Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ከአገራዊ ምክክሮች የመነጩ ምክረ ሐሳቦችን ሥራ ላይ ለማዋል ፈቃደኝነት ማሳየት ይጠበቅበታል›› አቶ ንጉሡ አክሊሉ፣ የማይንድ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

በ2012 ዓ.ም. ከተለያዩ ከማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡና በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ ሃምሳ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች የተሳተፉበት ምክክር ተካሂዶ በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ የዛሬ 20 ዓመት ሊገጥማት ይችላል ያሏቸውን አራት ዕጣ ፈንታዎች ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ የውይይትና የምክክር ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ግለሰቦች አንዱ፣ የማይንድ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋችነት የሚታወቁት አቶ ንጉሡ አክሊሉ እየተካሄዱ ስላሉ አገራዊ የውይይት መድረኮች አሁናዊ ሒደትና የቀጣይ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አገር እንዲህ ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት ከየቦታው ተሰባስቦ ለአገር አንድ ሥራ እንሥራ ብሎ መነሳት መልካም ጅምር ነው፡፡ እስኪ እርስዎ ወደዚህ ሥራ ለመግባት ምን አነሳሳዎትና በምን ሙያ ላይ እንዳሉም ቢነግሩን?

አቶ ንጉሡ፡- እኔ ለረዥም ጊዜ እዚህ አገር የምታወቀው በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋችነት ነው፡፡ እዚህ አገር በሲቪል ማኅበረሰብና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ብዙ ሥራ ሥሰራ ስለቆየሁ፣ ለረዥም ጊዜ በአካባቢ ተቆርቋሪ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ዓመታት ወደዚህ አገራችን እየሄደችበት ያለው መንገድ ትንሽ እያሠጋኝ ስለመጣ፣ የተወሰኑ ጓደኞቼን አሰባስቤ ዴስትኒ ኢትዮጵያ የሚባል አንድ ውጥን ጀመርን፡፡ በዚህም ዴስትኒ ኢትዮጵያ አራት የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዎች ተብለው የተለዩ ነጥቦችን በ50 የተመረጡ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንዲሠሩ ተደረገ፡፡ እነዚህ አራት ዕጣ ፈንታዎችም ሰባራ ወንበር፣ አፄ በጉልበቱ፣ የፉክክር ቤትና ንጋት የሚባሉ ናቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ንጋት የሚባለው መዳረሻ ከሁሉም የተሻለ ነው በሚል በሁሉም የፓርቲ መሪዎች ተደነገገ፡፡ ታዲያ ንጋት የሚባለው ዕጣ ፈንታ እንዴት ሊመጣ ይችላል ብለን ጠየቅን፡፡ በዚህም አንዱ ንጋት የሚመጣበት መንገድ የጠረጴዛ ዙሪያ አገራዊ ውይይት ሲኖር እንደሆነ ተመለከትን፡፡ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድና በምክክር መፍታት ስንችል ነው ንጋትን ማምጣት የሚቻለው አለበለዚያ ግን በኃይል ለመፍታት ከሞከርን ንጋት የሚባለው ነገር አይመጣም ስለተባለ፣ እኛ ደግሞ ያንን ሐሳብ ከግምት ውስጥ አስገብተን መፍትሔው አገራዊ ምክክር ነው ከተባለ ዴስትኒ ኢትዮጵያ ብቻውን ሊሠራው አይችልም አልን፡፡ ሌሎች እንደዚህ ዓይነት ምክክሮችን የሚሠሩ አካላት እነማን ናቸው ብለን በመፈለግ ከእነሱ ጋር ተነጋግረን አንድ ላይ በመሆን፣ ይህንን ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ኢንሼቲቭ ጠንስሰን ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መሥራት ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ስለኢትዮጵያ ከተተነበዩት አራት ዕጣ ፈንታዎች መካከል ንጋትን ወስዳችሁ መሠራት ከጀመራችሁ ዓመት ሊሞላ ትንሽ ነው የቀረው፡፡ እስካሁን ምን ታዝባችኋል? ንጋትን ለማሳከት እየሄዳቹሁበት ያለው ርቀትስ ምን ይመስላል?

