በጀሪን ኑበሌሱፊ
ከሰሞኑ የብሔራዊ ባንክ እከሌ ባንክን ጋራንቲ እንዳይሰጥ አገደ፣ እነ እከሌን ደግሞ የኢምፖርት ፈቃድ እንዳይሰጡ፣ ሌላውን ደግሞ የትርፍ ክፍፍል እንዳያደርግ ከለከለ የሚሉ ዜናዎችና እነሱን ተከትሎ የሚሰጡ አስተያየቶች በርከት ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ጉዳዮች በከረሙ አገራዊና ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት ቢከሰቱምና የማስተካከያ መፍትሔ ቢያሻቸውም፣ እንደሚጎፈላ ጎረምሳ ጀብዱን በአደባባይ ማሰማቱ ተቀባይነት ያለው አይመስለኝም፡፡ በተለይ የፋይናንስ ሥርዓቱን ሊጎዱ የሚችሉ ወሬዎችን በሚስጥር በመያዝ፣ ችግሮችም ካሉ ከባንኮች የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ጋር ጥብቅ ውይይት አድርጎ መፍትሔ ማፈላለግ የተቆጣጣሪው አካል ኃላፊነት ነው፡፡
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን፣ በብሔራዊ ባንክ የሚሰጣቸው ደረጃ (Camel Rating) ለሕዝቡ ይፋ አይደረጉም፡፡ ይኼም የፋይናንስ ተቋማት በእዚህ ረገድ ችግርም ቢያጋጥማቸው በየወቅቱ ክትትል ተደርጎ ማረም ስለሚቻል፣ እንዲሁም እነዚህ መረጃዎች ይፋ ቢደረጉም በባንኮች ተዓማኒነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ ጭምር ነው፡፡ ሴክተሩ ገና ያልጎለመሱ ወጣት ባንኮች፣ ያልጠነከሩ ልጅ ባንኮችና የተረገዙ ግን ያልተወለዱ ባንኮችን ስለያዘ ሁሉንም የመጠበቅ ሥራ የተቆጣጣሪው አካል ነው፡፡
ወጣት ባንኮችን በመምከር፣ ልጆችን መንገድ በመምራት፣ የተፀነሱትን በመንከባከብ፣ ከመንገድ ሲወጡም በመገሰፅ ማስተካከልም ዋነኛ ሥራው ነው፡፡ አሁን አሁን የምንሰማው ጉዳይ ግን በእጅጉ አሳዛኝና ባንኮችን ካጠፉት ጥፉት በላይ ሊጎዱ የሚችሉ ወሬዎች በራሱ በብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናት በሚዲያ ሲበተን ሲታይ፣ አረ ጎበዝ ምን እየተደረገ ነው ያስብላል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የኢምፖርት ፈቃድ አግጃለሁ ብሎ የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናት ሲያውጁ፣ ወዲያውኑ የባንኮች ስም ዝርዝር ከአገር አልፎ ለውጭ ባንኮችና አቅራቢዎች ተበትኗል፡፡ እነዚህ ባንኮች ከተቆጣጣሪው አካል ስለታገዱ አብራችሁ አትሥሩ የሚል መልዕክትም ተላልፏል፡፡
ምንም እንኳ ለሁሉም ባንኮች ክልከላው ወዲያውኑ ቢነሳላቸውም በመጀመርያ የተናፈሰው መጥፎ ወሬ ወይ ማስተካከያ አላገኘ፣ ወይ እርማት አልተወሰደበትም፡፡ ባንኮቹም በጭንቀት ደንበኞቻቸውን ላለማጣት ለማሳመን ከአገር አልፈው ወደ ውጭም ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የትርፍ ክፍፍል ዕድገትንም ብንመለከት ጉዳዩ በተለያዩ ባንኮች ላይ በስፋት የሚታይ ቢሆንም፣ ገና ልጅ የሆነው ባንክ ላይ ዕርምጃ ወስዶ ለሚዲያ ማስተላለፍ የልጅ ባንኩን ዕድገት ለመግታት ወይም የግለሰቦች ጦርነት ያለበት ይመስላል፡፡
