመደው ፕሮፓጋንዳ የመጋለጥ ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ትውልድና የአሁኑ እየተለያዩ ያሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን ግልጽነትን የተላበሰ አሠራር አለማስፈን ከትውልዱ ጋር ከማጋጨት ባለፈ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት የበለጠ ይጨምረዋል፡፡ ሕዝብ መንግሥትን ማመን አቅቶት ሌሎች አማራጮችን መመልከት ሲጀምር ችግሩ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ብልፅግና እንደ ገዥ ፓርቲነቱና አገርን እንደ መምራቱ ይህንን በሚገባ ማመን አለበት፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የአንድ ጎራ የበላይነትን ሳይሆን ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ የሚቀበል በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ይህ መርህ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ ሕዝብን ከሴራ ፖለቲካ ማላቀቅ አለበት፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አክብሮ እነሱ የሚስተናገዱበትን ምኅዳር ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካው ምኅዳር በመከባበር የሚስተናገዱበት ካልሆነ ሕዝብን ያስኮርፋል፡፡መጪውን ምርጫ ሒደት አሳምሮ የሕዝቡን ይሁንታ ለማግኘት በሁሉም መስኮች ግልጽ አሠራር ያስፈልጋል፡፡ የሴራ ፖለቲካ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ይህ ጨዋ ሕዝብ ቢታደል ኖሮ የሥልጣኑ ባለቤት እሱ ነበር፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ በስመ አውቅልሃለሁ እየተሸነገለ ፍላጎቱ ሊፈጸም ባለመቻሉ ላለፉት ዓመታት አገሪቱ ነውጥ ውስጥ ናት፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ያነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ ያገኙ የነበሩት በትክክል መነጋገርና መወሰን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ጥያቄዎች አቅጣጫቸውን እየሳቱ ለብሔር ግጭት ሲዳርጉ፣ ንፁኃን እንደ ቅጠል ሲረግፉ፣ የአገሪቱ አንጡራ ሀብት ሲወድም፣ ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚሉ ሥጋቶች በየቦታው ሲሰሙ፣ በአንድ ወቅት የአንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ተምሳሌት የነበረች አገር ላይ የጥፋት ደመና ሲያንዣብብ፣ ወዘተ. ቆም ብሎ ማሰብ ማንን ይጎዳል? የመንግሥት ዋነኛው ሥራሕዝብን ደኅንነት ማስከበርና ፍላጎቱን መፈጸም ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ለምን ያቅታል? ችግሮችን እየሸፋፈኑ በመጡበት መንገድ መቀጠል አላዋጣ ሲል፣ ለዘመኑ የሚመጥን አሠራር ማስፈን ተመራጭ ነው፡፡ ይህ ነው ለሕዝብና ለአገር የሚበጀው፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽነት የጎደላቸው መንግሥታት እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡ በሕዝባቸው ዘንድም ተቀባይነት አጥተዋል፡፡ ሕዝብ መንግሥት አላከበረኝም ብሎ ሲያስብ አምርሮ ይጠላዋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን የመረረ ስሜት ማስተካከል የሚቻለው ግልጽነትን በማስፈን ለአገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት መጣል ሲጀመር ነው፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ዜጋም ጥያቄ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሕዝብ ይህንን በተግባር መመልከት ሲጀምርና የተሳትፎ መጠኑ ሲጨምር መረጋጋት ይገኛል፡፡ የውይይት ባህሎች እየዳበሩ በነፃነት መነጋገር ይለመዳል፡፡ ይህ መልካም የፖለቲካ ባህል ወደ ጎን ተገፍቶ መከፋፈል ሲፈጠር ግን የውጭ ኃይሎች የሚፈልጉትን ዓላማ በቀላሉ ለማስፈጸም እጅ መጠምዘዝ ይጀምራሉ፡፡ የሴራ ፖለቲካ ለአገር ጠንቅ ነው፡፡

ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ የሚገነባ ሥርዓት ባይሆንም፣ ሒደቱ በሕዝብ ባለቤትነት እየተመራ መስመር እንዲይዝ ጥርጊያው ይመቻቻል፡፡ ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ተቀባይነት እያጡ፣ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ተግባራዊ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ መከባበርና መተባበር ብሔራዊ ዓርማ ይሆናሉ፡፡ ለግጭትና ለሁከት ክፍተት ስለማይፈጠር የሰላም አየር ይነፍሳል፡፡ ኩሩዎቹና አስተዋዮቹ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት መከባበር በሚባለው የጋራ ማኅበራዊ እሴታቸው ነው፡፡ አንዱ የሌላውን ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤና የመሳሰሉትን እያከበረ ከመኖርም በላይ ተጋብቶ የተዋለደው መከባበር በሚባለው ትልቁ እሴቱ ነው፡፡ ይህ እሴት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ተፋቅረውና ተሳስበው እንዲኖሩ ረድቷቸዋል፡፡ ለዘመናት ወራሪዎችን በጀግንነት እያሳፈሩ የዘለቁትም በዚህ ፅኑ እሴት ነው፡፡ አገር የሚመሩ ሰዎች በየደረጃው ባሉ ሹማምንት ካልተከበሩ፣ የጦር መሪዎች እንደ ማዕረጋቸው ደረጃ ኖር ካልተባሉ፣ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች ማግኘት የሚገባቸውን ክብር ከተነፈጉ፣ ዜጎችም እርስ በርሳቸው ካልተዋደዱና ካልተከባበሩ አዲሱ ትውልድ ምን ይወርሳል? በተለይ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ባሉበት በዚህ ከባድና ውስብስብ ጊዜ አገርን ከውጭ ጣልቃ ገብነት መታደግ የሚቻለው፣መከባበርና ለመተባበር ትልቅ ሥፍራ ሲሰጥ ነው፡፡ በአጉል ዕብሪት ውስጥ ተጀቡኖ መናናቅ የጠላት መሣሪያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝብን አለማክበር አገርን ለጠላት ማጋለጥ ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካ ይብቃ፡፡ የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነትም የሴራ ፖለቲካ ሰለባ አይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...