Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ያስገኛቸው ለውጦችና ተግዳሮቶቹ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ያስገኛቸው ለውጦችና ተግዳሮቶቹ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የመንግሥትን ቋት በመጠበቅ ለዓመታት ተጉዟል፡፡ ከነበረበትም ፈቅ አላለም፡፡ ብዙዎች እንዲያውም የነበረውን እያጣ የጭቅጭቅና ውዝግብ መድረክ ከመሆን፣ አለፍ ሲልም ለሕይወትና ለንብረት ውድመት መንስዔ ሲሆን የታየባቸው ዓመታት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዓምና የጀመሩት እንቅስቃሴ ያውም ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግራ በተጋባበት ወቅት፣ ሊጉን በአክሲዮን በማደራጀት የሄዱበት መንገድ የተስፋ ብልጭታን እንዲያዩ አድርጓል፡፡ ክለቦች ከሚዲያ መብት ጥቅም ማግኘት ጀምረዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠር በጀት እየመደቡ ዋንጫ ከፍ የሚያደርጉ ቡድኖች በሽልማት መልክ ይደርሳቸው የነበረው ከ150,000 እስከ 200,000 ብር ነበር፡፡ አሁን ግን የሚወርዱ ቡድኖችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ የሚያገኙበት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ውድድሩ ቀጥታ ሽፋን ስላለው የእያንዳንዱ ተጫዋችና ክለብ እንዲሁም አመራር ግለ ታሪክ ምን እንደሚመስል በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት አሠራር ተፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ ፕሪሚየር ሊጉ በሼር ካምፓኒው አማካይነት እንዲተዳደር መደረጉ ለእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን ተመልካች ያልነበራቸው ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች የግል ጥረታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሚታዩበት ሰፊ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በር ተከፍቷል፡፡ በአምስት የተለያዩ ከተሞች ሲካሄድ የቆየው የውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡ የሊጉ አክሲዮን ማኅበር እንዲህ ዓይነት ውድድሮች ሲያስተዳድር የመጀመርያው እንደመሆኑ ምን ጠንካራ ጎን ነበረው? ተግዳሮቶቹስ? በሚለው ወቅታዊ ጉዳይ የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በሱፐር ስፖርት አማካይነት ቀጥታ ሽፋን የነበረውን ውድድር መርቶ አጠናቋል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ የኋላ ታሪክ ከተጫዋቾችና አመራሮች ባህርይ ጀምሮ በብዙ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ዘንድሮ የነበረውን ሁኔታ እንዴት መግለጽ ይቻላል?

አቶ ክፍሌ፡- የ2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሊግ በይዘትም በአካሄድም በብዙ መልኩ ለየት ያደርገዋል፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአክሲዮን ማኅበር ተዋቅሮ ሥራ ለመጀመር ከጫፍ በደረሰበት፣ በመጀመርያው ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት የተቋረጠበት ዓመት መሆኑ፣ ክስተቱ ለአክሲዮን ማኅበሩ ፈታኝ ቢሆንም፣ ተስፋ ባለመቁረጥ ለቀጣዩ የ2013 ዓ.ም. ውድድር ዓመት ሊግ ካምፓኒው አዲስ እንደመሆኑ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ታሳቢ አድርጓል፡፡ ይህም የኮቪዱ ፕሮቶኮል ጉዳይና ውድድሩን በቴሌቪዥን ቀጥታ ሥርጭት እንዲኖረው (ብሮድካስት) ለማድረግ ከሱፐር ስፖርት ጋር ውል መፈራረም የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ሒደት በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት የነበሩት ፈተናዎች እንዲህ በቀላሉ ተነግረው የሚያበቁ አልነበሩም፡፡ አንደኛውና የመጀመርያው በኮቪድ ፕሮቶኮል መሠረት ስታዲየሞችን መምረጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተመልካቾች ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የኮቪድ ፕሮቶኮሉን ሥራ በሚመለከት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሠሩት ሥራ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ እንደሚታወቀው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሠራው ሁሉንም ውድድሮች ታሳቢ በማድረግ ሲሆን ሊግ ካምፓኒው ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉን በሚመለከት ሰነዱን ከሁለቱ ተቋማት በመውሰድ የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁሉም እንደሚያውቀው በዓመት ውስጥ ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ማመንጨት የሚችል ደጋፊ ያላቸው ክለቦች ስላሉ ያንን የሚያካክስ ሥራና ዕቅድ ማቀድን ስለሚጠይቅና ምን ይደረግ ለሚለው የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤትና ውድድሩን የሚመራው አካል እያንዳንዱን ወጪና ገቢ ግልጽ በማድረግ ካጠና በኋላ የጥናቱን ውጤት ለክለቦቹ ማቅረብ ስለነበረብን ያንን አድርገናል፡፡ በውሳኔው መሠረት እያንዳንዱ ክለብ ለዳኝነትና ለኮቪድ ፕሮቶኮልና ለተጫዋቾች ምርመራ በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ አቅጣጫ እንዲቀመጥለት ተደርጎ፣  ክለቦቹም መወዳደር እንችላለን የሚል ሐሳብ ላይ እንዲደርሱ ካደረገ በኋላ፣ ውድድሮቹ በስድስት ስታዲየሞች እንዲካሄዱ ተወሰነ፡፡ በአጋጣሚ የመቐለ ስታዲየም በፀጥታ ችግር ሲቀር በሌሎቹ ውድድሮች እንዲከናወኑ ተደርጓል፡፡ የሚገርመው ከተመረጡት የሐዋሳና የድሬዳዋ ስታዲየሞች ዝግጁ ስላልነበሩ ቅድሚያ ለአዲስ አበባ፣ ለጅማና ለባህር ዳር ስታዲየሞች ተሰጥቶ ሁለቱ እስከዚያ ዕድሳት እንዲደረግላቸው በሚል ስምምነት ላይ ተደርሶ ነው የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመርያው ዙር ውድድር እንዲያስተናግድ የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- ውድድሩ ቀደም ሲል እንደተገለጸው በሱፐር ስፖርት አማካይነት ቀጥታ ሽፋን ያለው መሆኑ ሲታወቅ የስታዲየም ምርጫ ላይ ለኮታዊ አሠራር ቅድሚያ ተሰጥቷል የሚል ቅሬታ ሲቀርብ ነበር፡፡ ሊግ ካምፓኒው ዕውን ስታዲየም ምርጫ ላይ መሥፈርት ነበረው?

አቶ ክፍሌ፡- ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ውድድሮች እንዲደረጉ ፕሮግራም ተይዞ የነበረው በስድስት ስታዲየሞች ነው፡፡ የመቐለ ስታዲየም በፀጥታ ችግር ምክንያት ማስተናገድ አልቻለም፡፡ ውድድሩ በአምስቱ ስታዲየሞች ከመጀመሩ በፊት ስታዲየሞቹን መገምገም ያስፈልግ ስለነበረ እንደተባለው የድሬዳዋና የሐዋሳ ስታዲየም በወቅቱ ዝግጁ አልነበሩም፡፡ ይህ ማለት ግን የስታዲየም ምርጫው ላይ ችግር ስላለበት ሳይሆን ጨዋታዎቹን ብሮድካስት ያደረገው ሱፐር ስፖርት ለቀጥታ ሥርጭት የሚያስፈልገው ቅድመ ሁኔታ የሥርጭቱን ጥራት ከመጠበቅ አኳያ እንዲስተካከል ከመመኘት ነው፡፡ ስለሆነም ውድድሩ ብሮድካስት በሚደረግበት ወቅት ክለቦች ማሟላት የሚገባቸው ከዲሲፕሊን ጀምሮ ኮታዊ  የሚባለው ነገር ፍፁም ከእውነታው የራቀ ነው፡፡ ምክንያቱም የቀጥታ ሥርጭቱ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ከመገንባት አኳያም የራሱ የሆነ ነገር ስለሚኖረው በሚል ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ ሌላው ውድድሩ ሲደረግ ሼር ካምፓኒው የስታዲየሙን ጥራት ከመጠበቅም ባሻገር ለባለ ሜዳዎቹ ከተሞች ድጋፍ በማድረግ ጭምር ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ከተማ የጎል መረብ ከመስቀል፣ መስመር ከማስመር ጀምሮ ታች ወርዶ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ውሳኔ በሚፈልጉ በእያንዳንዱ ጉዳይ ሳይቀር በመግባት ክፍተቶችን ለመድፈን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ያህል የእያንዳንዱ ሳምንት ጨዋታ ሲጠናቀቅ የቀጣዩ ሳምንት ኮሙዩኒኬሽን ጊዜውንና ሰዓቱን ጠብቆ ውሳኔዎችን ጨምር ለክለቦች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በሒደቱ በተግዳሮትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ አጋጣሚዎች ካሉ ቢገልጹልን?

