ለመኖሪያ ቤቶች የረዥም ጊዜ ብድር የሚሰጥና ‹‹ሰላም የቤቶች ብድር ባንክ›› የተሰኘ ባንክ ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡
ባንኩ ምሥረታውን በይፋ ባበሰረ በአምስት ወራት ውስጥ በሁለት ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ሥራውን መጀመር እንደሚችል የባንኩ መሥራቾች ጠቁመው፣ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሰ የሚመሠረቱ ባንኮች በአምስት ዓመታት ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንደኖራቸው ቢያስገድድም፣ ሰላም የቤቶች ብድር ባንክ ግን በሁለት ዓመታት ውስጥ የተባለውን ካፒታል እንደሚያሳድግ ተናግረዋል፡፡
ባንኩን ለመመሥረት ዓይነተኛ (ዋና) ምክንያታቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአሥር ዓመታት በላይ ያስመዘገበው ፈጣን ዕድገት በቀጣይም አሥር ዓመታት እንደሚቀጥልና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት 10.2 በመቶ መሆኑ እንደሆነ መሥራቾቹ ገልጸዋል፡፡
አገራዊ ዕድገቱን ተከትሎ የነፍስ ወከፍ ገቢ አሁን ላይ ካለው 1,000 ዶላር በ2030 ወደ 2,220 ዶላር እንደሚደርስ ግምታቸውን የገለጹት መሥራቾቹ፣ ጎን ለጎን የሕዝብ ዕድገት እንደሚቀጥልና በ2012 የሚገመተው 117 ሚሊዮን በ2035 181 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የተለያዩ ትንበያዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በአንድ በኩል የገጠር መሬት ይዞታ እየቀነሰ ስለሚቀጥልና የከተሞችም ነዋሪዎች ቁጥር 4.9 በመቶ እንደሚያድግ ስለሚገመት፣ በተጠቀሱት ተደጋጋፊ ምክንያቶች በየዓመቱ 400,000 የሚህሉ መኖሪያ ቤቶች ፍላጎት እንደሚጨምር ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ሌላ ለበርካታ ዓመታት ሲከማች የመጣ ሁለት ሚሊዮን ቤት ፈላጊ እንዳለ አስታውሰው፣ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ችግሮቹን ለመፍታት ሊከወን የሚገባው ትልቅ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊተገበር እንደሚገባና ጠንክሮ ከተሠራ የሀብት ዕድገት ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ገልጸዋል፡፡
በመኖሪያ ቤቶች ብድር ባንክ ላይ ለሚሠራ ባንክ ብቻ ከውጭ ባንኮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል አሠራር በሥራ ላይ ለማዋል በመንግሥት የተገለጸው አቋም፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ዋስትናዎች ልውውጥ ሥራ ላይ የሚውልበት ዕድል እየመጣ መሆኑ፣ ለእነሱ (ለመሥራቾች) አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡
ሰላም የመኖሪያ ቤት ብድር ባንክ ነባራዊ ሁኔታዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት፣ ለመኖሪያ ቤቶች እስከ 15 በመቶ ዝቅ ባለ ቅድሚያ ክፍያ ፍላጎትን የሚያሟላና እስከ 30 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ የሚከፈል ብድር ለሁሉም ዜጎች የፋይናንስ አቅርቦት ለማዘጋጀት ማቀዱን ገልጿል፡፡
የፋይናንስ ችግርን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት፣ ቤት ገዥዎች የሚቆጥቡት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባለድርሻ የሆኑ ሌሎች ቤት አልሚዎችን ጨምሮ የግሉ ዘርፍ፣ የመንግሥት አካላት፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይናንስና መሰል ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
ከመሥራቾቹ መካከል አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የሶል ሬብልስ የጫማ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤት ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁን፣ የባማኮን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ግርማ ገላው፣ አቶ ቴዎድሮስ ይልማና ሌሎችም በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል በተደረገው የምሥረታ ማስተዋወቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል፡፡ ሰላም የቤቶች ብድር ባንክ ከጎህ የቤቶች ባንክ ቀጥሎ ተመሠረተ ሁለተኛው ባንክ ነው፡፡