አቶ ንጉሡ፡- እንግዲህ ያየናቸው ሁለት ዓይነት ነገሮች ናቸው፡፡ እነሱም የሚመሳሰሉ ሲሆኑ፣ የመጀመርያው አገራችን ውስጥ ውይይት እያደረግን ቢሆንም ችግሮች እየተፈጠሩ መሄዳቸው የማይቀር እንደሆነ ነው ያስተዋልነው፡፡ እናም ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደ አገር ያየናቸው ብዙ ችግሮች ያነሳነውን ጉዳይ በበቂ ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ምክክር በአንድ በኩል ይካሄዳል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ግጭቶች፣ ብዙ የሕይወት መጥፋትና ጦርነት ድረስ ዓይተናል፡፡ በሌላ በኩል ግን ይኼ ሁሉ እየሆነ ኢትዮጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሌሎች በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገራዊ ምክክር እንደሚያስፈልጉት የተሻለ ፍላጎት እየተንፀባረቀበት ይገኛል፡፡ ስለዚህ ምንድነው እኛ የምናደርገው? ችግሮችን ማቆም አንችልም፣ ምንም አቅም የለንም፡፡ ነገር ግን በአገራዊ ምክክር እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየፈታን መሄድ እንችላለን፡፡ ምርጫው ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ቁጭ ብለን ችግሮች በራሳቸው ጊዜ እየፈነዱ እንዲሄዱ መጠበቅና ማየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ችግሮች በሚፈልገው መጠንና ርቀት ቢሄዱም እኛ ደግሞ እንዲፈቱ ይኼንን አገራዊ ምክክር በሚገባ ጀምረን መቀጠል አለብን የሚል ነው፡፡ እኛም ለዚህ ለሁለተኛው ስንል ነው አገራዊ ምክክሩን የቀጠልነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለሕዝባዊ ምክክር ሲታሰብ ሁለት ዓይነት አካላት አሉ፡፡ አንደኛው ምሁራን የሚባሉት ወይም ራሳቸውን እዚያ ውስጥ ያስገቡ አካላት፣ ሁለተኛው ደግሞ አጠቃላይ ሕዝቡ አለ፡፡ ምክክራችሁ የትኛው አካል ላይ የተመሠረተ ነው?

አቶ ንጉሡ፡- በምክክሩ እስካሁን በነበረበት ሒደት ሁለቱንም ያካተተ ቅይጥ አቀራረብ ነው የምንከተለው፡፡ አንደኛው ከራሱ ከኅብረተሰቡ ከታች ጀምሮ በሚደረጉ የተለያዩ ምክክሮች የኅብረተሰቡ አጀንዳና ጥያቄ ምንድነው የሚለውን እየጠየቅን ቆይተናል፡፡ በተለይ በሰላም ሚኒስቴር በኩል ማኅበረሰቡን ያማከለ ውይይት በሚደረግበት ወቅት እኛ የማይንድ አባላት ለማኅበረሰብ ተኮር ውይይት አመቻቾች ሥልጠና ሰጥተን በየጊዜው እየተከታተልናቸው ነው፡፡ ሕዝቡ ነፃ ሆኖ ጉዳዩን እንዲናገርና ሁሌም እንደሚባለው በማንቆለጳጳስ ሳይሆን፣ የሚሰማውን ጉዳይ እንዲናገር ነፃና ገለለተኛ የሆኑ የምክክር መድረኮች እንዲፈጠሩ ማስቻል ነው፡፡ ሁለተኛው ግን የተለያዩ የልሂቃን ቡድኖችን ነበር የምናናግረው፡፡ ለምሳሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ የወጣት ቡድኖች፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ደግሞ የሃይማኖት መሪዎችን ደረጃ በደረጃ በማወያየትና በማነጋገር ነበር የቆየነው፡፡ እነዚህን አካላት እያናገርን ግን ሁሉንም የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ አገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ በዚህ መሀል አያስፈልግም ያለን አካል የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ታዲያ ምን ላይ ነው መነጋገር ያለብን? ምንድነው የሚያጣላን? በምንድነው መስማማት ያለብን? ስንል የሚሰጡን አጀንዳ አለ፡፡ እኛም ያንን አጀንዳ እየመዘገብን አንድ ቋት ውስጥ እናስቀምጣለን፡፡ ስለዚህ ከታችም ከላይም አጀንዳዎችን እያሰባሰብስን ነው የምንሄደው እንጂ፣ ከልሂቃን ብቻ ወደ ታች የሚወርድ ነገር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እየተነሱ ካሉ አገራዊ ጥያቄዎች አንዳንዶቹ እንዲህ በቀላሉ የማይፈቱና የፍትሐዊነት ጥያቄ ያዘሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን እንዴት ልትመልሱ ወይም ልታስተናግዱ ትችላላችሁ? መንግሥትስ ዝግጁ ነው ወይ ለመስማት?