እንደምንሰማው ብሔራዊ ባንክ የሚደነግጠው ጥቆማ ሲደርሰው፣ ዕርምጃ ሲወስድ ደግሞ በማናለብኝነት ነው፡፡ አንድ ባንክ የባለአክሲዮኖች ስብሰባውን ሊያካሂድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ለዓመታት የቆዩ ችግሮችን በባንኩ ውስጥ በተከሰተ የቦርድና የማኔጅመንት ፍትጊያ ምክንያት አፈትልከው ሲወጡ፣ ወደ ስሜታዊ ዕርምጃ መግባቱም ዕርምጃውንም ካልሰማችሁልኝ ማለቱም የሚያስተዛዝብ ነው፡። በዕለቱም ከባለአክሲዮኖች በሚኖረው ምላሽ አንዳንድ የቦርድ አባላት ከብሔራዊ ባንክ አመራሮች ጋር ሆነው ባንኩ ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ነው፡፡
እነዚህ በጎሳና በሠፈር የተመሠረቱ ባንኮች በሠፈር አለቆቻቸው ካልሆነ በቀር፣ ከሌላ ሠፈር በመጣ ባለሙያ/ቦርድ አይመሩም የሚል አመፅ ከተሰናባቹ የቦርድ አባላት እንደ ነበር፣ ይህንንም አጀንዳ የሚያራግቡ (የሚደግፉ) ከሠፈሩ የወጡ የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣናትም እንደነበሩ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ባንኮችን የሚጎዱ ዜናዎች የሚናፈሱት ከስህተትም በስተጀርባ ባሉ ፍላጎቶች ምክንያት መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይኸው እኛም አንበላም አንጠጣም ብለን በገዛነው አክሲዮን ሊከፈለን የሚገባውን የትርፍ ድርሻ በጉልበት ተነጥቀን ቁጭ ብለናል፡፡
የፋይናንስ ሪፖርቶች ላይ የሚከሰቱ ስህተቶች የተለመዱና ማስተካከያዎችም ካሉ በሚቀጥለው የፋይናንስ ዓመት መታረም ሲችሉ፣ በማናለብኝ ስሜት የደሃውን ባለአክሲዮን ድርሻ መንፈግ አግባብ አይደለም፡፡ የአካውንቲነግ ሕጎች ይህንን አይከለክሉም፡፡ ታዲያ ዕግድን ምን አመጣው? በዕለቱ ባለአክሲዮኑ በጨዋ ደንብ የባንኩን አመራር ደግፎ ተሠለፈ እንጂ ሊመጣ የሚችለው ቁጣ፣ ለሌላም ባንክና ለመንግሥትም ይተርፍ ነበር፡፡ መንግሥትም ጉዳዩን ጊዜ ሰጥቶ ሊመረምረው ይገባል፡፡ አገራዊ በሆኑ ምክንያቶች አፋኝ ፖሊሲዎችና ብዙ ባንኮችን ያካተቱ ችግሮች፣ ነገር ግን ጥቂት ባንኮች ላይ ያነጣጠረ ዕርምጃ ጉዳይ ምንድነው ሊያስብል ይገባል፡፡ ‹‹ጁንታው አሁንም ከብሔራዊ ባንክ አልወጣም ብለው፤›› እንደተናገሩት ባለአክሲዮን ማለት ነው፡፡
እንግዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደፊት ሊራመድ የሚችለው ጠንካራ የቁጥጥርና አገርን ሊጠቅም የሚችል የፋይናንስ ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይም የሚከሰቱት ችግሮች መንስዔያቸውን መመርመር፣ ሲቻል ድጋፍ ሰጥቶ ከችግር ማላቀቅ፣ ካልሆነም የዕርምት ዕርምጃ ጉዳዩ ሥር ሳይሰድ መውሰድ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ አገራዊ በሆኑ ምክንያቶች እንደ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ መዛባትና የሀብት ችግር ለሚመጡ ጉዳዮች አገራዊ መፍትሔ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ሁሉንም