አቶ ክፍሌ፡- ውድድሩ ከኮቪድ-19 ጋር መገናኘቱ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ ጅምር ግን በሒደቱ ከገጠሙን ተግዳሮቶች ጠንካራ ጎኑ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ ይህ ማለት ችግሮች አልገጠሙንም ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ጨዋታ ከመካሄዱ በፊት እያንዳንዱ ክለብ ዳኛና አመራሮች ጭምር በየ72 ሰዓቱ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት እንዲያቀርቡ በማድረጉ ረገድ የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ዲሲፕሊንና ውድድር በሰዓቱ የመጀመር ችግር ቀደም ባሉት ዓመታት ከፍተኛ ክፍተት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ችግሩ እንዲቀረፍ ተደርጓል፡፡ በተግዳሮትነት ማንሳት ካለብን ልናነሳ የምንችለው ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በተለይ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች የኮቪድን ፕሮቶኮል ያከብራሉ ተብሎ የታመነባቸው ጥቂት ደጋፊዎች ሜዳ ገብተው ቡድናቸውን እንዲያበረታቱ ስምምነት ቢደረስም፣ ነገር ግን የሚደግፉት ቡድን ጎል በሚያስቆጥርበት ወቅት መሰባሰባቸው በተለይ ድሬዳዋ ላይ የኮቪድ-19 ሥርጭቱም ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ ደጋፊዎች እንዳይገቡ ውሳኔ ላይ መድረሱ ካልሆነ ይህ ነው የሚባል የጎላ ችግር ሳይገጥመን ነው ውድድሩን ያጠናቀቅነው፡፡ በእርግጥ ድሬዳዋ ላይ የገጠመን የኮቪድ-19 ሥርጭት ውድድሩን እስከ ማቋረጥ ሊደርስ የሚችል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የውድድር አዘጋጆችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከ28 የእግር ኳስ ዳኞች 18 ያህል ዳኞች በኮቪድ-19 የተጠቁበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ተጫዋቾች በችግሩ በከፍተኛ ደረጃ ከመጠቃታቸው የተነሳ በረኞች ተጫዋች ሆነው ውድድር ያደረጉበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡ ይሁንና ይህ ሁሉ ሆኖ አንድም ውድድር በችግሩ ምክንያት ሳይሸራረፍ በተያዘለት ፕሮግራም እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ውድድሩን በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላፍ ውል የተዋዋለው ሱፐር ስፖርት ሳይቀር ለሊግ ካምፓኒው አድናቆቱን ሰጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ውድድሩ ቀጥታ ሥርጭት በማግኘቱ የተማራችሁትና ያገኛችሁት ተሞክሮ  እንዴት ይገለጻል?