አቶ ንጉሡ፡- እንግዲህ በማንኛውም ጊዜ የተለያዩ ጥያቄዎች ያሏቸው ማኅበረሰቦች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ገሸሽ አናደርግም፣ ተመዝግበው ይቆያሉ እንጂ፡፡ ነገር ግን መጨረሻ ላይ ሁሉም ጉዳይ በውይይት የማይፈታ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ ጉዳይ ምናልባት የመንግሥትን ውሳኔ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔን ወይም የሕግ ማስከበርን፣ አንዳንዱ ደግሞ ምክክርን ሲፈልግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ጉዳዮች ምንም የሚገደቡ አይሆኑም፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰነ ቦታን ያማከሉ ሊሆኑ ይችላሉ ሌሎች መላ አገሪቱን የሚያማክሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እኛ የምናደርገው ገሸሽ ከማድረግ ይልቅ ውይይታችን ወደፊት እንዲቀጥል ነው፡፡ በአንድ በኩል በአገር ደረጃ የምንጀምረው አገራዊ ምክክር አለ፡፡ በሌላ በኩል በአንዳንድ በተወሰኑ ክልሎች ወይም በተወሰኑ ግለሰቦች የሚነሱ ጥያቄዎች ለምክክር የሚቀርቡበትን ሁኔታ እንፈጥራለን፡፡ እነዚህ አገራዊ ምክክር ላይ መቅረብ ባይችሉ እንኳ፣ በተለያየ ደረጃ ለምክክር እንዲቀርቡ መድረክ እናዘጋጃለን፣ ገለል አድርገን አንተዋቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ ሰላም መፍትሔ ለመፈለግ የሰላም ሚኒስቴር፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንና ሌሎችም መሰል ተቋማት ተመሥርተዋል፡፡ ነገር ግን እየታየ ባለው ሁኔታ ተቋማቱ ኖረውም ችግሩ እየበዛ ነው፡፡ እናንተስ ከእነሱ በተለየ ለሕዝቡ ምን ተስፋ ይዛችሁ መጣችሁ?