ሥራ እያገዱ፣ ዜናውንም የአደባባይ መነጋገሪያ ማድረጉ ችግሩን ከማባባስና ሌላ ዓላማ ላነገቡ ዓምደኞች መነጋገሪያ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ይልቁንስ በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ተዓማኒነት የሚሸረሽር እንደሆነ የሰሞኑ ዕርምጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለምሳሌ ያህል ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ዕጥረት በተመሳሳይ በናይጄሪያና በሌሎች አገሮች ባንኮች ላይ ተከስቷል፡፡ የእነዚህ አገሮች ተቆጣጣሪ ባንኮች ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል ችለዋል፡፡ በአገራችንም ይኼንን እንኳን ማድረግ ባይቻል አፋኝ የሆኑ ፖሊሲዎችን (ለምሳሌ 30 በመቶ የውጭ ምንዛሪን የመውሰድ) የመቀየር ወይም የማላላት ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ልክ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የቦንድ ግዥ ግዴታን እንዳነሳው ማለት ነው፡፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የውጭ ምንዛሪ ችግር የተባባሰው ከዚህ መመርያ በኋላ አይደለምን? ብሔራዊ ባንክ መንገደኛው ሁሉ ወረፋ ይዞ የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ይሰጠው ሲል አልነበር? ባንኮች አይሆንም ብለው ሲመልሱ ሲቀጣ አልነበር? ራሱ ብሔራዊ ባንክ ለእከሌ ይህን ያህል ዶላር ስጥልኝ ሲልስ አልነበር? ታዲያ የዚህ ሁሉ ውጤት ምንስ ሊያመጣ ነበር? ጎበዝ የተቆጣጣሪው አካላት ሥራ ማገድ ወይም የባንኮችን ሚስጥር መዘርገፍ አይደለም፡፡ የባንኮችን ሚስጥር መጠበቅ፣ ለችግሮቹም ከባንኮቹ ጋር መፍትሔ ማፈላለግም ነው፡፡ እንደምንሰማው ከታገዱት ባንኮች በተጨማሪ የተቀሩት ቢሆኑም፣ ያላቸው የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ ልዩነት የተዛባና መፍትሔ የሚፈልግ ነው፡፡ ይኼም የችግሩን ጥልቀትና ቀጣይነት ማሳያና የዕርምት ዕርምጃም የሚፈልግ ነው፡፡
እንደ ተቆጣጣሪ አካልም ችግሩን ተጋፍጦ መፍትሔ መፈለግ ባንኮችን የመታደግ ሥራ እንጂ፣ ታግደሃል የሚሉ ዕርምጃዎች የትም አያደርሱም፡፡ በተለይ ደግሞ በባንኮች ላይ የሚከሰቱ ችግሮች በውስጥ አሠራርና ሚስጥራዊነትን በጠበቀ በሳል የመፍትሔ ዕርምጃዎች ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ የግለሰብ ዕርምጃዎችን ግለሰቦች ላይ ለመጫን መሞከር ችግሩን የመፍራትና ኃላፊነትን የማሸሽ እንደሆነም ያሳያል፡፡ የባንክ ሚስጥሮችም የባቄላ ወፍጮዎች ሆነው የሚናፈሱ ሳይሆኑ፣ በጥንቃቄ ተይዘው ባንኮቹንም ኢንዱስትሪውንም በሚጠብቁ ሁኔታ ሊፈቱ ይገባል እላለሁ፡፡ ከላይ ከተፈጠረው ችግር ይልቅ ኢንዱስትሪውን የማጠልሸት አካሄድ ነገ መዘዙ የከፋ ነውና የሰሚ ያለህ ያስብላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