አቶ ክፍሌ፡- በዋናነት የጊዜና የሰዓት ጥቅም ምን እንደሆነ ተምረንበታል፡፡ እያንዳንዱ ክለብ የቡድን አመራር ውድድር ከመጀመሩ ከሁለት ሰዓት በፊት መድረስ ግድ ነበር፡፡ ይህም ክለቦቻችን ግንዛቤው ካላቸው ወደ መስመር ለመግባት ምንም ችግር እንደሌለባቸው ነው መረዳት የቻልነው፡፡ እያንዳንዱ ሒደት በግምገማ የተደረሰበትን ነው፡፡ ሌላው ውድድሮች እንደ ቀድሞ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመንቀሳቀስ ሲጠፋ የነበረውን ጊዜ በንድ በተወሰነ ቦታ ማድረግ ከጊዜና ከፋይናንስ አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጥታ ሽፋን አሰጣጡ ጭምር ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ተምረንበታል፡፡ እዚህ ላይ እንደ ችግር ሳልገልጽ የማላልፈው ደረጃቸውን የጠበቁ በተለይ ለቀጥታ ሥርጭት የሚመች በቂ ስታዲየሞች የሉንም፡፡ አለን ብለን መናገር የምንችለው ስታዲየም ሳይሆን ለስታዲየም ተብሎ የተጀመረ ግንብ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ስፖርተኞች የሚለብሱት መለያ ላይ እንደዚሁ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ ክለቦች ለቀጥታ ሥርጭት የሚያመች ወጥና ስታንዳርዱን የጠበቀ መለያ የላቸውም፡፡ ይህም ለሊጉ ጥራትም ሆነ ለልጆቹ ማርኬት መታረም እንዳለበት ተማምነናል፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒው የራሱ የሆነ ሎጎ ቢኖረውም ሥርጭት ላይ እንዲታይ አለመደረጉ ይጠቀሳል፡፡ ሱፐር ስፖርት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ጋር ውል ሲያደርግ ሥልጠናና መሰል ድጋፎችን በተጨማሪነት ለመስጠት ስምምነት ነበረው፡፡ ይሁንና በኮቪድ-19 ምክንያት ውሉ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በቀጣይ ግን እነዚህን በማሟላት ሥራውን መጀመር እንዳለበት ከሱፐር ስፖርት ጋር ተማምነናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሽልማትና ከሚዲያ መብት ጋር በተገናኘ ክለቦች ሊያገኙት የሚችለውን ጥቅም ዓይነትና መጠን ቢነግሩን?

አቶ ክፍሌ፡- ሽልማትና የሚዲያ መብትን በተመለከተ የዚህ ዓመቱ በዓይነትም ሆነ በይዘት ካለፉት ዓመታት በጣም ይለያል፡፡ ከስፖንሰር አድራጊ ድርጅቱ ከሚገኘው ገንዘብ 25 በመቶ ለሽልማት (ሜሪት)፣ ይህ ማለት ክለቦቹ ዓመቱን ሙሉ ተወዳድረው በሚያገኙት ደረጃ መሠረት በሽልማት መልክ የሚከፈላቸው ይሆናል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ዋንጫ ያገኘ ቡድን ሽልማቱ 350 ሺሕ ብር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ዓመት ግን ከአንደኛ እስከ 13ኛ ያሉት ቡድኖች ለምሳሌ የዋንጫ አሸናፊ የሆነው ፋሲል ከነማ 3.794,000 ብር በሽልማት መልክ ከሚያገኘው በተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ቡድን በሽልማት መልክ 3.617 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ በመሆኑ ተጨማሪ፣ 700 ሺሕ ብር፣ ሦስተኛው ቡድን 3.4 ሚሊዮን የነሐስ ተሸላሚ በመሆኑ፣ 350 ሺሕ ብር እያለ፣ ከደረጃ ውጪ ሆነው ለሚያጠናቅቁት አራተኛው 3.2 ሚሊዮን፣ አምስተኛው 3 ሚሊዮን፣ ስድስተኛው 2.9 ሚሊዮን፣ ሰባተኛው 2.7 ሚሊዮን፣ ስምንተኛው 2.5 ሚሊዮን፣ ዘጠነኛው 2.2 ሚሊዮን፣ አሥረኛው 2.1 ሚሊዮን፣ 11ኛው 2 ሚሊዮን፣ 12ኛው 1.8 ሚለዮን፣ 13ኛው 1.6 ሚሊዮን ከሽልማት ብቻ ሲያገኙ፣ ከሚዲያ መብት ደግሞ የመጀመርያ 50 በመቶ ከተከፈለው ክፍያ ውስጥ ክለቦች የነበረባቸው ዕዳ ተቀናንሶ እያንዳንዱ ክለብ በትንሹ ያገኘው ክፍያ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ሁለተኛውና ቀሪው 50 በመቶ ክፍያም ተከፍሎናል፡፡ እያንዳንዱ ክለብ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ይህም ወራጁ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ ነው የሚወርደው፡፡ ሼር ካምፓኒው እንዲቋቋም ምክንያት የሆነው ክለቦች የራሳቸውን ውድድር ራሳቸው እየመሩ በዚያው መጠን ገቢ እንዲያገኙ ከማሰብ ነው፡፡ እንዲታወቅ የምንፈልገው ሼር ካምፓኒው ከሚያገኘው 85 በመቶ ክፍያ የክለቦች ነው፡፡ በዚያ ላይ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ ዳኛና ኮከብ አሠልጣኝ እንደዚሁ እስከ 210 ሺሕ ብር የሚደርስ ሽልማት የሚከፈላቸው ይሆናል፡፡ ክለቦቻችን በዚህ ዓመት አልተጠቀሙበትም እንጂ ቢጠቀሙበት ኖሮ ባለ ሜዳ ቡድን እስከ ስምንት የሚደርሱ የስፖንሰሮችን ሎጎ በሜዳው ዳር ዳር በማስቀመጥ ገቢ ማግኘት የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው፡፡ በእርግጥ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ሌሎች አንዳንድ ክለቦች የሠሩ አሉ፡፡ ወደፊት ገቢው በጨመረ መጠን ክፍያውም በዚያው ልክ የሚያድግ ነው የሚሆነው፡፡ በመጨረሻም እያንዳንዱ ክለብ በውድድር ዓመቱ ሽልማትና ከሚዲያ መብት የሚከፈለው ተጠቃሎ ሰኞ በሸራተን አዲስ በሚኖረው የዕውቅና ዝግጅት ላይ የሚገለጽ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ከስታዲየም ስታንዳርድና ከዳኝነት ጋር በተገናኘ ምን የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ክፍሌ፡- የ2013 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ብዙ ነገር አስተምሮናል፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአገራችን ስታዲየም ተብሎ በጣም ብዙ የተገነቡ ግንቦች አሉ፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች ግን የሉንም፡፡ በቀጣይ ዓመት በትልቁ ልንሠራበት ከሚገባን ሥራ አንዱና መሠረታዊው የስታዲየም ስታንዳርድ ጉዳይ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ከዘንድሮ በተሻለ ለማድረግ ነው የምናስበው፡፡ ስለዚህ ስታዲየም መረጣ ላይ ልዩ ጥንቃቄ እናደርጋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በግሉ ሜዳ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ የሚገርመው የአዲስ አበባ ስታዲየም 48 ጨዋታ ሲያደርግ ድሬዳዋን ጨምሮ የተቀሩት 30 ጨዋታ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ጫና የነበረባቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የድሬዳዋ ስታዲየም በጫናው ምክንያት ጭቃ ቢሆንም በመብራት ደግሞ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ ሆኖ ነው የምሽት ጨዋታዎች ሲያደርጉበት ነበር፡፡ በቀጣይ ዓመት እያንዳንዱ ስታዲየም መብራት ሊኖረው እንደሚገባ ከሱፐር ስፖርት ጭምር አስተያየት ደርሶናል፡፡ ሌላው በሚቀጥለው ዓመት እንዲሻሻል የምንፈልገው ክለቦች ከተጨዋቾች የደመወዝ ክፍያ ጋር ያላቸውን አለመግባባት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ ዘንድሮ ትልቁ ክፍተታችን ነበር፡፡ ከዳኝነት ጋር በተገናኘም እንደዚሁ የምንሠራቸው ሥራዎች እንዳሉ ተመልክተናል፡፡ የ156 ጨዋታ ሙሉ ፊልም በእጃችን ይገኛል፡፡ ያንን በመጠቀም ጭምር የሙያ ማሻሻያ የምንሰጥ ይሆናል፡፡                        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...