አቶ ንጉሡ፡- እንግዲህ ምን የሚባል ነገር አለ? አንድ ሰው  ጨለማ ውስጥ ሲሆን ሁለት ምርጫ አለው፡፡ ወይ ጨለማውን መኮነን ነው፣ ወይም ሻማ ማብራት ነው፡፡ አሁን መንግሥትን ነቅስን አውጥተን ይህን አጥፍተሃል፣ ይህ ስህተት ነው፣ ያ ጥፋት ነው ብለን ልንናገር እንችላለን፡፡ ብዙ ይህን የሚያደርጉ አካላት አሉ፡፡ ሥራቸው ሆኖ የሚያደርጉትም አሉ፡፡ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንን ብንመለከት ወቀሳ የሚያነሱ አካላት አሉ፣ የሚያመሠግኑም አሉ፡፡ ሰላም ሚኒስቴርም ይሁን የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሲቋቋሙ በአዋጅ የተሰጣቸው ሥልጣን አለ፡፡ ያንን በአዋጅ የተሰጣቸውን ሥልጣን ቢጠቀሙበት በጣም ጥሩ አቅም ሊገኝበት ይችላል፡፡ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለምሳሌ ሥራው ብሔራዊ መግባባት ላይ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ከዋና ዋና የዕርቀ ሰላም አጀንዳዎች አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ላይ ለምን አብረን አንሠራም ተባብለን ቁጭ ብለን፣ በተለይም ከዋና ስብሳቢው ከካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ጋር ሳይቀር በደንብ ተነጋግረን አብረን ለመሥራት የምንችልባቸውን መንገዶች ቀይሰን እየሠራን ነው ያለነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለእኛም የሚጨምርልን ነገር አለ፣ ለእነሱም የሚጨመር ዋጋ አለ፡፡ ማለትም የጋራ ጥቅም የሆነ የአገር ጉዳይ ነው፡፡

እኛም ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር የምንሠራው በሕግ የተደነገገ ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ስላላቸው ነው፡፡ እናም ያንን ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ከእኛ ጋር ተባብረው ቢሠሩ በጣም ጥሩ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የዕርቀ ሰላም ኮሚሸንና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ውይይቶች ሲጀመሩና ሲጠናቀቁ ፀሎት እየተደረገ ነው፡፡ አባቶችም ከኋላ ሆነው ምክክሩን እየታዘቡ መጨረሻ ላይ ስንወጣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተያየት ስንጠይቅ፣ በይፋ እዚያው ቦታ ላይ የተናገሩት ከዚህ በኋላ በሚደረግ ውይይት እንዲሁም ብዙ አባቶች ይምጡና አጠገባችን ይሁኑልን ይላሉ፡፡ በጣም ጥሩ የሆነ መንፈስ ነው ያለው ብለውናል፡፡ እኛ ደግሞ ይህን በጎ ነገር እየመነዘርን ልንጠቀምበት ስለምንችል ነው ከእነሱ ጋር የምንሠራው፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን እያከናወናችሁት ያለው ተግባር ምን ያለመ ነው? መቼስ ይጠናቀቃል?

አቶ ንጉሡ፡- እንግዲህ አሁን ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ትርጉም ነው ያላት፡፡ በታሪክም አሁንም አንድ የቀረን ነገር የነገይቱን ኢትዮጵያ አብሮ መገንባት ነው፡፡ በታሪክ ባንስማማም ዛሬም ባለው ሁኔታ እንኳ አንስማማምና የቀረን የነገይቱ ኢትዮጵያ ሁሉም የሚመኛትና የሚፈልጋት አገር እንዴት ትሁን? ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ብንገነባ ነው የሁሉንም የተለያዩ ቡድኖች ፍላጎቶች የምናቀራርበው?  የአንዱ ፍላጎት የሌላውን በማይጎዳ መንገድ እያመቻቸንና ሰጥተን እየተቀበልን እንዴት ብንሄድ፣ ምን ዓይነት ቀመር ብናወጣ ነው ለሁላችንም ደስታ የምትሰጥ ኢትዮጵያ መገንባት የምንችለው?  የሚለው ነው የእኔ ትልቁ ጥያቄ፡፡ ለእኔ ደስ የሚለኝ አንተን ደስ ሊያሰኝ ይገባል፡፡ ስለዚህ የነገይቱ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ላይ አሰባስባ፣ ሁሉም የሚያከብሯት፣ ሁሉም የሚቀበሏት፣ ሥርዓቷንም ይሁን ጠቅላላ አወቃቀሯን የሚቀበሉት ኢትዮጵያዊያንን ድምፅ ሰምተን ሁሉም የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ በጋራ መገንባት ይቻላል? እስካሁን የለመድነው ምንድነው?  አንድ ወይም ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች ይኖራሉ፡፡ አንዱ በኃይል ፈርጠም ያለው ሌሎቹን ደፍጥጦ ይኼ ነው የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያ ብሎ ይነሳል፡፡ ነገር ግን እሱ የት አደረሰን?  ከእሱ ቀጥሎ ለሌላ ችግር ነው የዳረገን፡፡ እንደገና ያኛው ተቀብሎ ለሌላ ችግር ነው ያቀበለን፡፡ ካሁን በኋላ ሥር የሰደዱ ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ እየተመካከርን በትብብር መንፈስ እየፈታን ብንሄድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንፈጥረው ሰላም ዘላቂነት ያለው ይሆናል በኢትዮጵያውያንም መካከል የተሻለ መቀራረብ፣ በተለይም እውነተኛ የሆነውን መፈላለግ መፍጠር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ማወያየትና የምክክር መድረክ መፍጠር አንዱ ትልቅ የሚባል ጅማሮ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ ጉዳዮች ከእናንተ አቅም በላይ ብዙ ውሳኔ የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እስከ የት ድረስ ነው የእናንተ የማስፈጸም አቅም ሊሄድ የሚችለው?

አቶ ንጉሡ፡- ለእኛ አቅማችን ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ተሳታፊዎች ፍላጎት እስካያሳዩ ድረስ እኛ ዝግጁ ነን፡፡ አንድ የማናደርገው ነገር ግን ተሳታፊዎቹን በዚህ ሂዱ በዚያ ተጠምዘዙ አንልም፡፡ እነዚህ የአገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ተሰብስበው የሚያምኑበትን ነገር ማድረግ እንዲችሉ ሒደቱን እንቀርፃለን፡፡ ምን ማለት ነው ሳይንሳዊ ዘዴውን እናመቻቻለን፡፡ ያንን ሳይንሳዊ ዘዴ በመቅረፅ እየተቀራረቡ እንዲወያዩበት፣ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱበት፣ አንዳንዴ መቃቃር ሲመጣ ሊሸማገሉ የሚችሉበት መንገድ እያመቻቸን እንሄዳለን፡፡ በዚያ ሒደት ከተሳታፊዎች ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ጋር ጉልበታችን እሱ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ እስከ አሥር ዓመት ወይም ዘጠኝ ዓመት እናስኬደዋለን የሚል አቋም የለንም፡፡ አሁን እንደምናየው ረዥም ርቀት ሊያስኬደን የሚችል አቅም አለን፡፡ በተለይ በጠቅላላ በአገሪቱ የምንሰማው አገራዊ ምክክር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ነው፡፡ ሰዎች ከአሁን በኋላ ችግሮቻቸውን ከኃይል ይልቅ በምክክር መፍታት እንዳለባቸው ካለፈው ጊዜ በበለጠ አሁን እየተገነዘቡ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ተነሳሽነት ለእኛ ትልቅ ስንቅ ነው፡፡ ያንን ይዘን እንሄዳለን፡፡ ሁለተኛ ግን አገራዊ ምክክሩ እየተካሄደ ከአገራዊ ምክክሩ የሚመነጩ ሐሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል፣ አገርን የሚመራው መንግሥት ተነሳሽነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ማለት አገርን የሚመራ መንግሥት ከውይይቱ ወይም ከምክክሩ የሚመነጩ ሐሳቦችን አልቀበልም ካለ ምንም ልታደርግ አትችልም፡፡ ስለዚህ ሌላ አንድ የምናደርገው ነገር አንደኛ አሁን ያለው ገዥ ፓርቲና መንግሥት፣ ሁለተኛ ደግሞ በምርጫው ላይ የሚፎካከሩ ፓርቲዎችን በሙሉ አንድ ላይ ይዘን ነው የምንሄደው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ነገ ማንም መንግሥት ቢመሠርት የዚህን አገራዊ ምክክር ፋይዳ በሚገባ እየተረዳና እያወቀ ስለሚሄድ፣ ከአገራዊ ምክክሩ የሚመነጩ አገርን የሚያግባቡ ጉዳዮችን ወደ ተግባር ለማምጣት የተሻለና ጥሩ ፍላጎት ይኖራል ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን በየደረጃው ይህን እያደረግን ደግሞ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የጀመራችሁትን ተግባር ተቋማዊ በማድረግ ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ንጉሡ፡- አሁን አካሄዳችን እንደዚያ ነው፡፡ ስምንት ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነን ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥረናል፡፡ ገና እየሄድንበት ያለና ያላለቀ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ተቋሙን የት ቢሆንና እንዴት ቢመራ ይሻላል የሚለውን አሠራር እናደራጃለን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነት የምክክር ሁነቶችን ስታካሂዱ ለተወያዮቹ የቀመራችሁላቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ንጉሡ፡- ብዙ ዓይነት መንገዶች አሉን፡፡ ለምሳሌ የዴስቲኒ ኢትዮጵያን አሠራርና አካሄድ ዓይተህ ከሆነ በሐሳብ የተራራቁ ብዙ ፖለቲከኞች ሲጨዋወቱና ሲሳሳቁ ታይቶ፣ በጣም ተዓምር ተብሎ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ እንኳ በኤርትራ ለረዥም ጊዜ ሲቆዩ ተገናኝተውና ተነጋግረው የማያውቁ የፖለቲካ መሪዎች፣ በእኛ አማካይነት መነጋገር ችለዋል፡፡ ይህ አገራዊ የምክክር ሒደት ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን፣ እንደ አንድ አገር ደግሞ ቁጭ ብሎ መቀራረብና ማውራት የሚፈጠርበት ዓይነት ዘዴዎች አሉት፡፡ እስካሁን የተጠቀምንባቸውና ከአሁን በኋላም የምንጠቀምባቸው እንዳልኩህ ዝም ብሎ ደረቅ ውይይት ሳይሆን፣ ለዛ ያለው መቀራረብ የሚፈጥርና ጓደኝነት እየመሠረቱ የሚሄዱበት ይሆናል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ አካላት ከምክክሩ በኋላ ስልክ ተደዋውለው የሚቀራረቡበት ሁኔታ እየፈጠርን ነው፡፡ እኛም በሥራችን ተሳክቶልናል፡፡

ሪፖርተር፡አዳዲስ የምክክር መድረኮችን ለመፍጠር ነፃ የሐሳብ ውይይቶችን የሚያመቻቹ ተቋማት ከእናንተ ምን ሊማሩ ይችላሉ?

አቶ ንጉሡ፡- ከእኛ ሊማሩ የሚችሉት ነገር ምንድነው? ድሮ እኔ የፖለቲካ መሪዎቻችን ነበር የምተቸው፡፡ ቆይቼ ይህን ሒደት ከጀመርን በኋላ ያስተዋልኩት እነዚህ ይወያዩ፣ ይመካከሩ ያልናቸው አካላት አንድም ቀን ተገናኝተው አያውቁም፡፡ የሚመካከሩበት መድረክ አግኝተንላቸው ወይም አመቻችተንላቸው አናውቅም፡፡ ዝም ብለን እንገምታለን፡፡ እነሱ ተገናኝተው የማይግባቡና የማይስማሙ እንላለን እንጂ፣ እውነተኛ መድረክ አመቻችተንላቸው አናውቅም፡፡ ያን መድረክ በማመቻቸት ደግሞ እነሱ ባለሙያዎች አይደሉም፡፡ ማለትም የምክክር ባለሙያዎች ሳይሆኑ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ እኛ ያ ሙያ ያለን በተለይም በአመቻችነትና በአመራር ረገድ ሙያ ያለን ሰዎች ይህንን መድረክ ብንፈጥር፣ ተቀራርበው መነጋገር የሚችሉበትን መንገድ አገኘን ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ተናግረው ችግር አይፈጠርም፡፡ ደፍሬ መናገር እችላለሁ የሚሉበት መድረክ አመቻችተንላቸው መነጋገር ይችላሉ፡፡ አሁን እኛ የተማርነው ትልቁ ነገር ምንድነው? በዝግ የሚደረጉ መድረኮች ወይም ሚዲያ የሌለባቸው፣ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ የማይራገቡ ሲሆኑና አንዳንድ ዘዴዎችን ስንጠቀም፣ በጣም ጠንካራ የሚባል አቋም ያላቸው የፖለቲካ አመራሮች የምንላቸውን እንኳ የሚያዳምጡ፣ የሚደማመጡ፣ የሚስቁ፣ የራሳቸውን የግል ሕይወት ለሌሎች የሚያካፍሉ ናቸው፡፡ አብሮ መብላትና መጠጣት የሚችሉ ሰዎች እንደሆኑ ነው ያየነው፡፡ ይኼ የምናደርገው የምክክር መድረክ ሁሉንም ችግር ይፈታዋል እያልኩ ሳይሆን፣ ቢያንስ እኛ ይህንን የውይይት መድረክ አጠናክረን ማመቻቸቱን ከቀጠልን ይነጋገራሉ፣ ይመካከራሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ይህን መድረክ ካላዘጋጀንላቸው ዕድሜ ልካችንን ልንተቻቸውና ልንረግማቸው እንችላለን፡፡ ነገር ግን ምንም የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ካለ አንድ ብቻ ነው መንገዱ፣ መመካከር ብቻ፡፡ ለመመካከር ደግሞ በጠረጴዛ ዙሪያ የተመቻቸ ሁኔታ ያስፈልጋል፡፡ ደኅንነት ተሰምቷቸው የሚነጋገሩበት፣ ተቀራርበው የሚወያዩበት ጥሩ ከባቢ መፍጠር፡፡ ያንንም መፍጠር ችለናል፡፡ ካሁን በኋላም በዚያ መንገድ ነው የምንሄደው፡፡ ሌሎችም በዚህ መንገድ ቢሄዱ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን አገራዊ የምክክር መድረክ ስታመቻቹ በመንግሥት በኩል ያለውን ፍላጎት እንዴት ገመገማችሁ? በቀጣይስ ከመንግሥት ምን ትጠብቃላችሁ?

አቶ ንጉሡ፡- መንግሥት ስንል አንዱ ሀቅ ምንድነው ከ2010 ዓ.ም. በፊት ለሲቪል ማኅበረሱ የነበረውን ቦታ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ በተለይ እኛ በእነዚህ ተቋማት ስንሠራ የነበርን ሰዎች በደንብ እናውቃለን፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በጣም ጠባብ ነበር፡፡ የሚዲያው ምኅዳርም የተጨቆነ ነበረ፡፡ አንድ ትልቅ ነገር ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የተከሰተው የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቷል፡፡ ለምሳሌ ከበፊቱ በተሻለ የሲቪል ማኅበረሰቡ በጣም ስስና የማይነኩ (Sensitive) የሚባሉ ጉዳዮችን እንኳ አንስቶ መሥራት ይችላል፡፡ ያኔ ግን ለምሳሌ የሲቪል ማኅበረሰቡ የመብት ጥያቄዎች ላይ እንዳይሠራ በሕግ ታግዶ ነበርና የሲቪል ማኅበረሰብን አዋጅ፣ የሚዲያን አዋጅ፣ እንዲሁም ሌሎቹንም ጨቋኝ የነበሩ አዋጆችን አሻሽሎ ነው የጀመረው ይህ አሁን ያለው መንግሥት፡፡ መንግሥት ትልቅ ነገር አደረገ የምለው በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ነው፡፡ አሁን ያለው መንግሥትም ሆነ ካሁን በኋላ የሚመሠረት መንግሥት ይህንን ምኅዳር እያጠነከረ በሄደ ቁጥር፣ ችግሮቻችንን የምንፈታበት ፍጥነትና ጥራት እየተሻሻለ ነው የሚሄደው፡፡ ሁለተኛ መንግሥት ካሁን በፊት የምናውቀው በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ነበር፡፡ ይህ ማለት ውስጥ ገብቶ አጀንዳ መቅረፅ፣ ተሳታፊዎችን መለየት፣ ሁሉም ጉዳይ ላይ እጁን ሰዶ መሥራት ይፈልጋል፡፡ እንደዚያ በሚሆንበት ጊዜ ምናልባት ለጊዜው ያው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እንዳሉት ሰው ያደፍጣል፡፡ ነገር ግን አይሰማህም፡፡ ደግሞ ለውጥ አታመጣም፡፡ እናም ያየነው ነገር እሱን ነው፡፡ በተለይም ረዣዥም እጆች በሚኖሩበት ወቅት፡፡

ስለዚህ አሁን እኛ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ነው የምንሠራው፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የምናየው አዝማሚያ በጣም አበረታች ነው፡፡ በተለይ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ እንዳደረገው ዓይነት ሁነት ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ሲካሄድ ተሳታፊዎችም ይመሰክራሉ፡፡ ያንን የዴስቲኒ ኢትዮጵያ የሥራ ውጤት ይፋ ባደረግንበት ወቅት እንኳ የማንም እጅ አልነበረበትም፡፡ የመንግሥት እጅ ጭምር እንዳልነበረበት፡፡ ስንናገር ተሳታፊዎች ሲያጨበጭቡ ነበር፡፡ ያንን ለማረጋገጥም ምንም የመንግሥት እጅ አልነበረበትም፡፡ አሁን በምናደርገው ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ሒደት ውስጥ መንግሥት እንደ አንድ አካል ይሳተፋል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለውም፡፡ ካሁን በኋላም ይህ መንግሥትም ሆነ በምርጫ የሚመሠረት መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን ጣልቃ ገብነት ቢያቆም ጥሩ ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ምክር ነው፡፡

ሦስተኛው ምክር የሚሆነው በእንዲህ ዓይነት ምክክሮች የሚመጡ ውጤቶችንና የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በሰፊ ልብ ተግባር ላይ ለማዋል ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን የምናየው ነገር ምንድነው? መንግሥት የውይይቱን አካሄድ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ አንድም ጣልቃ ሳይገባ ጠንካራ ድጋፍ እየሰጠ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን በአገራዊ ምክክር የመጨረሻ ምዕራፍ፣ በምክክሩ የሚሰነዘሩ ምክረ ሐሳቦችን ሥራ ላይ ማዋል ነው የሚፈለገው፡፡ እነዚያን ምክረ ሐሳቦች ሥራ ላይ ስታውል መንግሥት ነው ዋነኛው ተዋናይ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ያን ጊዜ መንግሥት ከአገራዊ ምክክሮች የመነጩ ምክረ ሐሳቦችን ሥራ ላይ ለማዋል ፈቃደኝት ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ካልሆነ ግን የአገራዊ ምክክር ፍላጎት እንደገና ይዳፈናል፡፡ ሰውም እንደገና ወደ ኃይል አማራጭ እንዲሄድ ይገደዳል፡፡ ፖለቲከኞችም እንደዚያ ሊገደዱ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን በሰፊ ልብ አዳምጦ ያንን ሰዎች የተስማሙበት ጉዳይ ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጁ ቢሆን በጣም የተሻለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ምንጫችሁ ምንድነው?

አቶ ንጉሡ፡- ፋይናንስ በሁለት መንገድ ነው እየሰበሰብን ያለነው፡፡ አንደኛው ው እንደተለመደው ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ አገሮችን አንድ ላይ አሰባስብናቸው፡፡ ‹‹የአገራዊ ምክክር ጓደኞች›› የሚባል ቡድን ተመሥርቶ ከእነሱ ጋር ምክክር እያደረግን፣ ከመንግሥት ጋር እንደምናደርገው ጣልቃ ሳይገቡ ይህንን ጉዳይ አገር በቀል ባህሪውን ሳይለቅ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንዲህ ዓይነት አገር በቀል ውጥን በራሳችን አገር ልጆች መደገፍ አለበት፡፡ ያ ደግሞ የባለቤትነት መንፈስ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነትና ኃላፊነት ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም እያደረግን ያለነው አገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መድረክ እየፈጠርን ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...